ግርማ መንግሥቴ
የቁጥር ነገር የዋዛ አይደለም፤ ለምሳሌ “0” እና “1” ቁጥሮች ባይኖሩ ኮምፒዩተር አይኖርም ነበር። በተለይ “0” ባትኖር የቁጥሮችን ወደ ላይ ማደግ ማሰብ ባልተቻለም ነበር። እንደ ካባላህ (Kabbalah) ፍልስፍና ከሆነ ደግሞ ሁሉም ነገር ምንጩም ሆነ መሰረቱ ቁጥር ነው። (ሌላውን Numerology ባለሙያዎች ሊጨምሩበት ይችላሉ።)
ለመሆኑ ይህንን ቁጥር (10000000000000000 00000000) ሲያዩ ምን ይሰማዎታል? ዝም ብሎ የዜሮዎች ስብስብ ? የሂሳብ ተማሪዎች መራቀቂያና አእምሮ ማስሊያ የትምህርት ዘርፍ ? የአገራት የኢኮኖሚ እድገትና ውድቀት ? የዓለማችን ጂዲፒ ? (Zodiac) የኮከብዎ ቁጥር ? የምድር አሸዋ ወይም የሰማይ ከዋክብት ? (ትምህርቱ “astronomical figure” እንደሚለው)፣ በኬሚስትሪና ፊዚክስ መካከል የነበረውን ግንብ አፍርሶ የተገናኙበትን ድልድይ የሰራውን (Avogadro’s number) የአቮጋድሮ ቁጥር ? የግለሰብ ሀብት፣ ሙስና ወይስ ምን ? መልሱን ከነስሜትዎ ለእርስዎ ትተን የሚከተሉትን “ነገሮች” እናስቀምጣለን።
“ዚሊዮን” ምንድን ነው፣ “ዚሊየነር”ስ ማነው? የሚል ጥያቄ ከተነሳም መልሱን የመመለስ ግዴታ አለና ምንነትና ማንነቱን እንናገራለን። ምንጩንና መጠኑን በአሃዝ፣ ጊዜውንና አጠቃላዩንም እንደዛው አድርገን እናሳያለን። ከወዴት እንደሆነም በአቅጣጫ እንጠቁማለን። “How much is a zillionaire?” በሚል ጥናት ያካሄዱ ሰዎችን ዋቢ እያደረግን እምንለውን ሁሉ እንላለን።
እነዚህ ከፍተኛ ቁጥሮች በስም፣ ቁጥርና ወካይ ምልክታቸው ሲቀመጡ፤ (septillion) ሴፕቲሊየን (1,000,000,000,000,000,000, 000,000) ምልክቱ “Y”፤ (sextillion) ሴክቲሊዮን (1,000,000,000,000,000,000,000) ምልክቱ “Z” ፤(quintillion) ኳንቲሊዮን (1,000,000, 000,000,000,000) ምልክቱ “E”፤ (quadrillion) ኳድሪሊዮን (1,000,000,000,000,000) ምልክቱ “P” ሲሆኑ ትርጓሜያቸው፣ ፋይዳቸውና አካዳሚያዊ/ ቀመራዊ አሰራራቸው እንደየማንነታቸው ይለያያል።
በነገራችን ላይ (ሀንጋሪ 1946 “Pengo note” በሚል የሚታወቅ የ100,000,000,000,000,000,000 ገንዘብ ኖት ማሳተሟን ለሚያውቅ ቁጥሮቹ እዚህ መደርደራቸውን አይጠላም። ይህን ያህል ዲጂት ያለው pengő note ወደ ዩኤስ ዶላር ሲመነዘር $0.20 መሆኑንም ጠቆም አድርጎ ማለፍ ለአእምሮ ጨዋታ ያግዛልና አድርገነዋል። የእኛስ አካሄዱ አያሰጋምን?)
ከሁሉም ለየትና ቸገር የሚለው ደግሞ የዛሬው ርእሰ ጉዳያችን የሆነው (zillion) ዚሊዮን ሲሆን ትርጉሙም” ሊታመን በማይችል ደረጃ ሀብታም፤ ተቆጥሮ የማያልቅ ገንዘብ ያለው፤ በውድ እቃዎች የተሞላ እጅግ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ማንሀተን ያለው፤ የግል አውሮፕላን (ጀት) ባለቤት፤ በአስር ሚሊዮን በሚቆጠር ዶላር የተሰራ ቤት ካሊፎርኒያ ያለው ሰው እሱ ትክክልኛ የዚሊየነሮች ምሳሌ ነው።
ከዚህ ቀጥሎ አንባቢ ይህንን የ”ዚሊየነር” ብያኔ ይዞ ከጽሑፉ ጋር እንዲዘልቅ ይጠበቃል። ምክንያት ? “ዚሊዮን” እና “ዚሊዮናየር” የእለቱ ርእሰ ጉዳያችን ስለሆኑ። (የማርክሲዝም አባት ካርል ማርክስን እዚህ ጋር የሚያስታውስ ሰው የትዝብትና ብስጭት ጣራው ከሌሎቻችን ከፍ ማለቱ የሚገመት ነው።)
“ዚሊዮን” እኛ “ህልቆ መሳፍርት”፣ “የት የለሌ”፣ “መአት” ወዘተ እንደምንለው አይነት “መቁጠሪያ” ነው። ዚሊዮንን በትክክል የሚወክለው ቁጥር የለም እያልን ነው። አይኑረው እንጂ ግን በስምምነት “ዚሊዮን” ለአንድ መጠኑ ላልታወቀ ሀብትና ሀብታም መገለጫ ይሆን ዘንድ ከሌሎች ዝርያዎቹ (ሚሊየነር፣ ቢሊየነር …) ተርታ፤ ለዛውም የመጨረሻው ከፍታ ላይ ምኑም ምኑም ላልታወቀ ለተትረፈረፈ ሀብትና ሀብታም መለያና መጠሪያ በመሆን ተሰይሞ ይገኛል። አሁን ወደ ዋናው ጉዳይ እንዝለል።
እንደ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ /Global Financial Integrity/ ጥናት በ2014 ብቻ በማደግ ላይ ካሉት አገራት ወደ አደጉት አገራት $620 ቢሊዮን ብር በህገ-ወጥ መንገድ ወጥቷል። በዚሁ ጥናት ላይ እንደተጠቀሰው በዚሁ ዓመት አለማችን ከ$2 ትሪሊዮን እስከ $3.5 ትሪሊዮን የሚሆን ህጋዊ ገንዘብ አጥታለች። ከ2004 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ከየሀገራቱ ወደ ውጪ ሲሸሽ የነበረው ገንዘብ በየአመቱ በአማካይ $2.6 ቢሊዮን ነበር።
ፎርብስ ስለኢትዮጵያ ከጠቀሳቸው በርካታ የሚያስቁ፣ የሚያስደነግጡ፣ የሚያሳዝኑ፣ የሚያስተዛዝቡ፣ የሚያሳፍሩ፣ የሚያስጠሉ … እና በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከናወኑ ቅጥ የለሽ የሙስና ተግባራት መካከል በማርች 2017 ሪፖርቱ የጠቀሰው ይገኝበታል። (በሀገሪቱ የነበሩት መሪዎች ከአሜሪካ መንግስት ብቻ $30 ቢሊዮን በአገር ስም ወስደው መልሰው አሽሽተውታል።)
ከእኛ ጋር በተያያዘ 2010ን በተለይ የሚመለከቱ በርካታ ጥናቶች ያሉ ሲሆን ማእከላዊ ጭብጣቸውም ሆነ ግርምታቸው አገሪቱ በዛ ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ከውጭ ዶላር ያስገባችበት ዓመት ሲሆን፤ ያንኑ ብር በዛው ዓመት በህገ-ወጥ መንገድ መልሳ ወደ ውጪ በማውጣት እነዛው አበዳሪ ባንኮች ካዝና ውስጥ ያስቀመጠችበት ዓመት መሆኑ ነው። እውነትም “ናይ ትገርም ሻሸመኔ” (ኦ ሻሸመኔ) ያሰኛል።
እኛም በሀገር ቤት በየጋጥ ስርጓጉጡ፣ በየጋራ ሸንተረሩ፣ በየገደላ ገደሉ፣ በየዋሻና ፉካው ሁሉ፤ ሮቶው፣ እንስራው፣ ጣራው … ሁሉ ሳይቀር የተደበቁ ብሮች በጆንያ፣ ማዳበሪያ፣ ፕላስቲክ … ተደብቀው እየተገኙ፤ ጭራሽም ለምደነው ገንዘብ እስከ መሆናቸው ሁሉ እስኪጠፋብን ድረስ እያየንና እየታዘብን፤ እያፈርንም፣ እየተንጨረጨርንም እንገኛለን። ይህም ነው ዛሬ “ዚሊየነሮችን ፍለጋ” እንድንነሳ ምክንያት የሆነን። ቢያንስ ልናውቃቸው ይገባል።
“ቢሊየነር” የሚለው አደባባይ ወጥቶ ጥቅም ላይ የዋለው በነዳጅ የቶጀረው አሜሪካዊው ሮክፌለር (John D. Rockefeller) ጋር ተያይዞ ሲሆን በ1916 “የመጀመሪያው ቢሊየነር” ተብሎ በይፋ እውቅና ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ ነው። የመጀመሪያው ዚሊየነርስ ከየት ይሆን? ከኢትዮጵያ?ምንም ሆነ ምን፤ ትርጉሙ ምንም አለምን፤ በዚህ ዘመን ዚሊየነር መሆን የሚቻለው በሙስናና በዘረፋ ብቻ ነው። በመሆኑም ነው እስካሁን በይፋ “ዚሊየነር እከሌ” ሲባል የማይሰማው። ወደፊትስ?
ዛሬ አይደለም “ዚሊየነር” ገና ወደ “ትሪሊየነር”ነት ደረጃ የተጠጋ እንኳን የለም። እንኳን በግለሰብ ደረጃ ትሪሊየን ለአገራትም ብርቅ ነው። ይህን እንበል እንጂ (አጥኚዎቹ “indefinitely large” የሚሉት የገንዘብ መጠን ያለው)”ዚሊየነር” ግን የለም እያልን አይደለም። ለዚህ ደግሞ ከአፍሪካ በላይ ማሳያ የለም፤ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከኋላ ተነስታ እያስከነዳች ቢሆንም። በስልጣን መባለግ (economics of corruption) ምክንያት የሚደርሰውን ሳናካትት) ማለት ነው።
ጎበዝ ትሪሊዮን (1,000,000,000,000 ወይም tera) የሚለውን እንደ ዋዛ ማየት የለብንም፤ ትሪሊዮን ሰከንድን እንኳን ብንወስድና ወደ ሰዓት፣ ቀን ወር …. ብንለውጠው 32,000 ዓመት ሆኖ ነው የምናገኘው፤ እንኳን በብር ለማለት ነው። ዚሊዮንንም በዚሁ ቀመር እናስብ። ግን ግን አበሻ “አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል” ሲል ለካ ይህንን ሁሉ አስቀድሞ ተረድቶ ነው?
አሁን የብዙዎቻችን ጥያቄ “ይህን ሁሉ እዚህ መዘርዘር ለምን አስፈለገ?” የሚል ቢሆን ትክክል ሲሆን፤ እያንዳንዱ ከተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ አኳያ ምክንያት እንዳለው መግለፁም ትክክል ነው። በተለይ ከሚሊየነሮች ተነስቶ እስከ ዚሊየነሮች የሚዘልቀው የዓለማችን ባለሀብቶች ቁጥር፣ ሀብትና ማእረጋቸው ሲነሳ የግድ እነዚህ ከላይ በጥቅል ያነሳናቸው መሰረታዊያን መነሳታቸው የግድ በመሆኑ ነው። (ለጊዜው ሚሊየነርና ቢሊየነሮችን እዚህ ማንሳቱን አልፈለግነውም፤ በአሁኑ ዘመን ብርቅ ስላልሆኑ)።
የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊየነር የአማዞን መስራቹና አስተዳዳሪውና “ the world’s first trillionaire” በማለት ታሪክ ስሙን የሚያሰፍርለት ባለ $188.7 ቢሊዮን (በ27 ኦክቶበር 2020) Jeff Bezos ሊሆን እንደሚችል ያለምንም መጠራጠር እየተነገረ ሲሆን ይህም በ2026 እውን እንደሚሆን በጥናቶች ተተንብየዋል፤ Bezos የትሪሊየነርነት አክሊሉን ይደፋሉ ተብሎም ይጠበቃል። ይህ ሁሉ በስራ ነውና ይታወቃል።
ባንዴ ከBezos በላይ የተፈናጠሩትን፤ የእኛዎቹን ዚሊየነሮችን ግን አናውቃቸውም። ለምን? ከኳድሪለዮነር ጋር በተያያዘ የChris Reynoldsን ጉዳይ እናንሳ። የ56 ዓመቱ Chris ከኢንተርኔት ባንኪንግ አይነቶች አንዱ በሆነው Paypal ተጠቃሚ ነው።
በመሆኑም ወር መጨረሻ ላይ ወርሀዊ ሂሳቡን ለማወቅ አካውንቱን ሲከፍት ከPennsylvania የተላከለትን $92 (£60) ኳድሪሊዮን (ያገኘው በትክክል ሲቀመጥ $92,233,720,368,547,800 ነው) ያገኛል። እነሆ ዛሬ Chris Reynolds በዓለማችን የመጀመሪያው ባለ ኳድሪሊዮን ብር ባለቤት ለመሆኑ ዜና አውታሮችም ሊያወሩለት በቅተዋል። ይህ ሁሉ ምንጭ ይታወቃል። የእኛዎቹን ግን አናውቅም። ለምን?
ዳንጎቴ (Aliko Dangote) ከአፍሪካ የአንደኝነቱን ስፍራ ያለ ተቀናቃኝ ሲይዙ አጠቃላይ ሀብታቸውም ከ$15 ቢሊዮን ያላነሰ ሀብት ባለቤት በመሆን ከአፍሪካ ብቻም ሳይሆን ከዓለምም የመጀመሪያው ጥቁር ሀብታም ለመሆን ችሏል። ከዛው ከናይጄሪያ ሳንወጣ ሌላ ሀብታም የምናገኝ ሲሆን እሷም ፎሎሩንሶ አላኪጃ ነች።
አላኪጃ ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ፤ ከዓለም ደግሞ 3ኛዋ ሀብታም በመሆን ተመዝግባለች፤ አጠቃላይ ሀብቷም $1.0 ቢሊዮን (ጃንዋሪ 2020) ይገኛል። ይህ ሁሉ ምንጩ ይታወቃል።
የዓለማችን ቁጥር አንድ የሀብታሞች ከተማ ኒውዮርክ ስትሆን ሀብታቸው ከ$5 ሚሊዮን በላይ የሆኑ 120,605 ሰዎች ይኖሩባታል። ደስ የሚለው ከእነዚህ ውስጥ “በአቋራጭ የከበሩ፤ በሙስና የተነከሩ” በሚለው የክብር መዝገብ ውስጥ አንዳቸውም ስማቸው የለም።
ራሳቸውን ያበቁ፤ Self-Made ናቸውና ደረታቸውን ነፍተው ነው የሚኖሩት። (እዚህች ከተማ ውስጥ እስካሁን አይደለም ባለቤት አልባ ህንፃዎች አንድም ባለቤት አልባ ጎጆ እንኳን አልተገኘም።)
እንደ ክሬዲት ስዊስ ግሎባል ዌልዝ /Credit Suisse Global Wealth/ ሪፖርት ከሆነ በዓለማችን ያሉት ቁንጮ ሀብታሞች ($1 ሚሊዮን በላይ ሀብት ያላቸው) ከአጠቃላይ ህዝቡ አንድ በመቶ ሲሆኑ የዓለምን 44 በመቶ ሀብት ተቆጣጥረዋል። እንደ ኦክስፋም ጥናት ደግሞ የዓለማችን ስምንት (ከ1 እስከ 8ኛ ያሉት ብቻ) ቱጃሮች ሀብት ከሰው ዘር አጠቃላይ ሀብት ግማሹን ነው። የእኛስ ኢኮኖሚ በዚህ መልኩ ቢሰላ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? ተሰርቶ እንዲነገረን እንፈልጋለን።
ከላይ “ደም መጣጮች” የሚላቸውን በሚያስታውስ መልኩ ማርክስን አንስተን ነበር (አውዳሚነትን የሚያራምደውን ፍሬደሪክ ኒችም ሆነ አመፅን የሚያደፋፍረው ማይክል ፎከልትን ከዚሁ አኳያ ማንሳት ይቻላል)። ወደ ቅርቡ ዘመን ስንመጣም በርካቶችን እናገኛለን።
የጋናው ኑክሩሁማ (1961)፣ የታንዛኒያው ኔሬሬ (1966)፣ ኤም.ኤች. ክሃሊል ቲማሚ (African Leaders and Corruption)፣ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ (“When Dictators Steal” እና “As Nigeria Tries to Fight Graft, a New Sordid Tale” (እንደዚህ ዘገባ በናይጄሪያ ምድር ሚኒስትር ለሚኒስትር፣ የሴኔት አባል ለሴኔት አባል ሁሉ ጉቦ ይሰጣጣሉ።) እና የመሳሰሉት ስለሙስና ጽፈዋል፤ ሙስናን አውግዘዋል፤ የናይጄሪያው ጀነራል ሳኒ አባቻን አይነት ናይጄሪያን በሙስና ጎርፍ ጠራርጎ የወሰደ መሪና ስርአት አገላብጠው አሳይተዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ልክ የዛሬ ዓመት (ዲሴምበር 2019) ነው የአገራችን ከፍተኛ ባለስልጣናትና ተባባሪዎቻቸው በመቶ ቢሊዮኖች ዘርፈው ወደ ውጪ ባንኮች ማሸሻቸውን የነገሩን (ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በፓርላማ ንግግራቸው “የውጭ አገር መንግስታትን የሸሸውን ገንዘባችንን መልሱልን ብንላቸው ‘ባንኮቻችን አደጋ ላይ ይወድቁብናል፤ ሊዘጉ ሁሉ ይችላሉ’ አሉን” ያሉትን ያላስታወሰ ከዚህ ጽሑፍ ጋር በቀላሉ አይግባባም።) ይህ የሚያሳየን በአካልም ባይሆን በአምሳል ኦባሳንጆ እዚህ ነበር ማለት ነው።
እንደ ፎርብስ ዘገባ (ማርች 5, 2020) ዓለማችን አጠቃላይ/ድምር ሀብታቸው $158.3 ትሪሊዮን የደረሰ 46.8 ሚሊዮን ሚሊየነሮች ያሏት ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 2ሺህ 153 የሚሆኑት ቢሊየነሮች ናቸው። እነዚህ ሁሉ ከነሀብት ምንጮቻቸው ይታወቃሉ። ጥያቄው የእኛዎቹ ዚሊየነሮችስ ነው?
የእንግሊዟ ንግስት ኤልዛቤት $520 ሚሊዮን ያላቸው ሲሆን፤ የእንግሊዝ ሞናርኪ ባጠቃላይ $88 (ኤፕሪል 20, 2020) ቢሊዮን ሀብት እንዳላቸው ታውቋል። ወደ መሪዎች ስንመጣም ብቸኛና ተጠቃሽ ሀብታም የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ (“the first billionaire president” ተብለዋል)ን የምናገኝ ሲሆን የሀብታቸው መጠንም $2.5 ቢሊዮን (2020) መሆኑ ታውቋል። ይሄንን ሁሉ እናውቃለን። ስለ እኛ ዚሊየነሮች ግን ምንም አናውቅም። ለምን? ብር በየጓጥና ስርጓጉጡ፣ ጋራና ሸንተረሩ፣ ጫካና ገደሉ … ከባንኮች ሁሉ ተርፎ … እየተገኘ ዚሊየነሮች የሉም ለማለት ነው??
በ”Wealth-X Billionaire Census 2020” ላይ እንደተመለከተው ከአጠቃላይ ቢሊየነሮቹ 58% የሚሆኑት፣ “መጽሐፉ ጥረህ ግረህ …” እንዳለው፣ እራሳቸውን ለዚህ ያበቁ (self-made)ሲሆን 29.6% በመቶዎቹ ደግሞ በውርስና የግል ጥረት ለዚህ የበቁ ናቸው። ከዚህ የምንረዳው የታወቁ ቢሊየነሮቹ የሀብት ምንጭ ሁለት መሆኑን ሲሆን እነሱም “ሰርቶ” እና “ወርሶ” ናቸው። ከሙስና የፀዳ ይሏል ይህ ነው!!! የቢሊየነሮች የሚታወቅ ከሆነ የዚሊየነሮች የማይታወቅበት ምን ምክንያት አለ??? ሊነገረን፣ ሊነግሩን ይገባል።
በኖቬምበር 2019 ይፋ የተደረገው የUBS/PwC Billionaires ዘገባ በዓለማችን (በ66 አገራት) $2,101 ቢሊየነርስ አሉ።
የሁሉም ሀብት ሲደመር $8.5 ትሪሊዮን ይደርሳል የሚለው ይሄው የፎርብስን “የሴት ቢሊየነሮች ስም ዝርዝር” የጠቀሰ ሪፖርት ከእነዚህ ውስጥ ሴቶች 11.9% (197 ከ1,826) ብቻ መሆናቸውንም ያረጋግጣል። (አሜሪካዊቷ Alice Walton በ$65.9 ቢሊዮን አንደኛ ናቸው) የሴት ቢሊየነሮቹን የሀብት ምንጭ በተመለከተም 30 በመቶ በራሳቸው፤ የተቀረው በውርስ መሆኑን ያስረዳል። የእኛዎቹን ዚሊየነሮች ሀብት ምንጭስ ምን ብለን ነው የምናሰላው? በመቶኛስ እንዴት ነው የምንገልፀው? ይህን የሚነግሩን እራሳቸው ናቸውና እንፈልጋቸዋለን።
ባጠቃላይ የአፍታ ሚሊየነርነቱን ይሁን ብለናል፤ ምን እናድርግ ብለን የአፍታ ቢሊየነርነቱንም አልፈናል፤ ይህ እያለ እያለ …. ባይነግሩንም “ዚሊዮን” ላይ ደርሶ ዚሊየነሮችን አፍርቷል፤ ዚሊየነሮቹን ፍለጋው ይቀጥላል። አሜሪካዊ ራመር ላሴል ዲላርድ (በመድረክ ስሙ ፍሎ ሪዳ)ም ዚሊየነርን “Zillionaire” ያዜማል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20/2013