አቶ ተሾመ ብርሃኑ ከማል ይባላሉ። በጋዜጠኝነት፣ በደራሲነትና በታሪክ ጸሐፊነት ላለፉት 40 በትጋት፣ ያለመታከት ሲሰሩ ኖረዋል። ዛሬም በስተርጅና ከወጣቶችና ጎልማሶች በላይ በሕይወት ጉዟቸው የሰበሰቡትን እውቀት “ለትውልዱ ይድረስ” በሚል ውሳኔ እየጻፉ በብዙ ውጣውረድም እያሳተሙ ይገኛሉ።
በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮችን በመምዘዝ በጋዜጦች፣ መጽሔቶችና በመድረኮች ላይ ያለምንም ክፍያ አነቃቂና አስተማሪ ሃሳቦችን እያቀረቡ ይገኛሉ። አቶ ተሾመ የአገራቸው ወጣት በእውቀት እስኪበቃና ክንዳቸውንም እስኪንተራሱ ከማሳወቅ ወደኋላ የሚሉ አይመስልም። አቶ ተሾመ አብዛኛውን ጊዜያቸውን እውቀት ላይ በተለይም ንባብ ላይ እንደማሳለፋቸው ያወቁትን ለማሳወቅ የማይሰስቱም ናቸው።
በማኅበራዊ መገናኛ መስክም የተለያዩ ጉዳዮችን ከማሳወቅ አልፈው ሌሎች በሚጽፉት ሃሳብ ሥር በመግባት የተዛነፈውን አቃንተው፣ ስህተትን አርመው፣ ትውስታቸውን አካፍለው፣ ዘመንን አናጻጽረው አስተያየት በመስጠት ይታወቃሉ። ሆኖም አቶ ተሾመ ጎምቱ የጥበብ ሰው ቢሆኑም በቅጡ አልተነገረላቸውም ።
አንጋፋ ከሚባሉት ጋዜጠኞች መካከል ስማቸው የሚጠቀሰው ጉምቱ ጋዜጠኛ ተሾመ ፤ ከኢትዮጵያ ቴሌቨዥን ጀምሮ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ላይ በተለያዩ የጋዜጠኝነት እንዲሁም የአርታይነት ስራ ዘርፎች ላይ ለረጅም ዓመት ሙያዊ አበርክቷቸውን አድርገዋል። በሌላ በኩልም የተቋማት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ በመሆን ሰርተዋል። ከህጻናት የተረት መጻህፍት ጀምሮ እስላማዊ ትውፊትን ለትውልድ የማስተላለፍ ከፍ ያለ አቅም ያላቸውን መጻህፍትንም ጽፈዋል፤ እየጻፉም ነው። አገር በመቻቻል እንጂ የእኔ የእኔ በማለት አትለወጥም፤ ብልጽግናችንም እውን አይሆንም በሚልም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ላይ ሃሳባቸውን በማንሸራሸር ይታወቃሉ። የዛሬ የሕይወት ገጽታ አምድ እንግዳችን አቶ ተሾመ ብርሃኑ።
አቶ ተሾመ ብርሃኑ በ1943 ዓ.ም ሰቆጣ ከተማ በዛሬ አጠራሩ የዋግ ሀምራ ዞን ነው የተወለዱት።አቅማቸው ዝቅ ላሉት ቤተሰቦቻቸው ሶስተኛ ልጅ ሲሆኑ እንደ አገሩ ባህልና ወግም ቤተሰባቸውን በማገልገል ጎረቤቶቻቸውን በመታዘዝ ነው የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት።ትምህርትንም አንድ ብለው የጀመሩት በአካባቢው ባሉ አስተማሪዎች ቁርዓን በመቅራት ነበር።
“…… ተወልጄ ያደኩት ገጠር እንደመሆኑ አስተዳደጌም የገጠርን ባህልና ወግ የተከተለ ነው፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ቤተሰቦቼን እንጨት ለቅሜ በማቅረብ ኩበት በመሰብሰብ እንዲሁም የአካባቢዬ ሰዎች (ጎረቤቶቻችን) አህያ፣ ፈረስና በቅሎ ጠብቅ ሲሉ በመጠበቅ ነው ያሳለፍኩት” ይላሉ።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው በተወለዱበት አካባቢ በዋግ ስዩም አድማስ ወሰን ትምህርት ጀመሩ፤ በዚህ ትምህርት ቤትም እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ያለውን የትምህርት ሂደታቸውን በጣም ጥሩ ተማሪ ሆነው እንዳጠናቀቁት አቶ ተሾመ ይናገራሉ።
“……ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል የተማርኩት በተወለድኩበት አካባቢ ነው፤ ነገር ግን ሰባተኛ ክፍል ስደርስ አላማጣ ከተማ መሄድ ነበረብኝ በዛም የሰባተኛ ክፍል ትምህርቴን ከተከታተልኩ በኋላ ቀጣዩን የትምህርት እርከን ለመከታተል አዳጋች ሆነብኝ “ይላሉ።
አቶ ተሾመ በአካባቢው ከስምንተኛ ክፍል በኋላ ትምህርት ለመማር ብዙ መስዋዕትነት ይጠይቅ ስለነበር እርሳቸው ደግሞ እንደ አካባቢው ልጆች ስምንተኛ ክፍል ደርሰው ትምህርታቸውን ማቋረጥ ስላለፈለጉ ስደትን መምረጣቸውን ይናገራሉ።በዚህም ለትምህርታቸው ብለው ምንነቷን ወደማያውቋት የኔ ይሉት ሰው ወደሌላቸው ብቻ ችግርኛ ልጆችን ያስተምራሉ ሲባል ብቻ ወደሰሙበት አዲስ አበባ ከተማ መምጣትን ምርጫቸው አድርገው አዲስ አበባ ገቡ።
“…..ሰቆጣ ስምንተኛ ክፍልን የጨረሰ ተማሪ ትምህርቱን ለመቀጠል ወልደያ መምጣት አለበት፤ ነገር ግን ወልደያ ለመማር ከሰቆጣ ኮረም ሁለት ቀን በእግር መጓዝ ያስፈልጋል፤ ከኮረም ወደ ወልደያ ለመምጣት ደግሞ ሁለት ብር የትራንስፖርት ወጪ ነበር፤ ይህ ብቻም አይደለም ምግብ የሚበላው ተገዝቶ አልያም ቤተሰብ አቅሙ ኖሮት ከሰነቅ፤ ከቋጠረ ብቻ ነው፤ እኔ ደግሞ ይህንን ለማድረግ እናቴ አቅሙ የላትም፤ ስለዚህ የነበረኝ አማራጭ የምፈልገውን ትምህርት ለማግኘት አዲስ አበባ የተቸገሩ ልጆችን የሚረዱ በጎ ሰዎችን ለመፈለግ መምጣት ብቻ ነበር” ይላሉ።
ነገር ግን አቶ ተሾመ እነዚህን ደጋግ ሰዎች በቀላሉ ማግኘት አልሆነላቸውም መውጫ መግቢያዋን በማያውቋት አዲስ አበባ ከተማም ሌላ አስቸጋሪ ሁኔታ ገጠማቸው የሚያድሩበት አልነበራቸውም።የሚበሉት ነገርም አልነበራቸውም፤ ቤሳቤስቲን ሳንቲምም አልያዙም። ብቻ ግራ ግብት ቢላቸውም ተስፋ ግን ሳይቆርጡ ሶስት ወራትን ቆዩ።
የትምህርት ህልማቸው ይሳካ ዘንድ ከሚማሩበት የገጠር ትምህርት ቤት የያዟትን መልቀቂያ በመያዝ ወደበየነ መርዕድ (እድገት በህብረት) ትምህርት ቤት በመሄድ ይጠይቃሉ፤ ትምህርት ቤቱም እንዲማሩ ይቀበላቸዋል፤ ነገር ግን አሁንም የት ሆነው ምን እየበሉ እንደሚማሩ የሚያውቁት ነገር የለም።
“ ……ትምህርት ቤቱ መልቀቂያዬን አይቶ ሲቀበለኝ ሌላ ጥያቄ ደግሞ ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር አቀረብኩ፤ ምንም ረዳት የሌለኝ ብቻዬን በማላውቀው አገር ለትምህርት ብዬ የመጣሁ ታዳጊ መሆኔን ሲረዱም በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ማረፊያ ሰጥተውኝ እዛች እያረፍኩ (እያደርኩ) የስምንተኛ ክፍል ትምህርቴን ጀመርኩ” በማለት ይናገራሉ።
በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ በተሰጠቻቸው ማደሪያ እያረፉ ይማሩ ጀመር።አቶ ተሾመ ሌላም ችግር ነበረባቸው ለመማሪያ የሚሆን የትምህርት ቁሳቁስ የላቸውም ይዘዋት የመጧት ብጣሽ ወረቀት ከአንድ እርሳስ ጋር ብቻ ናት ያለቻቸው። ደብተር ገዝተው እንደ ተማሪዎቹ በቦርሳቸው ሞልተው የሚሄዱበት ሁኔታ ላይም አይደሉም፤ ይህንን ያዩ መምህራኖቻቸው ደግሞ በሁኔታው ግራ መጋባታቸው አልቀረም። እንደውም መማር የማይፈልጉ ዱርዬም ይመስሏቸው ነበር። ሙሉ በሙሉ እንደዛ እንዳይሉ ደግሞ የትምህርት ክትትላቸውና ሆነ የክፍል ተሳትፏቸው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አላስቻላቸውም። እናም በዚህ ግራ መጋባት ውስጥ ሆነው አቶ ተሾመን ከችግር የሚገላግል ለመምህራኖቻቸውም መልስ የሚሆን ቀን መጣ። እሱም አንድ በሁኔታው ግራ የተጋባ መምህር የእሳቸውን ሁኔታ ለማወቅ እንዲያስችለው በማለት ሁሉም ተማሪ የሕይወት ታሪኩን እየተነሳ ይናገር ብሎ አዘዘ።በትዕዛዙ መሰረትም ተማሪዎች ከወንበራቸው እየተነሱ ስለራሳቸው መናገር ጀመሩ አቶ ተሾመም ተራቸው ደረሰና ስለ ራሳቸው መናገር ጀመሩ።
“…..ዱርዬ ነው ብለው የጠረጠሩኝ አስተማሪዎች በሙሉ በተለይም ከእኔ ትምህርት አቀባበል እንዲሁም የክፍል ተሳትፎ አንጻር ግራ ገባቸው፤ እናም የሕይወት ታሪካችሁን ተናገሩ ሲባል የመጣሁበትን ያለሁበትን ሁኔታ ተናገርኩ፤ በብዙ ችግር ውስጥ ለመማር ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጬ በማላቀው አገር ያለምንም ረዳት እየኖርኩ መሆኔን ሲሰሙ በተለይም ልጃገረዶቹ አለቀሱ፤ “ በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
ከዛ በኋላ አቶ ተሾመ አብዛኛው ተማሪ ደብተርም ብዕርም እርሳስም ስላመጣላቸው እንደውም ከእነሱ በላይ ባለ ብዙ የትምህርት መሳሪያ ባለቤት ሆነው ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል ጀመሩ።የሕይወት ታሪካቸው በዛ መልኩ መሰማቱ ሌላም ትሩፋት ይዞላቸው መጣ። ተማሪዎች ከቤታቸው ምግብ ይዘው ሲመጡ ለእሳቸውን እንዲተርፍ አድርገው ማምጣት ጀመሩ፤ እንደውም ከምሳም አልፈው ለእራት ሁሉ ይተርፋቸው ጀመር።ለማደሪያ የሚሆናቸው ብርድ ልብስ እንዲሁም መቀየሪያ የሚሆኑ አልባሳትም አገኙ። አሁን አቶ ተሾመ ተረጋግተው ትምህርታቸውን መማር ቀጠሉ።
በዚህ ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ማታ ማታ ተማሪዎችን ማስጠናት ጀመሩ፤ በዚህ ስራቸው ደግሞ በወር አስር ብር አገኙ።ከደመወዝሙ በላይ ደግሞ ቀጣሪዎቻቸው ባህሪያቸውን እንዲሁም ጉብዝናቸውን ሲያዩ “በቃ እኛ ቤት መኖር ትችላለህ በማለታቸው የሚኖሩበትም ቤት በነጻ አገኙ። እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ በዚህ ሁኔታ ቀጠሉ። ታታሪው አቶ ተሾመም በአንድ ቤት ተወስኖ የነበረውን የማስጠናት ስራቸውን ወደሁለትና ሶስት ቤት በማሳደግ ገቢያቸውን ከፍ ማድረግ ቻሉ፤ ከዛ በኋላም ጥገኝነቱን ትተው ቤት ተከራይተው ትምህርታቸውን መማር ጀመሩ።
“ ….በጥረቴ ጥሩ እየሰራሁ ትምህርቴንም በአግባቡ እየተማርኩ ባለሁበት ወቅት የእድገት በህብረት ዘመቻ መጣ፤ ከአስረኛ ክፍል ወደ ሽሬ እንደስላሴ ዘመትኩ። ግዳጄን ጨርሼ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ግን ገቢዬም ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ስለነበር ዳግም ችግር ውስጥ ገባሁ። አሁንም ዳግመኛ የሚያስተምረኝ ሰው ማፈላላግ ጀመርኩ፤ አላህ ሲረዳኝም አንድ ደግ ሰው አግኝቼ ወጪዬን ችለው 11ኛ ና 12ተኛ ክፍልን እንድማር አገዙኝ”።
የ12ተኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ወስደውም ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመቀላቀል እድሉን አገኙ፤ በዚህም የአንደኛ ዓመት (ፍሬሽ ማን ኮርስ) እየወሰዱ ባሉበት ወቅት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የቴሌ ፕሪንተር ኦፕሬተር በመፈለጉ ማስታወቂያ አወጣ እሳቸው ሄደው በመመዝገብና በመወዳደር ስላለፉ ስራ ተቀጠሩ።
“……ዜና አገልግሎት እየሰራሁ ባለሁበት ጊዜ ከተለያዩ ሰዎች ጋር መተዋወቅ ጀመርኩኝ፤ ይህ መተዋወቄ ደግሞ የስራ አድማሴን እንዳሰፋ ሳያግዘኝ አልቀረም። ወዲያው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በጋዜጠኝነት የስራ መስክ ማስታወቂያ ማውጣቱን ሰማሁና ተመዘገብኩ፤ በወቅቱ ብዙ ተፈታኞች የነበሩ ቢሆንም እኔና ሶስት ሰዎች አለፈን መስሪያ ቤቱን ተቀላቀልን “ ይላሉ።
“…እኔ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መምሪያ ባልደረባ ሆኜ ስሠራ ድርጅቱ ፕሮዳክሽን ዋና ክፍል፣ ዜናና ሙዓለ ዜና ዋና ክፍልና ፕሮግራም ዋና ክፍል የተሰኙ 3 ዋና ክፍሎች ነበሩት። ይህ ልጅ የስነ ጽሁፍ ችሎታው ጥሩ ነው በሚል በፕሮግራም ዋና ክፍል ባልደረባ ሆኜ እንድሰራ መደቡኝ”።
ፕሮግራም ዋና ክፍል እንደተመደቡም ስራውንም የስራ ቦታውን እንዲሁም ባልደረቦቻቸውን እየተለማመዱ ከሄዱ በኋላ የህጻናት ፕሮግራም ክፍል ክፍት ቦታ የነበረው በመሆኑ የህጻናት ፕሮግራም እንዲያዘጋጁ ሆነ።በዚህም የልጆች ጊዜ ፕሮግራም አዘጋጅም አቅራቢም በመሆን ስራቸውን ጀመሩ።ይህንን እየሰሩም ከቆዩ በኋላ የፕሮግራም መሪ ቀጥሎም አስተባባሪ በመሆን ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ስራቸውን ከመስራታቸውም በላይ አስር ደቂቃ የነበረው የልጆች ፕሮግራም ሰዓቱም ከፍ እያለ ቀኑም እየተጨመረ መምጣቱን ያስታውሳሉ።
“…..ከ1970 እስከ 1976 ዓ.ም በነበረኝ የስራ ቆይታ የወጣቶች፣ ከየአቅጣጫውና የሴቶች ፕሮግራሞች አዘጋጅ በመሆን ሰርቻለሁ።በሌላ በኩልም በተቋሙ የፕሮግራም አስፈጻሚ፣ አስተዋዋቂ አዘጋጅም በመሆን አገልግያለሁ “ ይላሉ።
ትምህርትም ልምድም ሳይኖራቸው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው የተቀላቀሉት የጋዜጠኝነት ስራ ለአቶ ተሾመ ያን ያህል ከባድ አልነበረም ምክንያቱ ደግሞ አቶ ተሾመ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ጀምሮ የተለያዩ የአማርኛና እንግሊዘኛ መጻህፍትን ያነቡ ነበር።ይህ አንባቢነታቸው ደግሞ ሙያውን በቶሎ እንዲዋሃዱት ከዛም ሲያልፍ ደግሞ በውስጣቸው ያለውን ተሰጥኦ እንዲያወጡት እድል ጨመረላቸው።
“……ንባብ ለእኔ በጣም ቅርብ ነው። ስድስተኛ ክፍል እያለሁ ጀምሮ በዓመት እስከ መቶ መጻህፍት አነብ ነበር፤ አዲስ አበባ ስመጣ ደግሞ ከአማርኛ መጽሀፍት ወደ እንግሊዘኛ መጻህፍት በመሻገር ማንበብ ጀመርኩ፤ ወደ ወጣትነት እድሜ ክልል ስገባ ደግሞ ክላሲካል እንዲሁም ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን መጻህፍት ነበር የማነበው ፤ በመሆኑም መጽሀፍ ማንበቤ የጋዜጠኝነት ትምህርት ባይኖረኝም በስነ ጽሁፍ የተመረኩ ባልሆንም በዝንባሌዬ ብቻ ስራውን በአግባቡ እሰራው ነበር”።
በሌላ በኩል ደግሞ አንድን ስራ ሲጀምሩ ስለዛ ስራ አመጣጥ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዴት ባለው መልኩ ራሳቸውን ብቁ አድርገው መገኘት እንደሚችሉ አብዝተው ያነቡና ይመራመሩ ስለነበር ቴሌቭዥንም ምን ይፈልጋል የሚለውን ራሳቸውን በንባብ በማስተማር ብቁ ሆነው ለመገኘት መቻላቸውንም ያብራራሉ።
“…..በወቅቱ የጋዜጠኝነት ስራ በትምህርት ሳይሆን በተሰጥኦ የሚሰራ ነበር ማለት ይቻላል።ይህንን ያልኩበት ምክንያት ደግሞ አብዛኞቹ ትልልቅ ሰዎች ብሎም ጸሀፊዎች ያን ያህል በትምህርታቸው የገፉ አልነበሩም።እኔ ደግሞ ቢያንስ የዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ መሆኔ ከእነሱም ከፍ እንድል ያደርገኛል።ስለዚህ ለጋዜጠኝነት ስራው አላነስኩም ማለት ነው”።
ሆኖም የቴሌቭዥን ቆይታቸውን በማጠናቀቅ እንዲሁም የደመወዝ ልዩነት በመፈለግ ወደ ህጻናት አምባ የህዝብ ግንኙነት በመሆን ሄዱ።እዛም እየሰሩ የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ታስፈልጋለህ በማለት ወሰዳቸው።በ1980 ዓ.ም ደግሞ ህዝባዊ ቁጥጥር ኮሚቴ ወደሚባለው በመምጣትም የህዝብ ግንኙነት ረዳት ሃላፊ ሆኑ።
“……እዛ ሆኜ የህዝባዊ ቁጥጥር አምድ የሚባል የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ አምድ በመክፈት መጻፍ ጀመርኩኝ፤ እዛም ሆኜ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣም ጽሁፎችን እያበረከትኩ መተዋወቅ ጀመርን፤ ከየካቲት መጽሄት ዋና አዘጋጅ ከጋሽ ጸጋዬ ሀይሉ ጋርም ጥሩ የስራ ግንኙነት ኖረን፤ በ1983 ዓ.ም ህዝባዊ ቁጥጥር ብሔራዊ ኮሚቴ ተዘጋ፤ በዚህ ጊዜም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕሬስ ክፍል ሃላፊ ሆነህ እንድትሰራ ተብዬ ተሾምኩ” በማለት ወቅቱን ያስታውሳሉ።
ተወካዮች ምክር ቤትም ከ 1984 እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ የፕሬስ ክፍሉን እየመሩ የምክር ቤቱን ዜናም እየጻፉ ለአዲስ ዘመንና ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ይሰጡ ነበር ከፕሬስ ጋር ጥሩ ግንኙነት ፈጠሩ።ከዚህ በኋላም በ1987 ዓ.ም የፖለቲካውን ሁኔታ የሚችሉት ስላልመሰላቸው ወደ ፕሬስ ድርጅት ለመምጣት በወቅቱ የነበሩትን የስራ ሃላፊ አነጋግረው ፕሬስን ተቀላቀሉ።
“…..በወቅቱ በተወካዮች ምክር ቤት የነበረውን የፖለቲካ ሁኔታ የምችለው አልመስል ሲለኝ ቀደም ብዬም ጥሩ ግንኙነት ከነበረኝ የፕሬስ ድርጅት የስራ ሃላፊዎች ጋር በመነጋገር “መምጣት ትችላለህ እንደውም አዲስ መጽሄት ስለምናቋቁም ዋና አዘጋጅ ትሆናለህ አሉኝ” ፤ እኔ ዋና አዘጋጅ መሆን እንደማልፈልግና በሌላ መደብ ቢቀበሉኝ ግን እንደምሰራ ነግሬያቸው ሰንደቅ መጽሄት እንዲቋቋም ሆነ፤ እኔም ማኔጂንግ ኤዲተር ሆንኩ” ይላሉ።
ማኔጂንግ ኤዲተር ሆነው እየሰሩ ባሉበት ጊዜ ከዋና አዘጋጁ ጋር በሃሳብ መግባባት ባለመቻላቸው ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተዘዋውረው መስራት መጀመራቸውን ያስታውሳሉ።
“….ከጋሽ ጸጋዬ ጋር እየተግባባን ስንሄድ በሌሎች ተጽፈው የሚመጡትን ኤዲት እንዳደርግ ይሰጠኝ ነበር። አንዳንዶቹ በምጨምርላቸው አስተያየቶች ሲደሰቱ አንዳንዶቹ ይናደዱብኝ ነበር። አንዳንዱ የሚንቀኝ እንዴት እርሱ ሥራችንን ኤዲት ያደርግብኛል ማለቱንም አስታውሳለሁ። ለምሳሌ አንድ “ትልቅ ሰው” ብዙ መጻሕፍት የጻፈና የተረጎመ፣ እንዲሁም በጋዜጠኝነት ሙያ የሠራና የማከብረው ሰው፣ ኤዲት የተደረገውን ሥራ ካደነቀ በኋላ ጋሽ ጸጋዬ “ኤዲት ያደረገው ተሾመ ነው። አመስግነው” ሲለው ሰውነቱ ሲለዋወጥ አይቻለሁ። ሌላው ኢሠፓ ጽህፈት ቤት ትልቅ ቦታ የነበረው ዶክተርም እኔ እንዳስተካከልኩለት ሲያውቅ ዕብድ ሆኗል።
ትንሽ ሰው ሆኖ የትልቅ ሰው ሥራ ማየት ችግር ነው። የሚገርመው ግን ጋሽ መንግሥቱ ለማ ለመጽሔት የጻፏቸውን ጽሑፎች ከመታተማቸው በፊት አስነብበውኛል። አስተያዬቴንም ሰምተዋል። ብቻ የየካቲት መጽሔት ሠራተኛ ባልሆንም ከአንባቢዎች የሚመጡለትን በርካታ ጽሑፎች ወስጄ እንድመርጥለት፣ በጣም የሚማርኩኝ ጽሐፎችንም እንድዳስሳቸው ያደርገኝ ነበር። በዚህ ዓይነትም ተግባራዊ ትምህርት አስተማረኝ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
ከ1987 እስከ 1992 ዓ.ም በነበራቸው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የስራ ቆይታ በትልቁ ጋዜጣ ከ600 ገጽ በላይ ስራዎችን መስርታቸውን ይናገራሉ።በዚህ ውስጥም ከአንድ ሺ ያላነሱ ርዕሰ ጉዳዮችን መዳሰሳቸውንም እንደዛው።
አቶ ተሾመ ከፕሬስ ድርጅት ከወጡ በኋላም በተለያዩ ተቋማት ይስሩ እንጂ ከጋዜጣ ስራ ግን አልራቁም። በተለይም ከሪፖርተር ጋዜጣ ከ10 ዓመት በላይ የዘለቀ ግንኙነት ከ150 በላይ ትልልቅ አርቲክሎችን ጽፈዋል።
ስራ ከጋዜጠኝነት ውጭ
በጋዜጠኝነት ሙያቸው ብዙ አበርክቶን ቢያደርጉም ኑሮን ለማሻሻል ብሎም የስራ ዘርፍን ለመቀየር በማሰብ ስራ ማፈላለግ ጀመሩ። መጀመሪያ ያገኙትን ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የሚባለውን ተቋም ሆነ፤ እዛም ያጋጠማቸው ነገር ሲሰሩ ከቆዩት የጋዜጠኝነት ሙያ ፍጹም የተለየ ከመሆኑም በላይ የኢኮኖሚክስ እውቀትንም የሚጠይቅ ሆነባቸው፤ ነገር ግን ኢኮኖሚክሱንም አውቆ የተጣለባቸውን የመጽሄት ዝግጅት በአግባቡ ለመወጣት ሌት ተቀን ማንበብ ያዙ።
“….ፕራይቬታይዜሽን ከገባሁ በኋላ ኢኮኖሚክስን የሚመለከት መጽሔት ነበር የማዘጋጀው፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የኢኮኖሚክስ እውቀት ጠየቀኝ፤ ምንም የማውቀው ነገር ባይኖርም ሌት ተቀን አንብቤ በተረዳሁት ሁለት ሶስት መጽሔቶችን አዘጋጀሁ፤ ነገር ግን የምገፋበት አይነት አልመስልህ ሲለኝ ትቼ ወጣሁ።“
ይህንንም ስራ ትትው ከወጡ በኋላ ስራ ሲያፈላልጉ የኢትዮጵያ ጤናና ስነ ምግብ ኢንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በሚል ስራ አወጣ ተወዳድረው ገቡ።ነገር ግን አሁንም የገጠማቸው ነገር ሳይንስ ሆነ የሚያወሩት ሁሉ ከሳይንቲስቶች ጋር ነው።
“…..እኔ ያለኝ የመጀመሪያ ዲግሪ ነው፤ በመጀመሪያ ዲግሪ ደግሞ ከሳይንቲስቶች ጋር መነጋገርና መግባባት ትንሽ ከበድ ይላል፤ ነገር ግን አሁንም በማንበብ ራሴን ለመብቃት ጥረት አደረኩ፤ የመጀመሪያ ስራዬንም ለመጽሔት ዝግጅቱ ሰጠሁ፤ ከዛ በኋላ የተለያዩ ነገሮችን በማንበብ ራሴን እያበቃሁ ሰራሁ” ይላሉ።
በዚህ መልኩ ከሳይንቲስቶቹ ጋር ተግባብተው መስራት ቢችሉም ለውጥ ፈላጊ ናቸውና ይህንንም ስራ ብዙ ሊገፉበት አልፈለጉም እናም ወደ ኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት (ሺፒንግ ላይንስ ) በመሄድ አዲስ ስራ አመለከቱ። በወቅቱ መስሪያ ቤቱን ብዙ ሰዎች ይፈልጉት ስለነበር በእሳቸው የትምህርት ደረጃ እኩያም የሚበልጧቸውም ብዙ የሰሩም ሰዎች ለውድደር ቀርበው እሳቸው ግን ፈተናውን በማለፋቸው ወደ አዲሱ መስሪያ ቤታቸው ተቀላቀሉ።
“…..በአዲሱ ተቋም ላይም መጽሔት አቋቋምኩ ብዙ ጽሁፎችን መጻፍ ጀመርኩ፤ በመርከብም ከኢትዮጵያ ውጭ ሁሉ መሄድ ጀመርኩ፤ በጠቅላላው በጣም ጥሩ ጊዜን አሳለፍኩ።ነገር ግን በስራዬ ያን ያህል እርካታን እያገኘሁ መምጣት ስላልቻልኩ ጡረታዬን አስከብሬ ወደጽሁፍ ስራዬ አዘነበልኩ” ይላሉ።
መጽሐፍትን የመጻፍ ጉዞ
አቶ ተሾመ ምንም እንኳን ጡረታ የወጡት በ2000 ዓ.ም ቢሆንም መጽሀፍትን መጻፍ የጀመሩት ግን ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ነው።የመጀመሪያው የመጽሃፍ ስራቸውም የተረት አባት የሚል የልጆች መጽሀፍ ሲሆን ቀጥሎም ጥንቸልና ቀጭኔ፣ ደረቶ፣ የኤዞብ ተረቶችን ጽፈው ለህትመት አብቅተዋል።
“……በ15 የህጻናት መጽሀፍት ውስጥ ቢያንስ መቶ ያህል ተረቶች ተካተዋል፤ የህጻናት መጽሀፍትን እየጻፍኩ ግን ጎን ለጎን በተለይም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ስሰራ አዘጋጅ የነበረውን የህልም ፍቺ በማዳበር መጽሀፍ ላደርገው በማለት መጽሀፍ አድርጌ አሳተምኩት” ይላሉ ስለ ስራቸው ሲያወሩ።
በሌላ በኩልም “በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲሁም በእፎይታ መጽሄት ላይ እስላማዊ ጽሁፎችን እሰራ ስለነበር እግረ መንገዴን የኢማም አህመድ ኢብራሂምን ታሪክ ማጥናት ጀመርኩ፤ ይህንን ታሪክ ለመጻፍ በመላው ኢትዮጵያ እንዲሁም በጅቡቲ ሶማሊያ ምስራቅ ሱዳንን ኤርትራ መሄድ ነበረብኝ። እነዚህ ሁሉ አገሮች ሄጄ ብዙ ውጣውረዶችን አሳልፌ መጽሃፉን ጻፍኩትና ታተመ” ይላሉ።
ይህ ስራቸው ከብዙ ሰዎች ጋር ያስተዋወቃቸውና አድናቆትንም ያስገኘላቸው በመሆኑ ለቀጣዩ ስራቸው ተነሳሱ በመቀጠልም በአዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ የጻፏቸውን ታላላቅ ሰዎችና ጥቅሶቻቸው የሚል መጽሃፍ አሳተሙ።
“…..ይህንን እያደረኩ ድምጻችን ይሰማ የሚል የሙስሊም ሃይል ተነስቶ በመንግስትና በእምነቱ ተከታዮች መካከል ክፍተት ተፈጠረ ፤ እኔ ይህንን ነገር ያረግባል ብዬ ያሰብኩትን “መቻቻል” የሚል መጽሃፍ ጻፍኩ፤” በማለት በመንግስትና በእምነቱ ተከታዮች እንዲሁም በክርስትናና በእስልምና ሃይማኖት አማኞች መካከል የኖረውን ወዳጅነት የሚያሳይ መጽሀፍ ስለመጻፋቸው አቶ ተሾመ ይናገራሉ።
ይህንን ከጻፉ በኋላም ያመሩት የሲዳማ ንግስት ስለሆነችው “ንግስት ፉራ” ታሪክ ወደመጻፍ ነበር።ይህንን ትልቅ ታሪክ የያዘ መጽሀፍን ለመጻፍም ብዙ ፎክሎራዊ መጽሀፍትን ማገላበጣቸው ይናገራሉ።ይህንን ተመርኩዘውም የንግስት ፉራን ታሪክ የሚያትት በፎክሎር ላይ የተመሰረተ ልቦለድ ጻፉ።ነገር ግን ሲዳማ ክልል ሄደው በጋራ እናሳትም ቢሉ ፍቃደኛ ስላልሆኑላቸው አሜሪካን አገር የሚገኙ አንድ ወዳጃቸው ተባብረዋቸው መጽሀፉ ለህትመት ስለመብቃቱም ይናገራሉ።
አቶ ተሾመ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ግንኙነት በጣም ያሳስባቸው ስለነበረም “የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች አንድነት” በሚል መጽሀፍ አዘጋጁ፤ መጽሃፉን በድብቅ ቢያሳትሙም ከታተመ በኋላ ግን በወቅቱ ለነበሩት የኢህአዴግ ባለስልጣናት መስጠታቸውን ያስታውሳሉ። ነገር ግን በወቅቱ የትኛውም ባለስልጣን የሰጠው ጥሩ መጥፎም አስተያየት ባለመኖሩ መጽሃፉ ወደህዝቡ እንዲሰራጭ ስለመደረጉም ይናገራሉ።
“…..ከእነዚህ ስራዎች በኋላ በቀጥታ ያመራሁት ወደእስልምና መጻህፍት ነው፤ በዚህም ሀረር በመሄድ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ የሀረር አሚሮች፣ ኢማሞችና ሱልጣኖች የሚል ታሪክ ጻፍኩኝ፤ ቀጥሎም አዳል ሱልጣኔት እንዲታወቅም ሌላው የኢትዮጵያ ገጽታ የሚል መጽሀፍ አዘጋጀሁ፤” ይላሉ።
በጋዜጦች ላይ የጻፏቸውን የእስልምና ጽሁፎችንም በማሰባሰብ “እስላማዊ ስነ ጽሁፍ” የሚል መጽሀፍም ማሳተማቸውን ይናገራሉ።ሌላው “እስላማዊ ስልጣኔ በኢትዮጵያ” የሚል ነው ፤ የአፋር ታሪክ፣ ኩነባ (የነብዩ ሙሃመድ የሕይወት ታሪክ) የያዘ፣ የሙስሊም አዋቂዎች የሕይወት ታሪክ የያዘ መጽሀፍ ያዘጋጁ ሲሆን፤ በጠቅላላው አስር የሚሆኑ እስላማዊ መጽሀፍትን፤ አራት ያህል ጠቅላላ እውቀት ያዘሉ እንዲሁም 15 የህጻናት መጻህፍትን ጽፈው አሳትመዋል።በቀጣይም በተለይም በአዲስ ዘመን፣ ሪፖርተርና ሌሎች ጋዜጦች ላይ የጻፏቸውን ስራዎች አሰባስበው ወደ መጽሀፍ ለመቀየር እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ጎን ለጎንም የስራዎቻቸውን ታሪክ የያዘ መጽሀፍ አዘጋጅተው ለማሳተም እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑም ይናገራሉ።
የአራት ልጆች አባትና የሰባት ልጆች አያት የሆኑት አቶ ተሾመ ሁሉም ልጆቻቸው በጥሩ ሁኔታ ተምረው በመልካም ስራ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ይናገራሉ።
አቶ ተሾመ በስራ ምክንያት ህንድ፣ ቱርክ፣ ቤሎሪሺያ፣ ራሺያ፣ ቡልጋሪያ፣ ጣሊያን፣ አሜሪካ፣ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ ሄደዋል ከኢትዮጵያም ያላየሁት አገር የለም።
መልዕክት
እኔ የማስበው በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል የነበረው ስልጣኔ በአንድ ተቀምሮ ለኢትዮጵያ እድገት ለብልጽግናዋ ይውል ዘንድ ነው።ሙስሊም ሆኜ ክርስቲያን ልጠላ አልችልም ምክንያቱም ተወልጄ ያደኩት ክርስቲያኖች መካከል ነው።ላሊበላ የኔ ነው፤ ዋግ ያሉት ትላልቅ አብያተ ክርስቲያናት ያደኩባቸው ናቸው፤ አክሱም ጎንደር በጠቅላላው የኢትዮጵያ ስልጣኔ የእኔም ነው።የሙስሊም ስልጣኔ የኢትዮጵያ ስልጣኔ አይደለም ለሚሉ ደግሞ የጻፍኳቸውን መጽሃፍት መለስ ብለው እንዲመለከቱ እጋብዛለሁ።በአጠቃላይ የነበረን የእምነት አንድነትና መከባበር ኢትዮጵያን ወደፊት ያመጣት ይሆናል እንጂ የሚጎዳን አይሆንም።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረመ 29/2015