
ከተሞች ከመመሥረታቸው ጀምሮ የተለያዩ ዓላማዎች ኖሯቸው ሊመሠረቱ ይችላሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ባለው የዓለም ፋይናንስ ሥርዓት ምክንያት አንዳንድ ከተሞች የኢንቨስትመንት ዋና መዳረሻዎች እንዲሆኑ ታስበው የሚገነቡበት ሁኔታ እየተለመደ መጥቷል። አንዳንዶች ደግሞ የተለየ ዓላማ ባይቀረፅላቸውም ባላቸው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና የአየር ፀባይ በርካቶች ለኑሮ ይመርጧቸዋል።
ታስበውባቸው የሚመሠረቱት ከተሞች ካፒታልን ከመሳብ ባለፈ ፈጠራን ለማጎልበት፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የተለያዩ ዘርፎችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
የጀርመኗ በርሊን በፈጠራ የታጀበ ከተማ ሆና ተመሥርታለች። የጀርመን መንግሥት ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘላቂነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በርሊንን በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና በሥራ ፈጣሪነት መሪ እንድትሆን አድርጓታል።
በደንብ የተመሠረተ የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፍ ያላት ሲንጋፖርም እንዲሁ ለንግድ ተስማሚ ከተማ በመሆን ትታወቃለች። የፖለቲካ መረጋጋት ያላት ከተማ በመሆኗ ከመላው ዓለም የተወጣጡ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች እና ባለሀብቶች መዳረሻ መሆን ችላለች።
ኦስቲን ቴክሳስ የቴክ ፓወር ሐውስ ግንባር ቀደም የቴክኖሎጂ ማዕከል በመሆን በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ስሟ ይጠራል። በደማቅ የሙዚቃ ትዕይንት እና የባህል ብዝኃነት የምትታወቀው ይቺ ከተማ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ጎግልን፣ አፕል እና ቴስላን ጨምሮ በርካታ የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች ምርጫቸው አድርገዋታል።
በኢትዮጵያም እንዲሁ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ባፀደቀው ደንብ መሠረት የሸገር ከተማ አስተዳደር 160 ሺህ ሄክታር መሬት ይዞ፤ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን ከተመሠረተች ሁለት ዓመታትን አስቆጥራለች።
ከተማዋ ከምሥረታዋ ጀምራ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን በማሰብ የታቀደ መሆኑን ተከትሎ፤ ምቹ የኢንቨስትመንት መሠረተ ልማት ተዘርግቶላት አገልግሎት እየሰጠች ትገኛለች።
ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ አገልግሎቶችን በውስጡ በማካተት ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ዓለምአቀፍ ጉባኤዎችን ለማከናወን ምቹ ሆኖ በተገነባው በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል የሸገር ከተማ አስተዳደር አዳዲስ ሀሳብ የያዙ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሳተፉ ባለሀብቶችን ለማበረታታት፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና አዳዲስ ተጨማሪ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የሚያስችል ሸገር የኢንቨስትመንት ኤክስፖ በዚሁ ታላቅ ማዕከል አዘጋጅቷል።
የእዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እና በከተማዋ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ የሚገኙ ባለሀብቶችም ምርት እና አገልግሎቶቻቸውን በመያዝ በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል ተሰይመዋል። የሸገር ኢንቨስትመንት ኤክስፖ መክፈቻም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የውጭ ሀገር አምባሳደሮች እና ባለሀብቶች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በከተማዋ ባለፋት ሁለት ዓመታት በርካታ የኢንቨስትመንት ሥራ ተሠርቷል። በዚሀም ሦስት መቶ ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የኢንቨስትመንት ካፒታል ተመዝግቧል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደሳቸው ገለፃ፤ ከተማዋ ከተመሠረተች ጥቂት ዓመታትን ብታስቆጥርም በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል። ለአብነት ከተማዋ ስትመሠረት ምንም አይነት ሆስፒታል አልነበራትም፤ አሁን ግን አራት ትልልቅ ሆስፒታሎች ተገንብተዋል። ለወጣቶች 40 ቢሊዮን ብር ብድር ቀርቧል።
ከሁለት መቶ በላይ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 140 ኪሎሜትር የመንገድ ግንባታ ተካሂዷል። 8ሺህ የግብርና ምርቶች ማቅረቢያ ሼዶች ተሠርተዋል።
ሸገርን ስማርት ከተማ በማድረግ ሂደት የመሬት መረጃ አያያዝ ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ ተደርጓል። ዲጂታል ላይብረሪ እና ኢ ትራፊኪንግን ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው። በከተማዋ የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር በሚቀጥሉት ዓመታት ከምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድል ያላት ከተማ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ከንቲባው ማብራሪያ፤ የከተማዋ አስተዳደር የሸገርን ነዋሪዎች የሕይወት ደረጃ ለማሻሻል፤ ከተማዋን በኢኮኖሚ እድገት በፍጥነት ለማሳደግ የከተማዋን የኢንቨስትመንት አቅምና ዕድሎች በማጥናት መለየት ተችሏል። በጥናት ላይ በመመሥረት ኢንቨስትመንትን ማስተዋወቅና ቅበላን ማስፋፋት፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ እና የኢንቨስትመንት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
ሸገር ከተማ አስተዳደር ቴክኖሎጂን ያማከለ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቅበላን ተግባራዊ በማድረግ የአዲስ ፕሮጀክቶች ቅበላ በአዲሱ እቅድ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። ኤክስፖ ከተለያዩ የዓለም ሃገራት ባለሀብቶች በከተማዋ ኢንቨስትመንት ላይ መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
ሸገርን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጓትን ጉዳዮች ሲያብራሩ፤ ከተማዋ የኢንቨስትመንት ማዕከል ለመሆን ታስቦበት የተመሠረተ መሆኑ፤ የመሬት አስተዳደሩ ዘመናዊ መሆን፣ ለከፍተኛ ኢንቨስትመንት ምቹ መሬት መኖሩ እና ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ ሥራዎች የሚሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሸገር አዲስ እሳቤን ይዞ የመጣ ከተማ መሆኑን ጠቅሰው፤ እሳቤውም የምርት እና የኢንዱስትሪ ከተማ በመሆን የኢኮኖሚ ስበት ማዕከል መሆን ነው ብለዋል።
የኢኮኖሚ ማዕከል መሆንን ዓላማው የሚያደርግ ከተማ ማምረት፣ አምራችን መደገፍ እና ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀል እገዛ ማድረግ ይገባዋል ያሉት ከንቲባው፤ ሸገርንም የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ቀን እና ሌሊት እንደሚሠራ ጠቁመዋል። ኤክስፖውም የዚህ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከ150 በላይ አምራቾች እንደተሳተፉበት እና ከ30 በላይ የውጭ ዜጋ ባለሀብቶች እንዲሁም 10 ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች እንደተገኙበት ጠቁመው፤ ለሦስት ቀናት በቆየው ኤክስፖ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዜጎችም የጎበኙት በመሆኑ የሚፈለገው ውጤት ተገኝቷል ማለት እንደሚቻልም አመላክተዋል።
በሪልስቴት ግንባታ፣ የተለያዩ የቤት እና የቢሮ መገልገያ እቃዎች፣ የቆዳ ውጤት አምራቾች እና ሌሎች በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የተሠማሩ አምራቾች በኤክስፖው ላይ ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በኤክስፖ ላይ በመገኘት ካነጋገራቸው አልሚዎች መካከል የስሪ ኤፍ ኩባንያ ይገኝበታል። በኤክስፖው የድርጅቱ ምርቶች አልጋ፣ ሶፋ፣ የቢሮ ወንበር እና ጠረጴዛዎችን ይዘው በማዕከሉ ተገኝተዋል። የስሪ ኤፍ የሳሪስ የሽያጭ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ኃይሉ እንደሚናገሩት፤ ድርጅቱ ዓለምገና በሚገኘውም ማምረቻ እና በተለያዩ ቅርንጫፎች ከ400 በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ከሸገር ከተማ አስተዳደር ሌሎችም ከተማዎች ተሞክሮን ቢወስዱ የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ ሚና ይኖረዋል። ኤክስፖውም ጥሩ የገበያ ትስስርን ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን በመወከል አቶ ዘለቀ ሽንቡሬ ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ በስፍራው ተገኝተዋል። ተቋማቸው በሸገር ከተማ ላይ በርካታ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፤ በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ አካባቢ በመንግሥት እና የግል ዘርፍ ትብብር ለአንድ ሺህ አባወራ የሚሆን ግዙፍ ሕንፃ እያስገነባ ነው።
ተቋማቸው በሸገር ከተማ ቦረቦሩ የሚባል ትምህርት ቤት አስገንብተዋል። አቶ ዘለቀ ካፌ እና ሬስቶራንት፣ የክሬሸር ማሽን ተከላ እና የሪልስቴት ልማት ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ይናገራሉ። በከተማ አስተዳደሩ መልካም ድጋፍ እና ጥሩ አገልግሎት አሰጣጥ እንዳለ ያብራራሉ።
ሌላኛው የካንቫስ እና የቆዳ ጫማ ምርቶችን ይዘው በኤክስፖው የተገኙት በፋንታዬ የጫማ ማምረቻ ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ማሩ ናቸው።
በፋንታዬ የጫማ ማምረቻ ድርጅት አምስት ሺህ 400 ካሬ ቦታ በመያዝ ገላን አካባቢ እንደተገነባ የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ለ250 ሰው የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልፀዋል። በአካባቢው አልፎ አልፎ ከሚከሰተው የኃይል መቆራረጥ ውጪ ጥሩ መሠረተ ልማት እንዳለ ይናገራሉ።
የኢንቨስትመንት ማዕከል በሆነችው ሸገር ከተማ አስተዳደር የሚሰጠው አገልግሎት እና ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ ነው። ለአብነት ለጫማ አምራች ድርጅቶች ከቀረጥ ነፃ ሞልዶች እና ማሽኖች እንዳስገቡ እና ዘርፉ እንዲበረታታ ዕድል እንደከፈተ ገልጸዋል።
የእኒህ ኢንቨስትመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንደሰን ተስፋዬ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ተቋማቸው 300 ሚሊዮን ካፒታል ወጪ በማድረግ ለቤት እቃ መሥሪያ የፕላስቲክ ጥሬ እቃን እና ለፍራሽ መሥሪያ የፋይበር ጥሬ እቃን ያመርታል።
ተቋሙ ከኤክስፖ በሚያገኘው የገበያ ትስስር በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ፤ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣ እና ለበርካቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ድርጅት መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።
እንደአቶ ወንደሰን ገለፃ፤ የእኒህ ኢንቨስትመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሸገር ከተማ ሁለት የማምረቻ ማዕከላት አሉት። ቦታውም የተገኘው ከተማ አስተዳደሩ ለአልሚዎች የመሬት አቅርቦት ለማቅረብ ዕድሉን በማመቻቸቱ ነው።
ከፀጥታ እና ከደኅንነት አኳያም ስጋት የሌለውና ከብዙዎቹ የከተማ አስተዳደሩ ዘርፎች ጋር አልሚዎች ተቀራርበው የሚሠሩበት ዕድልም መኖሩን አብራርተዋል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባኤ ወ/ሮ ሳዕዳ አብዱረህማን፤ ሸገር ከተማን የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረው፤ በከተማው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ለሦስት ቀናት የቆየው የሸገር ኢንቨስትመንት ኤክስፖ ማጠናቀቂያ ላይ ለሞዴል አርሶ አደሮች፣ አገልግሎት ሰጪዎች እና አምራቾች የእውቅና እና የሽልማት ሥነሥርዓት ተካሂዷል።
በዕለቱም የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ብልፅግናን እውን ለማድረግ በምርት ራስን መቻል ወሳኝ ነው ብለዋል። አርሶአደሩ መጣባችሁ እየተባሉ የሚሸሹት ኢንቨስትመንት ሳይሆን፤ ሁሉንም የሚያካትት ኢንቨስትመንት ለሀገር እድገት ወሳኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሸገር ከተማ አስተዳደር ለአርሶ አደሮቹ የሰጠው እውቅና አርሶ አደሮች ግብር ከፋይ፣ የሥራ ዕድል ፈጣሪ፣ አምራች፣ ላኪ እና ገቢ ምርትን የሚተኩ መሆናቸውን ያረጋገጠ ነው ሲሉ የተናገሩት ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ ለአርሶ አደሮች የተሰጠው እውቅና አርሶ አደሮች ኢንቨስትመንት ሊያጠፋን ነው ብለው እንዳያስቡ ለማድረግ ያስችላል። የመንግሥትንም ሁሉን አካታችነት በማሳየት የኢንቨስተር ጥላቻ እሳቤ እንዲሰብር የሚያስችል ነው።
ጨምረውም የአሁኑ ዘመን አርበኝነት ማምረት ነው ያሉት አቶ መላኩ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓላማው ምርትን ማስፋት እና ገቢ ምርትን በመተካት የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት መቻል መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በምግብ ራስን መቻል ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ ምርቶችም ራስን መቻል እና ወደ ውጭ መላክም አስፈላጊ ነው። ተኪ ምርቶች ላይ በስፋት እየተሠራ ያለውም በዚህ እሳቤ ነው። ለዚህም በሸገር ከተማ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የመቻል ማሳያ ናቸው።
ሰፊ ሀገር እና ሰፊ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ መሠረተ ልማትን በማስፋት አምራቾችን የመደገፍ ሥራ እየተሠራ ነው። ፖሊሲዎችን በማውጣት አምራቾችን ለማበረታታት ብዙ ጥረት እየተደረገ ነው። የመንገድ እና ሎጂስቲክስ ሥራዎችንም በማዘመን የዘርፉን ዕድገት ለማረጋገጥ እየተሞከረ ነው። ይሄ በዘርፉ ያለውን ተስፋ የሚያሳይ ሲሆን፤ መጭው ዘመን የተሻለ ስለሚሆን አምራቾች እና ባለሃብቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ብቻቸውን ሊያሳኳቸው ያልቻሏቸውን በጋራ በጥምረት በመሆን መሞከር እንደሚገባቸው ጠቁመው፤ በአጠቃላይ ለሦስት ቀናት በቆየው ኤክስፖ የሸገር ከተማ አስተዳደር ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን መሳብ ዓላማው ያደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት የወደፊት ዕጣ ፈንታ በባህላዊ የፋይናንሺያል ከተሞች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በእነዚህ ንቁ እና ስለወደፊት በሚያስቡ ከተሞች ውስጥም የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት አዳዲስ እሳቤን በማምጣት ባህላዊውን ወደ ዘመናዊ መቀየር ካልተቻለ የከተሞች ካፒታል እንደሚጎዳ እየተገለጸ ነው።
በአጠቃላይ የሸገር ከተማ ምሥረታ የኢንቨስትመንት ከተማን ማስፋትን ያለመ በመሆኑ በከተማዋ በርካታ ስኬቶች እየተመዘገቡ ናቸው። የዚህ አይነቱ የከተማ አመሠራረትም የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው። በመሆኑም በሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ የኢንቨስትመንት ከተማ ምሥረታዎች ይስፉ የዛሬው መልዕክታችን ነው። አበቃሁ!
በመክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም