ሶሎሞን በየነ
ወደ 70ዎቹ የእድሜ ክልል የሚጠጉት አባት በደረሰባቸው በደል ልባቸው ተሰብሮ ከአንደበታቸው ቃላት ለማውጣት ሲቃ እየተናነቃቸው፤ በነገር ተጠብሶ አጋም በመሰለው ፊታቸው ላይ ከአይናቸው እንደ ሐምሌ በረዶ የሚወርደውን እምባ በእጃቸው የያዙት ሶፍት አልበቃቸው ብሎ እንደ ሕፃን ልጅ በጨርቃቸው እየጠረጉ የተፈጸመባቸውን ግፍና በደል ሲናገሩ አይደለም የሰውን ልጅ ይቅርና የአራዊትን ሆድ ያባባሉ።
እኚህ አባት ሥማቸው አቶ አፈወርቅ ክብረት ይባላል። ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በቱሉ ቦሎ ከተማ አባመቻል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ፤ ለጥበብና ለሥራ በነበራቸው ልዩ ፍቅር በለጋ ዕድሜያቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ እንጨት ሥራ ሙያ መግባታቸውን ይናገራሉ።
አቶ አፈወርቅ ወደ ሙያው ከገቡ በኋላም በአጭር ጊዜ በሙያው እንደተካኑበት ጠቁመው፤ ገና የ17 ዓመት ልጅ እያሉ በ1960 ዓ.ም ከ33 ተወዳዳሪዎች አንደኛ ወጥተው በፖሊስ መሃንዲስ መምሪያ በእንጨት ሥራ ባለሙያነት አስመራ ከተማ ይመደባሉ። አስመራ ከተማ በሥራ ላይ እያሉ ወይዘሮ ብርዛፍ ክንዴ የተባሉ የትግራይ ተወላጅ ጋር ተዋውቀው ትውውቃቸው ወደ ፍቅር አድጎ ለሦስት ጉልቻ መብቃቱን ይናገራሉ።
አስመራ ከተማ ላይ በአማረ ሰርግ የተጀመረው ትዳራቸው በልጅ ተባርኮ በፍቅርና በደስታ ስድስት ዓመታትን እዛው ከኖሩ በኋላ፤ አቶ አፈወርቅ ወደ ትውልድ ቀያቸው አዲስ አበባ ለመመለስ በነበራቸው ጉጉት በተደጋጋሚ ዝውውር ሲሞሉ ስለነበር ፍላጎታቸው ሰምሮ በ1966 ዓ.ም ጃንሆይ ከስልጣን በተወገዱ በሦስተኛው ቀን ዝውውር አግኝተው ከባለቤታቸው ጋር ወደ ትውልድ ቀያቸው መመለሳቸውን ይናገራሉ።
አቶ አፈወርቅ አዲስ አበባ ተመልሰው በፖሊስ መሃንዲስ መምሪያ ሥራቸውን ቀጠሉ። አስመራ በነበሩበት ወቅት መንግሥት ቤት ሰጥቷቸው ሲኖሩ ስለነበርና የቤተሰባቸው ቁጥር ትንሽ ስለነበር ጥሩ ሕይወት ይኖሩ ነበር፤ ነገር ግን አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ አስመራ ከወለዱት ከበህር ልጃቸው በተጨማሪ ሌሎች ልጆች ማፍራታቸውን ተከትሎ በወር ሳይጣራ የሚከፈላቸው 244 ብር የወር ደሞወዝ ከቀለብና ከልጆች ልብስ አልፎ በወር 18 ብር የቀበሌ ቤት ኪራይ መክፈል ተስኗቸው ሕይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ይናገራሉ።
ጌጃ ሰፈር አብነት ሆቴል አካባቢ በወር 18 ብር የቀበሌ ቤት ተከራይተው የቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸው የአንድ ዓመት ከሦስት ወር የቤት ኪራይ እዳ ውስጥ ገብተው ቀበሌ ከዛሬ ነገ ያባርረኛል እያሉ በጣም ሲጨነቁና ሲሰጉ እንደነበር አቶ አፈወርቅ አውስተው፤ በጥቅሉ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ የቤተሰብ አባል ማብዛታቸውን ተከትሎ የወር ገቢያቸው አይደለም የቤት ኪራይ ከፍሎ ለመኖር ይቅርና በልቶ ለማደር የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሶ የመላ ቤተሰቡ ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ይናገራሉ።
አቶ አፈወርቅ በልቶ ማደር ሲያዳግታቸውና አማራጭ ሲያጡ በፖሊስ መሃንዲስ መምሪያ በእንጨት ሥራ ባለሙያነት ይሰሩበት የነበረውን ሥራ ለቀው በወቅቱ ከህንድ አገር ይገባ የነበር የሴት ነጠላ ጫማ አይተው፤ ለምን ይህን ጫማ ተመራምሬ በአገር ውስጥ አልሰራውም ብለው ተመራምረው ይህን ጫም ከወር ደሞዛቸው 60 ብር አንስተው ቀሪውን ለባለቤታቸው ለአስቤዛ ሰጥተው መስራት እንደጀመሩ ይናገራሉ።
ነገር ግን ሁሌም አንድ ሰው የፈጠራ ሥራ ይዞ ወደ ሥራ ሲገባ ፈተና አያጣውምና ከባለቤታቸው ዘንድ ሥራህን ለቀህ ቁጭ ያልከው ጫማ ለመስራት ነው እንዴ የሚል ክስና ወቀሳ ከፍ ሲልም አምባጓሮ ድረስ መድረሳቸውን የሚናገሩት አቶ አፈወርቅ፤ ባለቤታቸው ቤት ውስጥ ጫማ አትሰራም ብለው ሲከለክሏቸው ኩሽና ውስጥ ሥራውን መስራት እንደጀመሩ ጠቁመው፤ በተፈጥሯቸው የጥበብ ሰው በመሆናቸው ከህንድ አገር ይገባ የነበረውን የሴት ነጠላ ጫማ በአገር ውስጥ አስመስሎ መስራት ብቻ ሳይሆን በበለጠ ጥራት ባለው መንገድ አሳምረው መስራት መቻላቸውን ይናገራሉ።
አቶ አፈወርቅ ሥራውን ሲጀምሩ ጥሬ ዕቃ የት እንደሚገኝ እንኳን እንደማያውቁና ሰው ጠይቀው ሸራ ተራ የሚባል ቦታ ሂደው ጥሬ ዕቃውን ገዝተው መስራት እንደጀመሩ ጠቁመው፤ በ60 ብር ካፒታል ኩሽና ውስጥ የተጀመረው ምርት ከህንዱ ምርት በልጦ በመገኘቱ ነጋዴው የህንዱን ጫማ በ27 ብር ሲረከብ የእርሳቸውን ምርት ግን በ37 ብር ማስረከብ መጀመራቸውን ይናገራሉ።
ነገሩ የሚታመን ነገር አይደለም። የኋላ ኋላ የእርሳቸው ምርት የህንድ (የውጭ)፣ የህንዱ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርት እየተባለ ሲሸጥ እንደነበር አቶ አፈወርቅ አውስተው፤ ጥሬ ዕቃውን መርካቶ እየገዙ ከህንዱ ምርት በላይ 10 ብር ጨምረው በመሸጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ትርፍ ከመሸጋገር ባለፈ በጣም ባለሀብት ለመሆን መብቃታቸውን ይናገራሉ።
በወር 18 ብር የቀበሌ ቤት የቤት ኪራይ ከፍሎና በልቶ ለማደር ተቸግረው ከነበረ አስቀያሚ ሕይወት ውስጥ ወጥተው የአንድ ዓመት የሦስት ወር ውዝፍ የቤት ኪራይ ከፍለውና ቤታቸውን አሸንፈው ከማደር ባሻገር ሀብት አፍርተው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ደሳለኝ ሆቴል አካባቢ ወደ 700 ካሬ ሜትር የሚጠጋ ላዩ ላይ ቤት ያለበት ቦታ በ1982 ዓ.ም ገዝተው ከ18 ብር የቀበሌ የቤት ኪራይ ወጥተው የራሳቸውን ቤት ሰርተው መግባታቸውን ይናገራሉ።
አቶ አፈወርቅ የተለያዩ የፈጠራ ሥራ በመስራት አፍሪካ ውስጥ ልዩ ሆነው የመታየት ህልም እንደነበራቸው ጠቁመው፤ ከ18 ብር የቀበሌ ቤት የቤት ኪራይ ወጥተው በ1985 ዓ.ም ቦሌ በገዙት ቦታ ላይ የሰርቪስ ቤት ሰርተው በራሳቸው ቤት መኖር ከጀመሩ በኋላ የጫማውን ሥራ ወደ ጎን ብለው ወደ ልጅነት የእንጨት ሥራ ሙያቸው ተመልሰው በግላቸው መስራት እንደጀመሩ ይናገራሉ።
የእንጨት ሥራውን በግላቸው መስራት ከጀመሩ በኋላ ጥሩ ትርፍ በማግኘታቸው አቃቂ ቃሊቲ ቦታ ገዝተው ኒያላ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ የተሰኘ ድርጅት ማቋቋማቸውን አቶ አፈወርቅ ገልጸው፤ ሁለት ባለ አራት ወለል ሕንፃና አንድ ባለ አንድ ወለል ሰፊ ወርክ ሾፕ (የመስሪያና የመገጣጠሚያ ሕንፃ) ሰርተው እንደዛሬ የእንጨት ሥራ ድርጅቶች ሳይበራከቱ አንቱታን ያተረፉና ጥራት ያላቸው የእንጨት ሥራ ምርቶችን ለኅብረተሰቡ ከማቅረብ ባሻገር ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ይናገራሉ።
ነገር ግን ከልጅነት እስከእውቀት ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩትን ቤትና ንብረት የስድስት ልጆቻቸው የልጅ እናትና ባለቤታቸው ወይዘሮ ብርዛፍ ባለጊዜነታቸውንና ወገኖቻቸውን ተመክተው ቤትና ንብረታቸውን ቀምተው እንደ ቆሻሻ ዕቃ እራቁታቸውን ከቤት አውጥተው ሜዳ ላይ እንደጣሏቸው አቶ አፈወርቅ እያለቀሱ ይናገራሉ።
የቅሬታ አቅራቢው ዝርዝር አቤቱታ
እንደአገር መከላከያ ሰራዊት ከጀርባዬ ስድስት ልጆች በወለደችልኝ በባለቤቴ እና ከፊት ለፊቴ ደግሞ ፍትህን በብሔር በሚሰጡ ፈርያ እግዚአብሔር በሌላቸው አረመኔዎች የደማሁነኝ የሚሉት አቶ አፈወርቅ፤ የ18 ብር የቀበሌ ቤት የቤት ኪራይ ከፍሎና በልቶ ለማደር ተቸግረው ከነበረ አስቀያሚ ሕይወት ወጥተው ቦሌ ቦታ ገዝተው ቤት ሰርተው ከገቡና የአቃቂ ቃሊቲውን ድርጅት ካቋቋሙ በኋላ ባለቤታቸው የቦሌውን ቤትና የአቃቂ ቃሊቲውን ድርጅት ሁሉንም በስሟ አድርገው ፈርመው እንዲያስረክቧቸው መጠየቃቸውን ይናገራሉ።
ባለቤታቸው በስሜ አዙርልኝ ስትላቸው ለምን ቤት ሙሉ ልጅ ወልደን ንብረቱ በአንቺ ስም ሆነ በኔስም ልዩነቱ ምንድ ነው የሚል ጥያቄ ቅሬታ አቅራቢው ሲያነሱ፤ በቃ በስሜ እንዲዞር እፈልገዋለሁ የሚል መልስ ባለቤታቸው መስጠታቸውንና ጉዳዩ ወደ ጭቅጭቅ ማምራቱን ይናገራሉ።
በዚህ ጉዳይ ቤት ውስጥ ጭቅጭቅ ሲፈጠር አንድ ትልቅ ሽማግሌ ሰው የአቶ መለስ ዜናዊ (የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር) አጎትነኝ የሚል አቶ ኃይሌ መከታና ሻለቃ ኪዳኔ ኪሮስ የሚባል ጦር ሰራዊት አባል መጥተው ‹‹ንብረቱን በስሜ አዙርልኝ ብላ ጠይቃሃለች ለምንድ ነው የማታዞርላት›› የሚል ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው አቶ አፈወርቅ ገልጸው፤ «እኔ እና እርሷ ልጆች ወልደን ከልጅነት ጀምሮ አብረን ያፈራነው ንብረት ነው።
ለምንድ ነው በእርሷ ስም የማዞረው? በኔም ሆነ በእርሷ ስም ምንድ ነው ልዩነቱ? አላደርገውም» የሚል መልስ ሲሰጡ የመለስ ዜናዊ አጎት ነኝ የሚሉት አቶ ኃይሌ መከታ የተባሉት ግለሰብ «አንድ ነገር እነግርሃለሁ መኖር ትፈልጋለህ አትፈልግም? ይቺን ነው በአጭሩ የምጠይቅህ” እንዳሏቸው እያለቀሱ ይናገራሉ።
«እነርሱ የሚሉኝ ነገርና እኔ የያዝኩት አቋም እንደማያዋጣኝ ተረዳሁት» የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ አላደርገውም ቢሉ ከመሞት ውጪ የትም ቢሄዱ ሰሚ እንደሌላቸው በአዕምሯቸው አውጥተው አውርደው «ቢገድሉኝ ከልካይ ስለሌላቸው መጥፎ ነገር ከሚደርስብኝ ቤቱን ባስረክብ ይሻለኛል» ብለው ለመጡት ሰዎች እሺ ንብረቴን በባለቤቴ ስም አዞራለሁ ብለው እንደተስማሙ ይናገራሉ።
የመጡት ሰዎችም የቦሌውን ቤት ፈርመህ የምታስረክበው ውልና ማስረጃ ሲሆን ድርጅቱን ደግሞ የምታስረክበው ድርጅት ስለሆነ ቦሌ የአገር ውስጥ ገቢ ነው ብለዋቸው፤ የቦሌውን ቤት ውልና ማስረጃ ሐምሌ 27 ቀን 1993 ዓ.ም ቀርበው በቀድሞው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17 ቀበሌ 19 የቤት ቁጥር 731 በካርታ ቁጥር 8719 የተመዘገበ ከባለቤታቸው ጋር ያፈሩትን ቤት ለባለቤታቸው ለወይዘሮ ብርዛፍ ተገደው ድርሻቸውን እንዲያስተላልፉ መደረጋቸውን ይናገራሉ።
የቦሌውን ቤት በባለቤታቸው ስም ካዞሩ ከሳምንት በኋላ ደግሞ ሻለቃ ኪዳኔ ኪሮስ የተባሉት ግለሰብ ድርጅቱ አገር ውስጥ ገቢ ስለሆነ ስም የሚዞረው በወቅቱ የአገር ውስጥ ገቢ መስሪያቤት ኃላፊ ከነበሩት ከአቶ ብርሃኑ ሃልፎም የሚባሉ ግለሰብ ጋር ካስተዋወቁዋቸው በኋላ እርሳቸው ቢሮ ዘንድ ቀርበው እንዲያስተላልፉ እንዳግባቧቸው ቅሬታ አቅራቢው ጠቁመው፤ ከአቶ ብርሃኑ ሃልፎም ከሚባሉት ግለሰብ ጋር በተዋወቁ በማግስቱ ከባለቤታቸው ጋር ቦሌ አገር ውስጥ ገቢ ሄደው እርሳቸውን ቢሯቸው አግኝተዋቸው ድርጅቱን በባለቤታቸው ስም ለማዞር የንግድ ፈቃዳቸውን ቁጥር ሰጥተው ድርጅቱ የእርሳቸው መሆኑና ምንም እዳ እንዲሁም ችግር የሌለበት መሆኑን ኃላፊው ካረጋገጡ በኋላ በባለቤትዎ ስም ለማዘዋወር ምንም ችግር የለም። ነገር ግን አሁን የዓመቱ አጋማሽ ስላለፈ አሁን ላይ የስም ዝውውር መፈጸም አይቻልም። በሚመጣው መስከረም ወይም ጥቅምት ግብር ገብራቹህ ክሊራንሱን ይዛችሁ ኑና ወዲያውኑ በባለቤትዎ ስም ይዞራል ብለዋቸው ለመጪው መስከረምና ጥቅምት ቀጠሮ ይዘው ከኃላፊው ጋር መለያየታቸውን ያወሳሉ።
አቶ አፈወርቅ በመስከረምና ጥቅምት ድርጅቱን በባለቤታቸው ስም ለማዞር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ውሎ አድሮ ድርጅቱን በባለቤታቸው ስም የማስተላለፉ ጉዳይ ተረሳስቶ አንድ ላይ እየኖሩ እያለ በ2002 ዓ.ም ድንገት ምሽት ሁለት ሰዓት የቤት ልብሳቸውን ለብሰው ሳሎን ቁጭ ብለው ዜና እየተከታተሉ ባለበት ወቅት ባለቤታቸው ከዛሬ ጀምሮ እዚህ ቤት ማደር ስለማትችል ውጣ እንዳለቻቸው ገልጸው፤ «ውጣ ስትላቸው አሁን እኮ መሽቷል እንዴት አሁን ውጣ ትይኛለሽ ሲሏት የተደጋገመ ቃላት አልፈልግም ውጣ ውጣ ነው ስትላቸው ባይሆን ብርድ ስለሆነ ኮቴን ከመኝታ ቤት ላውጣ ሲሏት የምን ኮት ነው» ብላ በቤት ልብስ በምሽት እንዳስወጣቻቸው ከአይናቸው እንደ ምንጭ የሚፈሰውን እንባቸውን በኮታቸው እንደ ህጻን ልጅ እየጠረጉ ቅሬታ አቅራቢው ይናገራሉ።
በዛ ጨለማ ወጥተው ከእህታቸው ቤት አድረው በበነገታው ሽማግሌ ይዘው ምን አጥፍቼ ነው ብለው መጠየቃቸውን የሚናገሩት አቶ አፈወርቅ፤ ሽማግሌዎች ተሰብስበው የግራቀኙን ችግር አድምጠው እርሳቸው እንደተበደሉ ፈርደው ባለቤታቸውን ገስጸው በሉ ተስማምታችሁ ልጆቻችሁን በጋራ አሳድጉ ብለው ቢፈርዱም ባለቤታቸው የሽማግሌዎቹን ውሳኔና ምክር አልቀበልም ማለታቸውን ይናገራሉ።
ባለቤታቸው ሽማግሌዎቹን እረግጠው ፍርድ ቤት ሂደው የጋብቻ ውላችን እንዲፈርስልኝ እፈልጋለሁ ብለው ጥያቄ ማቅረባቸውን አቶ አፈወርቅ ጠቁመው፤ ጋብቻው በህግ ቢፈርስም ነገር ግን ከቤት ሲወጡ አንዲት ወረቀት ሳያንጠለጥሉ የሕይወት ታሪክ ሰነዳቸውና ሌላው ቀርቶ ልብሳቸውን ሳይዙ እራቁታቸውን እንደወጡ ገልጸው፤ በስማቸው የተመዘገበ ሽጉጥ እቤት ትተው ስለወጡ ንብረትነቱ ይጠቅመኛል ብለው ሳይሆን ወንጀል ይሰራበትና እዳ ይከቱኛል ብለው ፖሊስ ጣቢያ ሂደው «ባለቤቴ ከቤት ስላባረረችኝ በስሜ የተመዘገበ ሽጉጥ እቤት ትቼ ወጥቻለሁ እስከዛ ወንጀል እንዳይሰራበት
ተመዝግቦ ይቀመጥልኝ» ብለው አመልክተው ፖሊስ ጣቢያውም አቤቱታውን ተቀብሎ ለባለቤታቸው መጥሪያ ከሰጠ በኋላ ከበላይ አካል እንዳታጣሩ እንዲያውም የመዘገባችሁትን መዝገብ ሁሉ አጥፉ ተብለን መዝገቡ እንዲሰረዝ ተደርጓል የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውና በእርሳቸው ስም የተመዘገበን ሽጉጥ በሕገወጥ መንገድ ባለቤታቸው እስካሁን ድረስ ታጥቃው እንደሚገኙ ይናገራሉ።
ይህም በእርሳቸውና በባለቤታቸው ዜግነት መካከል ያለውን ልዩነት አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ ጋብቻው በህግ ፈርሶ የንብረት ክርክር ሲደረግ የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዲስ ተሻሽሎ በወጣው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 73 መሰረት ባል ለሚስቱ ወይም ሚስት ለባሏ ከ500 ብር በላይ በስጦታ መስጠት ስለማይቻል/ ስለማትችል ውልና ማስረጃ ቀርበው ለባለቤታቸው በስጦታ የሰጡት የቦሌው ቤትና ለቤቱ የግንባታ ማስጨረሻ ከኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ የተበደሩት ብድር የጋራ ነው ብሎ ሐምሌ 18 ቀን 2003 ዓ.ም እንደወሰነላቸው ይናገራሉ።
አቶ አፈወርቅ ሐምሌ 19 ቀን 1993 ዓ.ም በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት በቁጥር 73/7/93 የቦሌውን ቤት ለባለቤታቸው በስጦታ ካዘዋወሩ በኋላ የነበረውን ሰርቪስ ቤት አፍርሰው ባለሁለት ወለል ዘመናዊ ሕንፃ ሲሰሩ ለግንባታ ማስጨረሻ ከኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ 798ሺ 116 ብር በሁለታቸው ስም ተስማምተው ተበድረው ሕንፃውን ካስጨረሱ በኋላ ኅዳር 22 ቀን 1999 ዓ.ም ሕንፃውን ለናሚቢያ ኤምባሲ አከራይተው እነርሱ ተከራይተው ይኖሩ እንደነበር ጠቁመው፤ ነገር ግን ነገ ከነገወዲያ ባለቤታቸው እንደምታባርራቸው በልቧ ታውቅ ስለነበረ እና ሲለያዩ ቤቱን ይካፈላል ብላ ስላሰበች እርሳቸው ሳያውቁ ቤቱ በባንክ እዳ ተይዞ ባለበት ወቅት ያለምንም ማስረጃ ለእናታቸው ወይዘሮ ኪሮስ ቀለታይ ኅዳር 19 ቀን 1999 ዓ.ም ውልና ማስረጃ ቀርበው በስጦታ ቤቱን ማስተላለፋቸውን ይናገራሉ።
አቶ አፈወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጠቅላላ የቤቱ ሰነድ ማስረጃ በዋስትና በባንክ መያዙ በሕግ እየታወቀ ሰነድ በሌለበት ቤቱን ለእናቷ ከማስተላለፏ ባሻገር አዲስ ተሻሽሎ በወጣው የቤተሰብ ህግ መሰረት በስጦታ የተሰጠው በፍርድ ቤት ቀርቦ ያልጸደቀ በመሆኑ፤ ለእራሷ ሳይጸድቅ ለሦስተኛ ወገን የምታስተላልፍበት እንዲሁም ቤቱን ለመስራት ምንም ወጪ ሳያወጡ ቤቱ በወይዘሮ ኪሮስ ስም የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ስለዚህ ቤቱን ጨምሮ በጋራ ያፈሩት ንብረት የጋራ ነው በሚል ባለቤታቸው ላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያስተላልፋል። የፍርድ ቤቱ ውሳኔን የተመለከቱት ባለበቤታቸው ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለታቸውን ይናገራሉ።
ጠቅላላ የቤቱ ሰነድ ማስረጃ በዋስትና በባንክ መያዙ በህግ እየታወቀ ሰነድ በሌለበት ውልና ማስረጃ ቀርበው ለእናታቸው የሥጦታ ውል መዋዋል መቻላቸው ወይዘሮ ብርዛፍ ምን ያህል በወቅቱ በወገኖቻቸው ተመክተው የፍትህ ሥርዓቱን ያሾሩት እንደነበር በግልጽ የሚያሳይ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ ከባለቤታቸው ጋር በጋራ ከቢዝነስና ኮንስትራክሽን ባንክ ተበድረው ሕንፃውን ሰርተው ኅዳር 22 ቀን 1999 ዓ.ም ለናሚቢያ ኤምባሲ እንዳከራዩ በመረጃ አስደግፈው ቢያቀርቡም የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ጽጌ ሃዋዝ በመረጃ ሳይሆን ብሔርን መሰረት አድርገው ወይዘሮ ኪሮስ ቀለታ ከልጃቸው በስጦታ ኅዳር 19 ቀን 1999 ዓ.ም ሰርቪስ ቤት ተረክበው ሰርቪስ ቤቱን አፍርሰው በርካታ ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገው ዘመናዊ ሕንፃ ስለሰሩበት ቤቱ ለባለቤታቸው እናት ይገባል በሚል መፍረዳቸውን ይናገራሉ።
አቶ አፈወርቅ ቤቱን ከባለቤታቸው ጋር ከባንክ ገንዘብ ተበድረው ሰርተው ኅዳር 22 ቀን 1999 ዓ.ም ለናሚቢያ ኤምባሲ ያከራዩበት ውልና ግብር የሚከፍሉበት ደረሰኝ እንዲሁም ከባንክ የተበደሩበት ህጋዊ ማስረጃ እያለ ወይዘሮ ኪሮስ ኅዳር 19 ቀን 1999 ዓ.ም ከልጃቸው በስጦታ ሰርቢስ ቤት ተቀብለው በርካታ ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገው ባለሁለት ወለል ዘመናዊ ሕንፃ በሦስት ቀን ውስጥ ሰርተውበታል ብሎ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው ፍርድ እውነት በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት ህግ እንዳልነበር ማሳያ ነው ብለዋል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጠቅላላ የቤቱ ሰነድ ማስረጃ በዋስትና በባንክ መያዙ በሕግ እየታወቀ ቤቱን ለሦስተኛ ወገን ይገባዋል ብሎ መፍረዱ የፍትህ ሥርዓቱ ምን ያህል ለአንድወገን ያደላ እንደነበር ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ እርሳቸውም የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ተቃውመው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለታቸውን ጠቁመው፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባል ለሚስቱ ወይም ሚስት ለባሏ የምትሰጠው ስጦታ ፍርድ ቤት ቀርቦ እስካልጸደቀ ድረስ ተቀባይነት የለውም። ቤቱ የወይዘሮ ኪሮስ ቢሆን ኖሮ ለቤቱ ግንባታ ባንክ ሄደው በተበደሩበት ነበር። ነገር ግን ባልና ሚስት በጋራ ተበድረው ቤቱን እንደገነቡት እየታወቀ ወይዘሮ ኪሮስ ለግንባታ ምንም ወጪ ሳያወጡና በስማቸው ውሃ፣ መብራት ወዘተ ሳያስገቡ የእርሳቸው ነው ብሎ መፍረድ ትክልል አይደለም ብሎ ተችቶ ክርክር የተነሳበት ንብረት የባልና የሚስት ነው ሲል ጥቅምት 7 ቀን 2005 ዓ.ም መወሰኑን ይናገራሉ።
ባለቤታቸውም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አሻፈረኝ ብለው ለሰበር ይግባኝ ማለታቸውን ቅሬታ አቅራቢው ገልጸው፤ ሰበር የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመሻር የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማጽናት ቤቱ ለባለቤታቸው እናት ለወይዘሮ ኪሮስ ይገባል ሲል ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም እንደፈረደባቸው ይናገራሉ።
አቶ አፈወርቅ ላባቸውን ጠብ አድርገው የሰሩትን ቤትና ንብረት ባለቤታቸው በወገናቸው ተምክተው ፍርድን እንዳሻቸው እያስቀለበሱ በሃሰት ንብረታቸውን እንደቀሟቸው ይናገራሉ። ‹‹ ሰበር ፍርድ ቤቱ ንብረቱ አይገባህም ብሎ ከፈረደብኝ በኋላ በፍርድ አፈጻጸም ወቅት ባለቤታቸው የፍርድ አፈጻጸም እንዳይጓተት በማሰብ ከኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በጋራ ከተበደርነው ገንዘብ ውስጥ ቀሪውን 220 ሺ 144 ብር ሙሉ ለሙሉ በአንድ ጊዜ በግሌ ስለከፈልሁ የፍርድ ባለዳው የጋራ የነበረውን ዕዳችንን በድርሻቸው ግማሹን (110 ሺ ብር) ሊጋሩ ስለሚገባ ፍርድ ቤቱ የፍርድ ባለዳውን የዕዳ ድርሻ በአፈጻጸሙ ከሚካፈሉት የጋራ ንብረት እንዲያወራርዱልኝ ወይም ከፍርድ ባለዕዳው የንብረት ድርሻ ላይ ተቀናሽ ተደርጎ ለፍርድ ባለመብት እንዲሰጠኝ ተጨማሪ ትዕዛዝ እንዲሰጠልኝ ስትል ለፍርድ አፈጻጸም ፍርድ ቤቱ መክሰሷ ማሳያ ነው። ፍርድ ቤቱም ቤቱን ለመስራት በጋራ አልተበደሩም እንዲሁም የተበደርነውን እዳ በጋራ እንክፈል ብዬ ስጠይቅ ፍርድ ቤቱ ንብረቱ አይገባህም የሚል ምላሽም ሰጥቷል።
በተቃራኒው ደግሞ በአንድ በኩል ቤቱ የአንተ አይደለም በሌላ በኩል በቤቱ የተበደርከውን ዕዳ ክፈል የሚል ክስ ማቅረቡ ምን ያህል የፍርድ ሥርዓቱ ብሔርን መሠረት ተደርጎ የሃሰት ፍርድ ይሰጥ እንደነበር ከዚህ በላይ ማሳያ የለም›› ብለዋል።
በአጠቃላይ በፍትህ ሥርዓቱ በብሔራቸው ዝቅ ተደርገው ይታዩ እንደነበርና ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ጭምር በብሄራቸው ከሰው እንደተፈጠሩ አድርገው እንደማይቆጥሯቸው እንዲሁም ያለ አግባብ ከልጅነት እስከ እውቀት ያፈሩትን ሃብት ባለቤታቸው በብሄራቸውና በወገናቸው ተመክተው ቀምተው ከቤት አውጥተው ሜዳ ላይ እንደቆሻሻ እቃ ተጥለው ሲያለቅሱ እንደነበር ገልጸው፤ «ጁንታው በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ መንግስት ህግን የማስከበር ዘመቻ እስከ ገባበት ወቅት ድረስ ባለፉት ዓመታት ቆራጭ ፈላጭ በነበሩት ሰዎች ላይ እምነት ስላልነበረኝ ብሶቴን አውጥቼ ለመናገር ባልችልም እኔም እንደ መከላከያ ሰራዊቱ ከጀርባዬ በባለቤቴ ከፊቴ ፍትህን በብሄራቸው እንዳሻቸው በሚያደርጉ ግብዞች የደማሁ ሰው ስለሆንሁኝ ደሜ የሚታፈስበት ወቅቱ አሁን ነው በሚል መታገል አለብኝ ወደ ሚለው መንፈስ መጥቼ ይሄው ህዝብና መንግስት ይፍረደኝ ብያለሁ» ይላሉ ቅሬታ አቅራቢው።
የፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ በአጭሩ
ጉዳዩ በመጀመሪያ ደረጃ የቀረበለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ በመ/ቁ 24342 ሐምሌ 18 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት ሐምሌ 17 ቀን 1993 ዓ.ም በውልና ማስረጃ መዝገብ ጽህፈት ቤት የተደረገው የስጦታ ውል በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 73 መሰረት በፍርድ ቤት ያልጸደቀ ስለሆነ ውጤት አልባ ከመሆኑም በላይ ይህንኑ ቤት ግራ ቀኙ ተጋቢዎች ከኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ለተወሰደው የብድር ገንብ በመያዣ ያስያዙት ስለሆነ ንብረቱ የባልና የሚስቱ የጋራ ሀብት ነው በማለት ወስኗል።
ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ በመ/ቁ 115393 ታህሳስ 26 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ንብረቱን አቶ አፈወርቅ ሐምሌ 27 ቀን 1993 ዓ.ም በውልና ማስረጃ /በአዋዋይ ፊት ለባለቤታቸው በስጦታ ያስተላለፉ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህ የስጦታ ውል ፈርሷል ለማለት ንብረቱ የጋራ ነው በማለት ከባንክ ገንዘብ የተበደሩበት መሆኑን በመጥቀስ ሣይሆን ስለስጦታ ጉዳይ ተፈጻሚነት ባለው የፍ/ብ/ህጉ ከቁጥር 2441 እና ተከታታይ ድንጋጌዎች መሠረት የተሻረ እንደሆነ ብቻ ነው። ከዚህም በላይ ንብረቱ ከባለቤታቸው ወደ ባለቤታቸው እናት ወይዘሮ ኪሮስ ኅዳር 19 ቀን 1999 ዓ.ም በተደረገ ሌላ ስጦታ ውል መተላለፍና ቤቱም ተሻሽሎ ስለመሰራቱ ተገልፆ እያለ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1815 እንደተደነገገው ውሉን ለማስፈረሳቸው የቀረበ ክርክርም የለም። ስለሆነም ሐምሌ 27 ቀን 1993 ዓ.ም የተደረገው የስጦታ ውል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2427፣2436፣ 1723 የተደነገገውን አላማ ስቶ የተደረገ በመሆኑ ህጉ በሚፈቅደው መሠረት ያልፈረሰ ስለሆነ የስር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይኽ ውል ዋጋ ያለው አይደለም በሚል የሰጠውን ውሣኔ ተሽሯል በማለት ከስር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሣኔ የተለየ ዳኝነት ሰጥቶበታል።
በፍርድ ባለእዳ የይግባኝ አቤቱታ መነሻነት ጉዳዩን በሁለተኛ ደረጃ የይግባኝ ክርክር የተመለከተው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበኩሉ ሁሉንም ወገኖች ካከራከረ በኋላ በፍ/ብ/ይ/መ/ቁ 76536 በሆነው መዝገብ ጉዳዩን ተመልክቶ ጥቅምት 7 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት አቶ ፈወርቅና ወይዘሮ ብርዛፍ ባልና ሚስት እንደነበሩና ጋብቻው በፍቺ ውሳኔ ፈርሶ የፍቺ ውጤቱን በሚመለከት የቀረበ ክርክር በመሆኑ ለጉዳዩ ተፈጻሚነት ያለው ሕግ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እንጂ የፍ/ብሔር ሕግ አይደለም።
ስለሆነም ምንም እንኳን አቶ አፈወርቅ ሐምሌ 27 ቀን 1993 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽህፈት ቤት ቀርቦ የስጦታ ውል ቢያደርግም ይኸው ውል በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 73 መሠረት በፍርድ ቤት አልጸደቀም፣ ቤቱንም ባለቤታቸው ወይዘሮ ብርዛፍ ለእናታቸው ለወይዘሮ ኪሮስ በስጦታ ቢያስተላልፉ ኖሮ አቶ አፈወርቅና ባለቤታቸው ወይዘሮ ብርዛፍ ቤቱን በመያዣ አስይዘው ባልተበደሩበት ነበር። ወይዘሮ ብርዛፍ በርካታ ገንዘብ ወጪ አድርጌያለሁ በሚል ያቀረቡት ክርክራቸውን በሁለቱ የሥር ፍርድ ቤት የታለፈ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም። ስለሆነም ክርክር የተነሳበት ንብረት የባልና ሚስት የጋራ ሀብት ነው ሲል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወስኗል።
በፍርድ ባለእዳ የይግባኝ አቤቱታ መነሻነት ጉዳዩን በሶስተኛ ደረጃ የይግባኝ ክርክር የተመለከተው ሰብር በበኩሉ ሁሉንም ወገኖች ካከራከረ በኋላ የሰበር መዝገብ ቁጥር 85731 ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ የሰጠው የመጨረሻ ፍርድ በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 73 የተመለከተውን ድንጋጌ ግብና ዓላማ ተንተርሶ ትክክለኛ አፈጻጸሙን ለተያዘው ጉዳይ ያዋለው ባለመሆኑ አንድ በህግ ፊት የፀና ህጋዊ ተግባር በሌላ ውል ተተክቷል የሚባልበትን አግባብ ሁሉ ያገናዘበ ከመሆኑ አንጻር ፍርዱ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ስላገኘሁት የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሽሬዋለሁ የሚከተለውን ውሳኔ አጽንቷል።
አንደኛ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በፍ/ብ/ይ/መ/ቁ 76536 ጥቅምት 7 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ተሽሯል። ሁለተኛ ይግባኝ ሰሚው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 115395 ታህሳስ 26 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በተለየ ምክንያት ቢሆን ፀንቷል። ሦስተኛ በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ ክ/ከተማ ቀበሌ 19 በቤት ቁጥር 731 ተመዝግቦ የሚገኘው ቤት ላይ አቶ አፈወርቅ አስቀድሞ ሐምሌ 27 ቀን 1993 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽህፈት ቤት ባደረገው የሥጦታ ውል የነበረውን መብት ያስተላለፈ ስለሆነ በዚህ ንብረት ላይ የይገባኛል ጥያቄ ለማቅረብ አይችልም። በንብረቱ ላይ መብት የለውም ብለናል። አራተኛ የሰበር ችሎት ያለውን ጉዳያቸውን ለመከታተል ሲል ግራ ቀኙ ያወጡትን ወጪና ኪሳራ በሚመለከት በየራሳቸው ይቻሉ ብለናል ሲል ሰበር ውሳኔውን አስተላልፏል።
የኢፌዴሪ የፍትህ ሚኒስቴር የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት
አቶ አፈወርቅ ክብረት ሐምሌ 19 ቀን 1993 ዓ.ም በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት በቁጥር 73/7/93 ለባለቤታቸው ወይዘሮ ብርዛፍ ክንዴ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት ስጦታ መስጠታቸውን ይታወቃል። ከስጦታ በኋላ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ መጋቢት 5 ቀን 1997 ዓ.ም ባልና ሚስት ተስማምተው ተበድረዋል። በዕዳ በተያዘ ቤት እንደገና ወይዘሮ ብርዛፍ ክንዴ ለእናታቸው ወይዘሮ ኪሮስ ቀለታይ ኅዳር 19 ቀን 1999 ዓ.ም ስጦታ ሰጥተዋል። በመሆኑም ይህ ውል ተገቢ ነው አይደለም መልስ እንዲጥ የፌዴራል ጸረ ሙስና ኮሚሽን በቁጥር 2148 በቀን 19/03/2007 ዓ.ም ለጠየቀው ጥያቄ ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ምላሽ፤ አንደኛ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት ባል ለሚስት ስጦታ መስጠት አይችልም ሚስት ለባል ስጦታ ልትሰጥ አትችልም። ሁለተኛ ኦርጅናል ካርታ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት ካልቀረበ ስጦታ መስጠት አይቻልም። እንዲሁም። በእዳና እገዳ የተያዘ ካርታ በስጦታ መስጠት አይቻልም። በሰነዶች ማረጋገጫና በምዝገባው ጽህፈት ቤት አይጸድቅም። በሁለቱም ሰነዶች የተደረገው ሰነድ ማረጋገጫ በህግ አግባብ የተፈጸመ አይደለም ሲል በ16/03/ 2007 ዓ.ም ምላሽ ሰጥቷል።
የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ አ.ማ
ባንኩ በቁጥር የኮቢባ/ዑቁቅ/1070/10 በቀን 12/04/2003 ዓ.ም ለፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በላከው ደብዳቤ አቶ አፈወርቅ ክብረት ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ብርዛፍ ክንዴ ጋር በመሆን ከባንኩ በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 17 ቀበሌ 19 በካርታ ቁጥር 8719 ለተሰራው ህንጻ ማስጨረሻ ብር 798ሺ 116 ብር ወስደው በአሁኑ ጊዜ ማለትም ከታህሳስ 12 ቀን 2003 ዓ.ም ቀሪ ዕዳ ብር 479ሺ 484 ብር እንዳለባቸው እና አቶ አፈወርቅ ከታህሳስ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በግላቸው የተበደሩትም ሆነ የተቀማጭ ሂሳብ የሌላቸው መሆኑን እናሳውቃለን ሲል ፍርድ ቤቱ በጠየቀው መሰረት ባንኩ መልስ ሰጥቷል።
ውድ አንባቢዎቻችን ቅሬታ አቅራቢው ስለኒያላ የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ድርጅታቸው ላይ ተፈጽሞብኛል ስላሉት በደልና ፍቃደኛ የሚሆኑ ከሆነም የባለቤታቸውንና የሌሎች አካላትን ምላሽ ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን። እስከዚያው ቸር እንሰንብት።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14/2013