አስቴር ኤልያስ
በቀጣይ አስር ዓመታት ውስጥ ህዝቡን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚያስችሉ ዋና ዋና ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ ሰፊ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅበት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በዚህ ውስጥ ከሚካተቱት መካከል አንዱ ከተሞችን ወደ ሊዝ ስርዓት ማስገባት መሆኑ ይጠቀሳል።
በእስካሁኑ እንቅስቃሴ በሀገሪቱ ካሉ ከተሞች መካከል 842ቱ ወደ ሊዝ ስርዓት ገብተዋል። ይህ ግን በሀገሪቱ ካሉት ከ2 ሺህ ከሚበልጡ ከተሞች አኳያ ሲታይ ውስን ነው። የተቀሩትን ከተሞች ወደ ስርአቱ ለማስገባት ሰፊ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ያመለክታል።
ከተሞቹን ወደ ሊዝ ስርአት ለማስገባት እየተካሄደ ስላለው ጉዳይ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እያደረገ ያለው ምንድን ነው? ለምንስ ነው ቶሎ ወደሊዝ ስርዓቱ መገባት ያልተቻለው ስንል የሚኒስቴሩን የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብዙዓለም አድማሱ በጠየቅናቸው ወቅት እንደገለጹት፤ ለክልሎች አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እገዛ ያደርጉላቸዋል። ለአብነትም ክልሎቹ ለሊዝ ስርዓቱ መነሻ ዋጋ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ፡ የቦታ ደረጃ መዘጋጀት አለበት።
ራሱ ሊዝን የሚከታተል ጉዳይን የተመለከተ ስልጠናም መውሰድ ስለሚገባ በእነዚህ ዙሪያ ስልጠናዎችን እንሰጣቸዋለን የሚሉት አቶ ብዙዓለም፣ ለዚህ ጉዳይ ደግሞ ማኑዋሎች እንዳሉ ነው የተናገሩት። ያዘጋጁት የመነሻ ዋጋ እና የቦታ ደረጃ ማኑዋል መኖሩንም ጠቅሰው፤ እዛ ላይ ግንዛቤው እንዲኖራቸው ስልጠና እንሰጣለን ይላሉ። ድጋፍ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ባለሙያዎችን እንደሚያሰለጥኑ ነው የሚያስረዱት።
ኃላፊው እንደሚሉት ፤ ከዚህ ውጭ ባለው ጉዳይ ራሳቸው ናቸው በዓመት ምን ያህሉን ከተማ ወደሊዝ ማስገባት እንደሚፈልጉ በከተማ ምክር ቤት የሚያስወስኑት። ይህን ሲያደርጉ ግን ለምክር ቤቱ የሚያቀርቡት የቅድመ ዝግጅት ስራው ማለቁን በማረጋገጥ ነው። ምክር ቤቱ ደግሞ ቀጥታ ወደ ሊዝ እንዲገባ ይወስንላቸዋል፤ አሊያ ደግሞ እነዚህ ከተሞች በዚህ ደረጃ ብቁ አይደሉም ብሎ ሊያነሳ ይችላል።
ለምሳሌ የትግራይና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎችን ብንወስድ አዲስ ከተሞች ሲመሰረቱና የከተማነት እውቅና ሲሰጣቸው አንድ ላይ ወደሊዝ እንዲገባ ነው የሚያስደርጉት። ይሄ የራሳቸው ልምድ ነው። በኦሮሚያ ክልል ያለው ተሞክሮ ደግሞ ከተማ ሆኖ ከተቋቋመ እና ትንሽ ከተንቀሳቀሰ በኋላ ነው ወደሊዝ የምናስገባው የሚለውን አካሄድ ይከተላሉ ።
አንድ ከተማ መጀመሪያ ሲቋቋም ትንሽ ከተማ የሚሆነው የአካሄድ ጉዳይ ነው። አንድ ከተማ ከተቋቋመ በኋላ እና ከመቋቋሙ በፊት ወደሊዝ ስርዓት ማስገባቱ ላይ ይኸኛው (ከተቋቋመ በኋላ አሊያ ሳይቋቋም በፊት) ይመጣል የሚል ነገር እንደሌለው ኃላፊው ተናግረዋል። ምክንያቱም ሁለቱም አካሄድ የየራሱ ጥቅምም ጉዳትም ያለው ነው ።
ለዚህም ነው እነሱ ይሻለኛል የሚሉትን አካሄድ የሚጠቀሙት። ከተማ ከሆነ በኋላ አንድን ከተማ ወደሊዝ ለማስገባት የሚደረገው ጥረት ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ሊዙን ማጸደቅን ይጠይቃል። ከተማ ከመሆኑ በፊት ከሆነ ግን ከተማነቱንም ለማሰጠት በሚደረገው ሂደት ወደሊዝ መግባቱንም ማጸደቅ ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ብዙዓለም እንደሚሉት፤ ከተሞች ወደሊዝ ስርዓት ለመግባት መዘግየት አሳይቷል የሚባለው አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው። ኦሮሚያ ክልል ደግሞ በተደጋጋሚ ከተሞቹን አዘጋጅቷል። ምክር ቤት አቅርቦ ማስጨረስ ነው። ሚኒስቴሩ የባለሙያዎች ድጋፍ አድርገንላቸው እነሱም የመነሻውን ዋጋ አዘጋጅተው ተሰናድተዋል። ነገር ግን ምክር ቤት ሊያጸድቅላቸው የግድ ይላል።
የሊዝ ጉዳይ ቀርቶ ከተማም ከመሪ ማዘጋጃ ወደ ማዘጋጃ እንዲሁም ከማዘጋጃ ወደ ከተማ አስተዳደር ሲሸጋገር ሊጽድቅ ግድ ነው። ለዚህ ደግሞ የከተማ ምክር ቤት ሊኖራቸው ይገባል። ከዚህ የተነሳ ከተሞች ወደሊዝ ስርዓት እንዲገቡ ሲደረግ በርካታ ጉዳዮች ቀድመው መሰራት እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ተያይዞ አብሮ የሚወሰን ጉዳይ ይኖራል ማለት ነው።
በአሁኑ ወቅት ከተሞችን ወደሊዝ ስርዓቱ በማስገባት ረገድ ይህኛው ክልል ከዚህኛው ክልል የተሻለ ነው የሚያስብል ነገር እምብዛም የለም ያሉት አቶ ብዙዓለም፣ ዋናው ነገር ደግሞ ወደ ሊዝ ስርዓት የማስገባቱም ጉዳይ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ አንድ ከተማ የተሻለ ነው አሊያም የተሻለ አይደለም የሚባለው ወደሊዝ ባይገባም የተሻለ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ሲፈጠር እንደሆነም አክለዋል።
የተሻለ የመሬት አስተዳደር መፍጠር ላይ ነው ትልቁን ስራ መስራት የሚገባው። ለምን ቢባል ወደሊዝ ባይገባም የመሬት አቅርቦት እና የመሬት አሰጣጡ ያለው አዋጁ ላይ እንደተጠቀሰው በጨረታና በምደባ ብቻ ነው። ወደሊዝ ስርዓቱ ስለገባ አሊያ ስላልገባ ብቻም አይደለም።
የትኛውም ከተማ ወደሊዝ ስላልገባሁ መሬቴን እንደፈለኩ እሰጣለሁ ማለት አይችልም። ይህ ስለሆነ የሊዝ ስርዓቱ የራሱ የሆነ አደረጃጀት ተፈጥሮለት ቅድመ ሁኔታም ተዘጋጅቶ እና የሚከታተል ባለሙያም ተመድቦለት፣ የራሱም በጀት ተመድቦለት የሚንቀሳቀስ ነው። ትልቁ ነገር የተሻለ የመሬት አስተዳደር ስርዓታቸውን በአግባቡ ሊመሩ የሚችሉ ከተሞችን መፍጠር ላይ ነው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ወደሊዝ ስርዓት ውስጥ ገብተዋል ተብለው በመሬት አስተዳደሩ ስርዓቱ ትልቅ ችግር ያለባቸው ከተሞች እንዳሉ ይታወቃል። ስለዚህ ትልቁ ጉዳይ ወደሊዝ ስርዓት የመግባትና ያለመግባት ጉዳይ ብቻ አይደለም ማለት ነው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየክልሉ ያሉ ከተሞችን በአስቸኳይ ይህን ያህል ከተማ ወደሊዝ ስርዓቱ አሁኑኑ አስገቡ የማለት ግፊት ማድረግ አንችልም፤ የእኛ ስራ አቅምን የማጠናከር ነው። ስለዚህም በምንችለው ሁሉ አቅማቸውን እያጠናከርን እንገኛለን። በአንድ ክልል ውስጥ ያሉት የመሬት ተቋማት አደረጃጀት ወደ አንድ እንዲመጣ ነው የእኛ ትልቁ ስራ ያሉት፤ ከተሞች የመሬት አስተዳደር ስርዓታቸው ተቀራራቢ እንደሆን ነው የሚፈለገው ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ትንሹም ላይ ሆነ ትልቁ ከተማ ላይ መሬት ላይ ያለው ነገር እንደ አገር የሚታወቅ ነው። ከዚህ አንጻር ትልቁ ነገር እሱን ማስተካከል ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት እያለ ያለው በቀጣይ አስር ዓመት ሁሉም ከተሞች ወደሊዝ ስርዓቱ መግባት አለበት ነው ብለዋል።
አሁንም ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥተናል ያሉት አቶ ብዙዓለም፣ በተመሳሳይ ለአመራሮችም ስልጠና በመስጠት ላይ እንገኛለን ብለዋል። በዚህ መልኩ ድጋፉ ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚቀጥል ይሆናል። ይህ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን ክልሉም በዛው ልክ ሐሳቡን ተረድቶ ወደ ከተማ ምክር ቤት መውሰድና ማስወሰን ይጠበቅበታል። ሚኒስቴሩ ቴክኒካል ነገሩንና ድጋፉን ነው የሚያደርገው በማለት ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ወደ ሊዝ ስርዓት የመግባት ፋይዳው የከተሞችን ተወዳዳሪነት ይበልጥ እንዲጨምር ያደርጋል። የገቢ አቅማቸውም ያድጋል። የመሬት አስተዳደር ስርዓታቸውም የተሻለ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013