ባለፉት ዓመታት በሁሉም የአገሪቱ ጫፎች በርካታ ችግሮች ተከስተዋል። አመጽ ተካሂዷል፤ ንብረት ወድሟል፤ ህይወት ጠፍቷል። ይህንን ተከትሎም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በየአካባቢው ለእስር ተዳርገዋል። የታሰሩት ዜጎች ምንም ያህል ይብዙ እንጂ በመንግስት በኩል የነበረው አንድ መሰረታዊ ጉዳይ የህግ የበላይነት የማስከበር ርምጃ ነበር። ይሁንና ከአመፁ ጋርም ሆነ ከዚያ ውጪ ቀደም ሲል ወጥተው የነበሩ የፀረሽብርና ሌሎች ህጎችንም ተንተርሶ እስከሀገር ክህደት በሚደርስ የወንጀል ክስ የተጠረጠሩ፤ የተከሰሱ፤ የተፈረደባቸውና በወህኒ የነበሩ ዜጎች ቁጥርም ቀላል አልነበረም።
በተለይም በ2009/10 ዓ.ም በአገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ በተደነገጉት ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ምክንያት በወንጀል ተሳትፋችኋል የተባሉ በርካቶች ይበልጡኑ ወጣቶች ለዕስር ተዳርገዋል።
በአገሪቱ በ2010 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሂደቱ ከፍተኛ ችግር የታየበት፤ አመጹ ብዙ አካባቢ የሸፈነበት፤ ዕስሩ፤ እንግልቱና ግጭቱ የበረታበት ሲሆን በውጤቱም የሀገሪቱን መሪ ከመንበሩ በገዛ ፈቃድ እስኪነሱ የሚያደርስ አንድምታም ነበረው። ይህንን ተከትሎም አዲስ የለውጥ መንፈስ ያነገበ አመራር መንበሩን በመጋቢት ወር ላይ ተረከበ። አዲሱ አመራርም በአገሪቱ ሰላምን ያሰፍናሉ፤ ህዝቡን ወደአንድነት ያመጣሉ፤ በየአካባቢው የተነሳውን አመፅ ያስቆማሉ ያላቸውን ውሳኔዎች አሳለፈ። ከነዚህም መካከል የይቅርታና የምህረት ጉዳይ ነው። በዚህም አዋጅ ቁጥር 1088/2010 የምህረት አሰጣጥና አፈፃፀም ስነስርዓትና በመቀጠልም በአዋጅ ቁጥር 1089/2010 የምህረት አዋጅ ወጥቶ እንዲጸድቅ አደረገ። ይህም አዋጅ ከሐምሌ 13/2010 እስከ ጥር 2011 በሚቆይ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ፤ ስራ የለቀቁ አመፅ ያስነሱ ተብለው የታሰሩ፤ ሲፈለጉ የነበሩ ሰዎች ምህረት እንዲደረግላቸው የፌዴራል የይቅርታና የምህረት ቦርድ ተቋቁሞ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል።
በዚህ የምህረት አዋጅ በሀገር ክህደት ተወንጅለው የነበሩ የመከላከያ አባላት እንዲሁም በሽብር ህጉ ተከስሰው የተፈረደባቸውና በክስ ላይ የነበሩ ሁሉ ምህረት እንዲደረግላቸው ተወስኗል። በዚህ ለስድስት ወራት በቆየው የምህረትና የይቅርታ ጊዜም ከ13 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ምህረት ተደርጎላቸው የምህረት የምስክር ወረቀት እንደወሰዱ የጊዜ ገደቡ ማብቃቱን አስመልክቶ ቦርዱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። እነዚሀ ምህረት የተደረገላቸውና የተለቀቁ ዜጎች ዛሬ የሰላም አየር እየተነፈሱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለው አዲስ ህይወት ለመምራት ተዘጋጅተዋል።
አዎን፤ በምህረት አዋጁ ተጠቃሚ ሆነው የተፈቱ ዜጎች ወይም አጠቃላይ የምህረት አዋጁ በውጤቱ ተፈቺዎችንና ቤተሰቦችን ያስደሰተና በህግ የበላይነት አከባበር ላይ እስከ ዛሬ ያልታየ እምርታ ያመጣ ነው ማለት ይቻላል። በዚህም መንግስት አስቀድሞ የገባውን ቃል ማክበሩን ያሳየበት ነውና የሚደነቅ ተግባር ነው። በቀጣይም በጉብዝናቸው ዘመን በትንንሽ ግጭቶች፤ በይቅርታ ሊታለፉ በሚችሉ ጥፋቶች ለወህኒ የተዳረጉ ዜጎችን እያስተማሩና እየመከሩ ወደ መደበኛ ማህበራዊ ህይወት እንዲቀላቀሉ የማድረጉ ተግባር ሊቀጥል ይገባል።
በአጠቃላይ መንግስት ያወጣውና ተግባራዊ ያደረገው ይህ የምህረት አዋጅ ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል። ውጤታማነቱ ግን በተቀመጠለት ዓላማና ዓላማውን ተከትሎም ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለሱ ከተደረጉ ዜጎች ከእስር ከተፈቱ በኋላ በአዋጁ ላይ ያልተዳሰሱ፤ ምናልባትም ከአዋጁ መንፈስ ውጪ የሆኑ ወይም በቀጣይ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ተከስተዋል። ለረጅም ጊዜ በወህኒና በእስር የቆዩ ዜጎች በዚህ የምህረት አዋጅ ተጠቅመው ሲለቀቁ የመደሰታቸውን ያህል፤ ወደውጪው ዓለም ሲቀላቀሉ የሚሄዱበት ግራ የገባቸው፤ ምን እንደሚሰሩ የተደናገሩ ብዙዎቸ ናቸውና አዲስ ጥያቄ አጭሯል። እነዚህን ዜጎች መልሶ የማቋቋሙና ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረጉ ተግባር ሊታሰብበት ይገባል እንላለን።
በርግጥም በምህረት አዋጁም ሆነ በሌሎች የይቅርታ መንገዶች ከእስር የተፈቱ ዜጎችን በእግራቸው እንዲቆሙ የማድረጉ ተግባር የቦርዱ ኃላፊነት አይደለም፤ ግን ደግሞ የመንግስት ነው። እናም መንግስት በፍጥነት አስቦ መፍትሔ ቢያዘጋጅ መልካም ይሆናል። በቦርዱ ኃላፊ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ምህረት አግኝተው ከተፈቱት ዜጎች መካከል ለበርካታ ዓመታት በወህኒ የቆዩ፤ አሁን ካለው የከተማ ማህበራዊ ህይወት በእጅጉ የራቁ እንዳሉ ተገልጿል።
እነዚህን ዜጎች በምህረት መለቀቃቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀው እንዴት ብለው ወደ ማህበረሰቡ እንደሚቀላቀሉ መቸገራቸውን ሲናገሩ በእጅጉ ያሳዝናሉ። እናም በዚህ ረገድ ያልተሰራ አንድ መሰረታዊ የቤት ስራ መኖሩን ያመለክታል። አዎን በምህረት የተፈቱ ታራሚዎች እንዴት ወደማህበረሰቡ ይቀላቀላሉ? ከባድ ጥያቄ ነው፤ መልሱም ከባድ ነው። ነገር ግን ከመንግስት እና ከህዝብ አቅም በላይ አይሆንም።
በመሆኑም እነዚህን ዜጎች መልሶ የማቋቋሙና ወደማህበረሰቡ የማቀላቀል ተግባር በምህረት አዋጁ ላይ ባይኖርም ችግሩ በመከሰቱ ግን ቸል ሊባል አይገባምና መንግስት መላ ሊያበጅለት ይገባል እንላለን። ከፌዴራል መንግስት በተጨማሪም እነዚህ ወገኖች የሚገኙባቸው ክልሎች መንግስታት ችግሩን ለመፍታት የበኩላቸውን ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ህዝቡም ዜጎች ከእስር ሲፈቱ ደስ ያለውንና መንግስትን ያመሰገነውን ያህል፤ ተገልለው ከነበሩበት ሲወጡ አዲሱን ማህበራዊ ህይወት ተቀላቅለው ኑሯቸውን በአግባቡ እንዲመሩ፤ አምራች ዜጎች ሆነው ቤተሰብ አፍርተውና መርተው እንዲኖሩ በማድረግ በኩል ሊያቅፋቸው፤ ሊደግፋቸውና ሊያቋቁሟቸው ይገባል እንላለን።