ራስወርቅ ሙሉጌታ
ገና በልጅነቱ፣ በለጋ እድሜው የደረሰበት የአካል ጉዳት እሱንም ሆነ ቤተሰቡን ተስፋ ያስቆረጠ ነበር። ግና እቤት ተቀምጦ ህመሙን ማዳመጥን አማራጩ ያላደረገው ወጣት ዛሬ ራሱን ችሎ ከመኖር ባለፈ ቤተሰብ ለመመስረትና ሌሎችንም ለመታደግ በቅቷል። ጋዜጠኛ ተስፋዪ ገብረማርያም ይባላል፤ በአሁኑ ወቅት የቲዲ ኤስ መልቲ ሚድያ ማኔጂንግ ዳይሬክተርም ነው። ለቤተሰቦቹ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ተስፋዪ የተወለደው በ1974 ዓ.ም ባሌ ጎባ የሚባለው አካባቢ ነበር።
ስድስት አመት እስኪሞላው ድረስ የነበረውን የልጅነት ግዜውን እንደማንኛውም ህጻን በሙሉ ጤነኝነት በደስታና በጨዋታ ያሳለፈ ቢሆንም ከዛ በኋላ ግን በተፈጠረበት የህክምና ስህተት ለአካል ጉዳተኝነት በመዳረጉ ነገሮች በነበሩበት ሊቀጥሉ ሳይችሉ ይቀራሉ።
ተስፋዩ ልጅ እያለ በጣም ቀይ ስለነበር እናቱ የሰው አይን እንዳይነካብኝ እያሉ እቤት ውስጥ ደብቀው ያኖሩት ነበር። አንዳንድ ግዜም እንግዳ የሚመጣ ከመሰላቸው በስስት በርሜል ውስጥ ይደብቁት ነበር።
በዚህ ሁኔታ ቆይቶ አንድ ቀን ከቤቱ ወጥቶ እየተጫወተ እያለ ያስመልሰዋል። እናት በቅርበት የነበሩ ሰዎች ስለነበሩ የእነሱ አይን ነክቶብኝ ነው ብለው ቢያስቡም በአካባቢው የወባ በሽታ ያሰጋ ስለነበር ወባ ከሆነ በሚል በቅርብ ወደሚገኝ የገጠር ጤና ጣቢያ ይወስዱታል።
እዛ እንደደረሰም ሀኪሞቹ ምርመራ አድርገው ታፋው ላይ መርፌ እንዲወጋ ሲያደርጉ ነበር ዛሬ ድረስ አብሮት ላለ ችግር ለመዳረግ የበቃው። በወቅቱ የተሰጠው መድሀኒት ለነበረበት ህመም መፍትሄ ቢሆነውም መርፌውን ሲወጉ ደምስሩን ነክተውት ስለነበር ተስፋዩ ውሎ ሲያድር እግሩን እየሸመቀቀው ይመጣል። እናም ደህና ሲሯሯጥ የነበረው ህጻን ተስፋዩ መራመድ እየተሳነው በደረቱ የሚሳብ ቁጭ ማለት የማይችል ታማሚ ልጅ ለመሆን ይበቃል።
ከዚህ ግዜ ጀምሮ ነበር ቤተሰቦቹ ከዘመናዊ ህክምና እስከ ጸበል አለ የተባለ ቦታ ይዘው እየተንከራተቱ ለማዳን ቢሞክሩም እነሱ በጠበቁት ደረጃ ጤናው ሳይመለስለት ይቀራል። እሱም አብዛኛውን የልጅነት ግዜውን በቤተሰቦቹ ትከሻ ላይ በመሆን በየህክምናውና ጸበል ቦታው በመንከራተት ለማሳለፍ ይገደዳል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ተስፋዪ ጤናዪን ይመልስልኛል ብሎ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአንድ ትልቅ ሆስፒታል ህክምናውን እየተከታተለ እያለ ደግሞ ሌላ ተደራቢ ችግር ይፈጠራል። በሆስፒታሉ ገብቶ የቀዶ ህክምና ሲደረግለት ከፍተኛ የደም መፍሰስ ስለገጠመው እግሩ ከሚጠበቀው በላይ የሰለለ ይሆንበታል። እናም ከወገቡ በላይ በጣም ወፍራም ከወገቡ በታች ደግሞ በጣም ቀጭን ያልተመጣጠነ ሰውነት ያለው ልጅ ይሆናል።
ከዚህ በኋላም መናገሻ ማርያም አካባቢ ወደሚገኘው ቸሻየር ማገገሚያ ማእከል በማቅናት እግሩ ላይ ብሬስ (ሁለት እግር ለይ የሚታሰርና ጠዋት እየተጠለቀ ማታ የሚፈታ እግርን የሚደግፍ ሰው ሰራሽ የብረት ጫማ) ተገጥሞለት ክራንች እንዴት መጠቀም እንዳለበት ተምሮ ይወጣል።
ቤተሰቡም ተስፋ በመቁረጥ ልጃቸው ከዚህ በኋላ ምንም ሊያደርግ ምንም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ባይመስላቸውም ሙከራቸውንና ልፋታቸውን አላቆሙም ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነበር አንድ በአካባቢያቸው ይኖሩ የነበሩ የ84 አመት አዛውንት የህይወቱን አቅጣጫ የቀየረ ታሪክ የፈጠሩት። አዛውንቱ የቤተሰቡን ልፋት የልጁን መንገላታትና ይሄ ነው የሚባል ውጤት አለመመዝገቡን ያስተውሉ ስለነበር ለቤተሰቦቹ በተለይ ለአባቱ «የሚረባ ለውጥ ላይገኝ ይህንን ልጅ ለምንድነው የምታንከራትቱት እናንተስ ለምን ትደክማላችሁ ይልቁንስ ለራሱም ለእናንተም ብሎም ለሀገር የሚጠቅም ልጅ እንዲሆን ለምን አታስተምረውም» የሚል ምክረ ሀሳብ ያቀርባሉ።
ተስፋዪ የህክምናው ውጣ ውረድ ስላልተጠናቀቀ ክራንቹን በየስድስት ወሩ መቀየር ስለነበረበትና የአዛውንቱንም ምክር በመቀበል ትምህርት መጀመር እንዳለበት በመወሰኑ ደብረ ዘይት አካባቢ ያሉ አጎቱ ጋር በመሆን ትምህርቱንም አዲስ የህይወት መስመርም ይጀምራል።
ተስፋዪ ትምህርቱን ይከታተል የነበረው አባቱ በወሎ ክፍለ ሀገር ኮምቦልቻ አካባቢ በልጅነታቸው ከወለዱት ልጃቸው አለምሰገድ ገብረ ማርያም ጋር ነበር። አለም ሰገድ በጣም ጎበዝ ተማሪ የነበረ ሲሆን ከክፍል አንደኛና ሁለተኛ ነበር የሚወጣው። በአንጻሩ ተስፋዪ አምስተኛ ክፍል እስኪደርስ ድረስ በትምህርቱም ጥሩ ውጤት አልነበረውም።
ይህም ሆኖ ተስፋዩ እቤት ሲውል ግዜውን የሚያሳልፈው ሬድዮ በማዳመጥ፤ ስእል በመሳል፤ ግጥም በመጻፍና መጽሀፍትን በማንበብ ነበር። በአንድ ወቅትም በኢትዮጵያ ሬድዮ ከልጆች አለም ፕሮግራም ላይ የገጠር እናቶችን ህይወት በተመለከተ ተወዳድሮ ለመሸለምም የበቃበት ግዜ ነበር።
ስድስተኛ ክፍል ሲደርስ ግን ባልታሰበ አጋጣሚ «ብልጭታ ከህሊና ማህደር» የሚል የጋሽ መንግስቱ ወልደማርያምን መጽሀፍ የማንበብ እድሉን ያገኛል። በመጽሀፉም በሁለተኛው የአለም ጦርነት ሁለት እግሩንና ሁለት እጁን ስለአጣው አንድ ሰው ታሪክ ያነባል።
ይህ ሰው ሰው-ሰራሽ እግርና እጅ ተገጥሞለት በአሜሪካ ትልቅ ቦታ ለመድረስ የበቃ ሰው ነው። የታጣው ሳይሆን የተገኘው ለቁም ነገር ያበቃል የሚል ንግግር ተናግሮም ነበር። አጠቃለይ ሀሳቡም ሰዎች ሲያጡ ያጡትን ብቻ እያሰቡ ከመጨነቅ ይልቅ ያላቸውን በማሰብ መጠቀም እንዳለባቸው ይመክር ነበር። እናም ተስፋዩ ከመጽሀፉ በመነሳት ያለኝ ነገር ምንድ ነው? ያጣሁትስ ምንድ ነው? ምንስ ልሰራ እችላለሁ? ብሎ ራሱን መጠየቅ ይጀምራል።
በዚህ ግዜ ነበር ለቤተሰቦቹም ለራሱም እስከዛሬ ድረስ የሚደንቀውን ስራ ለመስራት የበቃው። አንድ ቀን እናቱንና አባቱን ይጠራቸውና እናቱን በእኔ የተነሳ እስካሁን ብዙ መከራ አይተሻል አሁን ግን አንቺም እንድታርፊ ለእኔም በፈለኩ ግዜ ውሃ ቀድታ የምታጠጣኝ እህት ወይንም ወንድም እንድትወልጅልኝ እፈልጋለሁ ይላቸዋል።
ቤተሰቡ ይህንን ነገር በመስማታቸው በአንድ ወገን ተደናግጠው ባለማመን በሌላ በኩል ሰው መክሮ የላከውም መስሏቸው ደጋግመው ይጠይቁታል። እሱ ግን የመጽሀፉን ታሪክ በመንገር ከዚህ በኋላ ያጣውን ነገር ብቻ እያሰበ ለማላዛን ሳይሆን ማድረግ የሚችለውን እያደረገ ለመኖር መወሰኑን በልጅነት አንደበቱ በማይታመን ማስተዋል ይነግራቸዋል።
እናት ከአመታት በኋላ በስለት ልጅ ለማግኘት ይበቁና ኪዳኔ ብለው ስም ያወጡለታል። በአሁኑ ወቀት ኪዳኔ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ አመት የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው። ቀጥለውም ዛሬ በደብረዘይት ከተማ በመከላከያ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪ የሆነውን ደረጀን ለመውለድ ይበቃሉ። በዚህ ሁኔታ የተስፋዪ ቤተሰቦች ከሀዘንና ተስፋ ከመቁረጥ በመውጣት አዲስ የብርሃን ህይወት መኖር ይጀምራሉ። ተስፋዩም ከስድስተኛ ከፍል ጀምሮ ለደረጃ ከሚታጩት ተማሪዎች መካከል ለመሰለፍ ይበቃል።
ለተስፋዩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ደግሞ ዛሬ ለደረሰበት ህይወት ሌላ መሰረት የጣለለት ነበር። ተስፋዩ ገና ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ሲማር ክህሎቱን አይተው ጋዜጠኛ መሆን እንደሚችል ይመክሩት የነበሩ መምህሮቹን ሀሳብ ይዞ ነበርና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃን ሲቀላቀል በትምህርት ቤቱ ውስጥ ወዳሉት ክበባት ያመራል። ከነበሩት ክበባትም የስነ ጽሁፍ ውድድር ያካሄድ ስለነበር ጸረ ኤች አይ ቪ ክበብ ውስጥ ይገባል።
እዛም አንድ ጽሁፍ ውድድር ላይ ተሳትፎ ሁለተኛ በመውጣቱ ጽሁፉን ሲያቀርብ የሰሙት መምህር ገብረወልድ፣ መምህር ተካልኝና የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር የሆኑት መምህር ጌታቸው አንበርብር በተመሳሳይ ጋዜጠኛ መሆን እንዳለበት ይመክሩትና የትምህርት ቤቱን ሚኒ ሚዲያ ይቀላቀላል። ትንሽ ቆይቶም የክለቡ ሃላፊም ለመሆን ይበቃል።
ተስፋዩ በዚህ ወቅት «እንደ ስሜ ለራሴ ተስፋ የሰነቅኩበት ራሴን ማዳመጥ የጀመርኩበት ግዜ ነው» ሲል ይገልጸዋል። በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በመደበኛ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያበቃ ነጥብ ማምጣት ባይችልም በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በመግባትና ለሶሰት አመታት የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት በመከታተል በዲፕሎማ ለመመረቅ ይበቃል።
ተስፋዪ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ያሳለፋቸው ሶስት አመታት ግን እንዲህ እንደዋዛ በቀላል ያለፉ አልነበሩም። ዋናው ፈተና ደግሞ ከደብረዘይት ተመላልሶ መማር ስለማይችል አዲስ አበባ ይኖር የነበረው በቤት ኪራይ ነበር። ልብስ ማጠብ፣ ምግብ ማብሰልና ሌሎች የእለት ከእለት እንቅስቃሴዎች ያስቸግሩት ነበር። ይህም ሆኖ ተስፋዩ በኔሽን፣ በማክዳ፣ አዲስ ዜናና ሌሎች ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ ይፅፍ ነበር።
ትምህርቱን ጨርሶ ከወጣም በኋላ በኤፍ ኤም አዲስ ዘጠና ሰባት ነጥብ አንድ ላይ የህትመት እፍታ የሚል ፕሮግራም መስራት ይጀምራል። ነገር ግን በቅጥር ከመስራት ይልቅ የራሴን ስሜት እያዳመጥኩ ውጤታማ የምሆንበትን ስራ መስራት አለብኝ በማለት በወቅቱ ምንም ይባልለት ስላልነበረው አካል ጉዳተኝነት ፕሮግራም ቀርጾ ለመስራት መንቀሳቀስ ይጀምራል።
ለዚህ ያነሳሳው ደግሞ ያሉት ሚዲያዎች በርካታ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ቢሆንም የአካል ጉዳተኞችን ትኩረት አለመስጠታቸውን በማስተዋሉና የስራ ማስታወቂያ ሳይቀር ሙሉ ጤነኛ የሆነ እየተባለ የሚወጣበትና ለአካል ጉዳተኝነት ያለው ግንዛቤ መስመር የሳተበት ሰለነበር ነው።
በወቅቱ በፋና ኤፍ ኤም ዘጠና ስምንት ነጥበ አንድ «የሚያዳምጡበት ብቻ ሳይሆን የሚናገሩበት» በሚል መሪ ቃል ይሰራ ነበር። ተስፋዩም ይህንን ሀሳባቸውን ይዞ ወደራሳቸው ያቀናና የምናዳምጠውም የምንናገረውም አለን በማለት የአካል ጉዳተኞችን ድምጽ ለማሰማት «አንድ ድምጽ» የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም ይጀምራል።
ፕሮግራሙ ስለትዳርና አካል ጉዳተኝነት፤ ስለ ፍቅርና አካል ጉዳተኝነት፤ ስለ ትራንስፖርትና አካል ጉዳተኝነት እንዲሁም ሌሎች ወቅታዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳሰሱበት ነበር።
ከዚህ በኋላም የአሁኑ አዋሽ የቀድሞ ዛሚ ዘጠና ነጥብ ሰባት በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ “ድርሻችን” ፕሮግራምን በማዘጋጀት ለረጅም አመት ሲያገለግል ቆይቷል። በናሁ ቴሌቪዥንም ተስፋዩ ሾው አዘጋጅና አቅራቢ አንዲሁም ዜና አንባቢ በመሆን ሲሰራ ቆይቷል።
በእነዚህ ግዜያትም በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ በሰራቸው ስራዎች ሳምሶን አድቨርታይዚንግ ባዘጋጀው ዝግጅት ለሽልማት በቅቷል። በአሁኑ ወቅትም በአሀዱ ሬድዮ ዘጠና አራት ነጥብ ሶስት ‘አዲስ መንገድ’ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅና ባለቤት ሲሆን ላለፉት ሀያ አመታት የአካል ጉዳተኞች ድምጽ በመሆን ሲሰራ ኖሯል።
በቅርቡም በአፍሮ ሄልዝ ቴሌቪዥን ላይ ‘ጽናት ቶክ ሾው’ የተሰኘና በአካል ጉዳተኞች ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ለማቅረብ በባለቤቶቹና አስተዳዳሪዎቹ ሙሉ ድጋፍና ትብብር እየሰራ ይገኛል።
በቀጣይም ከተሳካለትና በትብብር ለመስራት የሚመጣ ፈቃደኛ ከተገኘ ቲ. ቲቪ. አፍሪካ የተሰኘና በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የሚሆን የአካል ጉዳተኞች የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ተስፋዩ በልጅነቱ የገጠመው ታላቅ ፈተና ህይወቱን ከማቃናትም ሆነ ትዳር ከመመስረትና የራሱን ጎጆ ከመቀለስም አላገደውም ነበር። ተስፋዩ በአሁኑ ወቅት ትዳር መስርቶ የሁለት ልጆች አባት ለመሆን የበቃ ሲሆን ከአመታት በፊት የነበረውን የትዳር አመሰራረቱን አንዲህ ያስታውሰዋል።
ከባለቤቱ ወይዘሮ ሰናይት በነበሩ ጋር የተዋወቀው እሷ አረብ ሀገር ሊባኖስ እያለች በፌስቡክ ነበር ግንኙነታቸውን የጀመሩት። በወቅቱ ተስፋዩ ፎቷዋን ሲያይ በጣም ነበር የሚማረክባት እናም ማን እንደሆነች ምን እንደምትሰራ እየጠየቃት እሱም የሚሰራውንና ያለበትን ሁኔታ እየነገራት ግንኙነታቸው እየተጠናከረ ይመጣል።
በዚህ መካከልም በመሀከላቸው የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ሁለቱም ሲያስቡ ቆይተው ነበርና እሱ የፍቅር ጥያቄውን ሲያቀርብላት ወዲያው ነበር የተቀበለችው።
ይህም ሆኖ ተስፋዩ ቤተሰቦቿን ሲያገኝ ምን ይፈጠር ይሆን የሚል ስጋት ነበረበት። ባለቤቱ ግን ገና ከጅምሩ ቤተሰቦቿ ነገሩን ተቀበሉትም አልተቀበሉትም የእነሱ ግንኙነት ላይ የሚያመጣው ለውጥ እንደማይኖር ቃል ገብታለት ነበር። እናም ተስፋዩ ሰናይትን ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ አየር መንገድ ተቀብሎ ሳታስበው ቀለበት ያደርግላታል። በዚህ ሁኔታ የመጀመሪያውን ስጋት ካለፈ በኋላ አንድ ቀን የእህቷ ሰርግ ላይ ከቤተሰቦቿ ጋር ለመገናኘት ይበቃል።
የገጠመው ነገር ግን እሱ ከጠበቀው በተቃራኒው ነበር። ሁሉም ቤተሰብ የተቀበለው በሙሉ ደስተኛነት ነበር ።
ተስፋዪ ለሁለቱ ልጆቹ አንደኛው የአብራኩ ክፋይ ሲሆን አንደኛው ደግሞ የሚያሳድገው ነው። የሚያሳድገው ልጅ የአብስራ ይባላል። የአብ ስራ እንዴት ልጁ ለመሆን እንደበቃም ተስፋዩ እንዲህ ይናገራል። የአብስራ እናት የተስፋዩ ባለቤት ጓደኛ ነች። የፍቅር ጓደኛዋ መጸነሷን ሲሰማ አይመለከተኝም በማለት ጓደኝነታቸው እንዲቋረጥ ያደርጋል።
ልጅቷ ደግሞ የነበረችበት ሁኔታ ምቹ ስላልነበርና ቤተሰቦቿም ሊቀበሏት ፈቃደኛ ስላልነበሩ ጽንሱን ለማስወረድ ትወስናለች። ተስፋዪና ባለቤቱ ግን ጽንሱን ማስወረድ እንደሌለባት ይነግሯትና ምንም እንኳን አንድ ላይ የሚኖሩ ቢሆንም ሴት ልጅ ከተወለደች ባለቤቱ፣ ወንድ ልጅ ከተወለደ እሱ ሀላፊነት ሊወስዱ ቃል ገብተው ልጁ እንዲወለድ በማድረግ ማሳደግ ይጀምራሉ።
በዚህ ሁኔታ ነበር ትናንት ለራሱ አይበቃም የተባለው፤ የሰው እጅና የሰው ድጋፍ ያስፈልገዋል የተባለለት ህጻን ለሌሎች ሰዎች ለመትረፍም የበቃው።
በርካታ አካል ጉዳተኞች አንድም ከራሳቸው በሚመነጭ ስጋት አልያም በቤተሰብና በአካባቢ ተጽእኖ ትዳር ከመመስረትም ሆነ ከሌሎች ፍላጎቶቻቸው ይገደባሉ የሚለው ተስፋዩ የራሱን ተሞክሮ በማንሳት የሚከተለውን ይመክራል። ሁሉም ሰው ያጣውን ሳይሆን ያለውን እያሰበ የፈለገውን ማድረግ አለበት። ለውጥ መጀመር ያለበት ከራስ ነው።
ከግለሰብ የተጀመረ ለውጥ ወደቤተሰብ ብሎም ወደ ማህበረሰብና ወደ ሀገር ያድጋል። በተጨማሪም ማንኛውም አካል ጉዳተኛ ለእያንዳንዱ ፈተና መንበርከክ የለበትም። ወላጆችም ቢሆን እንዲህ አይነት የቤተሰብ አባል ሲኖር ደፋር፣ በራሱ የሚተማመንና ባለው ነገር የሚጠቀም እንዲሆን መርዳት አለበት። የሀይማኖት ተቋማትም በየደጆቻቸው የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ለምነው እንዲኖሩ ሳይሆን ባገኙት አጋጣሚ እንዲማሩ፣ እንዲሰሩና ትዳር እንዲመሰርቱ መስበክ ይጠበቅባቸዋል ይላል።
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 21/2013