ስለ ሚተራሊዮን

በንጉሥ ሠገነት ላይ ቆማ፣ ከላይ እንደ ፀሐይ የብርሃን ጮራ የምትፈነጥቅ ውብ ልዕልት ነበረች ሚተራሊዮን። ላያት ሁሉ ፈገግታዋ የልብ ምትን የሚያዛባ ልዩ ሴት። ግን ምን ዋጋ አለው፤ አሁን ደስታን ተርባ ስለመደሰት ትናፍቃለች። ሰላምን ተጠምታ ለጥሟ የደረቀ ምራቋን ትውጣለች። በህመምና ስቃይ ተይዛ፣ ከሁለመናዋ ርቃለች። እጅግ የምታሳዝን ምስኪን ሆናለች። ግን ማንስ ነው የሚያዝንላት? ለረሃቧ ምግብ፣ ለጥሟ ውሃ የሚያቀብላት ማነው? ለእግዜር ብሎ የሚጸድቅባት፣ ለአላህ ሲል ሰደቃ የሚሠራባት የቱ ደግ ነው? አዎን ተስፋ አላት፤ ሚተራሊዮን ተስፋ አላት። ኢትዮጵያ ተስፋ አላት። እንዲያው ግን ለዚህ የዳረጋት ምን ይሆን?

“የእዚህ ሁሉ መከራ ምንጭ መንታ ችግር ነው። በየዘመኑ ያገባቻቸው ክፉና ስግብግብ ባሎቿ ራስ ወዳድነትና ጭካኔ የወረሱት ዓለም ዥንጉርጉር ልጆቿ ናቸው። ጀግናና ፈሪ፣ ጎበዝና ሰነፍ፣ ለጋስና ቀማኛ፣ አማኝና ቀማኛ የወለደችበትን ማህፀኗን ያልበላ አንጀቷን ተደግፈው ሲራገጡ የኖሩት ልጆቿ ችግሯን ካለማወቃቸው የተነሳ ይኼው ለርሷ ጤና ማጣት፣ ለራሳቸው ደግሞ መከራን ጋበዙ። ረሃብ፣ እርዛት፣ ጦርነትና ስደት ዕጣ ፈንታቸው ሆነ። … ለሕመሟ ማስታገሻ ለችግሯ መፍቻ ከልጆቿ ዘንድ እስካሁን አላገኘችም።” ይላል፤ በዶክተር አለማየሁ ዋሴ “ሚተራሊዮን” በተሰኘችው መጽሐፉ ውስጥ። የደራሲው አምስተኛ የልቦለድ ሥራው ናት።

የውበት አማልክት መስላ በሽፋኑ ስዕሉ ላይ የምትታየው ሚተራሊዮን፤ ኢትዮጵያን ትመስላለች። በወጣትነት መልኳ ላይ የሚነበበው ደምግባትና ቁንጅናዋ ሁሉም የሚመኛትና የምትስብ ዓይነት እጹብ ነች። ከፊት ተጎንጉኖ ከማጅራቷ ትይዩ በላይ ተራራ የሠራው የሀር ፈትል ጸጉሯ በብርሃን ፍንጣቂ አንዳች ምልክትን ይዟል። ከለበሰችው የሃበሻ ቀሚስ፣ ከላይ ስስ ነጠላዋን ጣል አድርጋ፣ በሃምራዊ ጥለት በተዋበው የአንገቷ ዙሪያ ከመሃል ማህተቧ ቁልቁል ወርዶ ስትታይ ከሁኔታዋ ጋር ታሳሳለች። ጎላ ያለው ዓይኗ ሩብ ጨረቃን የመሰለ ጸአዳነት ይታይበታል። ዳሩ ለሚመለከታት እንጂ፤ ውስጧ በአንዳች መብሰልሰል፣ በትካዜ ህመም ሰቅዞ ፊቷን ወደግራ አዙራና አቀርቅራ ነው የምንመለከታት።

ሚተራሊዮን ከሽፋን ስዕሏ የአሁኗን ኢትዮጵያን ተመስላ ስለመቀመጧ ብዙ ይነግረናል። ከወደ አናቷ ክምር ያለው ጸጉሯ፣ ስሩን ከትከሻዋ ላይ ያደረገ እንደ ዋርካ ያለ ግዙፍ ዛፍ ሆኖ ይታያል። ከዚህ ዛፍ የጀርባ ትይዩ ካለች የጀንበር ፀሐይ የተነሳ፣ የብርሃን ፀዳል ከቅርንጫፎቹ መሃከል እየፈነጠቀ ሲወጣ እንመለከታለን። ከጸጉሯ አቀማመጥ ተነስተን ከፊቷ ላይ ስልክክ ብሎ እስከወረደው አፍንጫዋ ድረስ ያለው ገጽታዋ የኢትዮጵያ ካርታን ቅርጽ ይዟል። አፍንጫዋን በካርታው ላይ ከመሃል እንደ ጀበና ጡጦ ሾጠጥ ብሎ የወጣውን ስፍራ በመመሰል፣ ከአንገት በላይ ያለውን ሙሉ ገጽታዋን ድንቅ በሆነ መልኩ ሰዓሊው ተጠበቦታል። የሚተራሊዮን ወደግራ ዞሮ ማቀርቀር አንድም ይህን ምስል ለማምጣት የተደረገ ቢመስልም፤ ግራን መመልከቷ ከመጽሐፉ ጭብጥ ጋር የሚሄድና በራሱ ትርጓሜ ልንሰጠው የምንችለው ግሩም አቀማመጥ ነው። ኢትዮጵያ ታማለች፤ ግን ከምስሏ ላይ ያረፈው የብርሃን ፀዳል ደህና የምትሆንበት ጊዜ እንደ ፀሐይዋ ዞሮ እንደሚመጣ ውስጧን በተስፋ ይሞላዋል። “ሀገር ስታጣ ሁሉን ታጣለህ” ይላልና ተስፋው የሁላችንም ነው።

ከጅምር እስከ ፍጻሜ መጽሐፉን የሚተርክልን አንድ ተራኪ ነው። በየመሃሉ ከተሰነጉ ምልልሶች ጋር ጥሩ በሚባል መልኩ ተዋቅሮ፣ ፍሰቱን ይዞ ይወርዳል። የታሪኩ መቼት ከኢትዮጵያ እስራኤል፣ ከእስራኤል ኢትዮጵያ እየተጓዘ፣ ከሁለቱም መነሻዎች ወደ አንድ መንገድ ለመምጣት ይዳክራል። ከጊዜ አንጻር ረዘም ያሉ ልዩነቶች ያሉበት ቢሆንም፤ በተምሳሌታዊ ወጉ ልንቃኘውም ጭምር ይገባል። በሃሳብ ደረጃ የማይነሱና የማይዳሰሱበት ጉዳይ የሉም። ከፖለቲካ እስከ ሃይማኖት፣ ከባህል እስከ ዲፕሎማሲ፣ ከማኅበራዊ እስከ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ከፍልስፍና እስከ ምክር ሁሉ የታጨቁበት ነው።

ከአንደኛው ጀንበር ምስኪኗ ሚተራሊዮን በያዛት ህመም ስትቃትት እየጠናባት በአካላዊ ሰውነቷ ጭምር ቆርቁዛ አሳዛኝ ሆናለች። ከስታለች። ጠቁራለች። ጉስቁልናዋ ከመልኳ ላይ አግጥጧል። በዚያ ላይ ደም ይፈሳታል። በሽታዋ ግርሻ ነው። በዚህ ከባድ ደዌ ተመትታ የመዳን መሻሯ ነገር አጠራጣሪ አድርጓታል። እርሷን ሊያድናት የሚችለው ዘመናዊ ሕክምናው ሳይሆን፤ በእጽዋት ላይ የረቀቀው የጥንት አባቶቻችን ጥበብ ብቻ ነው። መድኃኒቷም አንድ እጽ ብቻ ነው። እሱን ፍለጋ የሚላከው ሲሳይም፣ ከአዲስ አበባ ኢየሩሳሌም ገዳማትን እየማሰነ ይተርክልናል። ሲሳይ የተራኪነቱን ካርታ የሳበበትን ቁልፍ በደራሲው ተሰጥቶታል። ከጅምር እስከ ፍጻሜው፣ በገደል በሰርጡና በሜዳ ተራራው እየኳተነና እያስኳተነ ይተርክልናል። በትረካው ውስጥ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ቁርኝት የበዛና ሁሉን ለተፈጥሮ የሚያደላ ሆኖ ብናገኘው፤ ተራኪው የብዝኀ ሕይወት ተመራማሪ በመሆኑ ነው።

ታዲያ “ሚተራሊዮን” ብሎ ስም ለሁላችንም እንግዳ መሆኑ አይቀርም። ሲሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ እርሷን የተመለከተበትን አጋጣሚና ያንን ቅጽበት ሲነግረን ከሚያነሳው ጉዳይ አንዱ ይኸው ነው። “…እንዲህ ያለ የክርስትናም ሆነ የዓለም ስም ሰምቼ አላውቅም” ይላል። እርሷን የተመለከተው ወደ አንድ ገዳም እየሄደ፣ በመገዳሙ ውስጥ ይኖሩ ከነበሩ አባት ጋር ያወጋና ይመክር በነበረበት ጊዜ ነው። በዚያች በተመለከታት ቅጽበትም “ያልተበጠረ ዞማ ጸጉሯ፣ ያልተከረከመው ለስላሳ ጥፍሯ፣ የገረጣው ፊቷ፣ የተዛነፈው ቅርጽዋ፣ የተቀዳደደው ድሪቶ ልብሷ ውበቷን አደበዘዘው እንጂ አላጠፋውም ነበር” ሲል የነበረችበትን ሁኔታ ሲሳይ ይገልጸዋል። ከውስጧ የሚታየውን ነገር በቃላት ካሽሞነሞናት በኋላ እንደገና “…ከጉስቁልናዋና ከለበሰችው አዳፋ ልብስ ጋር አብረው የማይሄዱ የሚመስሉ ውብ ቅርጽ ያላቸውን እድሜ ጠገብ ጌጦች በአንገቷ ዙሪያ አስራለች” በማለት ከድሮ ማንነቷ ተራርቃና ተጠፋፍታ እንደምትኖር ይነግረናል።

ዓለም ሁሉ የሚፈራት፣ ታላቅና ገናና የነበረች ኢትዮጵያ ዛሬ መልኳ ይህቺኑ መሳይ ነው። ስንቱን ጥበብ ተጠባ፣ ስንቱን የዕውቀት ማድጋ እንዳልሞላች፣ የስልጣኔን ፋኖስ አብርታ በጨለማው ስንቱን እንዳልመራች ሁሉ…ዛሬ የሚታየው ጉስቁልና ረሃሀብ ቸነፈሯ ነው። የሚተራሊዮን በሽታ መጀመሪያው እንዲህ ባለው ስቆ በመቆዘም፣ ሆኖ ባለመሆን፣ ጠግቦ በመራብ፣ ፈክቶ በመጠውለግ፣ አግኝቶ በማጣት የወላለቀ ሕይወት ነው። አባ ለሲሳይ ባስተዋወቋት ጊዜ ስለ እርሷ ያሉት አንድ ነገር ደግሞ ነበር፤ “እየውልህ ከረጅም ዘመን ጀምሮ ደም ይፈሳታል። የሚፈሳት ደም ክብሯን፣ ፀጋዋን፣ ሀብቷን፣ አካሏንም ጭምር እንዲህ እንደምታየው አጎሳቁሏታል” በማለት በገዳሙ ውስጥ ያገኛቸው አባ አካለ ወልድ ለሲሳይ ይነግሩታል።

ገና መጽሐፉን ስንገልጥ፤ ተራኪው ሲሳይ ወደ ሀገረ እስራኤል ለማቅናት በመንጎዳጎድ ላይ እንደሆን እየነገረን ትረካውን ይጀምራል። የሚሄደውም ለመንፈሳዊ ጉብኝት ሳይሆን፤ የሚተራሊዮንን መድኃኒት የሚያገኙበት ምስጢር ያለው በእስራኤል ገዳም ውስጥ ካሉ አባቶች ዘንድ እንደሆነ ተነግሮት ነው። አባ አካለወልድ የተባሉ አባትም ይህን ተልዕኮ ለሲሳይ ሰጥተው እንደላኩት ነው የሚገልጽልን። ከሲሳይ መሳ ለመሳ የቆሙ ሁለት ገጸ ባህሪያትን ደግሞ እናገኛለን፤ ዶክተር ክብረ በዓል እና ነቢል የሚሰኙ። ሁለቱም የሲሳይ ወዳጆች ናቸው። ዶክተር ክብረ በዓል መንኩሶ አሁን ስሙ “አባ መዐዛ ቅዱሳን” ሆኗል። ነቢል ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይና ሌላኛው የልብ ወዳጁ ነው።

ገጸ ባህሪያቱ የተቀረጹበትን መንገድ ስንመለከት፣ ደራሲው ሆነ ብሎ ያደረገው አንድ ነገር እንዳለ እንገነዘባለን። በግራና በቀኝ ያሉትን ክብረ በዓልን እና ነቢል ወይንም ሲሳይ እና ነቢል የተወከሉበት ሁኔታ እንደ አንድ ክርስቲያንና ሙስሊም ወዳጆች ብቻ አይደለም። ታማሚዋን ሚተራሊዮንን በማዳን ሂደት ውስጥም፣ እኩልና ፍትሃዊ ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲጥር እንመለከታለን። ደራሲው የሄደበት መንገድ እጅግ የሚደነቅና ከዚህ ቀደም በድርሰት ሥራዎቻችን ውስጥ ሲኮነን ለኖረው ጉዳይ ምላሽ የሰጠበትም ጭምር ነው። ነገር ግን፤ ከሃይማኖታዊ ኮታው ይልቅ ነጻ ወዳጅነታቸው ገዝፎ ቢወጣ ደግሞ ይበልጥ ማራኪ ውበት ይኖረዋል።

በክብረ በዓልና በነቢል መካከል ግን መከባበር ብቻ ሳይሆን ጥልቅ ፍቅር እንዳለም እናያለን። “…እኔ ትክክል ሆኜ ከአላህ ፊት ስቀርብና ‹ወደ ጀነት ግባ› ስባል አንተ ስህተተኛ ሆነክ ‹ወደ ጀሃነም ሂድ› ስትባል ቸሩ አላህ ሆይ ኪብሩን ጀነት አብረህ ካላስገባህ ብቻዬን አልገባም እላለሁ ወይም ደግሞ አንተ ትክክል ሆነክ ክርስቶስ ፊት ስትቀርብ ‹ወደ ጀነት ግባ፣ ነቢል ወደ ጀሃነም ይሂድ› ሲባል ‹እሱንም ጀነት ካላስገባህ እኔንም ጀሃነም አስገባኝ› ትላለህ። በዚሁ መልኩ ሁለታችንም ሴፍ እንሆናለን” በማለት ነቢል ለክብረ በዓል ይናገረዋል። ይሄኔ በነቢል ንግግር እንባ የተናነቀው ክብረ በዓልም ከመቀመጫው ብድግ ይልና “አይዞህ በተለያየ መንገድ ብንጓዝም በቅንነት እስከሆነ ድረስ ፈጣሪ ቅን ፍርዱን አይነሣንም” በማለት ዶክተር ክብረ በዓል፣ ነቢልን ለማበርታት ሲሞክር እናያለን። አውዱ ተስፋ ውስጥን ማበርቻ ብቻ ሳይሆን አንዲት ሚተራሊዮንን ለማዳን ሃይማኖታዊ ልዩነቶች እንቅፋት ሊሆኑብን እንደማይችሉም የሚያሳይ ነው። በሁለት የተለያዩ ነገሮች ውስጥ አንድ ሆኖ እስከሞት ድረስ ለመዝለቅ የጋራ የሆነ አንድ ውስጣዊ ኃይልና ስሜት መገንባት ወሳኙ ነገር ነው።

ደራሲው ዶክተር አለማየሁ ዋሴ፤ ከሚተራሊዮን ጀርባ በዛ ያሉ የጉዞ ማስታወሻዎችን እንደተጠቀመ የሚያመላክቱ በርካታ ሁኔታዎችን እናገኛለን። በትረካው ውስጥ የሚያነሳቸውን የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ጸጋዎቿን የተመለከተበትና የገለጸበት መንገድ እጅግ ልዩ ናቸው። የሚጠቅሳቸውን ስፍራዎች የሚገልጻቸው ካነበበውና ከነበረው ጠቅላላ ዕውቀት በመነሳት እንዳልሆነ ያሳብቃሉ። ተፈጥሮን ከማድነቅ ባለፈ ምርመራ የታጀበ የመኪና ጉዞ በሲሳይና በወዳጁ ሲደረግ ያለውን እግር በእግር ይተርክልናል። ደራሲው ምናልባትም ሲሳይን በርሱ ወንበር ላይ በማስቀመጥ ያደረገው ረዥም የጉዞ ቅኝት ነው። ሁለቱ ወዳጆች በጉዟቸው ከገጠራማው አካባቢዎች ላይ በሚደርሱበት ጊዜ ከሚመለከቱት የተፈጥሮ ውበት መነሻነት የሚያንሸራሸሩ ሃሳቦችና ምልልሶች፣ ስለተፈጥሮ ሀብቶቻችን ገና ምኑንም እንዳልያዝን የሚያሳስቡም ጭምር ናቸው። ከመኪናቸው በመውረድ አፈርና ድንጋዩን ሳይቀር እየተመለከቱ ልዩና የማንገምተውን ያስመለክቱናል። እንዳለን እንጂ፤ የት ምን እንዳለን አናውቅም። በጉዞው ላይ ለምርምርና ጥናት የሚያበቁን ጠለቅ ያሉ ሃሳቦቹን ሁሉ ሲያነሱበት እንመለከታለን። አንደኛው የመጽሐፉ ጥንካሬና ውበትም ይኸው በተፈጥሮ ውስጥ ያለው ምልከታ ነው።

ነቢልና ሲሳይ ሲያደርጉት በነበረው ጉዞ፣ ከተፈጥሮው ጀርባ የተመለከቷቸው እረኞች ቀልባቸውን የሰወረው ነገር ነበር። በዚህ መካከል የነቢል ሁኔታ ያስገረመው ሲሳይ፣ አንድ ነገር እንዳስታወሰው ይነግረናል። “…አንድ ወዳጄ ሰሜን ተራራ በረዶ ከሚፈላበት ስፍራ እራፊ ጨርቅ የለበሱ እረኞችን አይቶ እሱ ራሱ ደራርቦ ለብሶ ብርዱን አልቻለውም ነበርና ሁኔታቸው ገርሞት፡-

“ልጆች አይደበርዳችሁም?“ ሲላቸው
“ጋሼ! ሀገር ይበርዳል እንዴ? “ብለው አሉኝ ብሎ አጫውቶኝ ነበር” ይለናል።

ልጆች፣ ምናልባትም ደግሞ ምንም ያልተማሩ እረኞች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ምላሻቸው ግን እንደ ዕድሜያቸው የልጅነት አነበረም። ጸጥ ባለ ውቅያኖስ ላይ እየሄድን ድንገት ቅጽበታዊ ሆኖ እንደሚነሳ ማዕበል፣ ጭር ባለ ሰላማዊ መንደር እየተጓዝን ድንገት ብው! ብሎ እንደፈነዳ ፈንጂ ያለ ምላሽ ነው። ሀገሪቱ ውስጥ የሚነፍሰው ነፋስ፣ የሚባረደው ውርጫማ ብርድ ለሚያየው የሚያንሰፈስፍ ነው። ፖለቲካው ከስጋ አልፎ ውስጥን የሚቆረጥም ብርድ ነው። ሰላም ማጣቱ የሚያርድ፣ የሚያንቀጠቅጥ ብርድ ነው። ከነፋሱ ጋር የሚነፍሰው የረሃብ ውርጭ ሆድን ከመሞርሞር አልፎ የሚያኮስስ ነው። ግን ታዲያ ሀገር ይህን ሁሉ ሰቆቃ ስላዘለች ትጠላለች እንዴ? በጭራሽ። የእረኞቹ ፍልስፍና ለአዋቂው የሚያስደነግጥ ነው። ቆም ብሎ ላስተዋለ ‹ምን ሆኛለሁ!…ምን ሆነናል!› የሚያስብል ነው።

“…ዘርፈህ ቤት ብተሠራ ይጨበጨብልሃል። ሰርቀህ ብትመጸውት ትመረቃለህ፣ 100 ሚሊዮን የሀገር ሀብት ዘርፈህ፣ አንድ ሚሊዮን ለቤተ ክርስቲያን ወይም ለቤተ መስጊድ ብትሰጥ ‘ምዕመናን እልል በሉላቸው ይባልልሃል’። ቢሊዮን አጭበርብረህ መልሰህ ሚሊዮን ለመንግሥት ፕሮጀክት ስትለግስ ከሀገሪቱ ባለሥልጣን ጎን ተቀምጠህ ‘የቁርጥ ቀን ልጅ‘ ትባላለህ።’

ብዙ ጊዜ ማስተዋል ያጎደለብን፣ ያልገባን ግን እንዲገባንም የማንፈልገው እውነት ነው። በመስጠት በመቀበል ውስጥ ያለብን ትልቁ ድክመትም ይኸው ነው፤ የሰጠ ሁሉ ለጋስና ቸር፣ መጽዋች ሁሉ ፈርሃ እግዚአብሄር ያለው ይመስለናል። ለሃይማኖታችን በጎ ያድርግ እንጂ፤ መቅደስ ቢረግጥ ስለ መንፈሳዊነቱ ጥርጥር አይገባንም። በሃይማኖታችን ስም ቢገድል ወንጀል መሆኑ ቀርቶ፣ ገነትና ጀነት የርሱ ናቸው። ባለሀብቱ ለመንግሥት ደህና ግብር ይከፈል እንጂ፤ ሕዝብን መዘበረ አልመዘበረ ግድ አይሰጥም። በስመ ርዳታ ‹ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንቆፍርላችሁ፣ መብራት እናስገባላችሁ፣ ትምህርት ቤት እንሥራላችሁ፣ ልጆቻችሁን ወስደን እናስተምርላችሁ…› የሚል ሁሉ ከሰማይ እንደወረዱልን መልአክ የምንቆጥር እንጂ፤ ለምን..እንዴት…ወዴት? ብለን የማንጠይቅ ምስኪኖች ነን። ይስጡን እንጂ ለምን እንደሰጡን ግድ አይሰጠንም። ዛሬ ‹ሌቦች› የምንላቸው በሱፍ ሽክ ብለውና ከረቫት አስረው፣ ሙሽራ የመሰሉ ናቸው። ‹እብዶች› የምንላቸው ብጭቅጫቂ ድሪቶ ለብሰው፣ ፌስታል የሚያንኳትቱትን ቢሆንም፤ እብዶቹ ግን ከተንፈላሰሰ ቪላ ጋር ቅንጡ መኪናዎችን እያፈራረቁ ‹እንቁልልጭ› በሚሉን ውስጥ ናቸው። እብዶቹ ከቀበሌ እስከ ሀገር በሚመሩን ውስጥ ናቸው።

“ዛሬ ምሥጢራዊ ነው የተባለውና ፈልጌ እንዳመጣው የታዘዝኩት ‹ቅርስ› ከእነርሱ ዘንድ ይገኛል ቢባል እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ጎርፍ ፈሳሽ ድንገቴ ሃሳብ ሊሆን አይችልም” ይላል ተራኪው ሲሳይ። ሆኖም እስራኤል ድረስ የኳተነበት ጉዳይ፤ እዚያ ካሉ አባቶች ፈቃድ ለማግኘት እንጂ የመድኃኒቱ ምስጢር ቀድሞም ከዚሁ ያውቁት እንደነበር አባ አካለ ወልድ በስተመጨረሻ ለሲሳይ ይነግሩታል። ነገር ግን ምንም ያህል ከቤተ እስራኤላውያኑ ጋር የተቆራኘ ቢሆን፣ ኢትዮጵያን ለማዳን ፈቃድ የምንጠይቀው ማንን ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ኢትዮጵያዊ ጥበብ ለመጠቀም የሌሎች ፈቃድስ ያስፈልገናል ወይ? ደራሲው ከምን አቅጣጫ እንደተመለከታቸው ግር ያሰኛል።

ሌላው ደግሞ፤ ተራኪው ከኢትዮጵያ እስከ እስራኤል በተገኘባቸው በእያንዳንዱ ስፍራዎች የሆነውን ነገር በተረከበት መንገድ እይታዎቹን ልናደንቅለት የምንችል ቢሆንም፤ ትንታኔው እየበዛ ከልቦለድነት መንፈስ እየወጣ፣ ወደ ታሪክ ነገራ ያደላል። በተለይ በኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ስፍራዎችን ሲጎበኝ በነበረበት ጊዜ፤ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮች አንስቶ፣ አንባቢው በሚያውቃቸው ነገሮች ውስጥ አንድ በአንድ ማብራሪያ እያስከተለ መሄዱ አሰልቺነት ሊያጎለብት ይችላል። ሃሳቦቹ እንዳሉ ሆነው፤ በተመጠነ ገለጻ፣ ስሜት ቆንጣጭ በማድረግ ልዩ የአተራረክ ስልት ቢጠቀም የበለጠ ውበት ይፈልቅ ነበር።

ሚተራሊዮን ግን፤ አሁንም መዳንን ትናፍቃለች። አሁንም ፈውስን ትሻለች። እንደ ሲሳይ መድኃኒቷን ፈላጊና ታዛዦች፣ እንደ ነቢል ቅንና ታማኞች፣ እንደ አባ አካለ ወልድ ያሉ አዋቂና መንገድ ጠቋሚ አባቶች ያስፈልጓታል። ከገጾች በላይ የሆኑ ሰፊና ጥልቅ ሃሳቦችን ስለያዘ መጽሐፍ ሁሉን ለማለት አይቻልምና ውቅያኖሱን መቅዘፉ ለናንተው አንባቢያን ይሁን።

በሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You