ትራምፕ ‘በፑቲን ቅር ብሰኝም፤ ተስፋዬ አልተሟጠጠም’ አሉ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ላይ “ቅር እንደተሰኙባቸው” ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ልዩ የስልክ ቆይታ ተናገሩ። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ፑቲንን ያምኗቸው እንደሆነ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እኔ ማንንም ማለት በሚቻል ሁኔታ አላምንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ትራምፕ ይህንን ያሉት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ለመላክ ማቀዳቸውን፤ እንዲሁም ሩሲያ ግጭቱን እልባት ለመስጠት በ50 ቀናት ስምምነት ላይ ካልደረሰች ማዕቀብ እንደሚጣልባት ካስፈራሩ ከሰዓታት በኋላ ነው። ትራምፕ ከዚህ ቀደም ጊዜው ያለፈበት ሲሉ ያጣጥሉት የነበረውን ኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት) የጋራ መከላከያ መርህ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።

ፕሬዚዳንቱ በፔንስልቫንያ ግዛት በነበረ የምርጫ ቅስቀሳ የግድያ ሙከራ አንድ ዓመት መሙላቱን ለማስታወስ ከቢቢሲ ጋር 20 ደቂቃ የፈጀ የስልክ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል። ከግድያ ሙከራ መትረፋቸው በህይወታቸው ለውጥ አምጥቶ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ በተቻለ መጠን ብዙም እንደማያስቡበት ተናግረዋል።”ቀይሮኝ ከሆነ ብዬ ማሰብ አልወድም” ያሉት ትራምፕ እሱን ማብሰልሰል “ህይወትን ሊለውጥ ይችላል” ሲሉ አክለዋል።

በዋይት ሃውስ ከኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩቴ ጋር ከተገናኙ በኋላ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ረዘም ያለ ጊዜ የሰጡት በሩሲያው መሪ ያደረባቸውን ቅሬታ በተመለከተ ነው። ትራምፕ በዩክሬን ያለውን ጦርነት የመቋጨት ስምምነት ላይ ለመድረስ ሩሲያ አራት ጊዜ እድሉ እንደነበራት ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከፑቲን ጋር ያለው ነገር ተቋጭቷል ወይ? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ “በእሱ ቅር ተሰኝቻለሁ ነገር ግን ገና አላለቀም። ነገር ግን ቅር ተሰኝቸበታለሁ” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ትራምፕ፤ ፑቲን የዩክሬን ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲያቆሙ እንዴት ያሳምኗቸዋል? ብሎ ቢቢሲ የጠየቃቸው ሲሆን እሳቸውም “እየሰራንበት ነው” ብለዋል። አክለውም “ በጣም ጥሩ ውይይት እናደርጋለን። ጥሩ ነው። ለመቋጨት ቅርብ ነን ብዬ አስባለሁ፤ ከዚያም በኪዬቭ ውስጥ አንድ ህንጻ ያፈርሳል”ሲሉ አስረድተዋል።

ሩሲያ በባለለፉት ሳምንታት በዩክሬን ከተሞች የምታደርገውን የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶች በማጠናከሯ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል። ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችው በአውሮፓውያኑ 2022 ነው። ፑቲንን ሰላምን እንደሚፈልጉ አጥብቀው የሚገልጹ ሲሆን፤ ነገር ግን የጦርነቱ ዋና መንስኤዎች ብለው የሚጠሯቸው ነገሮች በቅድሚያ ሊፈቱ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የጦርነቱ መነሻ የሩስያ ደህንነት ላይ የተደቀኑ የውጭ ስጋቶች እነሱም ዩክሬን፣ ኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት) እና “የምዕራባውያን ጥምረት” ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።ትራምፕ በዚህ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ ከዚህ ቀደም ያረጀ እና ያፈጀ ሲሉ የጠሩትን ኔቶን ጉዳይ አንስተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ኔቶን በዚያ መንገድ እንደማያስቡት አንስተው “በአሁኑ ወቅት የዚያ ተቃራኒ እየሆነ ነው” ለዚህም እንደ ምክንያትነት የጠቀሱት የጥምረቱ አባላት “ድርሻቸውን እየከፈሉ” ስለሆነ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

በቅርቡ ትራምፕ የአውሮፓ አገራት ዩክሬን ከሩሲያ ጨራሽ የአየር ጥቃቶች ራሷን ለመከላከል የምትተማመንበትን ‘ፓትሪዮት’ የአየር መቃወሚያ ስርዓት እንደሚልኩ እና መቀየሪያዎቹ ደግሞ በአሜሪካ እንደሚሰጡ አሳውቀዋል።

ትራምፕም ሆኑ ሩቴ ለኪዬቭ እንልከዋለን ስላሉት የመሣሪያ አይነት ባያብራሩም፤ ሩቴ ስምምነቱ “ሚሳዔሎችን እና ጥይቶችን” እንደሚያካትት ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያወጡ “ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች” ዩክሬንን ለመደገፍ “በአፋጣኝ ወደ ጦር ግንባሮች ይከፋፈላል” ብለዋል።”ዛሬ ቭላድሚር ፑቲንን ብሆን ከዩክሬን ጋር የሚኖረኝን ንግግር ጠበቅ አድርጌ ለመያዝ አጤናለሁ” ሲሉ ሩቴ፤ ትራምፕ ደግሞ መስማማታቸውን ግንባራቸውን በመነቅነቅ ገልፀዋል።

በታሪፍ በኩል ትራምፕ ሩሲያ በ50 ቀናት ውስጥ ከዩክሬን ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ካልደረሰች በቀሪ የንግድ አጋሮቿ ላይ የ100 በመቶ የሁለተኛ ወገን ታሪፍ እንደሚጥሉ መናገራቸውን አስታውሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You