በአዳራሹ መግቢያ በሰፊ ረከቦት ላይ የተደረደረው ሲኒ ቀልብ ይስባል። ለእንግዶች አቀባበል የተካሔደው የቡና መስተንግዶ አስደሳች ብቻ ሳይሆን፤ የቡና ጠዓሙም ልዩ ነበር። በተለይ ቡናው፤ የቡና ቁርስ ቆሎና ዳቦው ብቻ ሳይሆን የሀገር ባህል በለበሱ ትሁት ወጣቶች መስተንግዶው የሚቀርብ መሆኑ የሚያስደስት ነበር።
የተቆላ፣ የተፈጨና በጥሬ፣ ለናሙና በተለያየ ሀገር የተመረተ ቡናም በየጠረጴዛው ለእይታ ቀርቧል። የቡና ጣዕም በመለየቱ ላይም ቢሆን ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ በስፍራው የተገኘው እንግዳ ጭምር ተጋብዞ ነበር።
ምንም እንኳን ታዳሚዎቹ እንደባለሙያዎቹ ዝርዝር ነገሮችን ለመግለጽ ባይቻላቸውም፤ የተሻለ ጣዕም ያለውን ቡና በመለየት ስለቡናው የጣዕም ሁኔታ በመጠየቅ ለመረዳት ጥረት ሲያደርጉ ነበር። አቅራቢዎቹ ለታዳሚው ምላሽ የሰጡት የየራሳቸውን በማስረዳት ነበር። አንዳንድ አቅራቢዎች የየአካባቢያቸው መገለጫ የሆነውን በእጅ ጥበብ የተሰሩ አልባሳት፣ የእጅ ቦርሳዎችና ጌጣጌጦችም ከጎን ይዘው ቀርበዋል። እንዲህ ተዘጋጅተው የቀረቡት ብቻ ሳይሆኑ፣ በስፍራው የነበሩ ተጋባዥ እንግዶችም የየአካባቢያቸውን ባህል የሚያንፀባርቅ አልባሳት በመልበሳቸው ለዝግጅቱ ድምቀት ከመስጠታቸው በተጨማሪ ቀልብን የሚስብ ሆኖ ነበር።
ከሀገር ውስጥም ከውጭም የተጋበዙ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች ስለነበሩ፤ የቋንቋ ብዝሃነቱም ሌላው ገጽታ ነበረው። የቋንቋ ብዝሃነቱ የጋራ በሆነው ጉዳያቸው ላይ ከመሰባሰብና ምክክር ከማድረግ አላገዳቸውም፤ በጋራ ከመምከር በተጨማሪ፤ ተገበያይተዋል። ድባቡ የሚያስደስት ነበር። እንዲህ ደመቅ ያለውን ድባብ ለማየት የቻልነው በቡና ከልማት እስከ ግብይት በተሳተፉ ሴቶች ነው። አዘጋጆችም፣ ተሳታፊዎችም ሴቶች ስለነበሩ ደመቅ አድርገውታል። ዝግጅቱ የምክክር መርሃግብርም ስለነበረው በአዳራሹ የታደመው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ነበር። መርሃግብሩ በሴቶች የተዘጋጀና በሴቶች ላይ የሚመክር ቢሆንም፤ ወንዶችም በአጋርነት ታድመዋል።
አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደው በዚህ መርሃግብር ላይ ቡና አብቃይና ቡና ገዥ ከሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ሴቶች የተሳተፉበት ነበር። በሆቴሉ በተለያየ ዝግጅት ለሶስት ቀናት የተካሄደው መርሃግብር የተዘጋጀው ደግሞ ከልማት እስከ ግብይት በቡና ዘርፉ ላይ የሚገኙ ሴቶችን በመደገፍ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ኢንተርናሽናል ዊሜን ኢን ኮፊ አልያንስ ኮንቬንሽን በዘርፉ ላይ ከሚሠሩና አጋር ከሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነው።
በዚህ መርሃግብር ላይ በአካባቢያቸው የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቧንቧ ውሃ የሌለበት፣ ለእለት ምግባቸው የሚሆነውንም እህል በእጃቸው ፈጭተው የሚያዘጋጁ፤ በአጠቃላይ የኑሮ ጫና ያለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ከሚኖሩበት ከገጠሪቱ የኢትዮጵያ አካባቢ የመጡ በቡና ልማት ላይ የተሠማሩ ሴቶችም ተሳታፊ ነበሩ። ተሳታፊዎቹ ‹‹ሰደንኖኖ ቡና አምራች›› በሚል ስያሜ ማህበር መሥርተው በቡና ልማቱ ላይ የሚገኙ ሴቶች ናቸው።
ለእነዚህ የማህበር አባላት ሁሉ ነገር አዲስ ነው። ስብሰባው የተዘጋጀበት ሆቴል፣ አካባቢው ብቻ ሳይሆን፣ ከተለያየ አህጉርና ዓለምአቀፍ የተገኙ ተሳታፊዎች፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በመርሃግብሩ ላይ መገኘታቸው ተሳታፊ ሴቶቹን አስደስቷቸዋል። በዚህ የመጀመሪያ ተሞክሯቸው ደግሞ ግር መሰኘት ግድ ነው። ዝግጅቱን እንደትልቅ እድል ጭምር ሊያዩት እንደሚችሉም መገንዘብ ይቻላል።
በሌላ በኩል ለኑሮ አስቸጋሪ ከሆነ የገጠሪቱ ክፍል መጥተው የታደሙት እነዚህ ሴቶች ግን የየራሳቸው ብዙ የኑሮና የሕይወት ተሞክሮ ያላቸው ናቸው። የልፋታቸውንና የድካማቸውን ዋጋ አለማግኘታቸው ሳያንስ፤ የሚያግዛቸው አካል በማጣታቸው፣ እንዲህ ባሉ ተሞክሮዎች ላይ ለመሳተፍ እድሉን ባለማግኘታቸው ወደኋላ ቀርተው እንጂ የሚኖሩት ከራሳቸው አልፈው በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ በሚያስችላቸው ልዩ ተፈጥሮን በታደሉ አካባቢዎች ነው ።
በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ በያዘው ቡና መገኛ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ናቸው። ብዙ ድካም ሳይጠይቅ አነስ ያለ እንክብካቤ በማድረግ ሀብት ማፍራት የሚያስችል የጫካ ቡና ከሚለማበት ኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን ሰሌኖኖ ወረዳ የመጡት ሴቶች ከተሳታፊዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በዚህ አጋጣሚ ከአባላቱ መካከል ስለኑሮዋና የሕይወት ተሞክሮዋ፣ ስለገጠሯ ሴት ያጫወተችን ወይዘሮ ሲቲና ኡስማን ነች። ወይዘሮ ሲቲና ለሶስት ቀናት የተሳተፈችበት መርሃግብር ብዙ ነገር እንድትገነዘብ አስችሏታል። ወደ ሀብት ሊቀይር በሚችል የኢኮኖሚ ምንጭ ላይ ቁጭ ብለው ግን ደግሞ በኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ማለፍ እስከ መቼ? የሚል ቁጭት እንዲያድርባትም አድርጓታል። መርሃግብሩ አእምሮዋን እንደለወጠውና ተግታ ኑሮን ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ውስጥም አበርክቶ እንዲኖራት አነሳስቷታል።
ወይዘሮ ሲቲና በአካባቢዋ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ የመካፈል እድሉን ብታገኝም እንዲህ ሰፊ በሆነ መርሃግብር ላይ ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ ነው። መርሃግብሩን በአድናቆት ያየችው ሲሆን፤ እርስዋ እንዳለችው አዲስ አበባ ከተማ ስትመጣም የመጀመሪያዋ ነው። በሶስት ቀናት ቆይታዋም የቡና ግብይት የሚካሄድብትን ኢሴክስ የመጎብኘት እድሉን አግኝታለች። ገበሬው ለፍቶ ያመረተው ቡና በምን ሂደት ውስጥ አልፎ ለገበያ እንደሚቀርብ ለመገንዘብ ችላለች። ይሄን ሁሉ በማየቷ በቡና ልማትና ግብይቱ ላይ ጠንክራ እንድትሠራ ጥሩ መሠረት እንዳሆናትም ትገልጻለች።
ወይዘሮ ሲቲና የምክክር መድረኩንም ቢሆን ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኘችው ነው የነገረችን። በመርሃግብሩ ላይ ተሞክሯቸውን ሲያቀርቡ የነበሩ የሌሎች ሀገሮች በቡና ዘርፉ ላይ የሚገኙ ሴቶች ቋንቋቸውን ለመረዳት ባትችልም ሃሳቡን ከሌሎች በመረዳት መልካም የሆኑ ነገሮች ማግኘት መቻሏንና ለወደፊቱ የሚጠቅማትን ነገር እንዳገኘችበት አስረድታናለች።
ወይዘሮ ሲቲና ገና በ30ዎቹ እድሜ ውስጥ የምትገኝ በመሆኑ፤ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ዕድሜዋን በአግባቡ ለመጠቀም እንዳሰበች ትገልጻለች። የእርስዋ ወላጆችና የአካባቢዋ ነዋሪዎች ያለፉበት የኑሮ ውጣ ውረድና የሕይወት ዘይቤ በእርስዋና በተተኪው ትውልድ መደገም የለበትም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሳለች። እርስዋ ተለውጣ ለሌሎችም አርአያ መሆን እንዳለባት ከአጭር ጊዜ ቆይታዋ ትምህርት አግኝታለች። እኛም ትልቅ መነቃቃት እንደተፈጠረባትም ከሃሳቧ መረዳት ችለናል።
ወይዘሮ ሲቲና እንዳጫወተችን፤ አካባቢያቸው ለእርሻ ሥራ ምቹ ነው። የተለያዩ አዝእርቶችና ሰብሎች ይለማሉ። በቡና እና በማር ልማት ፤ በተለም በጫካ ቡና የታወቃል። ከዚህ የተፈጥሮ ፀጋ ተጠቃሚ ለመሆን ብዙ ልፋት አይጠይቅም። የሚያስፈልገው ጥቂት እንክብካቤ ማድረግ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ሳይደክሙ ከልማቱ ተጠቃሚ መሆን ቢችሉም የአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም የሴቶቹ ኑሮ ግን ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን አላለፈም።
በሴቷ ላይ ያለው ጫና ደግሞ የከፋ ነው። በአካባቢው የሚኖሩ ሴቶች የኑሮ ውጣ ውረድ አድካሚ ነው። ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም። ተፈጥሮ ለአካባቢው በሰጠው ፀጋ እንኳን ተጠቃሚ አይደለችም። ቡናው ሲደርስ ጫካ ሄዳ ለቅማ በምትሰበስበው ቡና የማዘዝ መብት የላትም። ቡናውን ሸጦ የተገኘውን ገቢ ወደ ኪሱ የሚከተው አባወራው ነው። አባወራ ባይኖራትም የሚጠቀመው ወንድ ልጇ ነው። ለዘይት፣ ለጨውና ለሌሎች ነገሮች የምታሟላው መልሳ እርሱን ገንዘብ በመ ጠየቅ ነው።
ማልዶ ከመኝታ መነሳት፤ አምሽቶ ወደ መኝታ መሄድ የሴቷ የእለት ተእለት ተግባር ነው። ማልዳ ለቤተሰቡ ቁርስ ማዘጋጀት፣ ውሃ መቅዳት፣ ለማገዶ እንጨት መልቀም የየአለት ተግባሯ ነው። በእርሻ ጊዜ ደግሞ በእርሻ ሥራ ላይ ለተሰማሩት የቤተሰብ አባላት ምግብ አዘጋጅታ ይዛ ማሳው ድረስ መሄድ ይጠበቅባታል። ወደ ቤት መመለስ የለም። በዚያው እርሻው ላይ የሚታገዝ ሥራ ካለ አብራ ትሠራለች።
በጉልጓሎ፣ በአረምና ሰብል ሲደርስ በመሰብሰቡ ላይም ትሳተፋለች። የደጁንም ከማጀቱ ሥራ ጋር ጎን ለጎን ታስኬዳለች። በእርግዝና ወቅት እንኳን እረፍት የሚባለው ለገጠሯ ሴት ቅንጦት ነው። ልጆች በማሳደግም ተጨማሪ ኃላፊነት ትቀበላለች።
ወይዘሮ ሲቲና በተለይ በቅድመ ወሊድና በድህረ ወሊድ ያለውን ሁኔታ ስታጫውተን፤ የገጠሯ ሴት ድካምና ልፋት እልህ አስጨራሽ ነው። በአካባቢያቸው የኑሮ ጫናውን የበለጠ ያከበደው፤ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውሃ አገልግሎት አለመኖር ነው። እህል አስፈጭቶ ለመጠቀም በኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር ምክንያት ከአካባቢያቸው የአንድና የሁለት ሰአት መንገድ በእግር መጓዝ ይኖርባቸዋል። መንገድ ባለመኖሩ የትራንስፖርት አገልግሎት የለም። ረጅም መንገድ ተጉዘው ደግሞ እህል ለማስፈጨት ረዥም ወረፋን ለመጠበቅ ይገደዳሉ። ወረፋ ሲጠብቁ ስለሚመሽ ወደ ወፍጮ ቤት አለመሄድን ይመርጣሉ። በዚህ ምክንያት በእጃቸው ፈጭተው ለመጠቀም ተገደዋል። በእጅ መፍጨቱን ጨምሮ ተደራራቢ የሆነው የጉልበት ሥራ ለከፋ የጤና ችግርም እየዳረጋቸው ነው።
እነዚህን ሴቶች በንጽጽር የእንጀራ ጠርዝ ከሚቆርጣቸው ከለሰለሱ እጆች ጋር ማቅረብ አዳጋች ነው። በዚህ አድካሚ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ በውሃ ቀጠነ ልደብድብሽ እያለ የሚነሳ አባወራም አይጠፋም። ከንዝንዝና ንትርክ ጋር የኑሮ ትግል ማድረግ ነገሩን የከፋ እንደሚያደርገው መገመት አያዳግትም። አካባቢው ላይ ወንዱ ከሁለት በላይ ሴት የማግባት ልምድ አለው። እንዲህ ያለው ተሞክሮ ያለው እምነታቸውን መሠረት ባደረጉ በአካባቢው ማህበረሰብ ክፍል ነው።
ወይዘሮ ሲቲና እንዲህ ባለው ማህበረሰብ ውስጥ ያደገች በመሆኑ ችግሩን ጠንቅቃ ታውቀዋለች። በልጅነቷም ከአካባቢዋ ርቃ ውሃ በመቅዳት፣ የማገዶ እንጨት በመልቀም፣ በቤት ውስጥም ሥራ በማገዝ፣ በእርሻውም ቢሆን በአረምና ጉልጓሎ ቤተሰቦችዋን በማገዝ የልጅነት ጊዜዋን አሳልፋለች።
አሁን ላይ በአድካሚው የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ከሚገኙት የአካባቢዋ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሽላ ለመገኘት የሚያስችላትን መንገድ ይዛለች። በአጋጣሚ ሆኖ የትምህርት እድል በማግኘቷ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ተምራለች። መማሯ ደግሞ በዛ በገጠር ሕይወቷን እየገፋች ቢሆንም፤ አማራጮችን እንድታይ አስችሏታል። ኑሮን ለማሸነፍ ተጨማሪ ገቢ በሚያስገኙላት ነገሮች ላይ ለመንቀሳቀስ ጥረት ታደርጋለች።
በመማሯ አሁን የምትገኝበትን ሰደንኖኖ ቡና አምራች ማህበር ከማቋቋም እስከ መምራት ደርሳለች። በትምህርቷ ገፍታ ቢሆን ደግሞ በተሻለ ደረጃ ላይ ትገኝ እንደነበርም በቁጭት ትናገራለች። እርስዋ እንዳለችው፤ ከ10ኛ ክፍል በኋላ ትምህርቷን ለመቀጠል አካባቢዋ ላይ አማራጭ አልነበራትም። 10ኛ ክፍል ድረስ ለመማር የቻለችው በየቀኑ ረጅም ኪሎ ሜትር በእግሯ ተጉዛ ነው። ከትምህርት ቤት መልስ ደግሞ በቤት ውስጥ ቤተሰብን በሥራ ማገዝ ግዴታዋ ነበር። ቤተሰቦችዋ እንድትማር ቢፈቅዱላትም ትምህርቷ ላይ ትኩረት አድታደርግና የጥናት ጊዜ እንደሚያስፈልጋት ግንዛቤው ስለሌላቸው በዚህ በኩል አላገዟትም። ምሽት ላይ እንዳታጠና ደግሞ መብራት የለም። 10ኛ ክፍል የደረሰችው በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፋ ነው።
በትምህርት መግፋት ባለመቻሏ ትዳር መመሥረትን እንደሁለተኛ አማራጭ በመያዝ ባል አገባች። በገጠሩ በአብዛኛው የተለመደው የትዳር አጋር የሚመርጡት ቤተሰቦች ናቸው። ወይዘሮ ሲቲና ግን ትዳር የያዘችው በዚህ መንገድ አልነበረም። በአጋጣሚ ከተዋወቀችው ሰው ጋር ፍቅር መሥርታ ስለነበር፤ ጎጆ የመሠረቱት ሁለቱ ተስማምተው ነው። እዚህ ላይም እርስዋ እድለኛ ሆና እንጂ የአብዛኞቹ የባለትዳሮች ታሪክ በቤተሰብ ምርጫ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አጫውታናለች።
ወይዘሮ ሲቲና የሁለት ልጆች እናት ናት። ፍላጎትዋ ልጆችዋ ከእርስዋ በተሻለ እንዲኖሩ ማድረግ ነው። በትምህርታቸው ጠንካራ ሆነው ሀገርን የሚለውጡ እንዲሆኑ የምትችለውን ሁሉ እንደምታደርግላቸው ነግራናለች። የትዳር አጋሯ እንደርስዋ ባይማርም በአስተሳሰብ የሚግባቡና የሚደግፋት እንደሆነ ገልጻልናለች። አሁን ላይ ኑሯቸውን እየመሩ ያሉት እርሱ የግብርናውን ሥራ በማጠናከር፣ እርስዋ ደግሞ አማራጭ በሆኑ የገቢ ማስገኛዎች ላይ በመንቀሳቀስ ነው።
ወይዘሮ ሲቲና እንዳጫወተችን አሁን ላይ የገቢ አማራጭ አድርጋ የያዘችው የቡና ልማቱን ነው። ከተቋቋመ ስምንተኛ ዓመቱን የያዘው ‹‹ሰደንኖኖ ቡና አምራች›› ማህበር ውስጥ እርስዋን ጨምሮ 208 ሴቶች በአባልነት ይገኛሉ። ማህበር መሥርተው ወደ ሥራ እንደገቡም በአካባቢያቸው ለሚገኘው የገበሬዎች የህብረት ሥራ ማህበር (ዩኒየን) ምርታቸውን በማቅረብ ገቢ ያገኛሉ። ከዩኒየኑም ብድር በመውሰድ ሥራቸውን በማሳደግ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት አድርገዋል። ይሁን እንጂ ያሰቡትን ያህል መጓዝ አልቻሉም። ያገኙት የገንዘብ ብድር መጠን አነስተኛ መሆንና አማራጭ ገበያ ለማግኘትም አለመቻላቸውን እንደምክንያት ታነሳለች።
እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ሆነው ያሉባቸውን የንግድ ክህሎት ክፍተት የሚሞላላቸው ድርጅት አግኝተው ሥልጠና እንደሰጣቸውም ገልጻለች። ‹‹ድርጅቱ የአካባቢያችን ችግር በተለይም የሴቷን የኑሮ ሁኔታ በደንብ ተገንዝቧል›› ብላ የገለጸችው የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) በሰጣቸው ሥልጠና ግንዛቤዋ ከፍ እንዳለም ታስረዳለች።
እርስዋ እንዳለችው፤ የአካባቢያቸው የአየር ፀባይ ዘጠኝ ወር በሙሉ የዝናብ ወቅት ነው። በዚህ የተነሳም ቡና ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ጥራት ያለው ቡና ለማምረት የተለያዩ ነገሮች እንደሚያስፈልጉ ግንዛቤ አግኝታለች። ጥራቱን ለመጠበቅ እንደ ሸራና ላስቲክ የመሳሰሉ ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉና ለእዚህ ደግሞ ገንዘብ ወሳኝ እንደሆነ ትናገራለች። አሁን ትልቅ ማነቆ የሆነባቸው ብድር ማግኘት ነው። መንግሥትም ሆነ ሌላ የሚያግዛቸው አካል ቢኖር ሌሎች ሀገሮች ካስመዘገቡት ውጤት በላይ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል እምነቷ ነው።
ወይዘሮ ሲቲና በኑሮ ለመለወጥ ውስጧ የተፈጠረው መነቃቃት በማህበር ውስጥ ብቻ ተወስና እንደማትቀር የሚያመላክት ነው። ከዚህ በኋላ ፍላጎትዋ በግሏም በቡና ልማቱ ላይ ጠንክራ የመውጣት ዓላማ አላት። እርስዋ እንዳለችው እቅዷ ከልማቱ እና ጥሬ ቡናን ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ እሴት ጨምራ ለገበያ የማቅረብ ዕቅድ አላት። እድገቱና ለውጡ የሚመጣው በዚህ መንገድ ሲንቀሳቀሱ እንደሆነ በመረዳትዋ ቁርጠኛ ሆናለች። በሌሎች እንቅስቃሴ መንፈሳዊ ቅናትም ስላደረባት በዘርፉ እድገት ለማስመዝገብ ወደኋላ እንደማትል ከስሜቷ ለመረዳት ችለናል።
የዕለቱ መርሃ ግብር ዋና ዓላምም እንዲህ እንደ ወይዘሮ ሲቲና ያሉ ጠንካሮች ጎልተው እንዲወጡና ለስኬት እንዲበቁ ነው። መርሃግብሩ የተመቻቸላቸው ጥንካሪያቸውን ሊያስቀጥል የሚችል አቅም እንዲያገኙ የሌሎችን ተሞክሮ እንዲቀስሙ የሚያስችል መድረክ ነው። በንግድና በተለያየ መንገድ ሀገራትን በማገናኘት ዘርፉ ላይ የሚገኙ ሴቶች ጎልተው በመውጣት የራሳቸውን ኑሮ ከመለወጥ ባለፈ በቡናው ልማት እስከ ገበያ ባለው ላይ ስመጥር እንዲሆኑ ማስቻል ነው። ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ደግሞ ሴቶች ጠንክረው ቡና ገዥዎችን ወደ ሀገራቸው ማምጣት እንዲችሉ ማድረግ እንደሆነ ከመርሃግብሩ መረዳት ችለናል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ከቀረበው መረጃ መረዳት እንደቻልነው ከቡና ልማት እስከ ቅምሻ ባለው ሂደት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ እስከ 70 በመቶ ያለውን ድርሻ ይይዛል። ይሁን እንጂ በሚሰሩት ልክ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ዘመናት ተቆጥሯል። ይሄንን በአዲስ አስተሳሰብ መለወጥ ግድ ይላል። በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር መታየትም ይኖርበታል። በተለይም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የመንግሥት ድጋፍ በተለይም ፖሊሲ በመቅረጽና ስትራቴጂ በማውጣት ረገድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የተለያዩ ባለድርሻ አካላትንም በማሳተፍ ሰፊ ተግባር ይጠበቃል።
ክፍተቶችን ለመሙላትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ሥራዎች ቢሠሩም በቂ እንዳልሆነ ይነገራል። አሁን ላይ ርብርብ ያስፈልጋል እየተባለ ያለው ለዚህም ነው። በጥቂት የእንቅስቃሴ ሥራ እንደነ ወይዘሮ ሲቲና ያሉ በልማቱ ላይ የሚገኙትን ቁርጠኛ ማድረግ ከተቻለ፤ ጠንከር ያለ ሥራ ቢሠራ ብዙዎችን ማፍራት ይቻላል።
በመርሃግብሩ ላይ በነበረን ቆይታ ሌላው ያስተዋልነው፤ የማህፀን ጫፍ ካንሰር በመከላከል ላይ የሚሠራ ድርጅት ከአዳራሹ ውጭ እራሱን እያስተዋወቀ ነበር። በቦታው ለተገኘው ታዳሚ ግንዛቤ የመፍጠሩን ሥራ ከመሥራት ባለፈ በዘርፉ ላይ የሚገኙ አካላት ትብብር ከፍ እንዲል መልዕክት ሲያስተላልፍም ነበር።
በእርግጥ ልማቱ በጤናማ ማህበረሰብ ካልተከናወነ የኩባንያዎች ህልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል። የድርጅቱ እንቅስቃሴ ልማቱ በሚከናወንበት ቦታ ብዙ ምቹ ነገር መኖር እዳለበትም የሚያስረዳ ነው። ከድርጅቱ አስተባባሪዎች እንደተረዳነው፤ ድርጅቱ ለመቋቋሙ መሠረት የሆነው ከልማቱ እስከ ግብይቱ ባለው ሂደት ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች በማህፀን ጫፍ ካንሰር በብዙ ስቃይ ውስጥ የሚገኙና ለሞትም የተዳረጉ በልማቱ ላይ የሚገኙ ሴቶችን በማየቱ ነበር። ይሄ ተነሳሽነት በአፍሪካም እንዲሰፋ በማድረግ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተነሳሽነቱን ወስዷል።
ድርጅቱ ሥራውን ወደ ኢትዮጵያም በማስፋት በአሁኑ ጊዜ በጉራጌ፣ ጌዲኦ፣ ሲዳማ፣ ጉጂና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በቡና ልማቱ ላይ ያሉ ሴቶች ለማህፀን ጫፍ ካንሰር በሽታ እንዳይጋለጡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ተጋላጭ ሲሆኑም አስፈላጊውን እገዛ እንዲያገኙ ለመርዳት እየሠራ ይገኛል።
እንዲህ በተጠናከረ የጤና አገልግሎት እንደነወይዘሮ ሲቲና ያሉ ጠንካራ የልማት አርበኞች ከዓላማቸው እንዳይስተጓጎሉ በጤናቸውም ጭምር መታገዝ እንዳለባቸው በቆይታችን ተገንዝበናል። በተለይም ብዙ አገልግሎቶች ተደራሽ ባልሆነባቸው ወይዘሮ ሲቲና እንደሚኖሩበት አካባቢ እንዲህ ያለውን በጎ ተግባር መከወን አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም