ሐዋሳ፡- የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ በአገሪቱም ሆነ በወጣቱ ጉዳይ ዙሪያ እንዲያሳካ የተጣለበትን ኃላፊነት ሊወጣ የሚችልበትን ቁመና እንዲይዝ ለማስቻል መስራት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ በጉባኤው ማጠቃለያም ወጣት አስፋው ተክሌ በሊቀመንበርነት፣ ወጣት አክሊሉ ታደሰን ደግሞ በምክትል ሊቀመንበርነት ለቀጣይ ሁለት ዓመት ተኩል ሊጉን እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡
አዲሱ የሊጉ ሊቀመንበር ወጣት አስፋው እንደተናገረው፤ ለውጡ እንዲመጣ ያደረገው ወጣቱ ነው፡፡ አሁንም እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ወጣቱ የላቀ ድርሻ አለው፡፡ እርሱም ይህ ኃላፊነት ሲሰጠው የተተኪ ወጣቶች መድረክ የሆነውን ሊግ ወጣቱን ለዚህ ተግባር እንዲተጋ የሚያስችል ቁመና እንዲፈጥር የሚሰራ ሲሆን፤ ለዚህም የአባላቱ ድጋፍና ተሳትፎ እጅጉን አስፈላጊ ይሆናል፡፡
እንደ ወጣት አስፋው ገለጻ፤ የአገር ሁለንተናዊ እድገትና ሰላም እንዲረጋገጥ ወጣቱ የማይተካ ሚና አለው፡፡ ከዚህ አኳያ ሊጉ ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ይሄን ማድረግ የሚያስችሉም አቅም ያላቸው ወጣቶችንም አቅፏል፡፡ የብሔረሰቦች ከለላ የሆነችና ሁሉም ህዝቦች በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን እውን ማድረጊያ ጊዜው አሁን እንደመሆኑም፤ ሊጉ ይሄን በማገዝ ሂደት፣ የወጣቱን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር የሚሠራ ይሆናል፡፡
የቀድሞው የሊጉ ሊቀመንበር ወጣት ሙቀት ታረቀኝ በበኩሉ እንደተናገረው፤ በቀጣይ የአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የወጣቱ ሚና ጉልህ እንደመሆኑ ይሄን ወጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ መጠናከር እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አዲሱ አመራር ወደኃላፊነት ሲመጣ ይሄንን ብቻውን የሚያሳካው ሳይሆን የሁሉንም ተሳታፊነት የሚጠይቅ ነው፡፡ እርሱም ቢሆን ለዚሁ ተግባር ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሊጉ በማጠቃለያ መድረኩ በሁለት ቀናት በነበሩ የቡድን ውይይቶች ላይ የተነሱ ጉዳዮችን አንስቶ የጋራ አረዳድ እንዲኖራቸው በጋራ መድረክ ዳግም ውይይት አድርጎባቸዋል፡፡ በዚህም በተለይ ሊጉ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ እንዴት መጠናከር እንዳለበት፤ ከእናት ፓርቲው ጋር በምን መልኩ አብሮ መስራትና በተለይም ጎልተው በሚነሱ የልማት፣ በወጣቶች ተጠቃሚነት፣ በሰላም እንዲሁም በማንነትና ወሰን ጉዳዮች ላይ ሚናውን መወጣት በሚችልበት፤ በሊጎች መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነትና ከክልላዊ አስተሳሰብ ወጥቶ ያሉ እድሎችንና ችግሮችን በጋራ ወስዶ በአንድነት አብሮ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት መክሮ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በዚህም ሊጉ ከእናት ድርጅቱ የሚጠቅሙትን በመውሰድ ነገር ግን ከቀደመው የእናት ድርጅቱ ቅኝት በመውጣት በአንድነት ለሁለንተናዊ የአገር እድነትና ሰላም መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ሊጉም ኢትዮጵያዊነት የሚቀነቀንበት፣ ሰላምም የሚሰበክበት መሆን እንዳለበትም መግባባት ተችሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለውጥ አለ ወይስ የለም፤ ፌዴራሊዝም ያስፈልጋል ወይም አያስፈልግም፤ ሚዲያዎች ዛሬስ ከአድሏዊነት ወጥተዋል ወይስ አልወጡም፤ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትስ በምን መልኩ መሆን ይኖርበታል፤ የሕግ የበላይነትና የሕገመንግሥት ጥሰት ተስተውሏል፤ የሚሉ ጉዳዮችም በስፋት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በዚህም ፌዴራሊዝሙ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ስለመሆኑ ነገር ግን በአፈጻጸም ላይ የሚታይ ግድፈት መታረም እንዳለበት፤ ለውጡም የአብዮት ሳይሆን የሪፎርም ይዘት እንዳለውና በብዙዎችም የታመነበት ስለመሆኑ፤ ሚዲያዎችም ዛሬም ከተጽዕኖና ከአግላይነት ነጻ ሆነው እየሰሩ እንዳልሆነ፤ የሕግ የበላይነትና የሕገ መንግሥት መከበርም ከለውጡ በኋላ ስለመኖሩ፣ ነገር ግን ብዙ መስራትን እንደሚጠይቅ የጋራ አረዳድ ተይዞበታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 22/2011
ወንድወሰን ሽመልስ