ማህሌት አብዱል
የተወለዱት አዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ አካባቢ ሲሆን ያደጉት ደግሞ በመሃል ፒያሳ ነው። ትምህርታቸውን አማሃ ደስታ ትምህርት ቤት እስከ ሰባተኛ ክፍል ተከታተሉ። ይሁንና ሰባተኛ ክፍል ገብተው እየተማሩ ባሉባት አንድ ቀን ከልጅነት ጀምሮ ይሹትና ይመኙት የነበረውን ህልም እውን የሚያደርግላቸውን ማስታወቂያ አነበቡና ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ዳዱ። በዚህም አልተወሰኑም፤ በአለባበስም ሆነ በስነምግባር የሚመሩለትን የውትድርና ሙያ ለመቀላቀል የቀዩ ጦር ጥንስስ በሚል ስር ተመዘገቡ።
በ1974ዓ.ም የአራት ተራራ ክፍለጦሮች ሲመለመሉ 21ኛ ክፍለ ጦር ባልደረባ ሆነው ወደ ሁርሶ ማሰልጠኛ ገቡ። ስልጠናቸውን እንዳጠናቀቁም ኤርትራ ተመደቡ። የደርግ መንግስት እስከወደቀበት 1983ዓ.ም ድረስም በሰሜናዊቷ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ የጦር ግንባሮች ተዘዋውረው ለአገራቸው ዳር ድንበር መከበር ታገሉ። በተደጋጋሚ ከመቁስል ጀምሮ ህይወታቸውን እስከማጣት የሚያደርስ መከራም አሳለፉ።
የደርግ ሥርዓት መገርሰሱን ተከትሎ ወደ ትውልድ መንደራቸው ቢመለሱም ያጋጠማቸው ልክ እንደአባዛኞቹ የደርግ ሰራዊት አባላት ያለምንም አጥጋቢ ምክንያት ከስራ መሰናበት ነው።
ከዚህም አልፎ የቀድሞው መንግስት ሰላይ ነበርክ በሚል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለእስር ተዳረጉ። ከስድስት ወር የወህኒ ቤት ቆይታ በኋላ በነጻ ቢፈቱም የደርግ ሰራዊት በመሆናቸው ብቻ ሥራ የሚቀጥራቸው አጡ። በዚህም ምክንያት የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ሲሉ የቀን ሥራ ለመስራት ተገደዱ።
በኋላም በማንኛውም ተቋም ለመቀጠር የሚያስችላቸውን የተሃድሶ ስልጠና ያለውዴታቸው ወሰዱ። እናም በአንድ የግል ባንክ ውስጥ በጥበቃነት ተቀጠሩ። የትምህርት ደረጃቸውን ካቋረጡበት ቀጥለው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን ወሰዱ። ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ባያገኙም በነበራቸው ታታሪነትና ትጋት የሚሰሩበት ተቋም ወደ ገንዘብ ያዥነት አሳደጋቸው።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ከሌሎች የትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን እንደቀልድ የመሰረቱት ማህበር ዛሬ ላይ በመላው የአገሪቱ ክፍል 274 ቅርንጫፎች ያሉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር ለመሆን ቻለ። በአሁኑ ወቅት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ የሆኑት እንግዳችን አስርአለቃ ተሾመ ምትኩ እንደእሳቸው በኢኮኖሚ ለተጎዱ የቀድሞ ሰራዊት ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ። እንግዳችን በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስዘመን ጋር ውይይት አድርገዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የውትድርና ዘመንዎ ምን ይመስል እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አስርአለቃ ተሾመ፡– ለመጀመሪያ ጊዜ በአውደ ውጊያ የተሳተፍኩት በ1974ዓ.ም ኤርትራ ከርከበት በሚባል ቦታ ላይ ነው። በወቅቱ ከሻቢያና ከወያኔ ጋር ይደረግ የነበረው ጦርነት ከባድና ብዙ ውጣ ወረድ ማለፍን የሚጠይቅ ነው። አብዛኞቻችን ወጣቶች የነበርን ቢሆንም በማሰልጠኛ ተቋሙ ባገኘነው ሥልጠና በስለን በመውጣታችን የነበረውን ችግር ለመቋቋም ሞከርን።
ጦርነቱ የውስጥም ሆነ የውጭ ተፅእኖም ስለነበረው ከነበረው አፍላነት ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ ጫና አሳድሮብን ነበር። በተለይም የውሃ ጥምና ረሃቡ ከፍተኛ የሆነ ፅናትን ይጠይቃል።
በሌላ በኩል በዚያ ግንባር ላይ ይመሩ የነበሩት ኮሎሬል እሸቱ ማሞ ላጋጠማቸው ውድቀት አብረዋቸው በነበሩ አመራሮች አማካኝነት በማይገባ መንገድ እንዲገደሉ መደረጋቸው ከፍተኛ የሞራል ስብራት አደረሰብን። በተለይም ናቅፋ በሚባል ግንባር ላይ መላው ሰራዊት እያየ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ መደረጋቸው ዛሬም ደረስ ከማልረሳቸው የጦርነቱ ጠባሶች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
አንገባ በሚባል አውደ ውጊያ ላይ ደግሞ የጦር አውዱ ከፍተኛ ቦታ ስለነበር አንድ ሻምበል ጦር ሙሉ ቦታው አስቸጋሪ በመሆኑ ቦንብ ብቻ ይዞ እንዲገባ ይደረጋል። በተቃራኒው ደግሞ የጠላት ሃይል ከፍተኛ ምሽግ ስለነበረው 118 ሰው ሆነን ገብተን በህይወት መትረፍ የቻልነው ከ20 አንበልጥም ነበር።
ከዚያ ውስጥም እኔን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉት የመቁስል አደጋ አጋጠመን። ክፍለ ጦሩም ከዚያ የተነሳ 21ኛ ቦንበኛ ተራራ ክፍለጦር የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት አርማችንም ቦምብ አርማ እንዲኖረው ተደረገ።
ሰራዊቱ በተበተነበት ወቅት እንኳን እኔ የነበርኩት አስመራ ደቀመሃሪ በምትባል ቦታ ጠረጴዛ በሚባል ተራራ ላይ ከጓዶች ጋር በመሆን ከፍተኛ ውጊያ ነበር ሥናደርግ የቆነው። በድንገት ነው ከዚያ ተራራ ላይ ወደ አስመራ አየር ማረፊያ እንድንመጣ ትእዛዝ የተሰጠው። በዚያም መሰረት በአውፕላን ተጭነን ወደ አሰብ በረርን። በወቅቱ አሰብ ሊያዝ ነው የሚል መረጃ ነበር የተላለፈልን።
ጠላት ከተማዋን እንዳይቆጣጠር በሚል ግዳጅ ተሰጥቶን ነው ወደዚያ እንድንሄድ የተደረግነው። አየር ማረፊያው ከአሰብ ከተማ ወደ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ነው እንድናርፍ የተደረግነው።
በመቀጠልም 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቤሉል በምትባል ስፍራ ተጓዝን። ያ አካባቢ ሳር የሚባል ነገር የማይበቅልበት፣ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ ሙቀትና በርሃማ የሆነ ቦታ ነው። በተለምዶ 90 እየተባለ የሚጠራውን ቦታ ጠላት ይዞ ስለነበር ለማስለቀቅ ከፍተኛ ውጊያ እያደረግን ነበር የነበርነው።
እየተዋጋን ሳለ ነው ፕሬዚዳንት መንግስቱ ሃይለማርያም ወደ ውጭ መሸሻቸውን የተሰማው። በእሳቸው ምትክም ሌተናል ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ተተክተው እንደሚሰሩም ተገነዘብን። ወዲያውንም አሰብ በጠላት ሥር ወደቀች። በመሆኑም ወፍ እንኳን መብረር በማይችልበት ጭልጥ ባለ በረሃ ውስጥ መግቢያውንም ሆነ መውጪያውን ስለማናውቀው ግራ ተገባን።
ከላይም ሆነ ከታች እንደ እቶን እሳት የሚለበልበውን በረሃ አቋርጠን ጅቡቲ ደረስን። ዱፍቲ ስንደርስ ወያኔ መንገዱን እንደዘጋው ሰማን። በመሆኑም የነበረን አማራጭ ወደኋላ በመሆኑ ወደ ጅቡቲ ተመለስን። ሆኖም ጅቡቲ ድንበር ሥንደርስ ጅቡቲ መንግስት አላስገባም አለን።
ከአሰብ የሚወጣው በርካታ ሲቪል ህዝብ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወደቅን። ያለውሃና ያለምግብ ከፍተኛ መከራ አሳለፍን። ከጅቡቲ በኋላ ደወሌ ድረስ በመኪና ገባን። በመቀጠልም ከድሬዳዋ አዲስ አበባ ግንቦት 27 ቀን ገባሁኝ። በወቅቱ ደግሞ ጎተራ ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ለአገሪቱ አንድነት ደሙን ያፈሰሰው ይህ ሠራዊቱ በዚያ መለኩ መበተኑ ተገቢ ነበር ይላሉ?
አስርአለቃ ተሾመ፡– እንደሃገር የሀገር ሠራዊት የሃገር ነው እንጂ የግለሰብ አይደለም። ወይም የአንድ ፓርቲ አይደለም። ሠራዊት ተብሎ ከመጀመሪያውኑም ሲደራጅ ሀገርን ከወራሪዎች ለመታደግ እንጂ ግለሰቦችን ወይም ፓርቲን ለመጠበቅ አይደለም። ይሁንና በወቅቱ አገሪቱን የተቆጣጠረው ቡድን አገሩን ለመጠበቅ ደሙን ያፈሰሰውንና አጥንቱን የከሰከሰውን ያንን ሰራዊት ልክ እንደጠላቱ አሽቀንጥሮ ነው የጣለው።
አስቀድሞም ቢሆን ቡድኑ የእናት ጡት ነካሽ መሆኑንና አገር የመበተን አላማ እንደነበረው ይታወቃል። አስቀድሞም ቢሆን ፕሬዚዳንት መንግስቱም ይህ ቡድን ለዘረፋና ለውንብድና የተደራጀ ሃይል መሆኑን ይገልፁ ነበር።
እኛም የምናውቀው ይህንኑ ነበር። አገሪቱን ከተቆጣጠሩ በኋላ ሰራዊቱን ባልባሌ መንገድ ሜዳ ላይ እንዲወድቅና እንዲለምን፤ ጭራሽ እንዳውም የትኛውም መስሪያ ቤት እንዳይቀጥር ሰርኩላር ደብዳቤ እስከመበተን የተደረሰበት ሁኔታ ነበር።
በ1983ዓ.ም አዲስ አበባ ስንገባ እጅግ በጣም የሚያሳዝን መከራ ነው ያሳለፍነው። ከዚያ አልፎም በየመንደሩ ተለቅመን እንደገና እስር ቤት ገብተናል። እኔ ማዕከላዊ አስር ቤት ውስጥ ከስድስት ወር ላላነሰ ጊዜ ታስሬ ያለምንም ምክንያት ተፈትቻለሁኝ። ለታሰርኩበት ምክንያት ደህንነት ነበርክ ቢሉኝም እኔ ግን ደህንነት አልነበርኩም። እኔ በሰራዊቱ ውስጥ ከባድ መሳሪያ ምድብተኛ ነበርኩኝ። ፈፅሞ የፖለቲካም ሆነ የደህንነት ስራ ውስጥ ተሳትፌ አላውቅም። አብዛኞቻችን ከእስር ባሻገር የኑሮ እንግልትም ደርሶብል።
በተጨማሪም ማህበረሰቡን አወናብደው ሰራዊቱ ጨፍጫፊና ገራፊ እንደነበር ነገርው አሳምነውት ነበር። እናም በጣም አስቀያሚና የሰው ልጅ ሊጠራበት የማይችል አይነት አፀያፊ በሆነ መንገድ ማንነታችን እንዲጎድፍ አድርገውታል። አሁን ያለው ትውልድ ያንን ግንዛቤ እንዲኖረው አድርገው እንዲያድግ አድርገውታል። ደስ የሚለው ነገር ያ ሁሉ ያሳለፍነው ነገር መንግስቱ ሃይለማርያም ‹‹የእኔን ሞት አታዩም፤እኔ ግን የእናንተን ሞት ቆሜ አያለሁ›› እንዳሉት እንደዚሁ ትንቢት ሆኖ እነሱ ሞተውና መቃብራቸው ውስጥ ሆነው እየናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ከእስራት ባሻገር በግሎዎ ያደረሰቦት ጉዳት በጥቂቱ ቢጠቅሱልን?
አስርአለቃ ተሾመ፡– እንደነገርኩሽ እዚህ እንደገባን ያጋጠመኝ እስር ነው። ከእስር ከወጣሁ በኋላ ግን ምንም አይነት የስራ እድል አልነበረኝም። በጊዜው ማግኘት የቻልኩት የቀን ሥራ ብቻ ነበር። ስለሆነም ራቅ ባሉ የከተማው አካባቢዎች በመሄድ የጉልበት ስራ እሰራ ነበር። ያኔ ደግሞ ይከፈል የነበረው ብር ለመጥቀስ እንኳን ይከብደኛል።
ግን ደግሞ ምንም አማራጭ ስለሌለኝ ያችኑ ገንዘብ ከቤተሰቦቻችን ጋር እንቋደስ ነበር። እንዳልኩሽ በጊዜው ማንም እንዳይቀጥረን ተደርገን ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ተሃድሶ መግባት አለባችሁ ተብለን ወደ ተሃድሶ ገባን። እንደአጋጣሚ ሆኖ እስር ቤት ስለቆየሁኝ እኔ በቀጥታ ታጠቅ ነው የገባሁት። እዛም ስልጠና ተሰጥቶኝ የተሃድሶ ወረቀት ነው ይዤ የወጣሁት።
አዲስ ዘመን፡- የተሃድሶ ወረቀት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አስርአለቃ ተሾመ፡– ተሃድሶ ማለት ባታምኚበትም አምነሽ በግድ የአመለካከት ለውጥ እንድታመጪ ታስቦ የሚሰጥሽ ሥልጠና ነው። ‹‹እኛ ብቻ ልክ ነን፤ በእኛ እመኑ›› የሚል አይነት ተፅዕኖ ለመፍጠር ነው ጥረት የተደረገው። ሕዝብ በድላችኋል ተብለናል። እኛ ግን ህዝብ ለመበደል ሳይሆን አገር እንዳይፈርስና የባህር በር እንዳናጣ ነው የታጋልነው። በመሰረቱ ተራ ወታደሮች እንጂ ህዝብ ለመበደል የሚያስችል እድሉም አልነበረንም።
እነሱ የሚሉት ነገር ውስጣችን ባይገባም ስራ ለማግኘት ስንል ብቻ ስልጠናውን ወሰድን። ምክንያቱም ሥልጠናውን ካልወሰድን በየትኛውም መንግስታዊም ሆነ የግል ድርጅት ተቀጥረን መስራት እንደማንችል ነበር የተነገረን። ተገደን ያንን ወረቀት ይዘን ከወጣን በኋላ ነው እንግዲህ ጥበቃም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን ማግኘት የቻልነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ የሰራዊት አባል ባለፉት 27 ዓመታት አገሪቱ ትመራበት የነበረውን የፖለቲካ ሥርዓት በምን መልኩ ነው የሚረዱት?
አስርአለቃ ተሾመ፡- አስቀድሜ እንዳልኩሽ 27 ዓመት ሙሉ እነዚህ ሰዎች ይዘውት የመጡት የራሳቸውን አላማና እቅድ ነበር። ይሄ እቅድና አላማቸውም ይህችን አገር ማጥፋት መዝረፍ ነው። ለዚህም አላማቸው መሳካት እንደመሳሪያ የተጠቀሙት ሰዎችን በዘርና በልዩነት ከፋፍሎ ማሰቃየት ነው።
ይህንን ጉዳይ ደግሞ ቀደም ብለንም እኛ የምናውቀውና የተረዳነው ነው። ምክንያቱም ከመጀመያውኑ ሲመጡ ድልድይና ትምህርት ቤት እያፈረሱ፣ ባንክ እየዘረፉ ነው አገሪቱን የተቆጣጠሩት። እና እነዚህ ሰዎች ከጥንስሳቸው ጀምሮ ዘራፊና ቀማኛ ከሆኑ ወደፊትስ ምን ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል?
የእገሌ ዘር እገሌን ጨቆነ በሚል ሃሰተኛ ትርክት ውስጥ ገብተው የማህበረሰቡን አዕምሮ ሁሉ አቃዥተው እርስበርስ አባልተው አገሪቱ ልትወጣው ወደማትችለው መዓትና መከራ ውስጥ ነው የከተቷት። አገሪቷን ሙልጭ አደርገው ዘረፉ። እነሱ የዘረፉት ገንዘብ ስራ ላይ ቢውል ኖሮ ዛሬ ይህች አገር የት ትደርስ ነበር?። ወጣቱን ሱሰኛ ፣ ስራ የማይወድ፣ አመጸኛ ፣ ስለሃገሩም ሆነ ስለታሪኩ ደንታ የሌለው አድርገው አስቀመጡት።
አሁን ላይ እኮ ስለሃገሩ ሲጠየቅ ትክክለኛ ምላሽ የሚሰጥ ወጣት ማግኘት ከባድ ነው። ብዙዎቹ ታሪካቸውን አያውቁም። ታሪኩን ስለማያውቅ ነው የተጎዳው። ስለዚህ ታሪኩን ባለማወቁ ያልሆነና ሃሰተኛ ትርክት እየተዘራበት እንዲኖር ተገዷል።
እንግዲህ ከዚህ ሁሉ ክፉ ዓመታት በኋላ ፈጣሪ በዘመኑ የሰሩትን ግፍ ቆጥሮና ተንኮል ሁሉ አይቶ ነው ይህንን ለውጥ ያመጣው። በዚህ ለውጥም እነዚህ ጠንከር ያሉ መሪዎች ተፈጠሩ፤ አገሪቱም ወደ ተሻለ የለውጥ መሥመር እየገባች ባለችበት ጊዜ ደግሞ ለሁለት አመት በቀያቸው መሽገው ተንኮል ሲያስሩና ሲቀምሙ ነው የኖሩት። ለሀገሪቱም ሆነ ለወጡበት ማህበረሰብ ሊጠቅማት የሚችለውን ስራ ከመስራት ይልቅ ለራሳቸው መቀበሪያ ጉድጓድ ሲቆፍሩ ነው የቆዩት።
ለመደበቂቸው ኮንክሪት ሲገነቡ ከርመው፣ በየክልሉ ለጥፋት አላማ የሚውል ገንዘብ እየበተኑ፣ ሕዝብ ሲያተራምሱ ነው የኖሩት። አንዱን ከአንዱ ሲያባሉና ሲያጋድሉ ከርመው መጨረሻቸው ግብዓተ መሬት ሆነላቸው። በጣም ደስ የሚለው ነገር ራሳቸው በቀሰቀሱት እሳት መጥፋታቸው ነው።
ከዚህም በላይ በመጨረሻው ትርክት ላይ እንደቀድሞው ሁሉ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ለማፍረስ የሞት ሞታቸውን ታገሉ። አሁንም በዚህኛው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በጣም የሚዘገንና የሚያሳዝን በደልና ክህደት ነው የፈፀሙበት። በአለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቁ መልኩ የሰው ልጅ ግንድ ላይ አስረው የረሸኑ ሰዎች ናቸው። ሰው አሰተኝተው መኪና የነዱ አስፈሪ ፍጥረቶች ናቸው።
ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ታንክ ሰው ላይ ነድተዋል። ካረዱትና ካሰቃዩት በተጨማሪ በመኪና የሰው ጭንቅላት ያፈረሱ አረመኔዎች ናቸው። መከላከያ ሰራዊቱ እነዚህን ከሃዲዎች ማሸነፉ ብቻ አይደለም የሚያስደስተኝ፤ ፍፁም በሆነ ወታደራዊ ዲሲፕሊንና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ንፁሃንን ከወንጀለኛው በመለየት ጉዳት እንዳይደርስ ያደረገው ጥንቃቄ ለእኔ ሌላኛው ድል ነው።
በሌላ በኩል በሄደበት ቦታ ሁሉ የአማራ ህዝብ እጣ ክፍሉ ሞትና መታረድ ነበር። ስቃይ ነበር የሚያጋጥመው። በገዛ አገራቸው ገብተው ምን ያህል ሰው ገለው እንደቀበሩ ይታወቃል። ያ ሁሉ ግፍ ቢደርስባቸውም የአማራ ሚሊሻና የአማራ ልዩ ሃይል ደግሞ አስደናቂ ስራ ነው የሰሩት። የማረኳቸውን ወስደው ምግብ ሲያበሉና ቆመው ሲያስተናግዱ ነው የታዩት። ከዚህ በላይ ድል ምን አለ?።
አዲስ ዘመን፡- እርሶዎ በውትድርና አለም በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል እንደመቆየቶ የትግራይ ሕዝብ ካለው ተስማምቶና ተቻችሎ የመኖር ባህል አንፃር የጁንታው አባላት የፈፀሙት ተግባር የሚመጥን ነው ይላሉ?
አስር አለቃ ተሾመ፡– እኔ የትግራይን ህዝብ እንደዚያ አይደለም የማውቀው። እኔ እዛ አካባቢ በነበርኩበት ዘመን በተለይም ኮይሃ እንደስላሴ የምትባል ቦታ ላይ ለሶስት ወራት ተቀምጪያለሁ። እዚያ በነበርንበት ወቅት ማህበረሰቡ ለሰው ያለው ክብርና በጎ ነገር በቃላት የሚገለፅ አይደለም።
ምንአልባት እኛ በነበርንበት ዘመን የነበሩት ሰዎች ለመግለጽ እንኳን ይቸግረኛል። በክፉም ሆነ በደጉ የሚያበሉና የሚያጠጡ ህዝቦች ናቸው። ለሁሉም መልካምና ቅንነት ያላቸው ሰዎች ናቸው።
ይህ ሲባል ግን የማንክደው ሃቅ ጁንታው አገር ውስጥ የፈለፈላቸው ሰዎች መኖራቸውን ነው። ተጠቃሚ አካላት አሉ። ይሄ ውሸት አይደለም። የተለየ ጥቅም አግኝተው የራሳቸውን ኑሮ አመቻችተው ዛሬ እጅግ በጣም በሚገርም ውድ በሆነ መኪና የሚንቀሳቀሱ ወገኖቻቸው አሉ።
እውነት እኮ ነው፤ ልንክደው አንችልም። ከዚህም አልፈው ደግሞ በሌሎች ክልሎችም ለሆዳቸው ያደሩትን ሰዎች ሰብስበው በጥቅም በመያዝ ሥልጣናቸውን የሚያራዝሙበት ሁኔታ እንዳመቻቹ ይታወቃል።
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ትግራይ ውስጥ ያሉ እናቶች አውነቴን ነው የምነግርሽ ዛሬም ድረስ ረጅም ርቀት ተጉዘው ነው ውሃ በጀርባቸው እየተሸከሙ የሚኖሩት። በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በጣም በርካታ ናቸው።
እርቧቸውና ጠምቷቸው የሚኖሩ እናቶች ናቸው ያሉት። እነሱ ግን በየከተማው በውስኪና በጮማ ሲንደላቀቁ ነው የኖሩት። ለዘመናት ሲዘርፉ ኖረው ደግሞ ለዚህ ምስኪን ህዝብ ያተረፉለት ነገር የለም። ደግሞም በእኔ እምነት የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን የሚጠላ ሕዝብ አይደለም።
ነገር ግን ተጠቃሚ የሆኑና እነሱን አቅፈው ይዘዋቸው የነበሩ ሰዎች መኖራቸው ግን ምንም ጥርጥር የለውም። በአደባባይ ላይ የምናየው ነገር አለ። አሁን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ሆነው ያኮረፉ ብዙ አሉ። ይህንን አይነት ግፍ የሰሩትን ሰዎች ደግፈው ለምን ተነኩብን ብለው አብጠው የሚፎክሩ ሠዎች አሉ።
እኔ እንደዚህ አይነት አቋም ያላቸውን ሰዎች ስመለከት አፍራለሁኝ። በወገኖቻችን ላይ እንደዚህ አይነት ግፍ የፈፀሙትን ሰዎች መቃወም ሲገባቸው ክብራቸውን ጥለው ሆዳውን የወደዱ ሰዎች አሉ። በሁሉም አካባቢዎች ከእነሱ ጥቅም ሲያገኙ የነበሩ ሰዎች ብዙ የተንኮል ስራ ሲሰሩ ነው የሚታዩት። በራሱ በመንግሥት ተቋም ውስጥም ብዙ አሉ።
አሁን ላይ ቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልል ላይ የምናየው ነገር የዚሁ ጉዳይ ማሳያ ነው። በኦሮሚያ ክልል ላይ ብሔር እየተለየ የሚገደለው የኦሮሚያ ወጣት ሰው የሚጠላ ሆኖ አይደለም። እኔ ሻሸመኔ ብዙ አመት ኖሪያለሁኝ። የዚያ አካባቢ ሕዝብ እጅግ በጣም ሰው የሚወድና የሚያከብሩ ናቸው።
ነገር ግን ላለፉት 27 ዓመታት ከፉና ሃሰተኛ የማንነት ትርክት የተሰጣቸው በመሆኑ መከፋፈሉና እርስበርስ የማባላት ውጥናቸው ፍሬ አፍርቶ እያየን ነው ያለነው። በጣም የሚያሳዝነኝ ደግሞ ላይጠቅማቸው ነገር እርስ በርስ እንዲባሉ ማድረጋቸው ነው። ሲዳማ ላይም ገብተው የሰሩትም ይታወቃል።
ይህንን ሁሉ አመት ሲገዙ ኖረው እስካሁን ያልሰጡትን መብት ስልጣናቸውን ባጡ ማግስት መብትህን አስከብር እያሉ አገር ሲበጠብጡና ሲያተራምሱ ነበር። በወላይታም ተመሳሳይ ስራ ነው የሰሩት።
ስለዚህ እኔ የትግራይ ህዝብ ብቻውን ተነጥሎ የመኖር ፍላጎት አለው ብዬ አላምንም። ለሆዱ ያደረና ጥቅም የተነካበት የጁንታው ደጋፊ በትግራይም ሆነ በሌሎችም አካባቢዎች አለ። የትግራይ ማህረሰብ ኢትዮጵያ አገሩን የሚጠላ ማሕበረሰብ አይደለም። ለዓመታት በግድ ወደመገንጠል ሃሳብ እንዲሄድ በጉልበት ይዘውት ነበር።
ግን በጉልበት የሚሆን ነገር የለም። አውሬው ጁንታ ጉልበቱ ተሰብሮ የትግራይ ህዝብ ዛሬም እንደጥንቱ ከሌላው ሕዝብ ጋር በሰላም እየኖረ ነው። መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገለት የሚያስፈልገው እየሆነ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- የትግራይ ማህበረሰብ ሕገወጦችን ለህግ አሳልፎ ከመስጠት አኳያ ምን ይጠበቅበታል ይላሉ?
አስርአለቃ ተሾመ፡– መንግስት እየወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ አድርገው ሃሰተኛ ወሬ እየነዙ ያሉ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ይህ ለእኔ ብዙም ውሃ አያነሳም። ምክንያቱም ሌላውም ክልል ላይ ወንጀል የሰሩ ወህኒ ወርደዋል። ለምንድን ነው እነሱ ብቻ በዘራቸው ተለይተው የሚጠቁት? እንዳውም ለዘመናት ያንን ክልል ይመሩ በነበሩት ሰዎች ነው ሌላው ማህበረሰብ በማንነቱ ተለይቶ ሲጠቃ የኖረው።
እኔ ለምሳሌ እዛ በነበርኩበት ግንባር ላይ በርካታ ኢትዮጵያን የሚወዱ ትግሬዎች ነበሩ። ለባንዲራቸው ሲሉ ከእኔ ጎን ተሰልፈው የወደቁ የሞቱ አሉ። እነዚህን ሁሉ ሰዎች ጠቅልለን የዘር ሃሳብ ሥለነዙባቸው ዘራቸውን ወግነው የሚናገሩት ነገር ለእኔ ቦታ የለውም። ነገር ግን አስቀድሜ እንደተናገርኩት ሆድአደሮች አሉ።
የትግራይን ህዝብ ነፃነቱን እንዳጣ ወይም በሚፈልገው መስመር ውስጥ ገብቶ እንደፈለገው ሊሆን እንደማይችል ሥለነዙበት ዛሬም ከስጋት ሙሉ ለሙሉ መውጣት ያልቻለው። እንዲህ አይነት ክፉ ትርክት ይዞ ያደገ ወጣት ስለሆነ ያንን ነው ሲያስተጋባ የምናየው።
ይህም ቢሆን ግን በምንም መስመር ወንጀለኛ ደብቀው የሚያስቀምጡበት አግባብ አላቸው ብዬ አላስብም። እንዴትስ ይታሰባል፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ እጅግ በጣም ዘመናዊ ጨዋ አገሩን የሚወድ ሆኖ ነው እንጂ እነሱ እንደፈፀሙት ግፍ ቢሆን ምን ነበር ሊፈጠር የሚችለው፡ ያ በታንክ የፈጩት እኮ የእኔ ወንድም ነው። እነሱ እንዳሰቡት ቢሆን ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር። ህዝቡ ጨዋ ነው።
ከዚህ ከተዋረደና ከወደቀ ጁንታ ጋር የትግራይ ህዝብ ወግኖ ሊቀመጥበት የሚችልበት ምንም አይነት አግባብ የለም። ምክንቱም ምንም ያደረጉለት ነገር የለም። በየበዓሉ የሞቱ ልጆቻቸውን ፎቶ ከማንሳት በስተቀር ለእነዚያ እናቶች የተረፈላቸው ነገር የለም። እኔ አንድ አውነት ልንገርሽ፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚያሳስት የሞተ ታጋይ ሁሉ በጦር ሜዳ የሞተ እንዳይመስልሽ።
በመሳሪያም የተቀየረ አለ። ጁንታዎቹ የገዛ ወገኖቻቸውን በጠብመንጃ ቀይረው ሲዋጉ የነበሩ አረመኔዎች እኮ ናቸው። በወገኖቻው ህይወት ላይ ተደራድረው ከውጭ ጠላት ጋር በማበር አገር እንድትበታተን ሲሰሩ ነበር።
ይቅርታ አድርጊልኝና ሌላ አንድ ነገረ ልንገርሽ፤ የአፋር ግመል ኢትዮጵያዊነቱን ያምናል፤ ባንዲራውንም ያውቃል። ነገር ግን በዚሁ አገር ውስጥ ዶክተርና ፕሮፌሰር የሆኑ ሰዎች በአገራቸው የሚያፍሩና ታሪክ የማያውቁ አሉ ። እነዚህ ሰዎች ከግመሉ በታች የሆኑ አሳፋሪ ዜጎች ናቸው።
እናም አገሩን የማያውቅ ምሁር በበዛት አገር ፤ላይ ሆንና እንዲህ አይነት ነገር ቢከሰት የሚገርም አይደለም። ዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጪያዬን እንዳለችው ሁሉ በመጀመሪያ አገር ሳይኖረን ስለሌላ ነገር ማውራት አንችልም። እኔ አስቀድሜ እንደነገርኩሽ ጅቡቲ ላይ ሆንን ሰዎች ሲሞቱብን አገራቸሁ ሄዳችሁ ቅበሩ ነው የተባልነው።
ዛሬም በየሀገሩ የምንሰማው አለ። በየአረብ አገሩ የተሰደዱ ዜጎቻችን የመንግስት ያለህ በማለት ከእስር እንዲያስፈታው እየተማፀኑ ነው ያሉት።
በመሆኑም በአገር የሚገኝ ክበርን በምንም ልትለውጭውም ሆነ ልታገኚው የምትቺው አይደለም። አገር ምን አይነት ክብር ሊሰጥ እንደሚችል ይሄ ትውልድ ማወቅ አለበት። በሀገሩ ላይ ሆኖ ችግርን ማሳለፍ ነው የሚሻለው። አገር የሌለን ቀን ጉዳችን ነው የሚፈላው። ዛሬም ቢሆን አልተገነዘብነውም እንጂ ጠላቶቻችን በዙሪያችን አድብተው እየጠበቁን ነው ያሉት።
እዚህ ከነበሩት ጥቋቁር ጅቦች ባሻገር የእኛን እድገት በማይሹ ነጭ ጅቦች በዙሪችን ተከበናል። እነዚህ ሰዎች እዚህ አገር ውስጥ እርስ በርስ ተበጣብጠን ሃይላችን እንዲዳከም የሚያደርጉበትን ስትራትጂ ህዝባችን ማወቅ አለበት። እነዚህን ሁሉ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች አስቀምጠን አገር እንድትፈርስ የተደረገበትበት ወቅት ላይ ነን። በየአገሩ አደባባይ ላይ ኢትዮጵያ ትውደም የተባለበት ዘመን ላይ ደርሰናል እኮ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ ኢትዮጵያዊ ደም ያለው፤ በሰው አገር ሳይቀር አገሩን ያዋረደበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። ትውልዱ ሁሉ ቆም ብሎ ማሰብ መቻል አለበት። ከዚህ ትውልድ የሚጠበቀው አንድ ሆኖ ጠላቶቹን መመከት ነው። ለዚህ ደግሞ ትውልዱ ስለሀገሩ ትክክለኛ ታሪክና ስለቀደሙት አባቶቹ ጀብዱ እንዲገነዘብ ማስተማር ይገባል።
በዚህ አጋጣሚ ሁሉ ጊዜ ስሰማው የሚያሳፍረኝን ነገር ልንገርሽ፤ይኸውም የወያኔ ጁንታ ላለፉት 27 ዓመታት ሙሉ ደርግን አሸነፍን ሲሉ እንሰማለን። እውነታው ግን ይህ አይደለም። ደርግን እኮ 33 ድርጅት ነው የታገለው። ያ ብቻ አይደለም ከሱማሌ ጋር ሆኖ ነው እኮ የገዛ አገሩን የወጋው። ብቻቸውን እንደተዋጉና ድል እንዳደረጉ የሚነዙት ሃሰት ነው።
አዲስ አበባን ይዞ ያስረከባቸው እኮ ሻቢያ ነው። ሥለዚህ የሌለ ትርክት የትግራይ ወጣትን መግበውት ነው ያሳደጉት። ያን ያህል ደንፍተውና ፎክረው ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው ጉዳያቸው ያከተመው። እናም ብቻቸውን ሲሆኑ የሚሆኑትን ለማየት ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች የውጭ ሃይሎች ተሰዶ የሄደውን የጁንታውን ክንፍ ለሽበር ስራ በማሰልጠን ወደ አገራቸው ሊልኳቸው ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው። ከዚህ አንፃር ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ይላሉ?
አስርአለቃ ተሾመ፡- የመንግስት አይን የንስር አይን ነው። እዚህ እኛ ቁጭ ብለን እንደምናወራው አይደለም። ትናንትና እኮ ወያኔዎች እነዚህን ማንም አይደፍራቸውም ሲባል ነበር። ግን ከሁለት ሳምንት በላይ አልዘለቁም። በጣም ገዝፈው ነበር ሲታዩ የነበሩት። ኢትዮጵያ በታሪክ ከውጭ ወራሪ ጋር ለሚደረግ ጦርነት ችግር ያለባት አገር አይደለችም። ዛሬም ሆነ ወደፊት።
ይህ ሕዝብ የተበታተነ ቢመስልሽም ነገር ግን የውጭ ጠላት ሲመጣ ዛሬም እንደጥንቱ ሆ ብሎ ነው የሚነሳው። ይህንንም በጁንታው ላይ በተወሰደው እርምጃ ማየት ትቺያለሽ። ያም ቢሆን ግን ጠላትን መናቅ አያስፈልግም። አንፈራም፤ ግን አንንቅም። ማይካድራ ላይ ሰው አርዶ ሱዳን የተሰደደው ቡድን ዳግም ኢትዮጵያን ይበጠብጣል የሚል ስጋት ባይኖረኝም ነገር ግን መጠንቀቅ ይገባል።
ድንበሩ በአግባቡ መጠበቅ አለበት። በዲፒሎማሲ መንገድም ሱዳን ውሥጥ ያሉ ወንጀለኞች ተይዘው በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባል። በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩት መሰረት መጠየቅ ያለባቸው ወንጀለኞች አገራቸው ላይ መጠየቅ መቻል አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። ከዚሁ ጎን ለጎን የየአካበቢው መስተዳደርና ህዝብ ፀጉረ ልውጥ የሆኑትን ሰዎች ነቅሶ አውጥቶ ለመንግስት አካል ማቅረብ ይጠበቅበታል። ራሱ ማህበረሰቡ አካባቢውን ማጥናት አለበትና መጠቆም አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም አመሰግናለሁ።
አስርአለቃ ተሾመ፡- እኔም እንግዳችሁ ስላረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013