አብርሃም ተወልደ
ወዳጄ ! ክፉ ቃል ተናግረውን ያልረሳናቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በጎ ቃል ተናግረውን ሁል ጊዜ የምናስታውሳቸው ሰዎችም አሉ። አየህ ባሻዬ ! መንፈሳችን ዝቅ ባለበት፤ ተስፋ በቆረጥንበት፣ መንገዳችን ሁሉ ድጥ እና ጨለማ በሆነብን ሰዓት የማጽናኛ ቃል የሰጡንን ሰዎች ፈጽሞ አንረሳቸውም።
ከየአቅጣጫው በተወረወሩብን መጥፎ ቃላት ምክንያት ስለራሳችን ያለን ዝቅተኛ አመለካከት ጠፍንጎ በያዘን ወቅት ደርሰው የማደፋፈሪያ የማነሳሻ ቃል የሰጡን ጀግኖች ሁሌም በልባችን ይኖራሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በአዎንታ የተሞሉ ከጎደለው ይልቅ ያለው የሚታያቸው ቀና የዘመን ፍርጥ ናቸው።
ስለዚህ እኮ ወዳጄ ! በአንደበታችን በጎ የሆነውን በመፈጸም ሌሎች በበጎ እንዲያስታውሱን መሆን አለብን እንጂ ቃላችን በሌላው ሰው ህይወት ውስጥ ጠባሳን የሚተው እንዳይሆን እንጠንቀቅ፤ ይህን ማለት ወዳጃችን ሲሳሳት እና ሲያጠፋ እያየን አንገስጸው፤ እንተወው ለማለት አይደለም፤ ይልቅ ጥፋት ሲኖር “በአገኘሁህ!” እና “እንኳንም እጄ ገባህ!” በሚል ስሜት ሳይሆን በፍቅር ለማረም ለቀጣይ እንዲሻሻል መምከር እጅግ መልካም ነው።
ክፉ ቃል የሚጎዳውን ያህል መልካም ቃል ይጠቅማል። ሰዎች በአሉታም ሆነ በአዎንታ የሚናገሩት ቃል ለረጅም ጊዜ ከውስጣችን አይጠፋም። በልጅነታችን ወላጆቻችን አስተማሪዎቻችን በቅርብ የሚያውቁን ሰዎች የተናገሩን ክፉም ሆነ በጎ ቃል ከአደግንም በኋላ ከአዕምሮአችን አይጠፋም፤ በተለይ በልዩ ሁኔታ የጠገኑን አሊያም የሰበሩን የእድሜ ልካችን ትዝታዎች ነው ሚሆኑት።
ታዋቂው ጸሐፊ መምህር ዶክተር መለሰ ወጉ በልጅነታቸው የገጠማቸውን ሲያነሱ “በህይወቴ ፈጽሞ ከማረሳቸው ትዝታዎቼ መካከል አንደኛው፤ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ የአማርኛ አስተማሪዬ አቶ ለማ ስለ እኔ የሰጡት አስተያያት ነው። አንድ ቀን በምሳ ሰዓት እጃቸውን ሳስታጥባቸው ምሳ ይዘውላቸው ከመጡት ባለቤታቸው ጋር ሲያስተዋውቁኝ ይህ ልጅ በትምህርት ዋዛ እንዳይመስልሽ !ጥይት ነው! አሏቸው።
የአቶ ለማ ንግግር ውስጤን አሞቀው፤ እኔም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ “ጥይት ተማሪ ነኝ” ብዬ አመንኩ። ማመን ብቻ ሳይሆን ጥይትነቴን ለማስመስከር ከዚህ በፊት ከማደርገው የበለጠ ትግል ማድረግ ጀመርኩ፤ የአቶ ለማ አስተያየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ እርግጠኛ ነኝ።
የደረሱበት ደረጃ ከደረሱ በኋላ ዶክተር መለሰ ስለመምህራቸው ስለአቶ ለማ ተናግረው አይጨርሱም፤ “መምህሬ በህይወት የሉም፤ የተናገሩት ግን በእኔ ውስጥ ይኖራል። በትጋት ትምህርቴን እንድከታተል ከድንቁርና ለመውጣት መማር ጠቃሚ መሆኑን እንዳምን ረድቶኛል። የአቶ ለማን መልካም ንግግር በሕይወቴ ፈጽሞ የማልረሳውን ያህል አንዳንድ ጎጂ የሆነ ቃል የሰነዘሩብኝን የክፉ ሰዎች ንግግርም አልረሳም።” ብለዋል።
የዶክተር መለሰም ሆነ የመምህሩ ሁኔታ አንድ ነገር ያመለክታል። ምንም ወጪ የሌለው አንድ ግለሰብን ግን ከታሰበበት ስለሚያደርስ መልካም ምክር እና ሀሳብ እንድንረዳ ይረዳናል። አየህ በሰዎች ውርደት ውስጥ የአንተ ክብር የለም፤ ወዳጅህን፣ ጓደኛህን፣ የስራ ባልደረባህን በማሸማቀቅ እና ድክመቱን በመፈለግ በየቦታው የወዳጅህን እክልና እና በመዝራት ለአንተ ክብር፣ ዝና፣ ሀብትም የሚያመጣልህ ይመስልህ ይሆናል።
ታዲያ ይህን ነውረኛ ምላስህን የሰሙ ሰዎች ያዝኑብሃል እንጂ አያደንቁህም፤ በብዙ ወዳጆች ዘንድ ውርደት እና ቅለት እንጂ አንዳች ሞገስ አይሆንልህም፤ ይመስልሃል እንጂ።
አንድ ታዋቂ አባባል አለ፤ የአንተ ሻማ ደምቆ እንዲበራ የሌላውን ጉረቤትህን ሻማ ማጥፋት አይገባህም›› የሚል፤ ይህ ደግሞ እውነት ነው። ሁለቱ ሻማዎች እንደበሩ በቆዩ ነው ደማቅ ብርሃን ለአካባቢው የሚሰጠው፤ ይህ ብቻ አይደለም፤ የአንተ ሻማ በሆነ አጋጣሚ ቢጠፋ ከወዳጅህ ትለኩሳለህ ። ስለዚህም ልክ እንደ ዶክተር መለሰ መምህር መልካም ሀሳብ አፍላቂ የሰውን መንገድ የምናቀና እንሁን።
ሰው መቼም ነገሩ ብዙ ነው። ትንሽ ስንዝር ሲያገኝ አብኩቼ ካልጋገርኩኝ የሚለው ነገር አለ። ወዳጄ ተገቢውን ቃል በተገቢው ጊዜ የሚናገር ሰው የሌላውን ሰው ስሜት ይጠብቃል፤ ለምሳሌ ለቅሶ ቤት ሄደን አንስቅም፤ እንዲሁም ሰርግ ቤት ሄደን አናለቅስም፤ ሀዘን ደርሶባቸው የተቀመጡ ሰዎች መስማት የሚፈልጉት የማጽናናት ቃል ነው እንጂ የሚወቅሳቸው የሚፈርድባቸው አይፈልጉም፤ ሰዎች መጽናናት ሲፈልጉ የሚፈልጉትን የተሰማቸውን የልባቸውን አፍስሰው ይነግሩሃል።
ታዲያ አንተ ከመፍረድ ይልቅ ማለትም ምን ኣይነት ደካማ ሰው ነህ እንዴት በዚህች ትንሽ ነገር ትረበሻለህ? እኔ አንተን ብሆን ኖሮ ንቄ እተወው ነበር፤ ከማለት ይልቅ ነገሩ ምን ያህል እንደጎዳህ አውቃለሁ፤ በጣም አዝናለሁ፤ ቻለው! በርታ! ይህም ያልፋል ብሎ የሚያጽናናቸው ሰው ነው የሚፈልጉት፤ስለዚህም ባሻዬ! በዚህ ምድር ለምንኖርባት ጥቂት ዕድሜ ደግ በማድረግ የሌሎችን የህይወት መንገድ አቅና! ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን አንዴ እንዲህ ተቀኝተው ነበር።
ጽድቅና ኩነኔ ቢኖሩም ባይኖሩም ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም አይህ ወዳጄ የፈጣሪውን ማለቴ የሰማይ ቤቱን ጉዳይ እንኳ ቸል ብንል ከክፋት በጤናው መስፈርት ደግነት ይሻላል፤ ለዚያውም ምንም አይነት ወጪ የሌለው በቀላሉ መልካም በመናገር ብቻ የሚፈጸም !
አየህ ወዳጄ! ለዚህም ነው ቅዱስ ቁርዓን “መልካም ንግግር ሰደቃ ናት” ያለው፤ ይህም መልካም ንግግር እንደ ትልቅ መጽዋእት በፈጣሪ ዘንድ እንደሚቆጠር የሚያሳይ ነው፤ መልካሙን አስብ፤ ተመኝ ደግሞም አድርግ፤ የአንተንም የወዳጅህንም መንገድ ታቀላለህ። አበቃሁ ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013