ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ነገር ያልታዩ ያልተሰሙ ገጠመኞችን ይዞ ይመጣል።በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛዬ ለልጁ ልደት ጠርቶኝ ከአዲስ አበባ ኮንደሚኒየም መንደሮች በአንዱ ተገኝቻለሁ።በዚህ ጓደኛዬ ቤት ስገኝ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።ወቅቱ ነዋሪዎች ገና ወደ ኮንደሚኒየሙ እየገቡ የነበረበት ወቅት ነበር።
ቤቱን ብዙ ወጥቼ ወርጄ ነው ያገኘሁት ።በጣም ተቸግሬ እንዳገኘሁት ለጓደኛዬ ነገርኩት።ሁለት ጊዜ ቤቱን ተሳስቻለሁ።መሳሳት ብቻም አይደለም አንኳኩቼ እየቀላለድኩ እስከ መግባት ደርሻለሁ ።ተሳስተዋል ስባል ነው የተመለስኩት።
ይህ ገና ወደ ኮንደሚኒየም ለገቡ ነዋሪዎችና በተለይ ለእንግዶቻቸው በጣም የተለመደ መሆኑን ነዋሪዎቹ ነገሩኝ።ያም ያም ቤቱን እንደ ተረከበ መሳሳቱን ይገልጻል።ቤቶቹ የአህያ መልክ ማለት ናቸው ፤አንድ አይነት ፤በእርግጥም እንኳን ለእንግዳ ለነዋሪዎችም ያሳስታሉ።
በመሳሳት ከታለፈም ጥሩ ነው።እንደ አሁን ቢሆን የሰው ቤት አንኳኩቶ ወይም ለመግባት ሞክሮ ይቅርታ ብሎ መመለስ አይቻልም፤አሁን ሌባ ስለበዛ አይደለም በር ከፍቶ ገብቶ ወይም አንኳኩቶ በአካባቢው ማለፍ ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባል።
ክፍል መሳሳት ሲታሰብ ዩኒቨርሲቲ እያለንም ክፍል መሳሳት ያጋጠማቸው ጥቂት አልነበሩም።ይህም በአብዛኛው ከአዲስነት ከተለወጠ አካባቢ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ስህተት ነው።
እንደ ሀዋሳ እና አዳማ ባሉ ሜዳ ላይ በተመሰረቱ ከተሞች ደግሞ መንገዶች እንግዳ ሰዎችን ሲያሳስቱ ይስተዋላል።ከመንገዶቹ መመሳሰል የተነሳ የሆነ ነገር ሲባልም የሰማሁ መሰለኝ።አዙሪት የሚባል ነገር አለ የሚል።ከመንገዶቹ ተመሳሳይነት በተነሳ ስንቶች የሚፈልጉትን ቤት ለማግኘት እግራቸው ቀጥኗል መሰላችሁ።
ሰዎች አዲስ አካባቢ ሲሄዱ ምልክት ሊሆኑ የሚችሉ ህንጻዎችን፣ድርጅቶችን ፣አደባባዮች፣ወዘተ እያሰቡ ካልተጓዙ በስተቀር የመንገዶች መመሳሰል ሰዎችን ለእንግልት ሊዳርግ ይችላል።
በቅርቡም በሀገራችን የገንዘብ ለውጥ በተደረገ ጊዜ ሰዎችን ለስህተት የተዳረጉበት ሁኔታዎች አጋጥመዋል።አሁን በስራ ላይ ያለው ገንዘብ እንዲህ ሊለመድ ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን ጉድ ሰርቷል። ይህ የሆነው ደግሞ መንግስት ስለገንዘብ ለውጡ በቂ ግንዛቤ ባስጨበጠበት ሁኔታ ነው።ይሁንና በግብይት ወቅት ሰዎች ለስህተት የተዳረጉባቸው ሁኔታዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።
ከእንግዲህ ወዲህ በቤተ መዘክርና በህሊና መደብር ብቻ የምናገኘው አሮጌው ብር ከአዲሱ ብር የሆነ ኖት ጋር የሚመሳሰልበት ሁኔታ ነበረ። እነዚህ ሁኔታዎች ታዲያ ተገብያዮችን ጉድ ሰርተዋል። አእምሯችን ከለመደው ገንዘብ ጎን ለጎን አዲሱ ገንዘብ በግብይት ላይ በነበረበት ወቅት የገንዘቦች የአሮጌውና የአዲሱ ገንዘቦች ቀለም መመሳሰል ግርታ አስከትሎ እንደነበር ይታወቃል፤ አጭበርባሪዎችም ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ተጠቅመውበታል።
አንድ ወዳጄ የገንዘብ ኖት ለውጡ በተጀመረበት አካባቢ አንድ ምሽት ላይ ከባንክ ብር ያወጣል፤ምግብ ቤት ገብቶም ምግቡን በልቶ መጠጡን ጠጥቶ ከፍሎ ይወጣል ፤ቤት ከደረሰ በኋላ በቴሌቪዢን አንዳንድ መረጃዎችን እያየ ብሩን ከኪሱ አውጥቶ መቁጠር ይጀመራል ።
ገንዘብ ይጎልበታል።በምን ምክንያት እንደ ጎደለ ማሰላሰል ይጀመራል።ግብይት እንዳልፈጸመበት እርግጠኛ ነው።አሁንም ያስባል፤ ያሰላስላል። “ምግብ ቤት ገብቼ በላሁ ጠጣሁ ከፍዬ ወጣሁ፤ ከነበሩት ሦስት የ200 ብር አዳዲስ ገንዘቦች አንዱን አጣሁት።ለካስ በስህተት ለአስተናጋጁ የአንድ መቶ ብር ኖት መስሎኝ አዲሱን የ200 ብር ኖት ሰጥቼው ኖሯል፤አሁን ሳስበው የአስተናጋጁ ነገር ትዝ አለኝ፤ገንዘቡን ተቀብሎ ገንዘቡን ኪሱ ከቶ እየተጣደፈ ሌሎቹን ማስተናገድ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ታወሰኝ ።” ሲል ያጫወተኝን አስታውስኩ።
በአንድ ወቅት የባንክ ፈጣን መክፈያ ማሽን ለመጠቀም አካባቢው ላይ ተገኝቻለሁ፤ አንድ ሽማግሌ ተረኛ ነበሩና ገንዘብ አዘዙ፤ገንዘቡ መጣላቸው፤ ቆጠሩ ።አሁንም አሁንም እየደጋገሙ ይቆጥራሉ።በዚህ መሀል እኔ የምፈልገውን ገንዘብ አወጣሁና ለተረኛ ለቀቅሁ።
ሽማግሌው አሁን እዚያው ናቸው።ብቻቸውን እንደማውራት እያላቸው ነው።አመኑኝ መሰል የቸገራቸውን ያማክሩኝ ገቡ ።ወደ ጉዳዬ ቶሎ መሄድ የነበረብኝ ቢሆንም፣የአዛውንቱ ጉዳይ አሳሰበኝ።እሳቸውም ባንክ ገብተው ሊጠይቁ ሲሉ ዘግተን ልንወጣ ነው ችግር ካለ ነገ ብቅ ይበሉ፤ይቻላል መባላቸውን ነገሩኝ።
ሰውየውን በድጋሜ ጠይቅሁዋቸው ፤አንድ ሺ ብር አዝዤ አምስት መቶ ብር ብቻ መጣልኝ አሉኝ፤ ገንዘቡን እያሳዩኝ።ደግመው አውጥተው ይሞክሩ ስላቸው “ሞክሬ ነበር ልጄ ቀሪው 50 ብር ብቻ ነው ይላል” አሉኝ።
ገንዘቡን አሳዩኝ፤ አዲሱ የብር ኖት ነበር ። በደንብ ሳየው የ200 ብር ኖቶች ናቸው። ገንዘባቸው ምንም እንዳልሆነና የወሰዱትም አምስት የ200 ብር ኖት መሆኑንና አንድ ሺህ ብር እንደሆነ ነገርኳቸው።እንደዚያ ነው ፤ይቅርታ ልጄ አንተንም አስቸገርኩህ፤ምን ላድርግ ብለህ ነው ፤ባለ መቶ ብር አስር ኖቶችን ስጠብቅ አምስት ቢሆኑብኝ ጊዜ ተደናግጬ ነው አሉኝ።አመስግነውና መርቀውኝ ተለያየን።
የእሳቸው እዳው ገብስ ነው፤ቀላል፤የጠፋ ወይም የተበላ ገንዘብ የለበትማ።በዚሁ ወቅት የተጭበረበሩ ግን አሉ።በጨዋታ በጨዋታ ነው የሰማሁት።አንድ ዶሮ ሻጭ በአዲሱ ገንዘብ በሰማንያ ብር ሁለት ዶሮዎች ሸጧል አሉ። ዶሮ ነጋዴው /ለዚያውም ዶሮ ነጋዴ/ በስምንት መቶ ብር ሁለት ዶሮ የሸጠ መስሎት ነው በሰማንያ ብር ሁለት ዶሮዎቹን የሸኘው።
ነጋዴው ጉድ ተሰራሁ፤ እንደዚህ ተበልቼ አላውቅም ፤ጉድ ተሰራሁ እያለ ክፉኛ ቢበሳጭም፣ ገዥዎች ግን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ዶሮዎቹን አፍሰው ሂደዋል።
ታክሲ ላይ በገንዘብ ለውጡ መጀመሪያ ላይ የተጎዳ ሌላም ሰው ገጥሞኛል።ግለሰቡ አቃቂ አካባቢ ነው የሚኖረው። ምሽት ላይ ታክሲ ተሳፍሮ ወደ ገላን ይሄዳል።ገና ብዙ የሚቀረው መንገድ ነበርና ሀሳብ ገብቶታል።በዚህ መሀል ሂሳብ ይጠየቃል። የጥድፊያንና የምሽትን ነገር አስቡት።አምስት ብር አውጥቶ ይከፍላል።ሁለት ብር መልስ እንዳለው አውቆ መልስ ሲል ይጠይቃል፤ረዳቱ ችላ ይለዋል።
ተሳፋሪው መውረጃው ይደርስና ይወርዳል።መልስ አልተቀበለም፤ሁለት ብር መልስ ነበረው፤ ፤አውቀው ነው የሚያዘናጉት ፤በቃ ይብላው ብሎ መንገዱን ይቀጥላል።
አካባቢው ይደርስና ትንሽ አርፍ ብሎ ወደቤት መግባት ይፈልጋል።አንድ ሁለት ልበል ብሎ ቡና ቤት ጎራ ይላል።ለማናቸውም ብሎ ኪሱን ይደባብሳል፤ያለውን የገንዘብ መጠን ማረጋገጥ ይጀመራል፤ የሆነ ብር ጎድሎታል።ለምን እንደ ጎደለ ማሰላሰል ጀመረ።ደነገጠ፤እንዴት ሊጎድል እንደቻለ ታወሰው። አምስት ብር መስሎት ለረዳቱ የሰጠው የ100 ብር አዲሱ ኖት መሆኑን ተረዳ። አዲሱ መቶ ብር በስራ ላይ ካለው ባለአምስት ብር ኖት ጋር በቀለሙ ይቀራረባል ለካ ። ረዳቱ ያንን ብር ለይቶ ወደ ኪሱ መክተቱም ታወሰው ፤ጅብ ከሄደ ..ነው የተባለው ።
መንግስታት፣ድርጅቶች ፣ወዘተ፣አዲስ አካባቢ ፣አዲስ አሰራር ፣ወዘተ. በህብረተሰቡ ዘንድ ግርታ እንዳይፈጥሩ በሚል ግንዛቤ በማስጨበጥ ስራ ላይ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ።
ለእዚህም በቅርቡ የገንዘብ ለውጥ ሊደረግ ሲል እና እየተለወጠ ባለበት ወቅት መንግስት በአዲሱ ብር ላይ ሰፊ ማብራሪያ መስጠቱን እዚህ ላይ ማስታወስ ይገባል። ይህ የሚሆነውም ወደ አዲስ ስራ መግባት በራሱ በተገልጋይ ዘንድ ሊያስከትል የሚችለው ችግር ሊኖር ይችላል ከሚል በመነሳት ነው።አዲስ አሰራር ሲመጣ፣አዲስ ነገር ሲፈጠር ማለማመድ ፣መለማመድ የሁሉም ግዴታ ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14/2013