አንተነህ ቸሬ
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ (የውጭ) መገናኛ ብዙኃንና ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለጉዳዩ የሚያሰራጩት ዘገባ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ተገቢ ያልሆነ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ነው።
ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለጉዳዩ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ (እንዲኖረው) አድርጎ እንደነበር ታዝበናል።
የዘመቻው ተዋንያን እነማን ናቸው? ምንስ እያሉ ነው?
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበር ዘመቻው ዓላማ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ የእንግሊዝ መገናኛ ብዙኃንን ያህል የተቀናጀ ዘመቻ የከፈተ አካል የለም።ቢቢሲን ጨምሮ፣ ሮይተርስ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ዘ ቴሌግራፍ፣ ሜይል ኤንድ ጋርዲያን፣ ዘ ኢንዲፔንደንትና ሌሎች በርካታ መገናኛ ብዙኃን (ድረ-ገፆችን ጨምሮ) የውሸት ዜና በማሰራጨት ዘመቻ ተጠምደው ከርመዋል፤ አሁንም በአልሞት ባይ ተጋዳይነታቸው ቀጥለዋል።
የእነዚህ ‹‹መገናኛ ብዙኃን›› የሐሰት ፕሮፓጋንዳና ውንጀላ ጠቅለል ያለ ምክንያት ‹‹ፀረ-ኢትዮጵያዊነት›› ነው።ይህ ኢትዮጵያን የመጥላት አባዜ እንግሊዝ ከከሃዲው የህ.ወ.ሓ.ት ጁንታ ጋር ካላት ወዳጅነትና ኢትዮጵያን ከማዳከም የዘመናት ሴራዋ የሚመነጭ ነው።
በመቅደላ ዝርፊያ፣ በሄዌት (ዓድዋ) ስምምነት ሴራ፣ በዓባይ ወንዝ ስምምቶች፣ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ፣ በድህረ-ፋሺስት አስተዳደርና በሌሎች ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የኢትዮጵያ ክስተቶች ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተሳተፈችው እንግሊዝ የኢትዮጵያ አንድነትና ጥንካሬ ምንጊዜም ቢሆን እንቅልፍ ይነሳታል። የጁንታው ዓላማና የእንግሊዝ ምኞት የተራራቀ አይደለም።
ይህ ቡድን ወልደው ያሳደጉት ውሸት፣ ጭካኔና ክህደት ከቁመቱ በላይ ረዝመው የማይታለፍ ቀይ መስመር እንዲያልፍ ሲያደርጉት እንግሊዝ ወዳጇና ለዓላማዋ ማስፈፀሚያ እንዲሆናት ስትደግፈው የቆየችውን ቡድን በውርደት ከታጀበ ሞት ለማትረፍ በመገናኛ ብዙኃኗ በኩል ላይ ታች ስትል ከርማለች። ዘመቻዎቹ አሁንም ቀጥለዋል።
ከእንግሊዝ በተጨማሪ የሌሎች አገራት መገናኛ ብዙኃንም በዚህ የፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።በዚህ ረገድ የአሜሪካ፣ የአውስትራሊያና የአረብ አገራት መገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ ተጠቃሾች ሆነው እናገኛቸዋለን።
እነዚህ አገራት የእንግሊዝ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች እንደነበሩ ሲታወስ የእንግሊዝን ተልዕኮ ተቀብለው በፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻው ላይ ተሳታፊ መሆናቸው የሚያስደንቅ አይሆንም። ከታዘብነው አንፃር የዘመቻውን ተሳታፊዎች በሁለት ምድብ ከፍለን እንመልከታቸው።
ሀ). ‹‹ነጭ ህወሓታውያን››
በዚህ ምድብ ስር የሚካተቱት ፀረ-ኢትዮጵያ ግለሰቦችና ቡድኖች በትውልድና በዜግነት የውጭ አገራት ዜጎች የሆኑና የኢትዮጵያን በጎ ነገር ማየት የማይፈልጉ መንግሥታት መልዕክተኞች ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ ‹‹ነጭ ህወሓታውያን›› ከህ.ወ.ሓ.ት ጁንታ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አምባሳደሮች ናቸው።ለግንዛቤ እንዲረዳን ከብዙዎቹ መካከል የጥቂቶቹን ማንነት በአጭሩ እንቃኘው።
አሌክስ ዲ ዎል
እንግሊዛዊ ነው። በታፍትስ ዩኒቨርሲቲ፣ በፍሌቸር የሕግና ዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ስር የሚገኘው የዓለም የሰላም ፋውንዴሽን (World Peace Foundation) ዳይሬክተር ነው። ‹‹የአፍሪካ ጉዳዮች አጥኚ›› የሚል ማዕረግም ተደርቦለታል። የኤድስ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናትና ምርምር ካውንስል ዳይሬክተር ነበርም ይባላል።
በኤርትራ ‹‹የነፃነት ትግል›› ወቅት የሂውማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) ‹‹ተመራማሪ›› ሆኖ ከሰራ ወዲህ ራሱን የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ አድርጎ ሾሞ መንግሥታትን አማክራለሁ ሲልም ቆይቷል።
የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ይበልጥ ትኩረቱን እንደሚስበው የሚናገረው ይህ ሰው፤ በተለይ በሱዳን ላይ ያተኮሩ መጽሐፍትንና ጽሑፎችን ጽፏል።ደቡብ ሱዳን ነፃ አገር እንድትሆን ከማዋለድ ጀምሮ ሕገ መንግሥቷን በማርቀቅ ሂደትም ጉልህ ተሳትፎ እንደነበረው ይነገራል።
ሰውየው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ አድናቂና ወዳጅ ነው። እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም ‹‹The Real Politics of the Horn of Africa ፡ Money, War and the Business of Power›› በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፉን ‹‹መታሰቢያነቱ ለአቶ መለስ ዜናዊ ይሁንልኝ›› ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ሰውየው ከህ.ወ.ሓ.ት ባለስልጣናት ጋር የቅርብ ግንኙነት እንደነበረው በመጽሐፉ ውስጥ አትቷል። ምን ይሄ ብቻ?! የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ሃሳብ አመንጪም ነው አሉ።
በዘመነ ህ.ወ.ሓ.ት/ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ የአራት ኪሎ ደንበኞች ከነበሩና ህ.ወ.ሓ.ት ከማዕከል ፖለቲካ በመባረሩ ምክንያት ካኮረፉ የውጭ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው አሌክስ፤ ስለወቅታዊው የሕግ ማስከበር እርምጃ ሲያሰራጭ የነበረው የውሸት መረጃ ሰውየው ተራ ውሸታም እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
በቢቢሲ በኩል ብቅ እያለ የሚያሰራጫቸው ጽሑፎቹ አስቂኝም አሳፋሪም ናቸው።ለአብነት ያህል ‹‹Tigray Crisis Viewpoint ፡ Why Ethiopia is Spiraling Out of Control›› የሚለው ጽሑፉ የህ.ወ.ሓ.ትን ጁንታ የዲሞክራሲና የመርህ ጠበቃ፤ የኢትዮጵያን መንግስት ደግሞ ፀብ ፈላጊና ራሱን መቆጣጠር የተሳነው አካል አድርጎ አቅርቧቸዋል። ያለምንም አሳማኝ ማስረጃ ጦርነቱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እያመራ እንደሆነም ጽፏል።አገር ሊያፈርስ ለተደራጀ ቡድን የሚሰጥ ምላሽ በአሌክስ ትንታኔ መሰረት ‹‹የእርስ በእርስ ጦርነት›› ነው።
የህ.ወ.ሓ.ት ባለስልጣናት ጭምር ያረጋገጡትን መከላከያ ሰራዊትን የማጥቃት የክህደት ተግባር ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ጦርነቱን የጀመረው ማን እንደሆነ ስላልታወቀ በገለልተኛ አካል ይጣራ ብሎ የጻፈ ሞኝ ነው።
[‹‹የሰሜን እዝን መሳሪያ ወስደን ለራሳችን አድርገነዋል … 45 ደቂቃዎችን የፈጀ የመብረቃዊ ጥቃት ኦፕሬሽን አድርገናል›› ብለው በአደባባይ የተናገሩትን ደብሪጽንና ጊኒውን ጠይቃቸው በሉልኝ]
ይባስ ብሎም የኢትዮጵያ መንግሥት በዘመቻው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ድሮን በመጠቀም ንፁሃን ዜጎችን እንደጨፈጨፈም ጽፏል። ይህ የፈጠራ ክስ ደግሞ የህ.ወ.ሓ.ት ሰዎች ተደጋጋሚ ማልቀሻ እንደነበር አይዘነጋም።
‹‹Ethiopia is Undermining the African Union›› በሚል ርዕስ ያስነበበው ጽሑፉ ደግሞ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ከመመስረት ጀምሮ ለተቋማቱ ያላትን ክብርና አበርክቶ የካደ የክህደት ዶሴ ነው።
አቶ መለስ ወደ ኒው ዮርክና ዋሺንግተን ዲ.ሲ ጎራ ሲሉ በሚዘጋጀው የቤት ውስጥ ፓርቲ ውስጥ ከሚጋበዙ የህ.ወ.ሓ.ት ወዳጆች መካከል አንዱ የነበረው አሌክስ፤ የኢትዮጵያን ስም በማጠልሸት የሚጽፋቸው ጽሑፎቹ የድግሱን ፌሽታ እያሰበ ብቻ በቁጭት የሚከትባቸው ትዝታዎቹ እንደሆኑ ለማወቅ ብዙ ምርምር አይጠይቅም።
[በነገራችን ላይ በዚህ የቤት ውስጥ ፓርቲ ላይ ተጋባዥ የነበሩ አሜሪካውያን ባለስልጣናትም የሕግ ማስከበር እርምጃውን ‹‹የጦር ወንጀል ነው›› በማለት ለጋባዣቸው ጠበቃ ሆነው ታዝበናል] … ያም አለ ይህ እውነታው አሌክስና መሰሎቹ ከሚጮሁት በተቃራኒው ነው!
ማርቲን ፕላውት
ይህኛው ‹‹ነጭ ህ.ወ.ሓ.ት›› ደግሞ የጋራ ብልፅግና አገራት የጥናት ተቋም (Institute of Commonwealth Studies) ባልደረባ፤ የቢቢሲ አፍሪካ የቀድሞ አርታኢ እንዲሁም ‹‹Understanding Eritrea››፣ ‹‹Fighting Britain››፣ ‹‹Understanding South Africa››፣ ‹‹War in the Horn››፣ ‹‹Who Rules South Africa›› የተባሉና የሌሎች መጽሐፍት ጸሐፊ ነው ይባላል። በብዙ አገራት የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባ በመፈትፈትና ግጭት በመቸርቸርም ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራው ፕሬዚዳንትና ከዐማራ ክልል መሪዎች ጋር በጋራ ሆነው ትግራይን እንደወረሩ፣ የህ.ወ.ሓ.ት ኃይል የፌዴራል መንግሥቱን የጦር ጀቶች መትቶ እንደጣለ፣ የሕግ ማስከበር ዘመቻው እንዳልተጠናቀቀ … የሚገልፁ በርካታ የሐሰት መረጃዎችንና ማደናገሪያዎችን ሲፈበረክ ቆይቷል።
ከዚያም አልፎ የትግራይ ሕዝብ የሽምቅ ውጊያ እንዲደረግና የተራዘመ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ለራሱም፣ ለፌዴራል መንግሥትም በአጠቃላይ ለመላው ኢትዮጵያ ተጨማሪ ችግር እንዲሆን የጅል ምክር መክሯል።
መቀሌ ከተማ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋሏ በተሰማበት ወቅትም ልክ የህ.ወ.ሓ.ት ሰዎች ሲሉት እንደነበረው ‹‹ገና ምን ተነክቶ! ውጊያው ገና ነው …›› በማለት የከሃዲውን ውርደት ለማመን ሲቸገር ተስተውሏል።
ቀደም ሲል ከሻዕቢያ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደነበረው ቢነገርም ራሱን ‹‹የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አድርጎ›› ከሾመ በኋላ ከኤርትራ መሪዎች ጋር ተቀያይሟል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም ማውረዷ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተጥሎባት የነበረው ማዕቀብ መነሳቱ ምቾት አልሰጠውም።
በአካባቢው ሰላም ከተፈጠረ የሚናገረው እንደሚያጣ ስጋት የገባው ፕላውት፤ ለማዕቀቡ መነሳትና ከኢትዮጵያ ጋር ለተፈጠረው ሰላም ዋናው ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መሆናቸውም ‹‹የዐቢይ ወታደሮችና ታማኞች›› እያለ ለሚጽፋቸው ብጥስጣሽ መልዕክቶቹ መንስኤ ናቸው። ‹‹ኤርትራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በማበር ህ.ወ.ሓ.ትን እየወጋች ነው›› የሚለው ተደጋጋሚ ለቅሶው የዚህ በቀል መነሻ ሳይሆን አይቀርም።
ሽቲል ትሮንቮል
ራሱን ‹‹የግጭት ጥናት ፕሮፌሰርና አማካሪ (Professor Of Conflict Studies/Conflict Advisor)›› ሲል የሰየመው የስካንድኔቪያው ሽቲል ትሮንቮል፣ በኤርትራ ስደተኞች ላይ ያተኮረ ጥናት አስተባባሪ ነበር።
የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነትን በጥቅሙ ላይ እንደተደቀነ አደጋ ቆጥሮት ስምምነቱን ጥላሸት በመቀባትና ህ.ወ.ሓ.ትን በማሞገስ ተጠምዶ ቆይቷል።ተመራማሪ ነኝ ብሎ የህ.ወ.ሓ.ትን ‹‹የጨረቃ ምርጫ››ም ታዝቧል።ስለሕግ ማስከበር እርምጃው ሲጽፍና ሲናገር የነበረውም የህ.ወ.ሓ.ት ወዳጅና ጠበቃ ሆኖ ነው።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምስቅልቅል ሴረኛ አሻራቸውን ያኖሩት፣ እ.አ.አ ከ1989 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩትና ዛሬ የተናገሩትን ነገ የማይደግሙት አቋመ ቢሱ ኸርማን ኮኸን … በውሸታምነታቸው ህ.ወ.ሓ.ትን የሚያስንቁ የከሃዲ ጠበቃዎች ናቸው።
[የእድሜያቸው ማምሻ ላይ የሚገኙት ፀረ-ኢትዮጵያው አዛውንት ኮኸን፤ ሰሞኑን በፃፉት የትዊተር መልዕክታቸው ‹‹ህ.ወ.ሓ.ት ከዚህ በኋላ በትግራይም ይሁን በመላው ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትርጉም ያለው ኃይል አይደለም›› በማለት የወዳጃቸውን ፍፃሜ እየመረራቸውም ቢሆን ለመቀበል የተገደዱ መስለዋል]
ጋዜጠኛና ተማራማሪ ብሎ ለራሱ ሹመት የሰጠው ዊልያም ዴቪሰን፣ ‹‹ተንታኝ፣ ጋዜጠኛ፣ ኢኮኖሚስት … ነን›› የሚሉት ሲሞን ማርክስ፣ ዊል ሮስ፣ ረሺድ አብዲ፣ ዊል ብራውን፣ ዴክላን ዎልሽ፣ ደቪድ ፓይሊንግ፣ ቶም ጋርድነር፣ ሎረን ታይለር፣ ጁሊያ ፓራቪቺኒ፣ ዋሲም ኮርኔት፣ አብዲ እስማኤል ሰመተር፣ ጂዮፍሪ ዮርክ፣ ዛሚራ ራሂም፣ ላቲሺያ ባደር (የሂውማን ራይተስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ሆና ለወንጀለኞች ጥብቅና የምትቆም)፣ ኒዛር ማኔክ፣ ጀምስ ባርኔት፣ ትሬቨር ትሩማ፣ ቶቢያስ ሃግማን፣ ፊሊፕ ማይን፣ ጀምስ ዶርሴይ፣ አና ካራ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች … እነዚህና ሌሎች ነጭ ህወሓታውያንና ፀረ-ኢትዮጵያውያን የከሃዲውን ወንጀል በመሸፈን ዓለም መላው ኢትዮጵያውያን ስለደገፉት የሕግ ማስከበር እርምጃ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።
ለ. ጥቁር ፋሺስቶች
እነዚህኞቹ ደግሞ በትውልድ/በዜግነት ኢትዮጵያውያን ሆነው ሳለ የህ.ወ.ሓ.ት ጁንታ ጠበቃና የኢትዮጵያ ጠላት ሆነው የቀረቡ ባንዳዎች ናቸው።እነዚህ ኢትዮጵያ ደግፋና ይሁንታ ሰጥታ ወክላቸው ሳለ ኢትዮጵያን የሚያፈርሱ የእናት ጡት ነካሽ ባንዳዎች ይቅር የማይባል ወንጀል የሰሩ የታሪክ አተላዎች ናቸው።
ጤና የሌለው የጤና ዳይሬክተር
እጅግ የሚያስገርመውና የሚያሳፍረው ነገር በኢትዮጵያ መንግሥትና በኢትዮጵያውያን ድጋፍና ይሁንታ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ለመሆን የበቁት ዶክተር ቴድሮስ ኣድሓኖም የአገራቸውን ጥቅም አሳልፈው በመስጠት ለአገራቸውና ለወገናቸው ደጀን በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ አሰቃቂ ጥቃት የፈፀመውን ህ.ወ.ሓ.ትን ለማትረፍ እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ነው።የኢትዮጵያ መንግሥትም ስለዳሬክተሩ የክህደት ተግባር እንደሚያውቅ ከዚህ ቀደም ተነግሯል።
እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዱ ያስተዛዝባል፤ግራ ያጋባልም።
ዶክተር ቴድሮስ በስራቸው ምክንያት ያላቸውን ዓለም አቀፍ ግንኙነት የኢትዮጵያን መንግሥት ለማስወገዝና እናት ድርጅታቸው የፕሮፓጋንዳና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኝ እየተጠቀሙበት ነው። መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደፈፀመ የተፃፉ መረጃዎችን በፌስቡክና በትዊተር አድራሻዎቻቸው ያጋራሉ።
የኢትዮጵያ ጠላት ከሆኑ አገራት/መንግሥታት ባለስልጣናት ጋርም አዘውትረው ታይተዋል። መቼም ‹‹ከግብጽ ሰዎች ጋር የሚታዩት ኢትዮጵያና ግብጽ በጤናው መስክ ያላቸውን ትብብር እንዲያሳድጉ ለመወያየት ነው›› ብሎ የሚያስብ ሞኝ አለ ተብሎ አይታመንም።
የክህደት አምባሳደሮች
ህ.ወ.ሓ.ት ከማዕከል ፖለቲካ ተገፍቶ ዋና ማዘዣ ጣቢውን መቀሌ ላይ ካደረገ በኋላ በአምባሳደር ወንድሙ አሳምነው የሚመራ ‹‹የትግራይ ወዳጅነት አገናኛ ቢሮ (Tigray Friendship Liaison Office)›› የተባለና የውጭ ግንኙነት ስራ የሚያከናውን ተቋም መስርቶ እንደነበር ይፋ ሆኗል።
ይህ ተግባሩ ደግሞ እሞትለታሁ ሲለው የነበረውን ሕገ መንግሥት ጭምር የሚፃረር ተግባር ነው።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ የአቶ መለስ ወዳጆችን ተጠግተው ብራሰልስ እየተመላለሱ ደጅ መጥናት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት እንዲቆም፣ የእርዳታ ድርጅቶች እርዳታ ወደሚስፈልጋቸው አካባቢዎች እንዲገቡና በትግራይ ክልል የተቋረጡ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች እንዲጀመሩ የሚጠይቀው የአውሮፓ ኅብረት የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ የውሳኔ ሃሳብ (2020/2881(RSP)) እንዲሁም በኅብረቱ የተጠየቁት ቅድመ ሁኔታዎች እስኪሟሉ ድረስ ታግዶ ይቆያል የተባለው የ90 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ጉዳይ ከዚሁ የአምባሳደሩ ደጅ ጥናት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ሞኝነት አይደለም።
ለብዙ ዓመታት በኒው ዮርክና በዋሺንግተን ዲሲ ‹‹በአምባሳደርነት›› የሰሩት ፍስሃ አስገዶም ረብጣ ዶላሮችን ተቀብለው የመንግሥታትን ገጽታ ለመገንባት ላይ ታች የሚሉ ድርጅቶች መነኻሪያ በሆነው የዋሺግተን ዲሲ አካባቢ መታየት የዘወትር ስራቸው እንደሆነ በአደባባይ እየተነገረ ነው።
ከጠንቋይ ያልተሻሉ ‹‹ዶክተሮች››
የአቶ መለስ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የነበረውና ከላይ ከተጠቀሰው ከአሌክስ ዴ ዎል ጋር በታፍትስ ዩኒቨርሲቲ፣ የዓለም የሰላም ፋውንዴሽን ውስጥ በ‹‹ከፍተኛ ተመራማሪ››ነት ሽፋን የሚሰራው ዶክተር ሙሉጌታ ገብረሕይወት፤ ህ.ወ.ሓ.ት የገዢነቱን መንበር ሲነጠቅ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን አስተዳደር ሲያብጠለጥል ነበር።አሁን ደግሞ ህ.ወ.ሓ.ትን ‹‹ለመታደግ›› እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ እየመራ ይገኛል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የስነ ሕዝብ ፈንድ ባልደረባው ዶክተር ኪዳነ አብርሃም ከዘመቻው አስተባባሪዎች አንዱ ናቸው ተብሏል።
የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ እንዲሁም የስደተኞች ፖሊሲ አዋቂ ነው የሚባለውና የትግራይን ‹‹ዲ ፋክቶ ስቴት (De Facto State)››ነት የወጠነው ዶክተር መሐሪ ታደለ ደግሞ የሕግ ማስከበር ዘመቻው የዘር ማጥፋትና የጅምላ ግድያ እንደሆነ ይሰብካል። ዶክተር መሐሪ ከበርካታ የአውሮፓና የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት ስላለው ይህን ግንኙነቱን ህ.ወ.ሓ.ትን ለማትረፍ ሲጠቀምበት ተስተውሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹የሐሰት መረጃ እያሰራጩ ስለሆነ በሕግ እፋረዳቸዋለሁ›› ብሎ የእስር ማዘዣ ያወጣባቸው ሌሎች ምሁራን፣ ጋዜጠኛና ተንታኝ ተብዬዎችም አሉ።
የወገን ምላሽ ምን ይመስል ነበር?
ከሁለት ሳምንታት በፊት በዚሁ አምድ ላይ ባሰፈርኩት የትዝብት ጽሑፌ፤ በውጭ አገራት ከሚኖሩ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል የውጭ መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበሩ እርምጃ እውነተኛና ሚዛናዊ መረጃ እንዲኖራቸውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር እንደማይቀርብ የሞገቱ ባለስልጣናት፣ ተቋማት፣ ምሁራን፣ ቡድኖችና ግለሰቦች እጅግ በጣም ጥቂት እንደሆኑ ገልጫለሁ።
ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት ከወከሉ አምባሳደሮች መካከል በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው ስለሕግ ማስከበር እርምጃው ጥሩ ጥሩ ማብራሪያዎችን የሰጡት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።ይህ በዲፕሎማሲው መስክ ገና ብዙ ስራ እንደሚቀረን ማሳያ ነው።
በሕግ ማስከበር እርምጃው ወቅት የታየው የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መረን የለቀቀ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ለዘመቻው የሰጠነው ደካማ ምላሽ፤ የዓለም ፖለቲካን፣ በተለይም ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን፣ የመረዳት ችሎታችንንና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያለን አቅም ያመላተ በመሆኑ ለነገ የማይባል አስቸኳይ መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባን ያመላከተ አጋጣሚ መሆኑን ታዝበናል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2013