ጆሀንስ በርግ ከተማ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ ውብ ከተሞች መካከል አንዷ ናት። ይህች ከተማ ወርቃማዋ ከተማ ተብላ ትታወቃለች። ከባህር ጠለል በላይ በ1 ሺህ 753 ከፍታ ላይ ትገኛለች። ይሄ መገኛዋ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኝ ሰፊ ዝርግ የሆነ ቦታ ነው።ከተማዋ የምትገኝበት ይሄው ሰፊ ዝርግ ቦታ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ባለቤት እንድትሆን ያስቻላት መሆኑ ይነገራል።
የከተማዋ ቀደምት ታሪክ እንደሚያመለክተው በከተማዋ ከ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሳን ተብለው የሚጠሩ ነገዶች ይኖሩ ነበር።በዚሁ ምዕተ ዓመትም ከመካከለኛው አፍሪካ የሚፈልሱ ዙሉ ተብሎ የሚጠራውን ቋንቋ የሚናገሩ ሶቶ ሳን የሚባሉ ጎሳዎች በብዛት እየፈለሱ መቀመጫቸው ሲያደርጓት ቆይተዋል። እስከ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም እነኚህ ማህበረሰቦች በአብዛኛው የከተማው ክፍል ላይ ለመስፈር መቻላቸው ይነገራል።
ብዙ ሰዎች ወደ ጆሃንስበርግ በፍጥነት መፍለስ የጀመሩት ግን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1886 ጀምሮ እንደሆነም ከድረ ገጽ የተገኙ ጽሑፎች ይጠቁማሉ። እንደ ሀገርም የኢትዮጵያ ከተሞች ቀንን ለመዘከር የወጡ የከተሞች ተሞክሮ መረጃዎችም ይሄንኑ ይጠቅሳሉ። የከተማዋ ስም ወርቃማዋ ለመሰኘት የበቃው ጆርጅ ሀሪሰን በተባለ አሳሽ አማካኝነት መሆኑም ይገለፃል።
ነገሩ እንዲህ ነው። ይሄ በዜግነቱ አውስትራሊያዊ የሆነና ጆርጅ ሀሪሰን የተባለ አሳሽ ወደ ከተማዋ ይዘልቃል።ከሙያው አንፃርም ተደጋጋሚ ፍተሻዎችን ያደርጋል። በሂደትም በአካባቢው ላይ ከፍተኛ የሆነ የወርቅ ክምችት መኖሩን ይረዳል። ይሄንንም ይፋ ያደርጋል። ወደዚሁም ጆሃንስበርግ ‹‹ወርቃማዋ ከተማ›› የሚል ስያሜ ይሰጣትና ልትጠራበት ትበቃለች። አሁን ድረስም በዚሁ መጠሪያዋ ጭምር ትታወቃለች።
በተለያየ ጊዜ ከተለያየ ቦታ የተገኙ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ‹‹ወርቃማዋ››የሚለው መጠሪያዋ ወርቅ በማውጣት የተሰማሩ የበርካታ ድርጅቶች ቀልብ ለመሳብ አስችሏታል።
ጆርጅ ሀሪሰን መጠሪያዋን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በአጭር ግዜ ውስጥ በርካታ ወርቅ አምራች ድርጅቶች ወደ ጆሃንስበርግ መጉረፍ ጀመሩ። በስፋትም ወርቅ በማውጣት ሥራቸው ላይ ተሰማሩ። በተፈጠረው የስራ ዕድልም በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ የሀገሬው ተወላጆች ወደ ጆሃንስበርግ በመሄድ በነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው መስራትንም ተያያዙት።
በወቅቱ አካባቢውን ያስተዳድር የነበረው ቦር ሪፐብሊክ የተሰኘው ነበር። ወርቅ ፍለጋ በመጡና የእንግሊዝ ሀገር ዝርያ ያላቸው ነጮች አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ባሳዩት ፍላጎት ደስተኛ አልነበረም።በእሱ ወገንና እንግሊዞች ባሳዩት ፍላጎት ምክንያትም በሁለቱ ፅንፈኞች መካከል ጦርነቱ ተነሳ።
ለሦስት ዓመታት ቆየ። በኋላም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1901 በእንግሊዞች አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ይሄም ወርቃማዋ ከተማ ጆሃንስበርግ ሙሉ ለሙሉ በነጮች እጅ ወደቀች።
በአካባቢው የወርቅ ማዕድን መኖሩ ከታወቀ ከአስር ዓመት በኋላ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በጆሃንስበርግ የሚኖሩ ነዋሪዎች ቁጥር 100 ሺህ ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ይጠቅሳሉ። በተለይም በዚያን ግዜ እንግሊዞች በኃይል ጥቁሮችን ከመካከለኛው ከተማ በማስወጣት ነጮች በሚኖሩበት ቦታ እንዳይቀላቀሉ ማድረግ ጀምረው ነበር ።
ይህም የአፓርታይድ ስርዓት ተብሎ ይጠራ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ ። ከመሀል ከተማው እንዲወጡ ይደረጉ የነበሩ የሀገሬው ተወላጆችም ከከተማው ወጣ ያለ ቦታ ላይ እየሰፈሩ መጡ።ይህ ቦታም ስዌቶ ተብሎ ይጠራ ነበር። ቆይቶም ደቡብ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነፃ በወጣች ሰሞን ስዌቶ ከጆሃንስበርግ ጋር ተቀላቅላለች።
በኋላም የደቡብ አፍሪካ ተወላጆች ይህን ስርዓት በመቃወም ለረጅም ዓመታት አሰልቺ ትግል በማድረግና ብዙ መስዋእቶችን በመክፈል ከ1901 እስከ 1994 ለዘጠኝ አስርት ዓመታት የዘለቀውን ግፈኛ የቅኝ አገዛዝ ስርዓትን በመገርሰስ ሀገራቸውን ከቅኝ ግዛት ነፃ ለማውጣት ቻሉ።
በ1994 የመጀመሪያውን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያካሄዱ ሲሆን በሀገሪቱ ለረጅም ዓመታት ሲታገል የቆየውና በማንዴላ የሚመራው ኤ ኤን ሲ በመባል የሚታወቀው ፓርቲ የብዙሃኑን ድምፅ በማግኘት ስልጣን ለመያዝም በቁ። ፓርቲውም በ11 የስልጣን ተዋረዶች በማዋቀር ከተማዋን ሲያስተዳድር ቆይቷል።ይህም ሰባቱ የስልጣን ተዋረዶች በነጮች ባለቤትነት የተያዘ ሲሆን የቀሩት አራት ደግሞ በጥቁሮች ይመራል። በኋላም በ2006 እአአ 11 የነበረው የስልጣን ተዋረድ ወደ ሰባት ዝቅ እንዲል አደረጉ።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የሚኖሩ ዜጎችን ስንመለከት በከተማዋ ነባር የሆኑ ጥቁር አፍሪካውያን 73 በመቶ፣ ከእንግሊዝ ሀገር የመጡ ነጮች 16 በመቶ፣ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የመጡ ዜጎች ሰባት በመቶ እንዲሁም ከእስያ የፈለሱ ህንዳውያን አራት በመቶውን የህዝብ ቁጥር ይይዛሉ። በከተማው የስራ ቋንቋ የሆነውን እንግሊዝኛን ጨምሮ አራት ቋንቋዎች ይነገራል። እነዚህም ዙሉ፣ አፍሪካንስና ዞሳ በመባል ይታወቃሉ።
ጆሀንስበርግ በአፍሪካ ከሚገኙ ከተሞች በኢኮኖሚ የሚስተካከላት ከተማ የለም። በቆዳ ስፋቷም ቢሆን በአፍሪካ ከግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዓለም አቀፍ ደረጃም ግዙፍ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ከተሞች ደረጃም የ48ኛ ደረጃን ለማግኘት የቻለች ከተማ ሆናለች።
በዚህም ከተማዋ ተግባራዊ ያደረገችው የከተማ ልማት ስትራቴጂ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር አስችሏታል። ይህም ከተማዋን የኢንደስትሪ ከተማ ከማድረጉም ባሻገር በጥቂት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስችሏል። በከተማዋ በተፈጠረው ሰፊ የስራ እድልም በመላው ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደዚች ከተማ እንዲተሙ ምክንያት ሆኗል።ከተማዋ በፍጥነት እየሰፋች እንድትሄድም አግዟል።
የህዝብ ቁጥር በፍጥነት እያደገ መጥቷል። በአሁኑ ወቅትም በዓለማችን ከሚገኙ ከተሞች በቆዳ ስፋቷ የ42ኛ ደረጃን ለመያዝ ችላለች።በህዝብ ቁጥር ከአሥር ዓመት በፊት የወጣ አንድ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በ5ነጥብ 8 ሚሊዮን የሕዝብ ቁጥሯ ደግሞ የ45ኛ ደረጃን ለመያዝ ችላለች።
የከተማ ልማት ፖሊሲያቸው የፈጠረው ምቹ ሁኔታም ከተማዋን የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ፣ የንግድና የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ትልቁን ሚና ተጫውቷል። ይህ ሁኔታም የከተማውን ነዋሪ የስራ ባህል በእጅጉ ቀይሮታል።በተለይም በሥራ የሚያምን ማህበረሰብ በመፍጠር ብዙዎችን ከድህነት አውጥቷል።
የተሻለ ኑሮ እንዲመሰርቱም አድርጓል። ይህ አሰራርም በከተማው ነዋሪዎች ላይ ልዩ የሀገር ወዳድነት ስሜትም ፈጥሯል። በተለይ ቀደምት ቅርሶችን በኃላፊነት ጠብቆ ከማቆየትና የከተማዋን ንፅህና ከመጠበቅ አንፃር ሚናው ቀላል አልነበረም።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013