አዲሱ ገረመው
እንዴት ይዟችኋል? የሰሞኑስ ብርድ እንዴት ነው? መቼም እንደ ኑሮ ውድነቱ በየዕለቱ እያመረረ ነው እንዳትሉኝ። ያው ከፈጣሪ በታች ሰሞኑን ስለሚሆነው የአየር ክስተት የሚነግረን ሜትሮሎጂ ብርዱ ቶሎ ይጠፋል ብሎናል ብዬ ነው።
ደግሞ የሜትሮሎጂን ዘገባ ተከትላችሁ የሸገር ሴት እህቶቻችን ብላቴና ልጅ ዘሎ የማይደርስበትን አጭር ቀሚስ ለብሳችሁ እንዳትወጡ አደራ። የናንተ መታመም ለኛም ይተርፋል። ነገር አበዛሁ መሰለኝ ፤ወደ ጉዳዬ ላምራ፡፡
እናንተዬ በሚገርም ሁኔታ አንዱን ነገር ተነጋግረንና አንሸራሽረን ሳንጨርስ ሌላ አዲስ ነገር ይወለዳል ፤ምን ይደረግ? አሁን ስለ ብርድ በማወራበት ቅጽበት በአገር ቤትም በውጭም በሁሉ ቦታ ወሬ በየሰከንዱ እየተለዋወጠ የሰውን ጆሮ እያደማ ነው። ምን ሰማሁ መሰላችሁ? ምንሰማህ አትሉም? ይኸውላችሁ ከሰሞኑ አገር ቤት ያሉ ሰርቆ አደር የሚባሉ ግለሰቦች ልዩ ትኩረት ሆነው እየተኮነኑ ነው። ስለ እነርሱ ባወራ ስቅ ይላቸው ይሆን እንዴ? ምን አገባኝ እንኳን ስቅታ ለምን በትንታ አይሞቱም። ምክንያቱም ሌቦች ናቸዋ።
ባሻዬ ወገንህን ወክዬ ጥሩ አክቲቪስት በመሆን መብቱን አስከብርልሃለሁ በሚል ከብዙ ሺህ ብር በላይ ሰብስቦ ቤቱ የተወሸቀው ሰውዬ ስራው ተደርሶበት ገንዘባቸውን የተበሉ ሰዎች ምሬት ሲያሰሙ ደርሰህበት ይሆን? እውነቴን ነው የምልህ የዚህ አይነት ጮሌነት መብዛቱን በየአካባቢዎች ስሰማ በዚህ ትልቅ ከተማ ውስጥ ብቻዬን የምኖር ያህል ነው የሚሰማኝ።
ከሰሞኑ አንዱ ወዳጄ ከውጭ አገር ስልክ ተደወለለት። “እገሌ የሚባል አክቲቪስት ታውቀዋለህ ወይ? በጣም ታዋቂ ነኝ ብሏል፤ ሰሞኑን ጎፈንድ ሚ ሊጀምር አስቧል፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይም እየፖሰተ ነው። እኔንም ብር ጠይቆኛል። እስኪ ብሩን ከመስጠቴ በፊት አጣራ…” ተባለ። ሰውዬው የወጣለት አጭበርባሪ መሆኑን ወዳጄ ስልኩን ለደወለለት ሰው ተናገረ። እንዲህ እንዲህ እያሉ ነገሮች በሌላ መንገድም ሲጠሩ እውነትም የሌባ ቁንጮ ሆኖ ተገኘ፡፡
ሁሉም ክፉ ነው ብዬ እየፈረጅኩ አይደለም። ያው ስሜትን ለመተንፈስ ነው። እኔምለው ቆይ ሰው አለማበዱ እንዴት ነው የሚታወቀው? እከሌ መጥፎ ተግባር እየሰራ እያየን አላበደም ለማለት የሚያስችል አሳማኝና ተጨባጭ ምክንያት እንዴት ማቅረብ ይቻል ይሆን? ስለ እውነት ግን ሰው ምን ነካው? እንዴት ያለ አንዳች ልፋት በነጻ ይበላል?
ዘመኑ ተለውጧል ስልህ፤ አሁን እኮ እንደ ድሮ “የኔ ፒክል፣ማል፣ፖንቃ…” እያለ የሚፖሰት ጠፍቷል። የሁሉንም ሰው ፖስት ስታይ ፓርላማ ውስጥ የሚኖሩ ይመስልሃል። አፖሳሰቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር በሆነ አብላጫ ድምጽ፣ በሆነ ተቃውሞ እና በሆነ ድምጸ ተዓቅቦ ፀድቆ የተፖሰተ ይመስልሃል። ጉዳዩ በፖስት ብቻ ቢያበቃ እኮ መልካም ነበር። እኔን የሚያመኝ በፖስትና አልጋ ወራሽ ጮሌዎች ወገኔ ገንዘቡ ሲበላበት ነው።
ዳያስፖራው ብሩን ሳይሰስት ለአክቲቪስት ነኝ ባዩ ይልክለታል። ከዚያ በቀን ሁለቴ በየፌስቡኩ ይወጣና ይሸልላል። ሰልፊ እየተነሳ በላይ በላዩ ይፖስታል። አመሻሹን ደግሞ ሌላ ታሪክ ውስጥ ይገባል። አረ የከልካይ ያለህ!
በስመ እንወክልሃለን ለገዛ ሆዳቸው የሚሮጡ፣ የሚኖሩ፣ በሀሰት የሚሸነግሉ ሰው የሆነ ፍጡር ያደርጋል ተብሎ የሚታሰበውን በሙሉ የሚያደርጉ እየመሰሉ ለገዛ ሆዳቸው የሚመላለሱ በርካታ “አቅጥልቪስቶች” ተበራክተዋል። እነዚህ ዋልታ ረገጥ የሆኑና አንድን ወገን ቆመንልሃል የሚሉ ሰዎች እውነትም የወገን መገፋት ያሳሰባቸው ሳይሆን በማጭበርበር ከውጭ አገራት ብር እያስላኩ ሆዳቸውን የሚሞሉ ናቸው።
ሰውን ለመጉዳት እንጂ ለመጥቀም የተዘረጋ ሲስተም ሳይኖራቸው በየቀኑ “አለን! ከኛ ሌላ ላሰር” በማለት በውዳሴ ከንቱ በስንት ላብ የተገኘውን የግለሰብ ገንዘብ የሚበዘብዙ ስንቶች አሉ መሰላችሁ። ሞራልና ሥነ ምግባርን በመርሳታቸው ከሐሳብና ከዕውቀት ይልቅ ለቁሳዊ ነገር ትኩረት ስላደረጉ ማታለልን ሥራ አድረገውታል።
ምስኪኑን ዜጋ በመሸወድ ሀብት ማካበት እንደ ትልቅነት፣ ክብርና ዘመናዊነት፤ ሀቀኝነትና ታማኝነትን ደግሞ እንደ ኋላ ቀርነትና ጅልነት በማሰብ የማጭበርበር ሥራቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደጉ ነው።
እነዚህ ጮሌዎች በራሳቸው ልክ የሚያስቡ ሕዝቡ በሚፈልገው ሳይሆን እነርሱ በሚፈልጉት፤ በሕዝቡ ማንነት ሳይሆን በራሳቸው ማንነት የሚለኩ ናቸው። ከቶውንም የሕዝቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ መልክእምድር፣ ዳራ አያውቁም። የሕዝቡ ጉዳት ጉዳያቸው አይደለም ፤ብቻ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ጩኸት በማሰማት ኢ-ህጋዊ አስራት በኩራት ይሰበስባሉ።
ቀንና ሌሊት ፖለቲካ እየፈተፈተ የሀሰት እንጀራ መብላት ግን ሲኦል ውስጥ አያስገባ ይሆን? በሰው አተካራ እንጀራውን የሚያበስል ዜጋ የበዛባት አገር! ጽናቱን ይስጥሽ! ይህን ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፤ እኛ ሰፈር ሱቅ ያለው አንድ ነጋዴ ከጭስ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ውዝግብ በመጠቀም ብዙ ኪሎ እጣንና ማጨሻ ሽጧል አሉ። እና የአክቲቪስት ነገርም እንዲሁ ነው። እዚያ ማዶ እሳት ሲቀጣጠል ውሃ አቅራቢ መስሎ የራሱን ቢዝነስ የሚያሯሩጥ።
ክፋትን፣ ሸርን፣ ተንኮልን፣ መርዘኝነትን፣ ዘረኝነትን፣ መከፋፈልን በአጠቃላይ ትውልድን ባተሌ በማድረግ ፖሊሲ ነድፈው የሚንቀሳቀሱትን መንግስትስ ስለ ምን ቸል አላቸው? ዝምታው ግን የዜጎች ሃብት አላስፈላጊ ቦታ ላይ እንዲፈስ መፍቀድ ይመስለኛል። በእርግጥ አቅምን በትልቁ ከሚፈትኑ ሌሎች ጉዳዮች አንጻር ይህ ቀላል ጉዳይ ቢመስልም እንዲህ አይነት ሌብነት መኖሩን ሪፖርት ማድረግ ለጥንቃቄ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
በዚህ መንገድ ስለሚያጭበረብሩ ሰዎች ሳስብ አንድ የቆየች ተረት ትዝ አለችኝ። “እማዬ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ” የምትለዋ። እነዚህ ጮሌዎች በእንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ ከገቡ ቆይተዋል። ይኸው ልማድ ሆኖባቸው ከመቆየቱ የተነሳ መታወቂያቸው ላይ ራሱ ሥራ የሚለው ቦታ ላይ “አጭበርባሪ” ተብሎ እስኪሞላ እየጠበቅን ነው።
ወገን ቸግሮኛል እርዱኝ ማለት እኮ በልመና ‹‹መርኅ›› ደረጃ ችግር የለውም። በግርግርና መረን በለቀቀ ጮሌነት ህዝብን የመሸወድ ታክቲክ ግን በሞራልም በህግም ሊያስጠይቅ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013