ለምለም መንግሥቱ
ከአራት ኪሎ ወደ ሜክሲኮ በህዝብ ትራንስፖርት እየተጓዝን ነው። አንዳንዱ ተሳፋሪ በአካባቢው እየተከናወነ ያለውን የአረንጓዴ ልማት አሻግሮ እያየ ከጎኑ ላለው አስተያየቱን ይሰጣል።ሌላው ደግሞ የግል ጨዋታ ይዟል። ከነዚህ መካከል አንዱ ተሳፋሪ የወዳጅነት ፓርክ አካባቢ ስንደርስ በአመልካች ጣቱ እያሳየ ‹‹ይኸው እዚች ጋር ነው የተወለድኩት›› በማለት እትብቱ የተቀበረበትን ሥፍራ ከጎኑ ላለው ይነግረዋል።ሰውየው ወጉን በመቀጠል።
‹‹ልጆች ሆነን በቤተመንግሥቱ ስናልፍ አንበሳና የተለያዩ የዱር እንስሳትን እናይ ነበር።ዛሬ እንኳን እንስሳቱ ሊኖሩ በቤተመንግሥቱ ውስጥ ያለው ያ ጫካ ይመስል የነበረው የዛፍ ተክል እንኳን ተመናምኗል። በውስጡ ያለው ቤት እንዲህ በግልጽ አይታይም ነበር ›› በማለት የልጅነት ጊዜውን እያስታወሰ በቁጭትም በምልሰትም ወጉን ቀጠለ፡፡
ጨዋታቸው እነሱን ብቻም ሳይሆን እኔንም ስቦኝ በምልሰት ወደ ኋላ ተመለስኩ፤ በቤተመንግሥቱ ውስጥ የነበረውን ጫካና የአካባቢውን ልምላሜ በምናቤ እየሳልኩ። እኔ አካባቢውን ሳውቀው አሁን የወዳጅነት ፓርክ በተሰራበት ቦታ ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዳለው ዛፍ አይነት በጣም ተጠጋግተው የተሰሩ ቤቶች እና ሰፊ ቁጥር ያለው ነዋሪ የሚገኝበት ነበር።አሁን ደግሞ ሥፍራው ለአረንጓዴ መናፈሻነት ውሏል።አይን ማረፊያ ህይወት ማደሻ ፤ እንዲህ እየተደመምኩ መውረጃዬ ደርሶ ከሸገር ባስ ወረድኩ፡፡
እንደው ስለአረንጓዴ ልማት ስናወሳ የከተማዋ ነዋሪዎች ለአረንጓዴ ልማት ምን ያህል ዋጋ እየሰጡ ነው? በአረንጓዴ ልማትስ ይዝናናሉ ወይ? ብለን ስንጠይቅ የብዙዎች ተሞክሮ ተመሳሳይ ነው።ልምዱ አናሳ ነው።በከተማዋ ውስን ቦታ ካልሆነ የአረንጓዴ ሥፍራም የለም።በእርግጥ በአንድ ወቅት ገንዘብ ተከፍሎባቸው ለሰርግ ሥነሥርዓት የሚውሉ እንደነበሩ አይዘነጋም ።
ፎቶ በስቱዲዮ፣ ሰርግ ደግሞ በአዳራሽ ከሆነ ወዲህ ግን ወደነዚህ መናፈሻዎች የሚሄድ እየቀረ መጥቷል።ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ፓርክና አረንጓዴ ሥፍራ ትኩረት አግኝቷል።በአንድ አካባቢም አረንጓዴ መናፈሻ ቦታዎች እየተዘጋጁ ሰዎችም ጊዜያቸውን እያሳለፉበት ይገኛሉ፡፡
እንደእኔ ታዝባችሁ ከሆነ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሳር ቤት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው አረንጓዴ ሥፍራ መተላለፊያ ላይ ስለሆነ ከቦታ አቀማመጡ ጋር ተያይዞም ትኩረት ይስባል።ቅዳሜ፣ እሁድና በአዘቦቱ ምሽት ላይ ጥንድ ሆነውና ለብቻቸው ጊዜ የሚያሳልፉ ሰዎች ይበዛሉ።
ሰርገኞችም የፎቶ ዝግጅታቸውን ሲያከናወኑ ይስተዋላል።እንዲህ ባማረ ቦታ መንፈስን እያደሱና የተለያዩ ኩነቶችን እያከናወኑ ማሳለፍ ያለውን ሥሜትና ለአካባቢውም በግላቸው ስለሚያደርጉት ጥንቃቄ በሥፍራው ካገኘኋቸው መካከል ወጣት ይትባረክ አበበ አንዱ ነው።
ወጣት ይትባረክ አረንጓዴ ሥፍራውን አዘወትሮ ይጠቀማል።በተለይ ጠዋት ጠዋት።በቅድሚያ በድልድዩ መወጣጫ ላይ ስፖርት ይሰራል።ስፖርቱን እንደጨረሰ ደግሞ በአረንጓዴው ሥፍራ ላይ እረፍት ያደርጋል። እርሱ በሚገኝበት ሰዓት በሥፍራው ብዙ ሰው ባለመኖሩ አዕምሮው ጭምር በፀጥታው ሰላም ያገኛል።አካሉንም መንፈሱንም አድሶ ወደ ሥራው ይሄዳል።ይሄን ልምድ አዳብሯል።ከአቅም በላይ ካልሆነ አዘወትሮ ይጠቀማል፡፡
ወጣት ይትባረክ ‹‹ገንዘብ ሳላወጣ ጤንነትገዝቻለሁ›› ይላል።ታዲያ እንዲህ ለሚጠቀምበት ሥፍራ ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚያደረግ ጠየኩት።‹‹እውነት ለመናገር ውሃ በማጠጣት ወይንም በሌላ ነገር ብረዳ ደስ ይለኛል።
ግን አላደረኩትም።ዕድሉን ባለማግኘቴ እንጂ ፈቃደኛ ነኝ።ብዙ ጊዜ አካባቢን የሚያበላሸው ለመፀዳጃ የሚውሉ እንደሶፍት፣ ማስቲካ፣ ምግብና የሀይላንድ ጠርሙሶች ናቸው። እኔ እነዚህን ነገሮች ይዤ ወደ ሥፍራው ስለማልሄድ አካበቢውን የሚበክል ነገር አላደርግም።ብዙ ሰው ይጠቀማል።
ግን ንጹህ ሆኖ ነው የማየው።ምናልባት አካባቢውን የሚንከባከቡ ሰዎች ተከታትለው አጽድተው ሊሆን ይችላል። በግሌ ሁሉም ሰው ባይንከባከብ እንኳን ቆሻሻ ባለመጣል ሊተባበር ይገባል›› ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ሌላዋ ያነገርኳቸው የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግሥት ተስፋዬ የልደታ ቅርንጫፍ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድ ቁጥጥር ባለሥልጣን የተሽከርካሪ ዘርፍ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ አረንጓዴ መናፈሻ ሥፍራ የሄዱት የሰርጋቸው ጊዜ እንደሆነ ነው ያስታወሱት። አምባሳደር መናፈሻ ነበር የሰርግ ዝግጅታቸውን ያከናወኑት።እርሳቸው እንዳሉት ትዳር ከመመሥረታቸው በፊት የነበራቸው ልምድ ቴያትር እና ፊልም ማየት እንጂ መናፈሻ ሄደው አያውቁም።
ትዳር ከመሰረቱ በኋላም ቀደም ሲል ይዝናኑበት የነበረው ቴያትርና ፊልም ቀርቷል። አሁን የሚሰሩበት የልደታ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ብዙ ጥንቃቄ የሚጠይቅና እርሳቸውም የሚሰሩበት የኃላፊነት ቦታ በመሆኑ ቀን በሥራቸው ተወጥረው ይውላሉ።ማታ ቤት ሲሄዱ የቤተሰብ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡
ባለቤታቸው በህይወት ስለሌሉ ልጆች የማሳደጉ ኃላፊነት እርሳቸው ላይ ነው የወደቀው።በመሆኑም ጊዜ የላቸውም። ቅዳሜ ግማሽ ቀንና እሁድን የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን በማሳለፍ፣ ልጆቻቸው በትምህርት ጠንክረው መልካም ዜጋ እንዲሆኑ ለእነርሱ ጊዜ በመስጠትና ትምህርታቸውን በመከታተል ነው ቀናቱን የሚጠቀሙባቸው።
ጊዜም ካገኙ ልጆቻቸውን ኬክ ጋበዘውና ዘና አድረገው ይመለሳሉ።በአቅራቢያቸው አረንጓዴ ሥፍራ አለመኖር ትኩረት እንዳይሰጡ እንዳደረጋቸውም ይገምታሉ። ‹‹ግን ደግሞ›› አሉ ወይዘሮ ትዕግሥት ‹‹እኔ ብቻ አይደለሁም ብዙ ሰው በአረንጓዴ ሥፍራ ጊዜ የማሳለፍ ልምድ የለውም።
ከሰዎች ጋር ስንጫወትም። አዲስ ስለተከፈተው የምግብና መጠጥ መዝናኛ ሥፍራዎች ነው መረጃ የምንለዋወጠው።አሁን ሳስበው በቂ ምክንያት የለም›› ሲሉ ይገልጻሉ። በቅርቡ ለህዝብ ክፍት የሆነውን አንድነት እና እንጦጦ ፓርክን እንኳን አለማየታቸው ከዚህ ቀደም ልምድ አለመኖሩ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው ታዝበዋል።ነገ ዛሬ የሚለው የጊዜ ቀጠሮም አዘናግቷቸው ፓርኮቹን እስከዛሬ ሳያዩዋቸው መቅረታቸውን ይናገራሉ፡፡
በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተሰሩት ፓርኮች ለመዝናኛ ብቻ ሳይሆን ታሪክም እንደሆኑና መጎብኘትም አለባቸው ብለው ያምናሉ።ጥሩ ነገርን ደግሞ ከሌሎች ከመስማት እራስ አይቶ ግንዛቤ መውሰድ የተሻለ እንደሆነም ይገልጻሉ።ወይዘሮ ትግዕሥት በሚኖሩበት 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አረንጓዴ የመናፈሻ ሥፍራ ባይኖርም በመንገድ ሲያልፉ የሚያዩዋቸውን አረንጓዴ መናፈሻ ሥፍራዎችን ያደንቃሉ።
ለአብነትም ወደ ቃሊቲ መንገድ መሄጃ ላይ የሚገኘውን የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መናፈሻን ይጠቅሳሉ። በሥራ አጋጣሚ አዳማ ሄደው ያዩት የኦሮሚያ ክልል ለተለያየ አገልግሎት የሚጠቀምበትን አባገዳ ከህንጻው አቀማመጥ ጀምሮ ውስጡ በአረንጓዴ ተውቦ ማየታቸው አስደምሟቸዋል።
በውስጡም ለማስታወሻ ፎቶግራፍ ተነስተዋል። እንዲህ ያሉ አካባቢዎችን ሲያዩ ከሀገራቸው ውጭ ያሉ እስኪመስላቸው ድረስ ነው በአድናቆት የሚገልጹት። በዚህና በሌሎችም አገልግሎቱ ባለባቸው አካባቢዎች በመሄድ ማሳለፉ ብዙ ነገር ማትረፍ እንደሚቻል ተገንዝበዋል። ወደፊት እርሳቸውም ለመጠቀም አስበዋል፡፡
የአረንጓዴ መናፈሻ ሥፍራዎችን አጠቃቀም በተመለከተም ወይዘሮ ትዕግሥት ትዝብታቸውን አካፍለውናል።እርሳቸው እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ትኩረት ሰጥተው እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ ህብረተሰቡም ለፓርኮችና በየአካባቢው ላሉ አረንጓዴ ሥፍራዎች የሚሰጠው ዋጋ እየተለወጠ መጣ እንጂ የቆሻሻ መጣያና ለተለያዩ የንግድ አገልግሎቶች ሲውል ነው በብዙ አካበቢ የሚስተዋለው።
የተተከሉ ችግኞችን የሚነቅሉና የለማውን አትክልት የሚያጠፉ ሰዎች መኖራቸው ደግሞ ሀገራዊ ስሜት ነበር ለማለት ያዳግታል።በተለይ በአረንጓዴ ልማትና ጥበቃ የክልል ከተሞች ከአዲስ አበባ ከተማ የተሻሉ እንደሆኑ ያስባሉ።አሁን ያለው ትኩረት ያለፉ ስህተቶች እንዲታረሙ ዕድል ሰጥቷል።መልካም አስተሳሰቡ የበለጠ ተሻሽሎ የአረንጓዴ መናፈሻ ልማቱ እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡
ህብረተሰቡ በመኖሪያ ግቢው አረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት ቢያደረግ ዕድገቱ የበለጠ ይሆናል ብለው ተስፋ የሚያደርጉት ወይዘሮ ትዕግሥት በግላቸው ባላቸው ቦታ ላይ ጤናዳም፣ ዳማከሴና ሌሎች የአትክልት ዘሮች በመትከል ለራሳቸው ደስታ በመፍጠር ላይ እንደሆኑአጫውተውኛል።እንዲህ ያለው ልማድ ልጆቻቸውም እንዲያዳብሩ በማድረግ በሀገር ደረጃ በሚሰራው ላይም ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ትዕግሥት እንዳሉት ስለ ፓርኮች አብዝቶ መነገር የተጀመረውም ሆነ አረንጓዴ መናፈሻዎችን በማስፋፋት ላይ ትኩረት የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እንደሆነ ነው የታዘቡት።‹‹ጥሩ የሆነ ነገር ለሁላችንም ያስፈልገናል።
ይሄ አስተሳሰብ ሁላችንም ሊኖረን ይገባል።አረንጓዴ ሥፍራን የሚያለሙና አካባቢን የሚያፀዱ ሰዎች ለጤናችን ለውበታችን የሚሰሩ በመሆናቸው ሊበረታቱና ሊከበሩ ይገባል።በግሌ በዘርፉ ላይ ያሉት የተሻለ ክፍያ ቢኖራቸው ደስ ይለኛል። እነርሱ ያሳመሩትን ሌላው ሲያበላሽ ለምን ብሎ የሚቆረቆር ሰው መፈጠር አለበት›› ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመንገድ ማካፈያዎች ሳይቀር አረንጓዴ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የሚያበረታታ ቢሆንም ይዞታቸው ሲቀጥል አይስተዋልም። በክረምቱ ተተክለው ያበቡት አትክልቶች በበጋ ይከስማሉ።እንክብካቤ ይጎላቸዋል። ለጎዳና ተዳዳሪዎች የሚውሉ አረንጓዴ መናፈሻዎችም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ስፍራው ወደ አፈርነት እየተቀየረ አረንጓዴነቱን ያጣል፡፡
እዚህ ላይ ትዝብታቸውን ያካፈሉን በአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አበበ ሻምበል በክረምቱ የሚያዩት ልምላሜ በበጋው ጠፍቶ ሲያዩ እጅግ ይቆጫሉ።በግላቸው አረንጓዴ ሥፍራ ላይ ጊዜ የማሳለፍ ልምድ ባይኖራቸውም ሌሎች ሲጠቀሙ ሲያዩ ግን ይደሰታሉ። በአንዳንድ አረንጓዴ መናፈሻ ሥፍራዎች የተዘጋጁት መቀመጫዎች ወደ ሥፍራው ለመሄድ የሚጋብዙ መሆናችውንም ይናገራሉ። በአረንጓዴ መናፈሻ ቦታ የመጠቀም ልምድ ጉዳይ የእርሳቸውም ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍል የተለየ አይደለም። ከጓደኞቻቸው ጋር ሲገናኙ ሻይ ቡና ለመባባል እንጂ እስኪ መናፈሻ ሥፍራ እናሳልፍ የሚል አልተለመደም።አረንጓዴ መናፈሻን እየወደዱት አይጠቀሙበትም።ለጊዜ ማሳለፊያ ወደ ሥፍራው ባይሄዱም በክረምት በሚከናወን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡
አቶ አበበ በግዴለሽነት ተክሎችን የሚያጠፉ ሰዎችን ይወቅሳሉ።የአረንጓዴ ሥፍራ ልማት ሥራ ከአካባቢ አካባቢ መለያየቱም ያስገርማቸዋል።እርሳቸው እንዳሉት ሁሉም ክፍለ ከተሞች እኩል የሆነ የአሰራር መዋቅር እያላቸው የተለያየ ሥራ መሰራቱ አግባብ አይደለም፡፡
አንዳንድ አካባቢ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መኖራቸውን እስኪጠራጠሩ ድረስ አካባቢው በአረንጓዴ ተውቦ ያያሉ።አስተዳደር አለው ወይ የሚያስብል የሚያሳፍር አካባቢን ይታዘባሉ።በአንድ ከተማ ውስጥ እንዲህ ያለ ዝብርቅርቅ የሆነ አሰራርና የአካባቢ ውበት መጓደል ከምን የመነጨ እንደሆነ ቢገምቱም የአካባቢው አስተዳደር ከደከመ ‹‹ደክመሀል አሻሽል›› የሚል እንዴት አይኖርም የሚለው ጥያቄ በአዕምሯቸው ይመላለሳል።አዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ጊዜ ለአካባቢ ብክለት ተጋላጭነቷ እየጨመረ መሆኑን የተናገሩት አቶ አበበ አረንጓዴ ልማቱ ቢስፋፋ ችግሩን በመጠኑም ቢሆን መቋቋም ይቻላል ብለው ያምናሉ፡፡
ተሞክሯአቸውንና ትዝብታቸውን ያካፈሉን የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት በአረንጓዴ የመናፈሻ ልማት ይበል የሚያስብሉ ሥራዎች ተሰርተዋል።በዚያው ልክም ክፍተቶች ያሉባቸው አካባቢዎችም አሉ። አብዛኛው በአረንጓዴ መናፈሻ የመጠቀም ልምድ ባይኖረውም።ሲያልፍና ሲያገድም በአይኑ በማየት እያደነቀው ነው።በመሆኑም ሁሉም የለማውን በመንከባከብ፣ ያለማውንም አብሮ በመሳተፍ ለአረንጓዴ መናፈሻ ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2013