
ትኩረታቸውን ስፖርት ላይ ያደረጉ በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በመላው ዓለም ይንቀሳቀሳሉ። እነዚህ ተቋማት የሰላምና የአንድነት መሣሪያ የሆነውን ስፖርት የሚደግፉ ሲሆኑ፤ የታዳጊና የወጣቶች ስፖርት ሥልጠናን ጨምሮ ባለሙያዎችን በማብቃትና የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ይታወቃሉ። እንደ አፍሪካ ያሉና ለስፖርት ከፍተኛ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች ባሉባቸው አህጉራትም ድጋፋቸውን በስፋት ይሰጣሉ።
በርካታ መሰል ተቋማት ከሚገኙባቸው ሀገራት መካከል በእግር ኳስ ስፖርት ገናና ስም ያላት ስፔን ትጠቀሳለች። ከእዚህ ቀደም ቅርጫት ኳስን ጨምሮ በተናጠል ከፌዴሬሽኖች ጋር ሲሠሩ ከቆዩ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የስፔኑ ‹‹ACCEDE›› ከኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ጋር ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሷል። መቀመጫውን በባርሴሎና ያደረገው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው በሴቶችና ስፖርት፣ ስፖርት አስተዳደር፣ የእግር ኳስ እንዲሁም ቅርጫት ኳስ ስፖርት ላይ መሆኑን ከሚኒስትሩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። በእዚህም በስፋት ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የብቃት ማሻሻያ ስልጠናዎችን የሚሰጡም ይሆናል።
ሚኒስትሩ ከተቋሙ ጋር ለመሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ ትኩረት በሚደረግባቸው ጉዳዮች ላይም በቅርቡ የመግባቢያ ሰነድ የሚፈራረሙ መሆኑንም በሚኒስትሩ የስፖርተኞችና ባለሙያዎች ልማት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ አበባ አማረ ጠቁመዋል። ሰነዱም በመሠረታዊነት ስፔን ውጤታማ በሆነችባቸው የእግር ኳስ እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች፣ በስፖርት አስተዳደር፣ ለባለሙያዎችና ስፖርት አስተዳደሮች ሥልጠና በመስጠት፣ የልምድ ልውውጥ በማድረግ እንዲሁም የስፖርት ትምህርትና ስልጠና ዕድሎችን ማግኘት በሚያስችል መልኩ ታልሞ የተዘጋጀ ነው። ከተቋሙ ጋር የሚኖረው ስምምነት ለ5 ዓመት እንዲቆይ የታሰበ ሲሆን፤ ከመሰል ተቋማት ጋርም ድጋፍ በሚያስፈልግባቸው የስፖርት ዘርፎች ላይ ለመሥራትም እቅድ ተይዟል።
በእዚህም መሠረት የመጀመሪያው ዙር ሥልጠና ትኩረቱን በስፖርት አስተዳደር ላይ ትኩረቱን በማድረግ በጋምቤላ፣ ጅማ እና ወልቂጤ ከተማና አቅራቢያ ያሉ 240 የሚደርሱ የክልል ባለሙያዎችን በሥልጠናው በማሳተፍ ተጀምሯል። በቀጣይም ሌሎች ክልሎች ላይ ተለይተው በተቀመጡ ዘርፎች ላይ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች የረጅምና የአጭር ጊዜ ሥልጠናውን ይሰጣሉ። ከእዚህም ባለፈ በየታዳጊና ወጣት ስፖርት ሥልጠና ማዕከላት ለሚገኙ ሠልጣኞችና አሠልጣኞችም ተግባራዊ ሥልጠና የሚሰጡ ሲሆን፤ ያመጧቸውን የስፖርት ትጥቅና ቁሳቁሶችን እንደሚያበረክቱም ኃላፊዋ ገልጸዋል። በሌላ በኩልም ሴቶች በስፋት ወደ ስፖርቱ መግባት እንደሚገባቸው፣ የስፖርት ሕክምና፣ የስፖርት ሕግ እንዲሁም ስፖርትና ትምህርትን በሚመለከት በሥልጠናው የግንዛቤ ማስጨበጫ ይሰጣል።
በሥልጠናውም የስፖርት አመራሩ፣ አሠልጣኙና ስፖርተኞች የሙያም ሆነ የግንዛቤ ደረጃ ያጎለብታል በሚል ይጠበቃል። እንደ እግር ኳስ ባሉ ስፖርቶች በተለይም ኢትዮጵያ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ካላት ፍላጎት ጋር በተያያዘ፣ በስፖርት ገበያ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አስተዳደር እንዲሁም በመሳሰሉት ላይም የልምድ ልውውጥ ማግኘት እንደሚቻልም ታስቧል።
የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ የተቋሙን ባለሙያዎች ተቀብለው አወያይተዋል። በእዚህም የፕሮጀክቱ ዓላማ የሚበረታታ በመሆኑ በተቀናጀ ሁኔታ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተደራሽነቱን እንደሚቀጥልና የተሻለ ውጤት ዘርፉ ማስመዝገብ እንደሚያስችል ገልጸዋል። ኢትዮጵያን በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ መንግሥት እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ በስፖርቱ ዘርፍ ይህን መሰል ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው ሥልጠናዎችን መስጠት አንዱ ማሳያ ነው። በመሆኑም እንደእዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች ቀጣይነት ሊኖራቸውና የሴቶችን የተሳትፎ ደረጃም ማሳደግ እንደሚገባም አሳስበዋል። የፕሮጀክቱን ውጤታማነት በመገምገም በቀጣይ አብሮ ለመሥራት የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያመላከቱት።
በብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም