ጽጌረዳ ጫንያለው
ትርፍነሽ ዋልተንጉስ ትባላለች። ቀደም ሲል የመከላከያ ሰራዊት አባል ነበረች። በተለይም በመገናኛ ኦፕሬሽን ሥራዋ ብዙዎች ያውቋታል፤ ያደንቋታልም። እንደውም ከስራ ወዳድነቷና ከታዋቂነቷ አንጻር ገና ትምህርት ላይ እያለች ነው ‹‹ሉሲ›› የሚል ቅጽል ስም የወጣላት።
ባለቤቷም ቢሆን በማዕረግ ከእሷ ቢበልጥም በሙያ ግን ተመሳሳይ ናቸው። በእርግጥ እርሱ በሙያው ውስጥ እየሰራ ይገኛል። እርሷ ደግሞ ሥራውን ለቃለች። ሆኖም ውትድርና ለእርሷ ህይወቷ እንደሆነ ታምናለች፡፡
በተለይ አሁን በባሏና መሰል ጓዶቹ ላይ በደረሰው ጥቃት ሙያውን መልቀቋ እጅግ አስቆጭቷታል። ተመለሱ ቢባል ደግሞ ነብሰጡር በመሆኗ ምክንያት ልታደርገው አለመቻሏ የባሰ ልቧን አሳምሟታል። ግን ባለቤቷ በትግል ሜዳ ላይ በመሆኑ አስደስቷታል።
ያው አሁን ያለበትን ሁኔታ ባለማወቋ ቢያስጨንቃትም። እንግዳችን እንድትሆን የመረጥንበት ምክንያት አሁን የባለቤቷ ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ እንደሆነ አለማወቋና የእርሷ የህይወት ልምድ ለሌሎች ጭምር መጽናኛ መሆኑን ስለተረዳን ነው።
ኮሎኔል ጋሻው ባዘዘው ሞላ ይባላል ። በሰሜን እዝ የአራተኛ ሜካናይዝድ ሁለተኛ ብርጌድ አዛዥ ነው። ጥቃቱ ከደረሰበት አምስት ሰዓት በኋላ አላገኘችውም። በተለይም አሰቃቂው በደል የእርሱም እጣ ፋንታ እንደሚሆን ገምታለች። እናም ይህ ኮሎኔል ማን ነው፤ ምን አይነት ባህሪ ነበረው፤ የአንቺስ የውትድርና ህይወት ምን ይመስል ነበር ስንል ለዛሬ ‹‹ የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናታልና ከህይወቷ ተማሩ አልን።
ልጅም እናት በልጅነት
ትውልዷ ኤርትራ አስመራ ውስጥ ከረን ተብላ በምትጠራ ቦታ በ1977 ዓ.ም ሲሆን ነው። በ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥን ተከትሎ ከኤርትራ ተፈናቅለው ወደ አዲስ አበባ መጡ። በአዲስ አበባ ቆይታቸውም ብዙ መከራን ተጎንጭተዋል። በተለይም ቋንቋ ባለመቻላቸው ላይ ቤተሰቡ ሥራ የሌለው መሆን እጅጉን ሲፈትናቸው የቆየ ምክንያት እንደነበር አትረሳውም።
የእንግዳችን ወላጅ አባት የደርግ ወታደር ሲሆኑ፤ እነርሱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እርሳቸው በዚያው ቀርተዋል። ብዙም ሳይቆዩም በዚያው ህይወታቸው አልፏል። እናም ለእናት ብዙ ስቃይ መግጠም ብቻቸውን ልጅ ማሳደግ መክበዱም አንዱ ነበር። ግን እግዚአብሔር ደግ ነውና ከመልካም ሰው ጋር አስተዋወቃቸውና ለልጃቸው ዳግም እውነተኛ አባት እንዲያገኙ ሆኑ።
እንደውም ለባለታሪካችን የስም እንጀራ አባት ሆኑ እንጂ ወላጅ አባት ከሚያደርገው በላይ ነበር የሚያደርጉላት። እርሷም ቢሆን ወላጇ እንደሆኑ ስለምታስብና ስለምትወዳቸው ዛሬ ድረስ በስማቸው እንድትጠራባቸው ሆናለች።
እርሳቸው ለእርሷ አባት ብቻም አልነበሩም። የውትድርና ሙያ መምህሯም ናቸው። በእርሳቸው አለባበስ፣ የውትድርና ሙያ ፍቅር ሁልጊዜ ትሳባለችም። ወደ ሙያው ውስጥ የመግባቷም ምስጢር ይኸው ነው። እናም ስለእርሳቸው መናገር አይሰለቻትም። በተመሳሳይ የእናቷም ፍቅር ለእርሷ ሀያል ነው። ከህጻንነቷ ጀምራ ለእርሷ የምታደርገው እንክብካቤና ርህራሄዋ ስሜቷን በሙሉ ይገዛታል።
በተለይም በስድስት ዓመቷ ከዚያ በመምጣቷ አዲሱ ከተማ ቶታል አካባቢ እድገቷን ስታደርግ ለእርሷ መኖር ሹርባ እየሰራች ጭምር ለፍታላታለች። ብዙ መስዋእትነትም ተከፍሎባት ዛሬ ላይ እንደደረሰች ታስታውሳለች። ስለዚህም ስለእናቷ ውለታ ለመናገር አንደበት እንደሌላት ታስረዳለች።
እነትርፍነሽ አዲስ አበባ ሲገቡ ቋንቋ ለመቻል እንኳ ፈተና ሆኖባቸው እንደቆየ ታነሳለች። የእናቷ ቶሎ ስራ አለማግኘት ከዚህ አንጻር እንደነበር አጫውታናለች። ግን ሁኔታዎች ባሉበት አይቀጥሉምና አባት ጎሽና ርግብ የተሰኘ የህዝብ ማመላለሻ ውስጥ በሹፍርና እናት ደግሞ በሹርባ መስራቱ ቤቱን ሙሉ እንዲያደርጉ አስቻላቸው።
የእነ ትርፍነሽ አባት እንደወላጅ አባቷ ሁሉ የደርግ ወታደር ስለነበሩ ቤቱ በወታደራዊ ስርዓት ነው የሚመራው። እናም ልጆች የተባሉትን ከማድረግ ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም። እርሷ ወንዳወንድ ባህሪ ቢኖራትም ከአባቷ ትዕዛዝ ግን ፈቀቅ ብላ አታውቅም።
በዚህም ጎበዝ ተማሪ፣ ጎበዝ የቤት ውስጥ ሰራተኛና ታዛዥ እንድትሆን አድርጓታል። በተለይ የአርብ አርብ የደብተር ፍተሻው ብዙ ነገራቸውን ያስተካከለላቸው እንደነበር አትረሳውም።
ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ በመሆኗ ደግሞ ከትምህርት ቤት መልስ በፈረቃ በቤት ውስጥ የማትሞክረው ሥራ የለም። መሞከርም ብቻ ሳይሆን ጠዋት ተነስታ እንደ እናት ለቤተሰቡ በሙሉ ምግብ ታዘጋጃለች። ታናናሽዎቿንም የመንከባከቡ ግዴታ የእርሷ ኃላፊነት ነው። እናም ገና ብዙም ሳታድግ ታናናሽዎቿን እንደ እናት መንከባከቧ ዛሬ ድረስ እህቶቿና ወንድሟ እናቴ እንዲሏት አድርጓታል።
እንግዳችን እናት ብቻ ሳትሆን ጨዋታ ወዳድም ነች። በዚህም ምንም እንኳን በቤት ውሎዋ ጊዜ ባታገኝም በትምህርት ቤት ቆይታዋ ግን የምትወደውን ሁሉ ተጫውታ ነው ያሳለፈችው።
የማትሞካክረው የጨዋታ አይነት አልነበረም። በተለይ የእግር ኳስ ጨዋታ በጣም ትወዳለች፤ የሚያክላትም አልነበረም። በተመሳሳይ በሚኒሚዲያም ትሳተፋለች። የምትጽፋቸው ግጥሞችና ልቦለዶች ብዙዎችን የሚስቡ ነበሩ።
ትምህርት
የትምህርት ሀሁ የተጀመረው አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ነው የጀመረው። እስከ አስረኛ ክፍልም እዚሁ ተምራ ትምህርቷን ቋጨች። ከዚያ ከ10ኛ ክፍል በኋላ የሙያ ትምህርት የተከታተለች ሲሆን፤ ኮምፒውተር፣ የምግብ ሙያ ተምራ ሰርተፍኬቶችን አግኝታለች። ከዚያ ሁልጊዜ የልጅነት ህልሟ የሆነውን ውትድርና ተቀላቅላ እንድትማር ሆናለች።
የመጀመሪያ የውትድርና ስልጠና የወሰደችው ብርሸለቆ ሲሆን፤ የገጠሟት አመራሮች እናትን የሚያስንቁና ሙያውን አብልጠው የሚያስወድዱ በመሆናቸው የበለጠ በሙያው ላይ እንድትመራመርና የተሳለች ወታደር እንድትሆን አግዟታል። ስምንተኛ ብርጌድ አራተኛ ሻለቃም ውስጥ በመሆኗ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ እንዲሆንላትም አስችሏታል።
በውትድርና ትምህርት የፖለቲካ ትምህርትም አንዱ በመሆኑ በፖለቲካው ዘርፍ በምታደርገው ተሳትፎና የትምህርት አቅሟ ከብዙዎች አድናቆት የሚቸራት ባለታሪካችን፤ እጇን አውጥታ ለመመለስ በተዘጋጀችበት ወቅት ነበር ድንቅነቷ የተነገራት።
ይህ የሆነው ደግሞ ድንቅ ነሽ ፣ ልዩ ነሽ ለማለት ‹‹ ሉሲ›› የሚል ቅጽል በማውጣት ነው። በወቅቱ ሰራዊቱ ብዙም አልተተዋወቀም ነበርና ትርፍነሽን ትቶ በወጣላት ቅ ጽል ስም መጥራት እንደጀመረም አትረሳውም።
ይህ ስሟ ብዙ ነገር እንዲያጋጥማት እንዳደረጋት የምታነሳው እንግዳችን፤ ከሁሉ የሚገርማት እናቷ በትክክለኛ ስሟ ፈልገዋት ማጣታቸውና በሉሲ ስሟ ሥራ ተመድባ መስራቷ ነው። የጓደኞቿማ አይነሳ። ግን ስሙን ስለምትወደው ዛሬ ድረስ በማህበራዊ ድረገጽ እንድትጠቀምበት እንደሆነች አጫውታናለች።
ቀጣዩ የትምህርት ጉዞዋ የሚወስደን ቢሾፍቱ ላይ ሲሆን፤ በረጅም ርቀት ኦፕሬተርነት ለአራት ወር ያህል ሰልጥናበታለች። ከዚያ ወደ ሁርሶ ተጉዛ በዚሁ የሙያ አይነት እና በምስጢር ዙሪያ ለአራት ወር ሰለጠነች። ትምህርቱ ሲጠናቀቅም ዳግም ወደ ቢሾፍቱ ተመልሳ በአድቫንስ ዲፕሎማ በረጅም ርቀት መገናኛ ግንኙነት እንድትመረቅ ሆነ። ከዚህ በኋላ ግን ትምህርቷን አልቀጠለችም።
ውትድርናን በሥራ
ውትድርናን ኑሮ እንጂ ሥራ እንዳልሆነ የምታምነው ትርፍነሽ፤ በህይወቴ ደስተኝነቴን ለማጣጣም መጀመሪያ የገባሁት ማዕበል መካናይዝድ ስምንተኛ አደይ አገራይ ውስጥ ነው። አሁን ማዕከላዊ ስለፈረሰ ደቡብ እዝ የተባለው ውስጥ። እናም በዚህ ቦታ ለሦስት ዓመት ያህል አገልግያለሁ። ግን የገጠመኝ አለቃ በጣም ጋጠወጥና ሴቶችን የሚያስቸግር በመሆኑ ፈተናዬ በዝቶ ነበር። ከዚያ ውጪ ያሉት ጓዶቼን ሳይ ደግሞ ችግሩን እረሳው ነበርም ትላለች።
ባለታሪካችን ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታዋ እጅግ የጠነከረ ነው። ሆኖም እርሱን ግን ባለው ባህሪ አትቀርበውም፤ ልክልኩንም ትነግረዋለች። ስለዚህም በምትሰራው ሁሉ አይረካባትም፤ ይበልጥም ተባራ ማየትን ይፈልግ ነበር። በዚህም ሀላፊነቱን ተጠቅሞ ለሴቶች የማይገባ ቦታ ጭምር ይልካታል።
እንዳሰበውም አንድ ቀን ኢትዮጵያ ከምትተማመንባቸው ምሽጎች አንዱ በሆነውና ወጥቶ ወርዶ ለመመገብ በሚያስቸግርበት ጎሶማ ምሽግ ላካት። ይህንን ሥራውን ደግሞ ማንም አልተስማማበትም ነበር። ግን ተቆጪ የሌለው ስለነበር በእንቢታ ትወጣው በሚል ከመድፈኛ አስተኳሾች ጋር እንድትሰራ ፈረደባት።
እርሷ በጣም ቀጭንና ምግብ ላይ ችግር ያለባት ነች። በዚያ ላይ እርሱ በሚያደርገው ነገር ትጨናነቅ ነበር። ግን ይህንን ሁሉ እያወቀ እንደላካት አትረሳውም። ነገር ግን ሳይደግስ አይጣላ እንዲሉ በዚያ ያሉ ጓዶቿ በሙሉ ያግዟት ነበር። ለ15 ቀን ግዳጅ ላይ በቆየችበት ጊዜም እነርሱ ካመጡላት ትመገባለች።
ካልሆነ ደግሞ ህመሟ እንዳይብስ በማሰብ ታች ሳትወርድ ስኳር በውሀ እየበጠበጠች ምግቧ አድርጋ ትውላለች። እንደ አዛዡ እሳቤ እርሷን ወድቃ ማየት ነበር። ነገር ግን እንደአሹ አይነት ሰዎች በሥሯ ስለነበሩ አልተረታችም። አብረዋት ተኝተው እንኳን ከእህትነት ውጪ አያስቧትም ነበርና በህይወት ለመቆየቷ የእነርሱ እጅ እንዳለበትም አጫውታናለች።
በወታደር ህግ ቢርብም ቢጠማም እንዲሁ እንቅልፍ ቢጥልም የማይታለፉ ነገሮች አሉ የምትለው ትርፍነሽ፤ ከእነዚህ መካከል አንድ ሰከንድ ማርፈድ አለመቻል አንዱ እንደሆነ ታነሳለች። በተለይ በኦፕሬተር ስራ ላይ የተሰማራ ሰው ሰዓት ልዩ መለኪያው ነው። እናም ጥንቁቅነቷን አስጠብቃ መቀጠል ግዴታዋ ነበርና እንዳደረገችው ትናገራለች።
አንድ ቀን ያለ ስህተቷ ስህተት የሚሰጥ አጋጣሚ የተፈጠረባት ባለታሪካችን፤ የወንድ ጓደኛዋ የፍቅር ደብዳቤ ጽፎላት ኖሮ ክፍለጦር ላለው ጓደኞች ሰጥቶ እርሷ ጎሳማ ምሽግ ውስጥ እያለች እንዲነበብላት ሆነ።
አጋጣሚውን የወደደው አዛዥም ንግግሩ እንዲጠለፍ አደረገ፤ በደብዳቤው ሁሉም ዘና ያለበትና ምንም ምስጢር ያልያዘ ስለሆነ ሁሉም እንኳን ደስ አለሽ ሲላትም እንደነበር ታስታውሳለች።
ሆኖም አዛዡ ምስጢር አወጣሽ ፤ የአገር ክህደት ፈጸምሽ ሲል የተቀዳውን ድምጽ እያስደመጠ መክሰሱን ተያያዘው። እንድትፈርምም ያስገድዳት ጀመር። እርሷ ግን ያለምንም ስህተት መፈረም እንደማትፈልግ ገለጸች። መግደልም ከመጣ እቀበለዋለሁ አለች። ሁኔታው የሚያስከስሳት እንዳልሆነ ሲረዳና እንዳላዋጣው ሲያውቅ ነገሩን ወደ ዲስፕሊን መራው። በዚህ ደግሞ አዛዡም ፈራጁም ራሱ ስለነበር ማዕከላዊ ብቸኛ ታሳሪ ሆና እንድትቆይ አደረጋት።
ለስሙ ማረሚያ ቤት ገባች ተባለ እንጂ ወደ አባቷ ቤት
እንደሄደች እንደተሰማት ያጫወተችን ትርፍነሽ፤ በአንድ ክፍል ውስጥ መታሰሯ ልዩ ቢያደርገውም እንክብካቤው ግን ከቤተሰብ ቤት አይለይም ነበር። እንደውም ከተፈታች በኋላ እዚያው መስራት እንደምትፈልግ ገልጻ እንደነበርና እንዳልተፈቀደላትም ነግራናለች። ግን ይህም ሆኖ የኦፕሬተርነት ሙያውን ከእርሱ ጋር ሆና እንድትሰራ አልተገደደችም። በዚያ ምትክ የአስተዳደር ሥራ ውስጥ ገብታ እንድትሰራ ተፈቀደላት።
ይህ ቦታ ፍጹም ወታደራዊ ፍቅር ያለበት ቢሆንም አንዳንዶች የሚያሳዩት ጸባይና የህመሟ ጉዳይ ለመስራት አላስቻለምና መልቀቂያ አስገብታ የህመም የክብር ስንብት ደብዳቤ ተሰጥቷት በክብር መከላከያን እንድትለቅ ሆናለች።
ውትድርና ለእርሷ
ውትድርና በብዙ መልኩ የሚገለጽ ሙያ ሲሆን፤ ልዩ ልዩ ባህሪያት ያሉት ነው። በተለይ እውነተኛ ምስጢር ጠባቂነትን ያስተምራል። ስለዚህም ወታደራዊነት ይህንን ባህሪ የተላበሰ ነው። በተመሳሳይ ግብረገብነት የሚገነባበት ትምህርት ቤትም ነው። በተለይ አንድነትን ከልብ የሚያስቀር፤ የግል ፍላጎትን ለመሠዋት የሚያዘጋጅ፣ ከራስ በላይ ለአገልጋይነት መታዘዝን የሚያስተምር እንደእርሱ ሙያ ያለ አይመስለኝም ትላለች።
ቀጠል አድርጋ ደግሞ ውትድርና ጽኑነት እና ክብርን የሚያስተምር መምህር፣ የአገር መሪ ጭምር የሚዘጋጅበት ቦታ፣ አካላዊ ጥንካሬን ሰጥቶ ጤና የሚያስጠብቅ ጤና ሚኒስቴርም ነው። ከሁሉም በላይ የአርበኝነት ጽንስ ሀሳብ ጠንሳሽ፣ የሀገር ታሪክ ቀማሪ ቤተመዘክር ነው።
የፍቅር ጥግ የሚታይበት ፍቅር እስከመቃብር የሆነበት ህይወትም ነው። ስለዚህ ይህንን ሙያ ሁሉም የሚመርጠው ይህንን ባህሪ ስለተላበሰ ይመስለኛልም ብላናለች። ምክንያቱም እርሷ የአስረኛ ክፍል ትምህርቷን ልክ እንደጨረሰች በ1997 ዓ.ም ሙያውን የተቀላቀለችው ይህንን ልዩ ነገር በአባቷ አማካኝነት ስለተረዳች ነው።
ከጉለሌ ክፍለከተማ ከተመለመሉት መካከል አንዷ ሆና ሙያውን አክብራ ለዓመታት የታገለችውም ለዚህ ፍቅሩ ነበር። በእርሷ የውትድርና ጊዜ የተባለችውን ስላገኘችው ደግሞ ደስተኛም ነበረች። ዛሬ ግን ጨካኝ የሆኑ ሰዎችን እንዴት እንዳመረተ ሊገባት እንዳልቻለ ትናገራለች።
ስለሙያው ክብር ሁለት ነገሮች በደንብ እንድታውቅ አድርገዋታል። የመጀመሪያው የአባቷም ሲሆኑ፤ ሁለተኛው በማንበብ ያገኘችው እውቀት ነው። ከዚያ ደግሞ በህይወት ኖራበት ሙያውን ከፍ አድርጋ እንድታየው አድርጓታል። ዛሬ በሆነው ነገር የተደናገጠችውም ለዚህ እንደሆነ አጫውታናለች።
የውትድርና ፍቅር ከቤተሰቤ የጀመረ ቢሆንም ብርሸለቆ በር ላይ ገና ስትደርስ ያነበበችው ጥቅስ የበለጠ ፍቅሩን የጨመረባት እንደሆነ የምታስረዳው ባለታሪካችን፤ ስትወጣ ስትገባ ‹‹ላብ ደምን ያድናል›› የሚለውን የዘወትር መፈክሯ እንድታደርገው አስገድዷታል። ምክንያቱም እንደ እርሷ አመለካከት ላብን ጠፍ አድርጎ መስራት እርካታን ብቻ ሳይሆን ህይወትንም ያድናል። ስለዚህም በእዚህ መንፈስ ስትሰራ እንደቆየች ትናገራለች።
‹‹የውትድርና ህይወት ራስን ለሰዎች ደህንነት አሳልፎ መስጠት፤ ስለ ሰው ልጅ መጨነቅ ስለሆነ በጣም የምወደው ሙያ ነው›› የምትለው እንግዳችን፤ ውትድርና የሥነምግባር ትምህርት ቤትም ነው።
ሰውኛ ባህሪን አላብሶ ከአገር ወዳድነት ጋር የሚያጣምርም ነው። ውትድርናው የሙያ ባለቤት የሚያደርግም ነው። በዚህም አገር በጥበቃ ብቻ ሳይሆን በሙያም እንድትበለጽግ የሚያግዝ ሙያ ነውና ወታደር በመሆኔ ሁልጊዜ ደስተኛ ነኝም ትላለች።
ቁጭት
ከእንባ ጋር እየቀላቀለች ነበር ይህንን ጊዜ እንዴት እያሳለፈች እንደሆነ የነገረችን። ምክንያቱም ያለችበት ሁኔታ ለአገሯ የምትታገልበት እድልን አይሰጣትም። እናም ሁሉም ነገር አለኝ፤ በተለይም የውትድርና ፍቅሩ ብላ እንዳትዘምት አድርጓታል። ነፍሰጡር ሆኜ እንኳን የህወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን የግፍ ጭፍጨፋ ብታገለው እረካ ነበር። ምክንያቱም ውትድርና ጦርነቱ ውስጥ መግባትም ብቻ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ምግብ አብስሎ ማቅረብም ትግል ነው። ግን ይህም ቢሆን ወራት ስለሆኑ የቀሩኝ አልችልም ትላለች።
ሌላው ቁጭቷ ወታደር ሆኖ ውስጥን በተግባር አለመግለጽ መቻል ምን ያህል እንደሚያም እያየሁ መሆኑ ነው ትላለች። ጽሁፍ ሆነ እንጂ የሆነውን ነገር ጮኬ ብገልጸው ምንኛ ያስደስተኛልም ብላናለች። ተግባሩ እናት በልጇ ላይ የማትፈጽመው አይነት ነው። ታዲያ በራሱ በመከላከያ ውስጥ ያለ ጓደኛ ይህንን ያደረገው እንዴት አስችሎት ነው ስትል ትጠይቃለች። ቀጥላም እንባዋን ሳታቋርጥ እያወረደችና ሲቃ እየተናነቃት ሰዎቹ ከሌላ አለም የመጡ መሆናቸውን እንዳምን አስገድዶኛልም ብላናለች።
ባለቤቷ ጥቃቱ ሲደርስ እያወሩ የነበረ ሲሆን፤ ከዚያኛው ወገን መልዕክት እየተነገረው ሳለ ነበር ስልካቸው የተቋረጠው። እንደውም ባልና ሚስት ሲኮን የእርሱ ህመም ጭምር ይሰማልና ችግር እንደደረሰበት ወዲያው ነበር የገባኝ ትላለች። እናም እንደሚያጠቋቸው ገና ከእርሱ ተለይቼ ሳልመጣ አውቀዋለሁ። ምክንያቱም ሆስፒታል ውስጥ ሳይቀር ተሰብስበው ሲያሴሩ አውቃቸዋለሁም ትላለች።
‹‹የሚያሳዝነው ጥቂት የጦሩ አባላት በብሔራቸው እየተመራረጡ የሚያደርጉት ነገር የሁልጊዜ ስጋቴ ነበር። ሰራተኛ ተብላ የምትቀጠረው ሳትቀር ሰላይ ነበረች። እናም ለባለቤቴ ሁልጊዜ እነግረዋለሁ። ግን እርሱ በወንድሙ መከዳትን አያውቀውምና ተያቸው ይለኝ ነበር›› የምትለው ባለታሪካችን፤ ‹‹ና ብዬ ሁልጊዜ ስጨቀጭቀው እኔ ፈሪ አይደለሁም። እነርሱን ፈርቼ እጄንም ሰጥቼ የ30 ዓመት ታሪኬንና የልጆቼን ስም አላበላሽም። እስከመጨረሻው ተፋልሜ ለኢትዮጵያዊነቴ እሞታለሁ፤ የውትድርና ሙያዬንም አስከብራለሁ›› ማለቱ ለዚህ እንዳበቃውም ታስረዳለች። በዚህም እንደምትቆጭ አጫውታናለች።
ሰሜን ዕዝን ጠይቁልኝ
እንባዋ በጉንጯ ላይ ኮለል እያለ ጉንጮቿን እየገመሰ መውረዱን ቀጥሏል። እኛም ብንሆን አጅበናታል። ምክንያቱም የምታወጣቸው ቃላት እንባን የሚያግዱ አይደሉም። በተለይ በሚያምኑት መከዳትን የገለጸችበት ሁኔታ መቼም ከአዕምሮ አይጠፋም። ከነገረችን ውስጥ ለማንሳት ያህል ጥቂቱን እንበል።
‹‹ባለቤቴ ገና ከቤቱ ሲወጣ ጀምሮ ለሙያውና ለአገር ክብሩ ሲል በጀግንነት እንደሚሞት አውቃለሁ። በመሞቱ አላዝንም። ምክንያቱም ታማኝ ወታደር ነው። ውትድርና በባህሪው ተገዶ ሳይሆን ተፈቅሮ የሚገባበት ስለሆነ ሞት ክብር እንጂ ውርደት አይሆንም። ከዚያ በላይ ደግሞ መጀመሪያም ሲወጣ ለአገሩ ፍቅር እንደሆነ አውቀዋለሁ። እናም ሞት በራስ ወዳድነት ሲሆን እንጂ በአገር ወዳድነት የሚሞቱት አይነት ከሆነ ፍቅር እስከመቃብር ነው። ግን ጓድነት ከእናት በላይ መሆን ሲኖርበት በራስ ወዳድነት ተሸንፎ ሲታይ እጅጉን አመመኝ›› ያለችው አንዱ ነው።
‹‹ሴትን አቅፎ እየተኛ ከወንድምነት ውጪ የማያስበው መከላከያ እንዴት ይህንን አደረገ ብዬ ልመን። በዚያ ላይ በክብር ተሰውቶ ቢሆን መቼም ቢሆን አላለቅስም፡፡›› የምትለው እንግዳችን፤ አሁን ላይ ፈቃድ እንደነበረውና ልጇን ስትገላገል ከጎኗ እንደሚሆን አስባ ነበር። ነገር ግን በችግሩ ምክንያት አይደለም መምጣት ያለበትም ጠፍቷታል። በእርግጥ በአለም ላይ ጭምር የማይሆነውን አረመኔ ተግባር ፈጻሚዎችን መታገል መቻሉ አስደስቷታል። በዚያው ልክ ደግሞ በጣም ወንድሜ በሚሉት መከዳታቸውና ደስታቸውን መነጠቃቸው መራር ሀዘን እንዲሰማት አድርጓታል።
በወታደር ህግ ጓዳዊ ፍቅር በጣም ከባድ ነበር። ፍቅር ብቻ ተብሎ እንኳን የማይታሰብበት። ግን ዛሬ ይህ ተቀይሮ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲህ ሆኑ የሚለውን ስሰማ ህመሙ ጸናብኝ ያለችን ትርፍነሽ፤ ነፍሰጡር ሆኜ ወሬ ባይገባ ገብቼ ብጋፈጠው እጅጉን እደሰት ነበር። አብሮኝ እያደረ ጥንካሬ ሲሰጠኝ የነበረውን ሰው ሲያርደኝ እመለከት ነበር ትላለች።
የእናት ልጅ ሊጨቁን ይችላል፤ ወታደር ግን በምንም መልኩ ይህንን ያህል ጭካኔ አያሳይም። ምክንያቱም ውትድርና እንደ እነ ሻምበል ሞገስ አይነትን ያፈራ ነው። እርሱ እንዳይሞትም እጸልያለሁ። ምክንያቱም የእረፍት ጊዜው ደርሶ ለዓመታት የተለያቸውን ቤተሰቡን ለማየት ጓጉቶ ሳለ የሙያ ግዳጅ ተጣለበት። ሆኖም ላለመፈረም ሽንጡን ገትሮ ተከራከረና የሚያሸንፈው ነገር ገጠመው። ይህም ባለቤቴ ሴቶችን ባንዲራ አሲዞ እንዲንበረከኩና እንዲለምኑት በማድረጉ ለባንዲራው ክብር ሲል እያለቀሰ እናትና ሚስቱን እንዲሁም ልጁን ትቶ ግዳጁን ተቀበለ። ግን እንዲህ ያሉ ወታደሮች በጨካኙ ጁንታ ግፍ ደረሰባቸውም ትላለች እንደ ጎርፍ የሚወርደውን እንባዋን ሳትገድብ።
ወታደርነት ገና መለዮውና ሬንጀሩ ሲደረግ ጀምሮ ነው ፍቅርንና መዋደድን አብሮ የሚያለብሰው። ስለዚህ ምንም ባይኖርሽ ታማኝና ሌብነትን እየተጸየፍሽ በሙያሽ ደስተኛ ትሆኛለሽ። ለዚህም ነው ባለቤቴ በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ፍቅርን ይዞ ዓመታትን ያሳለፈው። የጁንታው አመራሮች ግን ከዚህ የተለዩ ናቸው። የትግራይን ህዝብ የሚወዱ መስለው ከቆዩ በኋላ ህዝቡ የሚጠቀምበትን መሰረተ ልማቶች አፈረሱ። ለትግራይ ህዝብ ካለቻቸው ደመወዝ ላይ ቀንሰው ትምህርት ቤትና ሆስፒታል ሲሰራ የቆየን መከላከያ አረዱ።
በውትድርና ህግ በተኛበት መግደል አይደለም በጀርባ መምታት አይቻልም። በእነርሱ ዘግናኝ ሥራ ግን ህዝቡ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዳይሄድ አደረጉ። በእርግጥ ከእርሱ ይጠበቃል። ምክንያቱም ወትድርናን አልተማሩትም። ዲስፕሊንም አያውቁም። ካልተማረ ደግሞ መጥፎ ህሊና እንጂ ደግ ነገር ማምጣት ከባድ ነው። የትግራይ ህዝብ ግን ልዩ ነው። ማብላት እንጂ ማረድ አያውቅበትም። ይህንን የፈጸሙትን ወጥቶ ቢገላቸው እንደሚመኝ ይሰማኛል። ምክንያቱም እርሱን ጨምሮ ያሳፈረውን ወራዳ ተግባር ፈጽሞበታል። ስለዚህም ሰራዊቱ ውስጥም ሆነ ህዝብ ጋር ያሉ ትግራዊያን በጣም ደጎች ናቸው።
በእነሱ አጸያፊ ተግባር አብረው ሊጨፈለቁ አይገባቸውም ትላለች። እነዚህ አካላት ማንም ሞት አይመኝላቸውም። ሥራቸው በራሱ ይገላቸዋልና እንፍቀድላቸውም ብላናለች።
ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ
በውትድርናው አለም በሚሰሩበት ጊዜ ነው ትውውቃቸው የጀመረው። ሆኖም እርሱ ማንንም የማይቀርብ፤ የውስጡን መናገር የማይወድና ለስራው ታማኝ ለባንዲራና ለአገሩ ክብር አንገቱን ለሰይፍ የሚሰጥ ጠንካራ ወታደር ነው። እርሷ ደግሞ በተቃራኒው ተጫዋችና ከሁሉ ጋር ተግባቢ ነች። እናም የማይናገረውን በማናገር ነበር የቀረበችው። ይሁን እንጂ በዚያ መስመር ውስጥ ሆነው የፍቅረኝነት ጉዞን አልጀመሩም። እርሷ ከውትድርናው ከተሰናበተች ከዓመታት በኋላ ነበር በፌስ ቡክ ያገኘችው፡፡
መጀመሪያ ሰላምታ ተለዋወጡ። ሁኔታው አዲስ አልሆነባትም። ግን ስሙንና ማንነቱን ለማወቅ ብዙ ተቸግራ እንደነበር ታስታውሳለች። ጓደኞቿን ስጠይቅ ማን እንደሆነ ተረዳች። በዚህም ፌስቡክ ብዙ ተአምር ሰራላቸውና ለዛሬ ትዳራቸው አበቃቸው። ባለቤቷ ኮሎኔል ጋሻው ባዘዘው ሞላ ብዙዎች ከአክብሮታቸው የተነሳ ጋሼ እያሉ የሚጠሩት ነው። እርሷም ብትሆን በጣም ስለምትወደው ጋሼ ብላ ትጠራዋለች።
‹‹ጋሼ ባሌ ብቻ አይደለም፤ እናቴ ጓደኛዬም ጭምር ነው። አንዳንድ ጊዜ መንታ የሆንን ያህልም ይሰማኛል። ምክንያቱም የሆነ ነገር ሲደርስበት እኩል ያመኛል። ለአብነት ከዚህ ቀደም የመኪና አደጋ ደርሶበት በአምስት ደቂቃ ልዩነት ልቤ ሲደነግጥ ዳግም ስደውል ደህና ነኝ ብዙም አልተጎዳሁም ሲል ነበር ያጽናናኝ። እናም የሁለታችን ህመም በእኩል ደረጃ የሚስተናገድ ነው። በሰሜን እዙ ጥቃትም እንዲሁ ተሰምቶኝ ነበርና አውርተናል። ያው አሁን የት እንደገባ ባለውቅም›› ትላለች ስለ ባለቤቷ ስትገልጽ።
አሁን የሁለት ልጆች እናትና አባት ሆነዋል። ሦስተኛውም በመምጣት ላይ ይገኛል። እናም አምላክ ከፈቀደ ሁለቱ አብረው ሆነው ታሪክ እንደሚነግሩን ታስባለች።
መልዕክት
ክስተቱ አሰቃቂ ነገርን ቢያላብሰንም በጎ ጎንም አለው። ተረስቶ የነበረውን ወታደር እንዲታወስ እድል ሰጥቶታል። ለአገሩ ከመሞትም በላይ ቆሞ እጁንና እግሩን አጥቶ የሚሰቃይ ስንት ጀነራል እያለ ማንም ሳያየው ቆይቷል። ግን ጊዜ ሰጠውና መታየት ጀመረ። ስለዚህም ይህ ሁኔታ ሁሉንም በቦታው ያስቀመጠ መሆኑን ትናገራለች። አሁንም ቢሆን እየሰጠነው ያለው ክብር መቀጠል ይኖርበታልም የመጀመሪያ መልዕክቷ ነው።
ሌላው ያነሳችው ነገር እስከዛሬ እርሱ ደመወዝ እየላከላት መቆየቷን አሁን ግን እንደተቋረጠባት ነገር ግን ማንም የሚያያት ባይኖርም ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች። ለዚህ ምክንያቷ ጋሻው መሞቱ ባይረጋገጥም ለአገር እንደሞተ ሁሉ ይህም ልጅ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀላፊነት መሆኑን ስለምታውቅ ነው።
‹‹አሁን ያሉትን አመራሮቻችንን ያትርፍልን እንጂ ከዚህ በላይ ትምህርት ይኖራል ብዬ አላስብም። የብሔር ጉዳይ ያስቸግረናል የሚል እምነትም የለኝም›› የምትለው ባለታሪካችን፤ እንደ አገር የውትድርና ማማ ላይ ደርሰን እያሳየን ያለችንን አንድ አገር እየጠበቅንና እያጎለበትን ወደፊት መራመድ ላይ ማተኮር አለብን የመጨረሻ መልዕክቷ ነውና ተቀበልን። ሃሳቧ ይሳካላት ዘንድ እየተመኘንም ተሰናበትን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013