ኢትዮጵያ በአለም ዋንጫ ለመሳተፍ ባትታደልም በየጊዜው ኢትዮጵያን አጉልተው የሚያሳዩ ኢትዮጵያውያን ግን አልጠፉም። ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን መካከል ደግሞ ለዛሬ ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምዳችን እንግዳ ያደረግነው ኑሮውን በኳታር ያደረገው ኢትዮጵያዊው ሰአሊ ተሰማ ተምትሜ አስራት ነው።
ተሰማ የአለም ዋንጫው ሲጀመር አንስቶ በጥበብ ሥራው የበርካቶችን ትኩረት አግኝቷል፤ በሥራዎቹም ኢትዮጵያን አስተዋውቋል። ኳታርን ያደመቀበትና ኢትዮጵያ በአለም ዋንጫው ገዝፋ እንድትታይ ያደረገበት ሥራውን አሀዱ ያለው ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ አባት፣ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ባለውለታ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የበላይ ጠባቂ እንዲሁም የካፍ ፕሬዝዳንት በመሆን ላገለገሉት ታሪካዊው የስፖርት ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስዕል ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ በኳታር አደባባይ ላይ እንድትደምቅ ካደረጓት መካከል እርሳቸው በዋናነት ይጠቀሳሉና ነው። ለዚህ ውለታቸውም በስማቸው የስፖርት ማዕከል እስከመሰየም ተደርሷል። እናም ሁሉም አፍሪካዊ ተደስቶ ሞሮኮን በደገፈበትና በግማሽ ፍጻሜ ከአራቱ ውስጥ ሆና በገባችበት ወቅት ሰዓሊውም እርሳቸውን ይዞ ብቅ አለ።
‹‹እኔ የእርሳቸው ልጅ ነኝ፤ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ልጆችን ታፈራለች›› እያለም ሰበከ። አለምም ሰማው፤ ተደነቀበት። መነጋገሪያም ሆኖ ሰነበተ። ሞሮኮ የአለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ደርሳ ታሪክ ስትሰራ ትልቁን ሚና የተጫወተውን ኮከቧን ሀኪም ዚያችን ከሳለበት ምስል ስር የይድነቃቸውን ምስል አሳርፎበትም ነበር ብቅ ያለው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን አስከብሯታል። ለዚህ ሥራው ደግሞ በታዋቂው የኳታር ኢንተርናሽናል አርት ፌስቲቫል (QIAF) ላይ የአፍሪካ ብራንድ አምባሳደር ለመሆን በቅቷል። ማፕስ ኢንተርናሽናል የሚባል ትልቅ የአርት ተቋምም እንዲሁ በኳታር የአፍሪካ ብራንድ አምባሳደር አድርጎታል። ለ2022 የዓለም ዋንጫ ላይ በበጎ ፈቃደኝነት እንዲያገለግሉ ከተመረጡ ኢትዮጵያውያንም አንዱ ሆኗል።
እ.ኤ.አ በ2022 ላይ በተካሄዱት የኳታር ኢንተርናሽናል የአርት ፌስቲቫሎች ዓለም ዋንጫውንና አዘጋጇን ኳታር በሚያስተሳስሩ ጭብጦች የሰራቸው ስዕሎች በኳታር ንጉሳውያን ቤተሰቦች፤ መንግስታቸው፤ የስነጥበብ ተቋማት መሪዎችና የኢትዮጵያ ማህበረሰብም ተደንቀውበታል። ምስጋናም ተችሮታል። በዚህ ሥራው ኢትዮጵያን በልጆቿ እንድትኮራም አድርጓታል። ምክንያቱም በያሉበት ቦታ ዲፕሎማት የሚሆኑና ስለአገራቸው የሚሰብኩ ልጆች እንዳሉ አንዱ ማሳያ ሆኗል። ለመሆኑ ተሰማ ማን ነው፤ አስተዳደጉና ሌሎች የሰራቸውስ ሥራዎች ምን ይመስላሉ ካልን መልሱን እንካችሁ።
ትንሹ ተሰማ
ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። እንደማንኛውም ልጅ ቤተሰቡንና ጎረቤቶቹን በመታዘዝ የልጅነት ጊዜውን አሳልፏል። በተለይም ትልልቅ ሰዎችን ሲያገኝ አይቶ ማለፍ አይሆንለትም። የተሸከሙትን ተቀብሎ ፣ የደከሙትን ደግፎ ቤታቸው ያደርሳል። ከአዘዙትም በደስታ ይላካል። ይህ ባህሪው ደግሞ የዳበረው ከእናት አባቱ እንዲሁም እንደናትና አባት ሆነው ከአሳደጉት ጎረቤቶቻቸው የተማረው ነው። አሁንም ድረስ ከእነርሱ የወረሰው ነገር እንዳለ ያስባል።
በተጨማሪ መልካም ስብዕናውን ያዳበረበት ሌላው ቦታ የቄስ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ከትምህርቱ ባሻገር ብዙ መልካም ነገሮችን ተምሮበታል። ኢትዮጵያዊነትን በሚገባ ያየበትና የኖረበትም ሆኖለታል። ዛሬ እንዳይቸገር ለሰዎች መልካም እንዲሆን ያስቻለውም ይህ ነገሩ እንደሆነ ያምናል።
ተሰማ በሥራዎቹ ሁሉ ከመልካምነት ውጪ ሌላ እንዳያስብ ያደረገው መልካሙን ሁሉ እየተማረ በማደጉ ነው። በተለይም በሥዕል ስራው ውስጥ የሚንጸባረቀው ነገር በሙሉ ሰላም ብቻ እንዲሆን ያደረገው በዚህ አስተሳሰብ መቀረጹ እንደሆነ ያምናል። የልጅነት ፍላጎቱም በዚህ ላይ የተንጠላጠለው ለዚህ ነው። እርሱ ስዕልን መሳል ሲጀምር መጀመሪያ የሳለው መልካም አብሳሪዋንና ሰላም ምሳሌዋን እርግብን ነው። ከዚያ በጎነት የበዛበትን የገጠሪቱን ኢትዮጵያ መሰባሰብ ወደማሳየቱ ገባ።
ትንሹ ተሰማ የህጻናት መዋያ በሚቆይበት ጊዜም ሥዕል መለያው ነበር። በጣም የሚያስገርመው መምህሩ ጻፉ ያሏቸውን ቃላትና ፊደላት ሳይቀር ከማንበብ እና ከማጥናት ባሻገር በስዕል መልክ ፊደላቱን ያስቀምጣቸው ነበር። ይህ ሁኔታው ደግሞ የወደፊቱ ባለተሰጥኦ እንደሆነ ፍንጭ ያሳየበት ነው። ምክንያቱም በጣም በሚወደው ሥዕሉ አማካኝነት ትምህርቱን መከታተል መቻሉ ነው።
ትምህርት
ተሰማ ትምህርቱን አሀዱ ያለው በቄስ ትምህርትቤት ሲሆን፤ ቀለም ከለየና በቄስ ትምህርት የሚፈልገውን እውቀት ከጨበጠ በኋላ መዋለ ሕጻናት ገባ። ከዚያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ኮተቤ አካባቢ በሚገኘውና ብዙዎችን በአፈራው ደጃዝማች ወንዲራድ ትምህርት ቤት ገባ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በዚሁ ትምህርትቤት ነው ያጠናቀቀው። በዚህ ቆይታው ደግሞ የደረጃ ተማሪ ብቻ ሳይሆን በስዕል ጥበቡ ትምህርት ቤቱን የሚያገለግል ልጅ ነበር። ለትምህርት አጋዥ የሆኑ ስዕሎችን በመሳል አበርክቶ አድርጓል።
ይህ ብቃቱ ደግሞ ከልጅነት ሕልሙ እንዳይወጣ አድርጎታል። እናም የ12ኛ ክፍል ውጤቱ ጥሩ ቢሆንም ሌሎች የትምህርት መስኮችን ለመምረጥ አልፈለገም። በስዕሉ መስክ ለመማር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጥበባት እና ዲዛይን ትምህርት ቤት በአሁኑ አለ ፈለገ ሰላም የስነጥበብ ትምህር ቤት ተመዘገበ። በመጨረሻም በግራፊክስ ጥናት የትምህርት መስክም ለመመረቅ ቻለ። ለስዕልና ግራፊክስ ሥራውም አጋዥ የሆኑ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስዷል። አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረቱ። ምክንያቱም በእርሱ እምነት ትምህርት ሕይወትም፣ ለውጥም ነው።
ከአዲስ አበባ እስከ ኳታር
ሥራ ከተባለ ጅማሮው የሚሆነው በትምህርት ላይ እያለ የሚያዘጋጃቸው የስዕል ኢግዚቢሽኖች ናቸው።በብሄራዊ ሙዚየም ስዕሎቹን የማሳየት እድል ገጥሞትም እንዲሁ የተሻሉ እድሎችን ያገኘበት ነው። በህፃናትና ወጣቶች ማዕከል እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጀምሮ በፈረንሣይ እና ጣልያን የባህል ማዕከላት በተጨማሪም አዘጋጅቶ በአፍሪካ ህብረት (OAU) እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት UNHCR, UNDP,UNICEF, UNESCO, UNV ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎችን ሰርቷል ።
ከዚያ በቅጥር ደረጃ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራውን ጀመረ። ይህም ቢሆን በምርጫ የተከናወነ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ60 አመታት በፊት ለአውሮፕላኑ ዲዛይነር የሚቀጥረው ከአዲስ አበባ የስነ-ጥበባት እና ዲዛይን ትምህርት ቤት የተማረና የተሻለ ውጤት ያለውን ሰዐሊ ነው። በወቅቱም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዕጩ ሰዓሊያን መካከል ከተመረጡት ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ ሆኖ ሊቀጠር ችሏል። ለአምስት ዓመትም አገልግሏል። በዚያ ጊዜም ቢሆን ያለውን እድል በመጠቀም የሀገር ገፅታ ግንባታ ላይ ይሳተፍ ነበር።
ተሰማ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሰፈር ውስጥ መሸለም፣ መመረቅና መታዘዝ የለመደ በመሆኑ ያ ልምዱ እንዲቆም አይፈልገም። ሰዎች ባያደርጉለት እንኳን እርሱ አድርጎ ይህንን መልካም ነገር ማጎልበት ይፈልጋል። በዚህም በአየር መንገድ እየሰራ ከበርካታ ሀገራት ኤምባሲዎች ጋር ይገናኛል። የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በሚያደርጓቸው መልካም ነገሮች ስዕልን በመጠቀም ለመልካም ሥራዎቻቸው ያመሰግናቸዋል። በዚህም ሁልጊዜ ከፍተኛ አድናቆት ይቸረዋል።
ለአምስት ዓመት በኢትየጰጵያ አየር መንገድ ኤርክራፍት ፔንቲንግ ዲፓርትመንት (የአውሮፕላኑ አርማ ላይ፤ ከቦዲውና ከሴፍቲ ጋር የተያያዙ ስራዎች) ከሰራ በኋላ የተሻለ እውቀት እና ልምድ ለማካበት ወደ ኳታር በማቅናት ኑሮውን በዚያው አደረገ። ሀሳቡ ተሳካለትና በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት አገኘ። በእርግጥ ይህ ነገር የሆነለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለው ታላቅ ስም እንዲሁም ባካበተው ልምድ ነው። እናም ልክ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይሰራ እንደነበረው ሁሉ ኳታር አየር መንገድም ኤርክራፍት ፔንቲንግ ዲፓርትመንት መስራት ጀመረ።
አሁን በ ኳታር አየር መንገድ ስራውን በመስራት ላይ ይገኛል።ተሰማ በአየር መንገድ ሥራው ብቻ የታጠረ አይደለም። ከዚያ ጎን ለጎን ከሙሉ ሰዐሊ በማይተናነስ መልኩ በኳታር ውስጥ ባሉ የስዕል ማዕከላት ውስጥ ይሳተፋል። ኢግዚቢሽን ያዘጋጃል። ምንም እንኳን ኑሮው ኳታር ቢሆንም የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራትን በሥዕል ሥራው ጎብኝቷል። ለምሳሌ፡- ጣልያን፣ እንግሊዝ ፣ ስዊድን፣ፈረንሳይ፣ ሆላንድ፣ አየርላንድ፣ጅቡቲ፣ በመሄድ የስዕል ኢግዚቢሽን አዘጋጅቶ አገሩን አስተዋውቋል።
በኳታር ውስጥ ቀደም ሲል የፊፋ የአረብ ሀገራት ዋንጫ በበጎ ፍቃደኝነት አገልግሏል። በዚያ ባሳየው የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎቱ ደግሞ ለኳታር የ2022 የአለም ዋንጫ በጎ ፍቃደኛ ሆኖ እንዲመረጥ አድርጎታል። ከሀገሪቷ ንጉስ ሼሕ ታሚም ቢን ሐማድ አልታኒ ኸሊፋ የምስጋና ደብዳቤ ተበርክቶለታል። ከዚህም በተጨማሪ በስነጥበቡ ዘርፍ በኳታር ለተከታታይ አራት ዓመታት ማፕስ ኢንተርናሽናል በሚባል ትልቅ የአርት ተቋም በስነጥበቡ ዘርፍ ባበረከተው አስተዋጽኦ በኳታር የአፍሪካ ብራንድ አምባሳደር በመባል ትልቅ ክብርን አግኝቷል። ይህ ደግሞ በግሉ አፍሪካን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርግ አግዞታል። በተለይም አገሩ ኢትዮጵያ ልዩ ትኩርትን እንድታገኝ ከማድረግ አኳያ የድርሻውን እንዲወጣ እድሉን ሰጥቶታል።
የሥዕል ዲፕሎማሲነት
ዲፕሎማሲ ማለት ውጤታማ በሆነ መንገድ ከሌሎች ሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታ ነው። በተለያየ ተወካዮች መካከል የፖለቲካ ግፊት ሳይኖር የሚደረግ የድርድር ጥበብ ነው ይባላል። በአለም አቀፍ ዓይን ሲታይ ደግሞ ዲፕሎማሲ የተለመዱ ጉዳዮች የጦርነትና ሰላም፤ የንግድ ግንኙነቶች፤ የኢኮኖሚ፣ ባህልና የሰብአዊ መብት ጥበቃ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ተደርጎ ይወሰዳል። እናም ሰዐሊ ተሰማ እነዚህን ነገሮች አስተባብሮ ከመስራት አኳያ ያስመሰግነዋል። ምክንያቱም በሙያው አገሩን አሳውቋል። መልካሞችን የምታፈራውን ኢትዮጵያን በአለም መድረክ ላይ ከፍ አድርጓታል።
ኢትዮጵያ በራስ መተማመን ስሜት የምትጓዝና ነገሮችን በምክንያታዊነት የምታሳልፍ መሆኗን ለማሳየትም ሞክሯል። እንዴት ከተባለ መጀመሪያ የምናነሳለት እድሎችን በመጠቀም ኢትዮጵያ ማን ናት የሚለውን የገለተጠበት መንገድ ነው። ይህም በኳታር በተካሄደው የአለም ዋንጫ ላይ አጀብ ያስባለው ሥራው ነው።
ተሰማ ‹‹ አንድ ሰዓሊ በአካባቢው የሚያሸተውን፤ የሚሰማውን እና የሚያየውን ነገር ፈጥኖ ይመለከታል። የሚስለውም ከዚህ በመነሳት ነው። ስለዚህም ኳታር እ.ኤ.አ በ2010 የአለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ካሸነፈችበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ፈተናዎች ገጥመውታል። በጎረቤት ሃገራት ማለት ነው። እንደ ሰዐሊ ያንን ችግር በተለያየ የአሳሳል መንገድ በመጠቀም አጉልቶ በማውጣት ለኳታር ያለኝን ምልከታ ሳንጸባርቅ ቆይቻለሁ። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ለኳታር ያላቸው ምልከታ ምን እንደሚመስል ያሳየ ነበር። የሚያስገርመው እነዚያ የሰራኋቸው ሥራዎች ትንቢታዊ ነገር ሆነው ኳታር በብቃት አስደናቂ በሆነ መልኩ የዓለም ዋንጫውን ማዘጋጀት ቻለች። በዚህ የኳታር መንግስት እጅግ ተደስቶ ነበር። ይህ ግን ጎልቶ የወጣው ከአለም ዋንጫ ጋር ተያይዞ ለየት የሚያደርገውን ሥራ ይዤ በመውጣቴ ነው›› ይላል።
የኳታር አለም ሲጀመር ስታዲየሞቹ አካባቢ በመሄድ የየሀገራቱን ደጋፊና ታዋቂ ተጫዋቾችን በቀጥታ በሃያ እና በሰላሳ ደቂቃ ውስጥ በመሳል ለደጋፊዎች ትልቅ ድጋፍ በማድረግ አስገራሚ ትዕይንት ፈጥሯል። ሞሮኮ ከአስመዘገበችው ከፍተኛ ውጤት ጋር ተያይዞ የሳለው ስዕልም እውቅናን አስችሮታል።
‹‹ እጅግ የተከበሩ ይድነቃቸው ተሰማን ታሪክ በዚህ የአለም ዋንጫ ላይ ማስቀመጥ መቻሌ በሀገሬም ሆነ በሞሮኮ ህዝብ እንዲሁም ፕሮግራሙን ለመሳተፍ በመጣው በርካታ ማህበረሰብ ውስጥ ደስታን መጫር ችያለሁ። ለአፍሪካ የእግር ኳስ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ትልቅ አባት በመሆናቸውም ሁሉም ሰው እንዲያከብረኝ ሆኜበታለሁ። በተለይም ሞሮኳዊያን በእጅጉ ተደስተውብኛል። በአፍሪካ ካርታ ውስጥ የሞሮከውን እግር ኳስ ተጨዋችና እርሳቸውን በማድረግ በመሳሌም ልዩ ምስጢራዊ መልዕክት እንዳስተላለፍኩ ይሰማኛል›› ብሏል የነበረውን ሁነት ሲያብራራ።
ይህ ሥራው በሚኖርበት ሀገር እና በሚሰራበት መስሪያቤት ከፍተኛ የሆነ አድናቆትና ክበር ያገኘበትም እንደነበር ያወሳል። በርካታ ሽልማቶችም ተበርክተውለታል። በተለያዩ ሚዲያዎችም ላይ ከፍተኛ ሽፋን የተሰጠው ሲሆን ኳታር ፔኒንሱላ፣ በአውስትራሊያ፣ የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ፣ ዘሃበሻና በኢትዮጵያዊያን ሚዲያዎች የስዕል ሥራውን ከፍተኛ ሽፋን ተሰጥቶታል። በመሆኑም ለእርሱ ልዩ ነው የሚያስብለው አገሩን ማስተዋወቁ እንደሆነ ያስረዳል። አገሩን በማክበሩ ደግሞ እጅግ ደስተኛ ነው። እርሱ እንደሚለው አገርን ከፍ ማድረግ ራስን ማጉላት ነው። በከፍታውም መሸለም ነው።
‹‹ ዲፕሎማት የመግባባት ችሎታ ያለው እና ሁሉን አቀፍ የዳበረ ስብዕና ያለው ሰው ነው። ተፈጥሯዊ ባህሪን ወደ ተግባር መቀየርንም ይጠይቃል። ስለዚህም ዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት ሰጥቻለሁ ስል በእነዚህ መለያ ባህሪያቱ አማካኝነት ነው። ምክንያቱም አንድ ዲፕሎማት በቂ ትምህርትና ስለ ሀገሩ ባህል እምቅ ችሎታ ያስፈልገዋል። ያለን የተጠራቀመ አቅም መጠቀምንም ይጠይቃል። ይህ ደግሞ በታሪካዊ ልምድ መጎልበት መቻል አለበት። እናም እኔ ይህንን አድርጌዋለሁ ብዬ አስባለሁ። በማንኛውም አስቸጋሪ እና ያልተጠበቀ ሁኔታ ውስጥ አልፌ የተሻሉና የሚያስደምሙ ትንግርቶችን እየፈጠርኩ ዛሬ ደርሻለሁ። በቀጣይም በአገሬ ጉዳይ ይህንኑ ሳደርግ እኖራለሁ›› ባይ ነው ሰዓሊ ተሰማ።
አገርን በዲፕሎማትነት ለማገልገል ግድ ከአገር መወከልና አምባሳደር መሆን አይጠበቅብንም። ሁሉም አገሩን የሚወድ ሰው በሄደበት ቦታ አምባሳደርም ዲፕሎማትም መሆን ይችላል። ግድ መሆንም አለበት። ነገር ግን መሰረታዊ የሚባሉ ነገሮችን ማወቅ ያስፈልጋል። በተለይም ዲፕሎማት ለመሆን ምን ይጠበቅብኛል የሚለውን መገንዘብ ግድ ነው። ምክንያቱም ሳናውቀው ልናጠፋ እንችላለን የሚለው ባለታሪካችን፤ የውጭ ሀገራትን ባህል እና ወጎች ማወቅ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ ነገር እንደሆነ ያነሳል። ምክንያቱም ለአገር ለመስራት በጎነቱ፣ፈቃደኝነቱ ቢኖርም እነርሱን የሚገዛ ሥራ፣ እነርሱን ወደሀሳባችን የሚያመጣ ተግባር ካልከወንን በስተቀር ራሳችንን አደጋ ውስጥ ከተን አገራችንን ልናስወቅስ እንችላለን።
ስለሆነም ምን ይወዳሉ ፣ምን ይጠላሉ፤ ባህላቸው ምን ይመስላል የሚለውን መርምሮ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ከዚያ የማስታወስ ችሎታችንን ተጠቅመን በከፍተኛ የሥራ አቅምና ግንዛቤ አገራችንን ከፍ ወደማድረጉ መጋበት እንችላለን ሲል ይመክራል።
በአሁን ዘመን አገራት እንዳለፈው ዘመን በየአገራቱ በመደቧቸው አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ላይ ብቻ ተማምነው ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ጊዜ አይደለም። ምክንያቱም ከቴክኖሎጂው መስፋፋት ጋር ተያይዞ የመጣው የዲጂታል ዲፕሎማሲ ቀድሞ የሚሰራቸው በርካታ ተግባራት አሉ። እናም ይህንን ተረድቶ መስራት እንደሚያስፈልግ የሚያምነው ተሰማ፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለአገሩ በመጨነቅ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ያከናውናል።
አንዱ ከሰላም ስምምነቱ ጋር በተያያዘ በኳታር ከሚገኙት የደቡብ አፍሪካ፣ የኬንያና የናይጄሪያ ኤምባሲ ጋር ግንኙነት በማድረግ ለሰላሙ ላበረከቱት አስተዋዕጾ የማመስገን ሥራ ለመስራት ተንቀሳቅሷል። ይህም በእንዲህ እንዳለ ለናይጄሪያ ሕዝብ እና መንግስት በኤምባሲው አማካኝነት ያለውን አክብሮት በስዕል አማካኝነት ገልጿል። ‹‹ለአገሬና ለሕዝቤ ላደረጉት መልካም ስጦታ አመሰግናለሁ›› ብሏልም።
የሥዕል ሥራው ‹‹አፍሪካዊያን ለአፍሪካዊያን›› የሚለውን ውህድ የሚያሳይ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደምም ይህንን የተለመደ ተግባሩን ያደርግ ነበር። እናም በአሁኑ ስምምነት ደግሞ በርቱ ለማለት ሁሉንም ሊያስደስት ይችላል ያለውን ስዕል ሰርቶ አበርክቷል። ከቀሪዎቹ ሁለት የአፍሪካ አገራት ጋርም ይህንኑ ተግባሩን ለመከወን የቀጠሮ ጊዜን እየጠበቀ እንደሆነ አጫውቶናል። ለናይጀሪያው አምባሳደር ስዕሉን በሚያስረክብበት ጊዜ ብዙዎች እንደተደመሙ ይናገራል።
ከኢትዮጵያውያኑ አንዱ በስነጥበብ ሙያው አስደናቂ የዲፕሎማሲ ሥራ በማከናወንና የኳታር የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ በማሟሟቅ የተሰካለት ሰዓሊ ተሰማ፤ በሌሎች መድረኮች ላይም ዲፕሎማት ሆኖ ያውቃል። ለምሳሌ የ‹‹ኖሞር ዘመቻ›› አንዱ ነበር። ብዙዎችን የማነቃቃትና ለኢትዮጵያ ክብር እንዲቆሙ የማድረግ ሥራ ሰርቶበታል። በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሸለሙበት የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ ላይ ሰፊ ሥራ ሰርቷል። በአካባቢ ጥበቃ ላይ፣ በጤና ላይ በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ስዕልን በመጠቀም ትላልቅ መልዕክትቶችን ያስተላልፋል። ብዙዎቹ ደግሞ ተወዳጅነትን ያተረፉለት ናቸው።
የሕይወት ፍልስፍና
በመሸለም፣ በመመረቅና በመታዘዝ ያምናል። እነዚህ ሦስት ነገሮች ደግሞ ማንነቱን እንደሚቀይሩትና ከፍ እንደሚያደርጉትም ያስባል። በተለይ ሰዎችን በማክበር በመታዘዝ ራስን ለመሆን መጣር የሁልጊዜ መመሪያው ነው። በእነዚህ መርሆቹ ውስጥ ተጉዞ አገሩን ማኩራትም ዋነኛ ዓላማው ነው። ሁልጊዜ አገር ከራስ ትበልጣለች የሚል መፈክር አለው። ምክንያቱ ደግሞ በአገር ውስጥ ራስን ማድመቅ ይቻላል ብሎ ማሰቡ ነው።
የቤተሰብ ሁኔታ
ተሰማ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ሲሆን፤ ሁሉንም በአገሩ ባህልና ወግ አሳድጓቸዋል። ልዩ ተሰጥኦዋቸውን እንዲለዩና በዚያም እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል። እርሱም ሆነ ባለቤቱ ተደጋግፈው የሚሰሩ መሆናቸው ደግሞ ልጆቻቸው በደስታ እንዲያድጉ መሰረት ጥሎላቸዋል። በተለይም ባለቤቱ የሁሉ ነገር ምሰሶ እንደሆነች ያስረዳል። ለዛሬ እዚህ መድረሱ የእርሷ ድርሻ ላቅ ያለም መሆኑን ያነሳል። በተጨማሪም ለስኬቱም ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ትልቅ ሚና ተጫውታለች። ከእግር ኳሱ ጋርም በተያያዘ የልጁ ጸጋዘአብ ተሰማ ልዩ ፍላጎት ገፋፍቶት እንደገባበትና ለዚህ እንደበቃም አጫውቶናል።
ምኞት
ለሃገሬና ለህይወቴ የምመኘው አንደኛ ወደ ሀገሬ በመመለስ ያለኝን እውቀት ለወገኔ ለህዝቤ ማድረስን ነው። አዲሱ ትውልድ በአዲስ አስተሳሰብ እንዲራመድ የአቅሜን ማበርከት እሻለሁ። ያለኝ እውቀት ልምድ የወገኔ እንዲሆን እፈልጋለሁ።
በሁለተኛ ደረጃ ስዕል በመሳል የተለያዩ አስተማሪ የሆኑና ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሥራዎችን ማከናወን ምኞቴ ነው። በተለይም በአካባቢ ጥበቃ፣ በጤናና ማህበረሰባዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት ባደርግ ደስ ይለኛል። ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች አገርን ከፍ አድርገው ትውልድን ያንጻሉ። በመስራት የሚደሰት ማህበረሰብንም ይፈጥራሉ።
ስዕልና እይታው
‹‹ ስፖርትና ኪነጥበብ የተለየ ገጽታ ያላቸው ነገሮች አይደሉም። ሁሉም ሰላምን መስበኪያና የተረጋጋች አገር መፍጠሪያ ናቸው። አገርን በኢኮኖሚ ማበልጸጊያም እንደሆነ እሙን ነው። ምክንያቱም በስፖርት ሰበብ ብዙ ቱሪስት ወደ አገር ውስጥ ይጎርፋል። እናም ከፍተኛ ገንዘብ መሰብሰብ ይቻላል። በዚያው ልክ ባህልን ማስተዋወቂያና ማንነትን መስበኪያ ነው። የእርስ በእርስ ትስስርን ማጎልበቻም ነው።
እናም እድል ማግኛ ስለሆነ ለተጠቀመበት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማንነትን ይገነባል፤ ይገልጣልም። ላልተጠቀመበት ደግሞ በተቃራኒው ይሆናል። እኛ በሰው አገር ላይ ሆነን ሳይቀር አገራችንን መግለጥ የቻልነው የእድል ትርጉሙ ስለገባን ነው።›› የሚለው ተሰማ፤ በኳታሩ አለም ዋንጫ ከ51 በላይ የስነጥበብ ባለሙያዎች 102 የስዕል ሥራዎችን ባቀረቡበት ኤግዚብሽን ላይ የስዕል ሥራዎቹ በልዩ ጭብጡ አነጋጋሪ ሆነውለታል። ምክንያቱ ደግሞ ስዕልን የሚያይበት እይታ ነው።
እንደሱ እምነት ስዕል የሕይወት መመሪያ ነው። የጤንነት ስሜት መለኪያና ማረጋገጫ ነው። ሰላም መግዢያና ለሌሎችም ማጋቢያ ነው። ስዕል ከሌሎች ጋር መግባቢያና መቀራረቢያ ቋንቋ ነው። ሰው ማግኛ፣ ዘመድ ማፍሪያም ነው። አገሬን ማስታወሻና ማሳወቂያም ነው። ቤተሰቤንና ራሴን ማኖሪያም ጭምር ነው። በአጠቃላይ ስዕል ሕይወት ነው ይላል።
መልእክት
ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ ሲወጡ የራሳቸውን ማንነት ማስከበር ላይ በእጅጉ መጣር አለባቸው። በተለይም ወደ አረብ አገራት የሚጓዙት። በትክክለኛው መስመር ወጥተው አቅማቸውን ማሳየት ላይ መስራት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ያን ጊዜ የሚኖራቸው ክብር የማይናድ ይሆናል። ለራሳቸው ሆነው ለአገራቸው የሚያተርፉም ያደርጋቸዋል። ከአገር የሚወጣው ተለውጦ ለመመለስ እንጂ ለመንከራተትና የውሃ አለያም የሞት ሲሳይ ለመሆን አይደለም። እናም መስመሩም መንገዱም ለውጥ በሚያመጡበት ላይ መሆን ይገበዋል የመጀመሪያ መልዕክቱ ነው።
ሌላው ከሰላም ስምምነቱ ጋር ተያይዞ ያነሳው ጉዳይ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን ሰላም ወዳድና ባለታሪክ ሕዝቦች ናቸው። ከብዙ አገራት የሚለዩትም በይቅር ባይነታቸው ነው። ስለዚህም አሁን በስምምነቱ የአደረጉትን መልካም ነገር በሁሉም ተግባራቸው ሊያረጋግጡት ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም በሙያው ማገዝ ይኖርበታል። ምክንያቱም በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልምና።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30 /2015