ዳግም ከበደ
መቼም የእቃ አጠቃቀማችን ነገር በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት ከሆነ ቆይቷል። በተለይ በመንግስት ተቋማት የምንሰራ ሰዎች ከመብራትና ከውሃ ጀምሮ ሁሉን ነገር የጠላት ገንዘብ ነው የምናደርገው። ይህ ተግባር የተቋማት አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ በእያንዳንዱ ሰራተኛ ዘንድ ይስተዋላል ፤ የአስተዳዳሪዎቹ ግን ለየት ያለው ነው፤የማይጠቀሙበትንም እቃ ለማበላሸት አልያም ሌሎች እንዳይጠቀሙበት ለማድረግ አይቦዝኑም።
እስከ ቅርብ ጊዜ በሁሉም የመንግስት ተቋማት ሊባል በሚችል ደረጃ የተበላሹ እቃዎች መኪናዎችና የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈባቸው ንብረቶችን በመጋዘኑና በየግቢው አጭቆ ማስቀመጥ የጌጥ ያህል የሚወሰድ ነበር።
እድሜ ለካይዘን አንዳንዶቹን ከዚህ አይነቱ ችግር ታድጓቸዋል፡፡ በአንዳንድ ተቋማት ደግሞ አገልግሎት የማይሰጡ እቃዎችን በወቅቱ ካለማስወገዳቸው ባሻገር ለበለጠ ጉዳትና ብልሽት በሚዳረጉበት ሁኔታ በየቦታው ወሽቀዋቸው ማየት የተለመደ ነው።
በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ከሚገኙ ሆስፒታሎች በአንዱ ለረጅም አመታት የተቀመጠውና የኩላሊት ህክምና ለመስጠት የሚረዳው ማሽን ለዚህ አንድ ማሳያ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ ማሽኑ ለአመታት መቀመጡን ካለማወቃቸው ባሻገር ምን አገልግሎት እንደሚሰጥ የማያውቁ የተቋሙ ባለሙያዎች መኖራቸው በራሱ የኃላፊዎች ሰራተኞችና ተቋማት አልተገናኝቶምን ፍንትው አድርጎ ያመለክታል።
አንዳንዶቹ ንብረት በማስወገድ ሂደት አንዳች ጥቅም ካላገኙ በቀር ስለእነዚህ እቃዎች አጀንዳ አይዙም፤ ንብረት ማስወገድ ምስጋና የለውም ብለው በማመን ማስወገድን እንደ ትርፍ ስራ ይቆጥሩታል። ሌላው ቀርቶ በሰው ጤና ላይ ችግር ሊያደርሱ የሚችሉ ኬሚካሎችን ሳይቀር ትኩረት ባለመስጠት በንብረት ክፍላቸው አጭቀው የሚኖሩም አሉ። እነዚህ ንብረት ቤቶችም ሆኑ ንብረቶች ትኩረት የሚያገኙት በሚመለከታቸው አካላት የኦዲት ጉዳይ ሲነሳ ለዚያውም ለአንድ ሰሞን ብቻ ነው።
እዚህ ሁሉ ውስጥ እንድገባ ያነሳሳኝ በቅርቡ በስራ ምክንያት ከአዲስ አበባ ወጥቼ የገጠመኝ ጉዳይ ነው። እኔ የሄድኩበት የስራ ጉዳይ በመኪና ብልሽት በመስተጓጎሉ ለተወሰኑ ሰአታት በአንድ ድርጅት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ለመቆየት ተገደን ነበር። አብረውኝ ከነበሩት ሰዎች መካከል ደግሞ በአውቶ መካኒክና በማሽን ቴክኖሎጂ የተመረቀው የቅርብ ጓደኛዬና የስራ ባልደረባዬ ይገኙበታል።
የተወሰነ ሰአት ከተቀመጥን በኋላ እግራችንን ለማፍታታት በግቢው ውስጥ መዘዋወር ስንጀምር ከህንጻው ጀርባ በርካታ መኪናዎችና ማሽኖች ሳር በቅሎባቸው ዳዋ ለብሰው ተመለከትን። እንደዚህ አይነት ነገር በአዲስ አበባም በየትኛውም የመንግስት ተቋም ቁጥሩ ይለያይ እንጂ ስንመለከት እኔ እምብዛም ትኩረቴን አልሳቡትም ነበር።
ጓደኛዬ ግን ስለአካባቢው ሲያጫውቱን የነበሩትን የጥበቃ ሰራተኛ አስፈቅዶ ወደማሽኖቹና መኪናዎቹ ተጠጋ። እናም እላያቸው ላይ እየወጣ በአትኩሮት ሲመለከታቸው ከቆየ በኋላ አንደኛውን ትልቅ የአስፋልት ማንጠፊያ ማሽን አንድ ቦታው ላይ በሶፍት ጠራርጎ ተመለከተው፤ በፍጹም መገረምና ንዴት ይሄ እቃ በዚህ ጊዜ ውስጥ እንዴት ሊበላሽ ቻለ? ከተመረተ አስር አመት እንኳን አልሆነውም፤ በዛ ላይ በቀላሉ ሊጠገን የሚችል ነው።
መለዋወጫዎቹም አዲስ አበባ እንደ ልብ ይገኛሉ ሲል አጉተመተመብን። ቀጠል አድርጎም በአቅራቢያችን ስላሉት ማሽኖችና መኪናዎች ሰፊ ገለጻ ሲያደርግልን ቆየ፤ ስለሁሉም ነገር ሲያወራ ግን በቀላሉ መጠገን እንደሚችሉ በዚህ ሁኔታ አመታትን ከጨመሩ ግን አንዳቸውም አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ እያሳሰበን ነበር።
በነገሩ በደንብ መብከንከኑን የተመለከቱት የጥበቃ ሰራተኛ ቀስ ብለው ተጠጉትና «ኧረ እዛ መጋዘን ብትሄድ ያገር ጉድ ታያለህ ፤ያው አሁን አንዳንድ ጊዜ እየመጡ ስለሚወስዱት ቀነሰ እንጂ» አሉ ፈራ ተባ በማለት። የመጋዘኑ በሩ ክፍት እንደሆነ ሲጠይቃቸው «አይ ክፍትስ አይደለም ፤ ግን ከጀርባ ሙቀት ለመከላከል ተብሎ በወንፊት የተሰራው መስኮት እንደልብ ያሳይሀል» አሉት፤ ሄዶ እንዲያይ በመጋበዝ አይነት።
ወዳጄ ጣደፍ ጣደፍ እያለ ወደ መስኮቱ ሄደ እኔም ለምን ይቅርብኝ ብዩ ተከተልኩት፤ መጋዘኑ በተለያዩ አዳዲስ መለዋወጫዎች ተሞልቷል፤ ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው እስኪጠግቡ አቧራ መቃማቸው ብቻ ነበር። ጓደኛዬ እስኪጠግብ የተከመረውን መለዋወጫ ካየ በኋላ ይሄኔ አንድ የግል ድርጅት ቢሆን ይሄንን ሁሉ እቃ ሸጦ ፎቅ ይሰራ ነበር ።
እዚህ ያሉት አስተዳደሪዎች ግን በደብዳቤ መለዋወጥ ብቻ በህዝብ ገንዘብ የተገዛንና በስንት ልመና በእርዳታ የመጣን ንብረት ስንት ነገር መስራት፤ ስንት የህዝብ ችግር መቅረፍ እየተቻለ እንዲህ ሲጫወቱበት ምንም አይሰማቸውም፤ ለነገሩ ማን ይቆጣጠራቸዋል አለኝ ፡፡እኔ አንዳች መፍትሄ እሰጠው ይመስል እያፈጠጠብኝ።
ጥበቃው ጠጋ ብለው ፈራ ተባ እያሉ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንስቶ ላለፉት ስድስት አመታት እዚሁ በጥበቃ ሰራተኝነት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ያለፈውን ሁለት አመት ፕሮጀክቱ ከተቋረጠ በኋላ የሆነውን ይነግሩን ጀመር።
የዛሬ ሁለት አመት ፕሮጀክቱ ሲቋረጥ በግቢው በርካታ መኪናዎችና ማሽኖች ነበሩ ፤ መጋዘኑም ሙሉ ነበር። በየወቅቱ እየመጡ እቃ ያወጣሉ፤ ሲጀመር ለእኛ መውጫ ወረቀት ይሰጠን ነበር፤ ከተወሰ ጊዜ በኋላ ግን እሱም ቀርቶ በቃል ነው የምንታዘዘው።
መጋዘን የምትሰራውም ልጅ ሳትኖር ቁልፍ ይዘው መጥተው እቃ ያወጣሉ፤ ከቆሙት ማሽኖችና መኪናዎችም ፈተው ቀይረው የሚወስዱት እንዳለ እናውቃለን። እንያውም አንድ ቀን እንዳጫጭናቸው ጠርተውኝ የጫነውን አይነት ተመሳሳይ እቃ ዋናው የወጣበት ካርቶን ውስጥ አብሬያቸው መልሼያለሁ።
እናንተም ስትመጡ መኪና ተበላሽቶባችሁ ሳይሆን ለዛው መስሎኝ ነበር አሉ ፈራ ተባ በማለት። ከአዛውንቱ መግለጫ በኋላ የጓደኛዬን ማብራሪያ መስማት አላስፈለገኝም ሆን ተብሎ ግልጽ ዘረፋ እየተካሄደ እንደሆነ ገብቶኛል ።
ማን ያውቃል በወሬ ወሬ እንደምንሰማው ምናልባት ደግሞ አንድ ቀን ዘረፋቸውን ሲጨርሱ በመንደር ጎረምሳ ቃጠሎ እንዲደርስ ያደርጉና ፋይላቸውን ያዘጉ ይሆናል። ግን እስከ መቼ ?
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013