
በ18ኛው ክፍለ ዘመን ስኮትላንዳዊው ጄምስ ብሩስ ከካይሮ እስከ ጣና ድረስ ተጉዞ የዓባይ መነሻ ጣና ሀይቅ መሆኑን እስኪያውጅ ድረስ፣ ኢትዮጵያ የታላቁ ወንዝ ምንጭ መሆኗን ዓለም አልተረዳም ነበር። በተመሳሳይ መልኩ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘመን እውን እስኪሆን ድረስ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም ዓባይን መገንባት እንደሚችሉ ዓለም አልተረዳም ነበር። አሁንም ኢትዮጵያውያን በራሳችን አቅም በአፍሪካ ግዙፍ የተባለውን ግድብ ገንብተን ማጠናቀቃችን አልዋጥ ያላቸው ወገኖች መኖራቸውን እየተመለከትን ነው።
ጋሼ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በዓባይ ጉዳይ ግብጽና ሱዳንን አደራድራለሁ ብለው ሲንደረደሩ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ አንድ ጽሁፍ አስነብቦ ነበር። ጽሑፉ የአንድ ገበሬን እና ዝንጀሮን ታሪክ ታክኮ የቀረበ ነው። እንደሚከተለው ይነበባል።
አንድ ገበሬ ማሳው ላይ በቆሎ እየዘራ አፈር ይመልሳል። የተዘራ በቆሎን ከአፈር ውስጥ አውጥቶ የሚበላ ዝንጀሮ ደግሞ ቁጭ ብሎ በአንክሮ ይመለከተዋል። ገበሬው ሥራውን ጨርሶ ወደ ቤቱ ለማቅናት ሲነሳ ዝንጀሮ ከነበረበት ጉብታ ወርዶ ተጠጋው። ከዚያም «ምንድን ነው ስትዘራ የነበረው» ብሎ ጠየቀው። ገበሬውም ከአፈር አውጥቶ ለመብላት አይመችምና «ተልባ ነው የዘራሁት» አለው። በዚህ ጊዜ ገበሬውን ያላመነው ዝንጀሮ «ለማንኛውም ጭረን እናየዋለን» አለው።
ኢትዮጵያም በዓባይ ጉዳይ ከግብጽ ጋር በምታደርገው ድርድር እየተከተለች ያለችው ይህን ጭሮ የማየት ፖሊሲ ነው። ግብጽ አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት የሚሳተፉበት ድርድር እንዲካሄድ ጥያቄ ስታቀርብ ኢትዮጵያ አሻፈረኝ ያላለችው ለዚህ ነው። ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ሌባ ጣታቸውን እያወዛወዙ ተደራዳሪዎቹ ወደ ዋሽንግተን እንዳያመሩ አስጠንቅቀው ነበር። ተደራዳሪ ቡድኑ ከቤተ መንግሥት እንጂ ከማኅበራዊ ድረ ገጽ ትዕዛዝ ስለማይቀበል በድርድሩ ሂደት ሲሳተፍ ቆየ። በኋላ አክሮባቲስቷ አሜሪካ በብርሃን ፍጥነት ከታዛቢነት ወደ ዳኝነት ስትሸጋገር ኢትዮጵያ መድረኩን ጥላ ወጣች።
ከአምስት ዓመታት በፊት የተሰነዘረው ይህ ሃሳብ ዛሬም የማይሠራበት ምክንያት የለም። ምክንያቱም ያ ጊዜ ገላጋይ ሆነው የቀረቡት ጋሼ ዛሬም በዚያው አቋማቸው ተገልጸዋል። ሰሞኑን ባደረጉት የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት በሳበ ንግግራቸው ዳግሞ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጀንዳ አድርገውታል። ሀገራቸው ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች የሚል እምነት እንዳላቸው የጠቀሱት ጋሼ፣ ግድቡ ለግብፅ የውሀ አቅርቦት ስጋት እንደሆነ ተናግረዋል።
ቆፍጠን ብለው ‹‹ግብጽ የእኛ ጥሩ ጎረቤት ናት። የእኔም ጥሩ ወዳጆች ናቸው። ይሁንና ግድቡ ወደዚያ የሚሄደውን የዓባይ ወንዝ ውሀን ዘግቷል›› ብለዋል። ጨምረውም ‹‹እኔ ግብፅን ብሆን የዓባይ ወንዝ ውሀ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። እና ግድቡ ትልቅ ችግር በመፍጠሩ በዚያ ላይ እየሠራን ነው። ይፈታል ብለን እናምናለን።›› ካሉ በኋላ የዓባይ ውሃ ለግብፅ የሕይወትና የገቢ ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።
የታችኛዋ ሀገር ሰውዬ በጋሼ ንግግር ጮቤ መርገጣቸውን የተረዳንበትን አስተያየት እንካችሁ ለማለት ጊዜ አላጠፉም። የዓባይ ውሃን በተመለከተ ጋሼ ለተናገሩት ነገር አድናቆት አለን ብለዋል። በኤክስ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ጋሼ ላደረጉት ንግግር ግብፅ ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች ነው ያሉት።
በዚህ ብቻ አላበቁም፤ ይህ የጋሼ ንግግር በሥልጣን ዘመናቸው ግጭቶችን ለመፍታትና ጦርነቶችን ለማስቆም ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አመላካች ነው። በዩክሬይን፣ በፍሊስጤምና በአፍሪካ ውስጥ ያሉትን ውስብስብ ፈተናዎች ለመፍታትና ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ያላቸውን እምነት በድጋሚ አረጋግጠዋል በማለት እጅ መንሻ ውዳሴ አቅርበዋል።
ቀጠል አድርገውም፤ ጋሼ የኢትዮጵያን ግድብ በተመለከተ የሁሉንም አካላት ጥቅም የሚያስጠብቅ ፍትሀዊ ስምምነት እንዲደረግ ያላቸውን ፍላጎት አንጸባርቀዋል። የዓባይ ውሀን ለግብፅ የሕይወት ምንጭ እንደሆነ በመግለፅ ላደረጉት ንግግር ከፍተኛ አድናቆት አለን። ጋሼ ለቀጠናው ሰላም፣ ደህንነትና መረጋጋት ያላቸውን ራዕይ እንደግፋለን ብለዋል።
ጋሼ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ እንዲህ ያለ መግለጫ ሲሰጡ ይህ 2ተኛ ጊዜያቸው ነው። ነገሩ ቁጥቋጦም ሲያድግ ዛፍ ይሆናል አይነት ስለሆነ ከኢትዮጵያ በኩል እንዳች መልስ መሰጠት አለበት የሚል ውትወታ ከግራ ቀኝ ሲሰማ ነበር። በግድቡ ዙሪያ ያሉ ሁኔታዎችን በቅርበት የሚከታተሉ አንድ ምሁር ለአንድ ሀገራችን ሚዲያ በሰጡት አስተያየት፤ እንዲህ ያሉ ተደጋጋሚ ያልተገቡ አስታየቶች ምላሽ ካልተሰጣቸው አላስፈላጊ ቀጠናዊ ውጥረቶችን ሊያባብሱ ይችላሉ። እነዚህን አሳሳች አስተየቶችን ለመፍታት እና ማስተካከያ እንዲደረግበት የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ማጠናከር አለበት። የግድቡን ግንባታ ስንጀምር የታችኛዋ ሀገር በዲፕሎማሲው ረገድ የነበራን ከእኛ የተሻለ አቅም ተጠቅማ ምንም አይንት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፋ ከውጭ እንዳናገኝ አድርጋናለች። ግድቡን በራሳችን አቅም መገንባታችን ሀገራዊ እንድነትን የፈጠረና ኢትዮጵያውያን ከተባባርን ከፊት ለፊታችን የሚኖርን የትኛውንም ተራራ መሻገር እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት ግዙፍ ፕሮጀክት በመሆኑ ትርጉሙ መልከ ብዙ ነው ሲሉ መክረዋል። መንግሥትም ተገቢውን ነገር አድርጓል።
ጋሼ “እኔ ግብፅን ብሆን ናይል ወንዝ ውስጥ ውሀ እንዲኖር እፈልጋለሁ። እሱ ችግር ላይ ሥራ እየሠራንበት ነው፣ ይፈታልም። በዓለም ትልቅ ከሚባሉት ግድቦች አንዱን ከግብፅ ወጣ ባለ ቦታ ነው የገነቡት። የናይል ወንዝ የግብፅ ሕይወት ነው። ይህንን ደግሞ መውሰድ እጅግ አስገራሚ ነው፣ ይህንን በፍጥነት እንፈታዋለን ያ ደግሞ ትልቅ ችግር ሆኗል” ሲሉ መደመጣቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሩ የሚገኙትን የጋሼ ሰው ጠርቶ አነጋግሯል። በዚህ ጊዜም የኢትዮጵያን እውነት እና መሬት ላይ ያሉ ሀቆችን ለጋሼ ሰው ማስረዳት ተችሏል።
ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ መዋጮ እና በሀገር ውስጥ ሀብቶች የተገነባ ነው። ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ገንዘብ በማግኘት በዓባይ ወንዝ ላይ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ለመገንባት ለበርካታ ዓመታት ብዙ ሙከራ አድርጋ የነበረ ቢሆንም በላይኛዋ ሀገር ብርቱ ተፅእኖ መክሸፉ የአደባባይ ሀቅ ነው። ለዚህም ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መላው ኢትዮጵያውያን በሚያደርጉት አስተዋጽኦ መገንባት ብቸኛ አማራጭ ሆኖ የተገኘው።
ለታችኛዋ ሀገር የውሃ ደህንነት ምንም አይነት ስጋት እንደማይፈጥርም ቲክኒካል በሆነ መንገድ መረጋገጡ የማይካድ ሀቅ ነው። 15 ዓመታት የዘለቀው ውትወታ አስኳል የቅኝ ግዛት ዘመን የእውር ድንብር ውል አሁንም ገዢ ይሁን የሚለው ወልጋዳ አቋም ነው። ነገሩንኮ ቆም ብለን ካሰብነው አይናችሁን ጨፍናችሁ እናሞኛችሁ አይነት ቀልድ ነው። መቼም እንዲህ ያለውን ነገር ጅል አይሙት እንዲያጫውት ብለን አናልፈውም።
ጋሼ እንደሚሉት ዓባይ የታችኛዋ ሀገር ሕይወት አይደለም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ በአንድ ወቅት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ ግብጽ የውሃ ችግር የለባትም። እንዲያውም ውሃ በብዛት ታባክናለች። በርሃ ላይ በተሠራው አስዋን ግድብ ብቻ ከ10 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ ይባክናል። ሁለተኛ ግብጽ ውስጥ የሚሠራበት የውሃ አጠቃቀም የጎርፍ መስኖ ጥንታዊ የሆነ የመስኖ አሠራር ነው። ውሃውን በቦይ እየወሰዱ ከትልቁ ቦይ በትንሹ ቦይ እያደረጉ ከዚያ ደግሞ በቀጭኑ ቦይ እያደረጉ እጽዋትና አትክልት ውስጥ ውሃ በጎርፍ ያሰራጫሉ። ይሄ በርሃ ውስጥ የሚሠራውን እርሻ ቢያለማም በእርሻ ቦታ ላይ የሚፈሰውና የሚንጠለለው ውሃ እጀግ በከፋ መንገድ ለትነት የተጋለጠ ነው። እዚያም ላይ ከ10 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ ይባክናል። ይሄ ብቻ አይደለም አሁን ግብጾች የናይልን ውሃ ከተፈጥሮ ተፋሰሱ በብዙ አቅጣጫ እየወሰዱ እያባከኑት ነው።
አንደኛ በርሃ ውስጥ በሠሩት ቶሽካ በሚባለው ትልቅ የእርሻ ልማት ከአምስት ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ያለ ውሃ ወስደው ያባክናሉ። ይሄ አንድ ትልቅ የማባከኛ መንገድ ነው። ሌላው የናይልን ውሃ እንደገና በቀይ ባሕር ከታች በመሬት ስር በቱቦ ወስደው በሲናበርሃ ላይ ሻርም አል ሼክ የሚባለውን አሁን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔው የተካሄደበትን ከተማ አልምተውበታል። በከተማው የሚገኘው የውሃ አገልግሎት የእርሻን ሥራና ሌሎች የመንደር ልማቶችን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ከናይል ወንዝ የሚገኝ ነው። ይሄም ትልቅ ብክነት ነው ማለት ይቻላል። ሌላው አሁን ፕሬዚደንት አልሲሲ በቀይ ባሕር ጫፍ ላይ በስዊዝ ካናል አጠገብ በጣም ትልቅ ዘመናዊ ከተማ እየገነቡ ነው። ይሄ በዓለም ላይ አዲስ ፕሮጀክት ተብሎ በእነሱ በኩል ትልቅ አድናቆት የሚቸሩት ነው። በርሃ ላይ ያንን ሕንጻና መንገድ ለመገንባት የናይልን ውሃ ከተፈሯዊ ተፋሰሱ ውጪ ቆልምመው ወስደው ነው የሚጠቀሙበት። ስለዚህ ብዙ አይነት የውሃ ማባከን ሥራዎች እያካሄዱ ስለሆነ ውሃ እየቆጠብን ነው ወይም ልንቆጥብ ነው የሚሉት ነገር ትክክለኛ አይደለም። ሌሎች ውሃ እየከለከሉን እኛ ግን ውሃ ቆጣቢ ነን ብለው ለዓለም ለማሳየት በአብዛኛው ለፕሮፖጋንዳ እና ሌሎችን ለመወንጀል የሚጠቀሙበት እንጂ ከባሕር ውሃ ጨው ለይተው ለመጠቀም ከሚያደርጉት ሙከራ ውጪ የተቀሩት ጉዳዮች ውሃ የማይቋጥሩ ናቸው።
ግድቡ ለታችኞቹ ሀገራት ስጋት የሚሆንብት ምክንያት የለም። እንዲያውም ኢትዮያ እያካሄደች ያለችው የተፈጥሮ ጥበቃ እነርሱን ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለይም የአየር ንብረትን በሚያሻሻልና የኢትዮጵያንም ልማት እጅግ በጣም ተስፋ ባለው መሰረት ላይ የሚያኖር ሥራ እየተሠራ ነው። በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ለአየር ንብረቱ ተስማሚ የሆኑ የውሃ ትነትን የሚቀንሱ እና የውሃ ግኝቱን ከፍ የሚያደርጉ ተክሎችን በሰፊው ተተክለዋል። ኢትዮጵያ የተያያዘችው ከአየር ንብረት ጋር የተስማማ የእድገት አቅጣጫ በተለይ በታዳሽ ኃይል በኩል የሚኖረው አስተዋጽኦ ከራሷ አልፎ ጎረቤት ሀገራትን የሚጠቅም ነው።
ጋሼ ማስተላለፍ የነበረባቸው መልዕክት የኢትዮጵያ ጎረቤቶች በሕዳሴ ግድብ እና ለወደፊትም በሚሰሩ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች ላይ ትብብር እንዲያደርጉና በቀና መንፈስ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ተንቀሳቀሱ የሚል መሆን ነበረበት።
መግነጢስ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም