አዲስ አበባ፡- ‹‹ከበቀል ስሜት በመውጣት ለሁላችንም የምትበቃ በመቻቻል፣ በመፈቃቀርና በመከባበር የምንኖርባት የጋራ ሀገር መገንባት እንችላለን›› ሲሉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) የፖለቲካና ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ተማም ባቲ ተናገሩ፡፡
አቶ ተማም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ አንዱ ብሔር ይሄ ብሔር ጨቁኖኛል ከሚል የበቀል ስሜት መውጣት ይገባል፡፡ መወያየት መነጋገር ሀሳብን ማንሸራሸር እንጂ ጎራ መለየት አያስፈልግም፡፡ ሁሉም ዜጋ ከራሱ ክልል አልፎ በጋራ በዚህች ሀገር ጉዳይ መነጋገር፣ መወያየትና መምከር ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን ለሁላችንም የምትበቃ በመቻቻል፣ በመፈቃቀርና በመከባበር የምንኖርባት የጋራ ሀገር መገንባት እንችላለን፡፡
‹‹እስከአሁን የሕዝብ ውክልና አግኝቶ ኢትዮጵያን የመራ መንግሥት የለም፡፡ ያለፉት መንግሥታት የበደሉት በደል የትኛውንም ሕዝብ አይወከልም፡፡ ስርዓቱ ነው ያደረገው›› ያሉት አቶ ተማም፤በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን የሚመሩት አካላትም ጥፋት ቢፈጽሙ የትኛውን ብሄር ወክለው አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) በዋነኛነት የኦሮሞን ሕዝብ መብት ለማስከበር ቢታገልምም የሌላውም ከኦሮሞው ጋር የሚኖር ሕዝብ ነጻነቱና መብቱ ሙሉ በሙሉ መከበር አለበት የሚል እምነት አለው ያሉት ኃላፊው፤ ‹‹የኦሮሞን ሕዝብ መብት ስናስከብር የሌላውን ሕዝብ መብት ጎድተን አይደለም፡፡ መሆንም የለበትም፡፡ ለተፈጠሩባት ሁሉ የተመቸች ኢትዮጵያን ነው መፍጠርና መገንባት የምንፈልገው፡፡ ይሄንን የምንፈጥረው እኛ ብቻችንን አይደለም፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አንድ ላይ ሆነው የሚፈጥሯት አዲስ ኢትዮጵያ ነች›› ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ተማም ማብራሪያ፤ ፓርቲያቸው የኢትዮጵያ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይፈልጋል፡፡ ሁሉም መብቱና ነጻነቱ በእኩልነት ተከብሮ የሚኖርባትን ኢትዮጵያን መፍጠርና መገንባት ዓላማው ያደረገ ሲሆን፤ በኦሮሞ ፓርቲነት ስም ሲንቀሳቀስ ይሄንን ዓላማ የሚቀበል ማንኛውም ብሔርና ማንኛውም ሰው የፓርቲው አባል መሆን ይችላል፡፡
-ከኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) የፖለቲካና ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ተማም ባቲ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ በገጽ 11 ይመልከቱ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
ወንድወሰን መኮንን