የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎችን እያጠናቀቀ ነው

አዲስ አበባ፡- ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ጊዜያት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሥራት አፀደወይን (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንቱ አሥራት አፀደወይን (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፡- የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ራስ ገዝ እንዲሆን ከተመረጡት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲውን ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠራ መቆየቱን ገልጸው፤ ስለራስ ገዝነት ዓለምአቀፍና ሀገር አቀፍ ተሞክሮዎችን መውሰድ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከሀገር ውስጥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከውጭ ሀገራት የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከተለያዩ ራስ ገዝ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮዎችን መውሰዱን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም ከፈረንሳይ ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ ለመውሰድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸው፤ ተሞክሮዎችን በመውሰድና በማዳበር ዩኒቨርሲቲው የምርምርና ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አመላክተዋል፡፡

ራስ ገዝነት ዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና የአስተዳደር ነፃነት የሚያጎናጸፉ ተልዕኮዎቻችን ላይ ትኩረት አድርገን ጥራት ያለው መማር ማስተማር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ ምርምር ሊሰጥ የሚያስችል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህም ከ40 በላይ የሚሆኑ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡

ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉ ሀብት መፍጠሪያ የገቢ ተቋማት ተፈጥረዋል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በተለይ ተቋማቱ ከ2013ዓ.ም ጀምሮ ከመማር ማስተማሩና ከምርምሩ ጋር እንዲተሳሰሩ ከማድረግ ባሻገር ገቢ እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ተቋማት መማማሪያና ምርምር መሥሪያ በመሆን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፡- ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ያሉ ገቢ የሚያገኝባቸው ተቋማትን ተፈጥረዋል፡፡ ሞዴል ፋርማሲ ያለው ሲሆን በእነዚህ የጤና ባለሙያዎች ይሳተፉሉ፡፡ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጥራት ያለው መድኃኒት በማቅረብ ገበያ ያረጋጋል፡፡ በዚህም ለብዙዎች የሥራ ዕድልን መፍጠር ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ)ና የምሕንድስና ማማከር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በእነዚህም መምህራንና በቀጥታ ተያያዥ የሆኑ ትምህርት ክፍሎች ይሳተፋሉ፡፡ ትምህርታቸው አብረው እየተገበሩ ሙያቸውን እያዳበሩ ለመማር ማስተማሩም የመመራመር አቅም እየጨመሩ ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌሎች የሀብት መፍጠሪያ የእንጨትና ብረታብረት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የማተሚያ ቤት፣ የሲኦሲ ማዕከል እና ሌሎች ከአስር በላይ የሆኑ ዘርፎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ራስ ገዝ ለመሆን አቅምን ከመፈጠር አኳያ ሰፊ ሥራዎችን መሠራታቸው ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ስለራስ ገዝ ምንነት እንዲያውቅ ማድረግ፣ አውቆት ጥቅሙን ተረድቶ በአፈጻጻም አጋዥ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ማኅበረሰቡ ወደ ራስ ገዝነት ሁለንተናዊ ፋይዳ ዙሪያ ተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር በተደጋጋሚ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተሠርተዋል ብለዋል፡፡

ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ይገኛሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በቀጣይም ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር የሚያግዙ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ብለዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You