አዲሱ ገረመው
እግዜር ይይልህ!! ሌላ ምን እላለሁ። ባንተ ባመጣኸው ጣጣ የስንቱ ፊት ተሸፈነ። የኔስ ይሁን አንዴ ፈርዶብኛል። አሁን እስቲ ኢንጆሪ የመሰለ ክንፈር ይሸፈናል? ቆይ ከንፈር ተሸፍኖ ውበት እንዴት ይታያል? ስንት ከንፈር መሰለሽ እኮ ቀለም ሳያገኝ ጦሙን ውሎ ጦሙን ያደረው። እኔ እንኳን ይኸው ከመጋቢት ጀምሮ ከንፈር ካየሁ ስንት ወር ሞላኝ መሰለህ።
እኔን ያሳሰበኝ ፉንጋ ሴቶች ይዋቡባቸው የነበሩ ኮስሞቲክሶች እረፍት ማግኘታቸው አይደለም። እውነቴን ነው! እኔን ያስጨነቀኝ በእስኪኒ ጅንስ የተወጠረውንና በባዶ የተቆነነ ቦርጫቸውን የሚያስኮመኩሙንን አይደለም። እኔን ያስጨነቀኝ በኮሮና ምክንያት የታጉቱ ውበቶች ናቸው።
አንዳንዶቻችን እኮ እጅግ የከንፈር ወዳጆች ነን። ይህንን ልክፍት ለጠላትም አይስጠው። ከንፈር ከመውደድ የተነሳ በጠዋት ስጋ ቤት ገብቶ ለንቦጭ በግንፍሉ ሳይበላ ወደ ሥራ የማይሄድ ሰው ቁጥሩ ትንሽ አይደለም። ምን ዋጋ አለው ኮሮና ስንቱን ከንፈር ከራዳር እይታ ውጭ አደረገብን።
የሥራው ጠባይ ሆኖ ጠዋት ቢሮ ስገባ የለት ጠበኛ አታሳጣኝ ብዬ ነው የምጀምረው። ጠብ ካላጋጠመኝ እንጀራ አላገኝ። ታዲያ የጠበቃ ሥራው ምንድነው። በኮሮና ምክንያት ፍርድ ቤት ተዘግቶ ስለነበር ባዶ ቢሮ ውስጥ ሆኜ እንቅልፍ ሲያንጎላጅጀኝ አንዲት ባለ ጉዳይ ዘው ብላ ገባችና “ምን ልርዳሽ” አልኳት።
“ባሌ አቃጠለኝ ለበለበኝ” ስትለኝ “የለመኑህን የማትረሳ ጌታ እንጀራ ላክልኝ ማለት ነው” ብዬ ቃሏን ለመቀበል እንዲመቸኝ “ማስክሽን አውልቀሽ ድምጽሽን ከፍ አድርገሽ ንገሪኝ” አልኳት፤ ወለቅ ስታደርገው የአንጆሊና ጆሊን ከንፈር የሚያስንቅ የከንፈር እምቡጥ ብቅ ሲል ኤሌክትሪክ እንደያዘው ሰው ድርቅ ብዬ ቀረሁ። እግዜር ይይልህ ኮሮና፤ሌላ ምን እላለሁ።
የከንፈርና ጥርስ ናፍቆት ጉዱ ተዘርዝሮ አያልቅም። በአንዱ ቀን ድንገት አንዲት አንቀጽ ሠላሳ ስንትን ማስቀየር የሚችል ከንፈር ያላት ማስኳን ረስታ ይሁን ሆንብላ ሳታደርግ በአጠገቤ ስታልፍ፤ ክው ብዬ “ጤና ይስጥልኝ ፤የጣዝማ ማር ለመሰለው ከንፈርሽ ሰላምታ ይገባዋል” ብዬ እጅ ለመንሳት ከወገቤ ቀንጠስ ብዬ ሰላምታ አቀረብኩ።
አንዳች አካፋ የሚያህል እግር በካልቾ ከመቀመጫዬ አንስቶ ሰማየ ሰማያት (ግነት አለባት) አድርሶ ሲመልሰኝ ኤርታሌን የሚያህል ቦታ ውስጥ እሞቦጭ ስል አፍንጫዬ ለመተንፈስ አስቸግሮኝ ነፍሴን ለማትረፍ ሲሟገቱ ሆስፒታል ተገኘሁ። ይህ ድርጊት አንድ ነገር አስተምሮኛል። ለቆነጃጅት ሴቶች ሰላምታ ከማቅረቤ በፊት ጸሎት ማድረግ እንዳለብኝ።
የምታምረዋ ጉብል በሰመመን ታየችኝ። በከንፈር እጥረትና በሥራ መጥፋት ስብከነከን በዚሁ አጋጣሚ ኮሮና ሆዬ ድንገት ከች ብሏል ለካ። እግዜር ይይልህ ኮሮና። የሰውነት ሙቀቴን ከመስፈሪያ በላይ አድርጎት፤ ደረቴ ላይ የድንጋይ መቀነት ተቀምጦ ትንፋሽ ሲያጥረኝ አፋፍሰው ወሰዱኝ። የተመደበችልኝ ነርስ ማስክ አድርጋ አይጥ እንደዋጠ እባብ አይኗ ይንከራተታል። ሳስበው ግን ከንፈሯ ቆንጆ ሳይሆን አይቀርም።
ወደኔ ጠጋ ከማለቷ ሀይለኛ ንፋስ በመስኮት በኩል መጥቶ ጸጉሯን በታተነው። ወዲያው ነርሷ ያደረገችውን ታዘብኩና አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ለካ ድሮ ድሮ ሀይለኛ ንፋስ ሲመጣ ሴቶች ቶሎ ብለው ቀሚሳቸውን ይይዙ ነበር፤ አሁን ግን ቶሎ ብለው ፀጉራቸውን እንደሚይዙም ተገነዘብኩ።
ሀኪም ቤት ነርስ ጸጉር ይሸፍን የሚል ፕሮቶኮል አለ እኮ። ጎበዝ ይቺም ተዘንግታ ነበር። እቺው ነርስ ትኩሳቴን ለክታ የምትነግረኝ ነገር አልሰማ ሲለኝ ርቀትሽን ጠብቀሽ ማስክሽን አውልቀሽ ንገሪኝ ብላት ቀልደኛ ብላኝ ሄደች። አስተያየቷ ግን ልቤ ውስጥ አስቀምጬሃለሁ የሚል ቢመስልም እኔ ግን እዚያው እመቀመጫዬ ላይ ነኝ። እግዜር ይይልሽ ቻይና።
ለአፍታ እንቅልፍ ሸለብ አደረገኝና በኮሮና ትኩሳት በእንቅልፌ ሰማየ ሰማያት ድረስ ሄድኩ። ሰውነቴ እንደ ገና ዳቦ በላይና በታች እሳት ይነድበታል። ነርሷ ቆማ ታየኝ ኖሯል ለካ። አየር አጠረኝ ጎበዝ እየሞትኩ ነው እንዴ ኧረ አየር… ወይኔ ጠበቃው ለዚህችው እድሜ ነው ያ ሁሉ ልፋት? “መሸ በከንቱ” አሉ ባህታዊው።
አቤት የሰማይ ቤት መንገድ ማማሩ በእግሬ ስኳትን እያንጎራጎርኩ “ አሁን የኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ እንቡጥ እንቡጥ ያለ ከንፈር አንድ ቀን ሳላይ” የሰማይ ቤት መንገድ፣ “መንገድ ብሎ ዝም” ነው። መቼም ይሄንንም መንገድ የኛዎቹ አይሰሩትም፤
ምን በወጣቸውና ነው እንዲህ አድርገው አሳምረው የሚሰሩት። የኛ መንገድ እኮ የምርቃት እለት የተጎዘጎዘው ሳር ተጠርጎ ሳይነሳ የመንገድ ጥገና ይጀመራል። ደግሞ ከሁሉ የሚገርመው በጋውን ተኝተው ክረምት ሲመጣ ነው መንገድ የሚጠግኑት። እንደው ግን ሬንጅና ውሃ እንዴት ማጠበቅ ተቻላቸው። ቤተ ሙከራ አለን አይደል? በቃ እርሱ መልስ ይስጥበት።
እናም ወደ ጉዳዬ ልመለስ ቻይና የሥራዋን ይስጣትና ኮሮና በሚል ተልካሻ ምክንያት በአካል ሆስፒታል በአይነ ህሊናዬ ደግሞ ተጉዤ የሰማይ ፍርድ ቤት በራፍ ላይ ደረስኩላችሁ። ተመስገን አልኩ፤ ፍርድ ቤት ካለ ዳኛ አለ ማለት ነው። ዳኛ ካለ ደግሞ ጠበቃ ያስፈልጋል ማለት ነው። ጊዜ ማባከን አያስፈልግም። ቶሎ ወደ ሥራ።
በር ላይ አንዱ አሮጌ ክላሰር ይዞ ተቀምጧል። ጠጋ አልኩና ጤና ይስጥልኝ ወዳጄ ብዬ እጅ ሰጠሁት። ቀልጠፍ ብሎ የአስቆሮቱ ይሁዳ ከእስራኤል አንተስ ከወዴት ነህ ሲለኝ ጠበቃ መሆኔን አስቀድሜ በመንገር ከኢትዮጵያ አልኩት።
አቤት የስደት ቀጠሮ ይግባኝ ጠይቄ መልስ እስኪሰጠኝ ስንት ዘመን አለፈ። ኮሮና እስኪያልፍ ጠብቅ ተባልኩ። እኔ ግን በችሎቱም ቦታ ሆኜ በማስክ የተሸፈኑ ውበቶች ይናፍቁኝ ነበር።
ይሄ ማስክ ምንም እንኳን በአጥንት ግንባታ መዘግየት ምክንያት የተወላገዱ ጥርሶችን ከለላ ቢያበጅለትም ጥሩ ከንፈሮችን፣ ሰልካካ አፍንጫዎችን፣ እንደወታደር ሰልፍ የተሰደሩ ጥርሶችን… ውበት መሰወሩ ቅር ያስብላል። ቢሆንም ከጤና አይበልጥምና ይሁን! ኮሮና እግዜር ይይልህ! ሌላ ምን እላለሁ!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2013