ራስወርቅ ሙሉጌታ
ቤተሰብ የማህበረሰብ መሰረት ነው የበርካታ ጤነኛ ቤተሰቦች መኖር ጠንካራ ማህበረሰብ ብሎም ሀገር ለማቆም የሚረዳ ይሆናል። ቤተሰብ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚቀረጽበት የመጀመሪያው ተቋም ነው። በአሁኑ ወቅት በሳይንሳዊ መንገድ የተጠኑ ጥናቶች ባይኖሩም በርካታ ቤተሰቦች በችግር ወስጥ ያሉ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች ግን አሉ።
ከነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በይሉኝታም ሆነ ከዛሬ ነገ ይሻላል በሚል በአንድ ጎጆ ውስጥ ለሰው ይምሰል ባለትዳር ሆነው ቢኖሩም እቤታቸው ውስጥ ግን ሰላም የሌላቸው ጠንከር ሲልም አልጋና ምግብ ለይተውም የሚኖሩ አሉ።
ሌሎች ደግሞ የቤተሰብና የአካባቢ ተጽእኖ በመፍራት አልያም የግዜን ዳኝነት እንጠብቅ ብለው የሞቀ ጎጇቸውን ትተው ወጥተው አቅም ያላቸው ቤት ተከራይተው ያልሆነላቸው ደግሞ ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ጋር በመቀመጥ ኑሯቸውን ይገፋሉ። ጨከን ያሉት ደግሞ አንተ ትብስ አንቺ ትብስ ተባብለው የጀመሩትን ሶስት ጉልቻ ከዳር ማድረስ ተስኗቸው ፍርድ ቤት ድረስ በመሄድ በይፋ ትዳራቸውን አፍርሰው ልጆቻቸውን ለመበተን ይበቃሉ።
ለመሆኑ ይህንን የሀገር መሰረት የሆነ ተቋም ዘላቂና ውጤታማ ለማድረግ ምን መደረግ አለበት ስንል በኢምፓክት ኢትዮጵያ የሳይኮሎጂካል አገልግሎቶችና የማኅበረሰብ ጤና ማማከር ማኅበር የሥነልቦና አማካሪና የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑትን አቶ አለማየሁ ጥበበን አናግረናል።
አቶ አለማየሁ እንደሚናገሩት ለጥንዶች መለያየትም ሆነ መራራቅ ቀዳሚው ምክንያት አለመግባባት ነው። ቤተሰብ ለመመስረት ወደትዳር የሚገቡ ሁለት ጥንዶች ምንአልባትም ከሁለት በፍጹም የተለያየ ቤተሰብ ማህበረሰብና አስተዳደግ የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። በቤተሰብ ወስጥ ለሚፈጠር አለመግባባት የመጀመሪያ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ደግሞ በጥንዶቹ መካከል ያለው ጠንካራ ያልሆነ ግንኙነት ነው። ሁለት ጥንዶች በአንድነት መኖር ሲጀምሩ ሁለት የተለያዩ ፍላጎቶችን ይዘው ሲሆን በትዳር የሚቆዩት እነዚህን ሁለት የተለያዩ ነገሮች አስታርቀው አቀራርበው ወደ አንድ ማምጣት ሲችሉ ነው።
እነዚህን ፍላጎቶች ለሟሟላት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሁለቱ ጥንዶች ሚና የተለያየና በተለያየ መንገድ የሚገለጥ ሲሆን ይህንን በአግባቡ በመወጣትና ባለመወጣት ሂደት የሀሳብ አለመግባባቶች ይፈጠራሉ።
ይህ ተፈጥሯዊ የሆነና ሊከሰት የሚችል የሚጠበቅ ጉዳይ ሲሆን ጠንካራ የሆነ ግንኙነት የሚያስፈልገውም ይህንን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ሳይካረር እንዴት መፍታት እንችላለን የሚለውን ለመወሰን ነው። በመሆኑም ሁለት ጥንዶች ወደ ትዳር ከመሄዳቸው በፊት በትዳር ውስጥ ምንም አይነት ችግር ቢፈጠር አውርተው ተነጋግረው ለመፍታት ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል።
እንደዚህ አይነት ዝግጅት ያደረጉ ጥንዶች ምንም አይነት ችግር ቢገጥማቸው ለመወያየት ኃላፊነት ለመውሰድና የተፈጠረውን ችግር ለማስተካከል ስለሚፈቅዱ ችግሮች የመባባስ ዕድላቸው ጠባብ ነው። ለትዳር ራሳቸውን የሚያዘጋጁ ሰዎች መጀመሪያ ሊያደርጉት የሚገባው የምክር አገልግሎት ማግኘት መሆን አለበት። ባለሙያ ክፍተቶችን በመለየት ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ ብሎ ከተለያየ ሁለት ማህበረሰብ የመጡና አንድ ሊሆኑ የሚፈልጉትን የማብቃትና የማዋሀድ ስራ ይሰራል።
ጥንዶች ወደ ትዳር ሲሄዱ የሚያደርጉት የራሳቸው ቁሳዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ዝግጅት እንደተጠበቀ ሆኖ የምክር አገልግሎትም ከተለያዩ አካላት ሊያገኙት ይችላሉ። በኢትዮጵያ በሳይንሳዊ መንገድ የትዳር ማማከር አገልግሎት የሚሰጡት በጣም አነስተኛ ናቸው።
አነስተኛ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡም የምክር አገልግሎት የመጠየቅ ልምድ ዝቅተኛ ነው። በሀይማኖት ተቋማት ግን ከሃይማኖት ትምህርት ጋር በማቀናጀት ለትዳር የሚያደርጉትን ዝግጅት የመደገፍ ስራ የሚሰሩ አሉ፤ እነዚህም ጥቅም ስላላቸው ወደ እነዚህ መሄድ።
ጥንዶች በጓደኝነት በነበሩበት የቅርርብ ደረጃ በትዳር ሊቀጥሉ አይችሉም ወደ ትዳር ሲገባ በጓደኝነት ግዜ ከነበረው የተለየ አዳዲስ ምናልባትም የማይታወቁና በአንደኛው ወገን ቅቡልነት ሊኖራቸው የማይችል አዲስ ባህሪ ሊከሰት ይችላል። አዳዲስ ፍላጎቶች ይመጣሉ::
ኃላፊነት መውሰድ የግድ እየሆነ ይመጣል። ስለዚህ ለውይይት እድል እየሰጡ በየግዜው ከሚመጡ ነገሮች ጋር ራስን እያስማሙ ለመጓዝ ዝግጅት ማድረግም ይጠበቃል። በአብዛኛው እንደዚህ ላሉ አዳዲስ የባህሪ ለውጦችን ለመቀበልና ለማስተዳደር ዝግጁ ያልሆኑ ጥንዶች ትዳራቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል ትዳራቸውንም መቆጣጠር ይሳናቸዋል።
ኃላፊነትንም በተመለከተ በተፈጥሯዊ ሂደት የሚመጡ ሁነቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል የልጆች መወለድ አንዱ ነው። የልጆች ወደ ቤተሰብ መምጣት ለጥንዶች የኃላፊነት መጨመርን ያስከትላል ይህም በገንዘብ፤ በግዜ፤ በቁርጠኝነት፤ በቤት ውስጥ የስራ ድርሻ በመከፋፋል፤ መተጋገዝና በሌሎችም ሊሆን ይችላል።
እነዚህ ሁላ ነገሮች ለመከወን በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚፈጥሩት የራሳቸው የሆነ ጫና አለ። ጫናውን በማለፍ እነዚህን ኃላፊነቶች ሳይታክቱ ለመውጣት በጥንዶች መካከል ካለመሰልቸት በየጉዳዩ በየወቅቱ ያለው የመነጋገር የመወያየት ባህል የዳበረ ሊሆን ይገባል።
ሁለተኛው የመራራቅና የመለያየት ምክንያት የመቻቻል አቅም ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ አብሮት የሚኖረው ሰው ቢሆንልኝ ቢያደርግልኝ ብሎ የሚያስበውና የሚፈልገው ነገር ይኖረዋል።
እነዚህም ከገቢ፤ ከአለባበስ፤ ከባህሪ፤ ከማንነት፤ ከልጆች አስተዳደግ ወዘተ ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህም መስፈርቶች በግዜ ሂደት ሊቀያየሩ ይችላሉ፤ ይህም ተፈጥሯዊ ነው።
ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ያለው ነገር እንዳለ ሆኖ ሰው በመሆኑ የሚጎድለውም ነገር ይኖራል። ሁሉም ሰው በተፈጥሮው በሁሉም ነገር ሙሉ አይሆንም ስለዚህ ሁሉም ፍላጎት ይሟላል ተብሎ መጠበቅ የለበትም። በተጨማሪ ሰዎች በግዜ ሂደት ውስጥ በተሞክሮ የሚቀያየሩባቸው ሁኔታዎች አሉ።
ለምሳሌ አንድ የማይጠጣ የነበረ ሰው በአንድ ክስተት ወደ ትዳር ከገባ በኋላ የሚጠጣበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በመሆኑም አንዱ ሊያጣው የሚችል ሊያጎድለው የሚችል እንዳለ ሁሉ ከሌላኛውም ወገን የማይሟላ ነገር ስለሚኖር እየተደጋገፉ እየተቻቻሉ ለመኖር ራስን ማዘጋጀት እንጂ ፍጹማዊ የሆነ ነገር መጠበቅ ተገቢ አይደለም። እንደዚህ ማሰብ ካልተቻለ ሁል ግዜ ለግጭት ለጭቅጭቅ መንስኤ የሚሆን ነገር በጥንዶቹ መካከል አይጠፋም ማለት ነው።
ይሄ ማለት ግን በሰዎች ላይ ያለን ክፍተት እንዳለ ተቀብሎ መቀጠል ማለት አይደለም ምቹ ሁኔታና ግዜ ፈልጎ ጉዳዮቹን በምክንያትና በውጤት የሚያስከትሉትን ነገር የሚያጎድሉትን ነገር በማንሳት እንዲስተካከሉ አልያም ጨርሰው እንዲወገዱ መወያየትና መተማመን ይጠበቃል።
በዚህ ረገድ የሚደረጉ ውይይቶች ግን ጥንቃቄ የሚፈልጉ ናቸው። በመሆኑም ጥንዶች ለውይይት ሲቀመጡ አንዱ አንዱን ለማሳመን አልያም ለማሸነፍ ወይንም አንተ፣ አንቺ ጥፋተኛ ተብሎ ለመፈራረጅ፤ ለመወቃቀስ ሳይሆን በመግባባት የተነሱበትን ችግር ለመፍታት ሊሆን ይገባል።
ውይይቱም ልጆችን ወይንም ቀሪውን ቤተሰብ ሰላም በሚነሳ መልኩ ሊደረግ አይገባም። ለዚህም ስሜታዊ በመሆን ነገሮች እንዳይባባሱ የሚመቻቸውን ቦታና ስሜታቸው ጥሩ የሆነበትን ግዜ ሊመርጡ ይችላሉ።
በሌላ በኩል መቻቻል የሚለው ነገር የራሱ ገደብ ሊኖረው ይገባል። መቻቻል መፈጸም፣ መሳካት ያለባቸው ሁለት የተለያዩ ፍላጎቶችን የአንድን ሰው በመገደብ በማለፍ አልያም ሙሉ በሙሉ በማስቀረት የሚደረግ ነገር ሊሆን ይችላል። ይህ የሚደረገው ለትዳር ለአብሮነት ቅድሚያ በመስጠት አልያም የአንድ ሰው ደስታና ስሜት ለመጠበቅ ሊሆን ይችላል። በአብዛኛው ለትዳሬ ስል ለልጆቼ ስል አልያም ነገሮች ይስተካከላሉ በሚል ጥሩ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሲኖሩ ይስተዋላል።
ነገር ግን መቻል ብቻውን በቂ የማይሆንባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ አንዱ ወገን ትዳርን የሚጎዳ የሰውን ስሜት በተደጋጋሚ የሚያቆስል መሰረታዊ ችግሮች ካሉበት መቻል አለበት በሚል ብቻ መቀመጥ ተገቢ አይሆንም። ይልቁንም ለማስተካከል መሰራት አለበት። አንዳንድ ሰዎች በመቻቻል ስም ዝምታን ሲመርጡ ይስተዋላሉ።
ነገሩ ግን እየተባባሰ የሚሄድ ትዳርን ወደአልሆነ አቅጣጫ እየመራ የሚሄድ ከሆነ በመቻል ስም ነገሮች እንዲባባሱና ምንአልባትም መመለስ መስተካከል የማይችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ በር ሊከፍቱ ይችላሉ።
በመሆኑም መቻሉ እንዳለ ሆኖ ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለመቅረፍ መስራት አለባቸው። ይህም ግን እንደ ጭቅጭቅ ንዝነዛ ሊታይ ይችላል ነገርግን ሁሌም ለመፍታት መስራት እንጂ ያልተገቡ ችግር የሚፈሩ ባህሪዎች እያሉ በመቻቻል ስም ዝም ብሎ መቀመጡ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል።
ሌላው የጥንዶች አብሮነት መሰናክል የሚሆነው ከተለያዩ አካላት የሚመጡ ጣልቃ ገብነቶች ናቸው። ትዳር በሁለት ግለሰቦች መስማማት መግባባትና መተማመን እንዲሁም ውሳኔ በጋራ ለመኖር የሚደረግ ስምምነት እንደመሆኑ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለሁለቱ ሀሳብና ፍላጎት መሆን አለበት።
ሰዎች ካደጉበት ማህበረሰብ በሚያገኙት አቻን ተመሳሳይን የመፈለግ አዝማሚያ ይኖራቸዋል። ይሄ እንደተጠበቀ ሆና ያደግንበት ቤተሰብ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ የሚያከብረው የሚፈቅደው የሚከለክለው እሴት አለው ይህም የሚፈጥረው ተጽእኖ በመኖሩ ጥንዶች ሳይፈቅዱ የሚያደርጓቸው ነገሮች አሉ። በዚህም እነሱ ሳይፈልጉ በቤተሰብ ፍላጎት እንዲያገቡ ያደርጋቸዋል።
ይህ ሲሆን በትዳር ውስጥ መኖር ሲጀምሩ ምንም እንኳን የቤተሰብ መፈቃቀድ ቢኖርም ጥንዶቹ ላይስማሙ ይችላሉ። ይሄ ለመገናኘት ብቻ ሳይሆን ለትዳር ካላቸው ፍላጎት እንዲፋቱ ለማድረግም ሊሆን ይችላል።
አንዳንድ ግዜ ደግሞ በተለይ ከቅርብ ቤተሰብ ከባለትዳሮቹ ፍላጎት ውጪ አብሮነታቸውን ቢፈቅዱም በዚህ ግዜ ልጅ ውለዱ፤ ይህን ቀድማችሁ አድርጉ፤ እንዲህ ተቆጣጣሪው፤ ይህን ሊያደርግልሽ አልያም ልታደርግልህ ይገባል እያለ ጣልቃ የሚገባም ይኖራል።
ሌላው ለጣልቃ ገብነት በር የሚከፍተው ራሳቸው ጥንዶቹ የገቡበት ህይወት ውስጥ መተማመን ሳይኖራቸው በጥርጣሬ የሚኖሩ ከሆነ ነው ። እነዚህ ጣልቃ ገብነቶች በምክረ ሀሳብ ደረጃ የሚቀርቡ ከሆነ ችግር ላይኖራቸው ይችላል ነገር ግን ጫና በመፍጠር ከሆነ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው የሚያመዝን ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ እነዚህን ተጽእኖዎች በመሻገር ምንም ይሁን ምን ለራሳቸው ስሜት ቅድሚያ በመስጠት ጓዳኛቸውን ሊቀበሉ ይችላሉ።
እንደነዚህ አይነት ችግሮችን ለመቋቋም አንደኛ እያንዳንዳቸው ጥንዶች በራሳቸው የመቆም ልምድና ቅድሚያ ለትዳር አጋራቸው መስጠትን ማዘውተር አለባቸው። ምንም እንኳን እነዚህ ምክሮች ወይንም ጣልቃ ገብነቶች ከምንወዳቸው ከምናከብራቸው ሰዎች የሚመጡ ቢሆንም በተረጋጋ መንፈስ ነገሮችን በማየት አይሆንም የማለት በራስ የመተማመን መንፈስ ልምድ ሊኖራቸው ይገባል።
ባጠቃላይም ይሄ ትዳር ይሄ ቤተሰብ የኔ ነው ችግርም ቢፈጠር ተጎጂው እኔው ነኝ፣ የደስታውም ቀዳሚ ተጠቃሚ እኔ ነኝ በሚል ስሜት በኃላፊነት ሁሉንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ መሆንና መቀበል ለትዳርም ትልቁን መስዋዕትነት መክፈል ይገባል።
ምንም እንኳን መለያየት በምንም መልኩ የማይመከር ቢሆንም እነዚህ ነገሮች ተደርገው ስምምነት መፍጠር ካልተቻለና ጥንዶች የግድ ሆኖ መለያያት ላይ ከደረሱም ከተሸናፊነት ስሜት ወጥተው ሊያደርጉት ይገባል።
ይህም ማለት ልጆች ሊበተኑ የተበላሸ ህይወት እንዲመሩ የሚያስገድዳቸው ሁኔታ እንዳይፈጠር ትዳሩ በሰላም እንደተጀመረ ሁሉ በሰላም እንዲቆም ሁለቱ ጥንዶች ፈቃደኛ መሆንና መስራት አለባቸው። አብረው ሊኖሩ የማያስችላቸው ትልቅ ሁኔታ ከተፈጠረ በሰላም ተለያይተው የየራሳችን የሚሉትን ህይወት መመስረት ይጠበቅባቸዋል።
ብዙ ግዜ ሁለቱም በስምምነት በተመሳሳይ ሰሜት ለመለያየት ላይወስኑ ስለሚችሉ ባለሙያ ማማከር ይገባል። ይህንንም ለማድረግ በመጀመሪያ ባሸናፊነትና በተሸናፊነት መንፈስ ሳይሆን ልዩነትን በመቀበልና እውቅና በመስጠት፤ በስምምነት ካልሆነም በሕግ አግባብ በልጆች በንብረት ላይ በመስማማት መለያየት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14/2013