‹‹ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርጥ የምርምርና ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ይሠራል›› – የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር)

በጥንታዊዋ የጎንደር ከተማ የሚገኘው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቷ ከሚገኙ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ነው። ዩኒቨርሲቲው ከተመሠረተ 70 ዓመታት፣ ማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100 ዓመታትን በማስቆጠር ከ70 ዓመታት በላይ በላቀ አበርክቶ ዘልቋል። በእነዚህ ረጅም ዓመታት ጉዞው ከ100ሺህ በላይ ምሩቃንን ለሀገር ያበረከተ ሲሆን የአካባቢው የጤና አገልግሎት ሽፋን በመስጠትና ተማሪዎችን በማስተማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ አሁንም እያበረከተ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት 12 የምርምር ማዕከላትን አቋቁሟል። በ22 ጊቢዎች 11 ኮሌጆች ያሉት አንጋፋ ተቋም ሲሆን 89 የቅድመ መደበኛ፣ 300 የሁለተኛ ዲግሪ፣ የሦስተኛ ዲግሪና የድህረ ዶክተራል ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ40ሺህ በላይ ተማሪዎች እያስተማረ ይገኛል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ ተልዕኮውን እየተወጣ የሚገኘው የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የምርምር ፕሮጀክቶች በመሥራትም ጭምር ነው። በመሆኑም በተያዘው በጀት ዓመት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው 22 የምርምር ፕሮጀክቶችን አስመርቋል።

የዛሬው ወቅታዊ እንግዳችን አንጋፋውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየመሩ የሚገኙት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) ናቸው። ከእንግዳችን ጋር ቆይታ አድርገናል።

አዲስ ዘመን፡- የአንጋፋው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሁናዊ ቁመናና የሥራ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አስራት (ዶ/ር)፡– ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሚኒስቴር ባደረገው የዩኒቨርሲቲዎች ልየታ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ተመድቧል። ዋናዋና የትኩረት መስኮቹም ተለይተዋል። ዩኒቨርሲቲው በዋናነት የሚታወቀው በጤናው ዘርፍ ነው። በጤናው ዘርፍ አንዱ የልቀት ማዕከል ሆኖ ተመርጧል። በአራት (በግብርና፣ በስቴም (በሳይንስ፣ በሒሳብና በኢንጂነሪንግ)፣ በትምህርትና በማህበራዊ) ዋና ዋና የትኩረት መስኮች የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንዲቀጥል ተመርጧል።

በአሁኑ ሰዓት መደበኛ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት፣ ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል። 89 የቅድመ መደበኛ እና 300 የሁለተኛ ዲግሪ፣ ሦስተኛ ዲግሪና ድህረ ዶክተራል ዲግሪ ፕሮግራሞችን ይዞ ከ40ሺ በላይ ተማሪዎች እያስተማረ ይገኛል።

የዩኒቨርሲቲው በአሁናዊ እንቅስቃሴም ሰላማዊ ነው። መደበኛ ሥራ ላይ ይገኛል። የማመር ማስተማር ሥራውን በተሳካ መልኩ የተገባደደ ነው። የአመቱ የምርቃት መርሃ ግብር ሐምሌ 12 በደማቅ ሥነሥርዓት ይከናወናል። የዩኒቨርሲቲውን 70ኛና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት አካባበር አካል ተደርጎ በተለየ ሁኔታ ለማስመረቅ ታስቧል። የዚህ ዓመት የምርቃት መርሃ ግብር ልዩ የሚያደርገው በዓሉን ታሳቢ በማድረግ ቀደም ሲል ከዩኒቨርሲቲው ተመርቀው የወጡ ምሩቃን በድጋሚ የሚመረቁበትና ድጋሚ ቃል ኪዳን የሚገቡበትና መርሃ ግብርን ጭምር ያካተተ ነው።

ሌሎች ሀገር አቀፍ የሆኑ ማካከሻ ትምህርት ፈተናዎች፣ የመውጫ ትምህርት ፈተናዎች እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ፈተናዎችም እንደአንድ መደበኛ ሥራዎች ይዘናቸው ሥንሠራቸው የመጣናቸው ናቸው። ስለሆነም በዚህ ዓመትም በተሳካ ሁኔታ እየተካሄዱና ቀሪዎችንም ለማካሄድ ዝግጅታችንን እያጠናቀቅን እንገኛለን።

በምርምሩም ረገድ አብዛኛው የምርምር ሥራዎቻችን ከተማ ተኮር ናቸው። በተለይ በከተማ ግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ ሰላምና ደህንነት፣ የከተማ ሀብት (ገቢን) ከማሳደግ፣ ዘመናዊ ከተማ/ስማርት ሲቲ/ በመፍጠር እና ከተማው በኮሪዶር ልማት ከማገዝ አኳያ ሰፋፊ የሆኑ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ በ2017 የትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበት ሦስቱ ተልዕኮዎች መማር ማስተማር፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ሥራውም በተሳካ ሁኔታ እየተጠናቀቀ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎች በመሥራት ለሀገር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ምን ይመስላል?

አስራት (ዶ/ር)፡– የምንሠራቸው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ሁሉም አሁን በእጃችን፣ በአካባቢያችን እና በሀገራችን ላይ ያሉ ችግሮችን ሊመልሱ የሚችሉ ከሆኑ ብቻ ነው ፈንድ የምናደርገው። የምርምር አጀንዳዎችን ባለድርሻ አካላትን አሳትፈን ቀርጸናል። በግብርና ከሆነ ከክልሉ ግብርና ቢሮ፣ ከአካባቢው ግብርና ጽሕፈት ቤቶች እና የሚመለከታቸው የግብርና ምርምር ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን አጀንዳዎቻችንን ቀርጸናል።

ትምህርትም እንዲሁ ጎንደርና አካባቢው፣ እንደ አማራ ክልልና እንደሀገር ያለው ችግር ምንድነው የሚለውን ለይተናል። በጤና ዘርፍ በተመሳሳይ ተለይተዋል። በሁሉም ዘርፎቻችን በእጃችን ያሉና ወቅቱ የሚጠይቃቸው ችግሮች ምንድናቸው፣ የትኛውን የሀገር ችግር፣ የትኛውን የአካባቢያችንን ችግር ሊመልስ ይችላል? የሚለውን ካልያዝን በስተቀር ፈንድ አናደርግም። የምናወጣቸው የምርምር ጥሪዎች ይህንን መሠረት ያደረጉ ናቸው። በምርምር ሂደቱም ከዚህ ቀደም ተመራማሪው ብቻ ነው የሚሠራው። አሁን ላይ ግን ባለድርሻ አካላትም ይሳተፋሉ። አሁን ተጠቃሚውን ጭምር በማሳተፍ ያለበትን ችግር እንዲያስረዳ ከማድረግ አኳያ እየተከተልን ያለው አሠራር ችግሮች እንዲፈቱ አስችሎናል።

በዘንድሮ ዓመትም 14 የሚሆኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በጎንደር ከተማ ተሠርተዋል። እነዚህ የምርምር ፕሮጀክቶች የጎንደርን አሁናዊ ሁኔታ ሊፈቱ የሚችሉና በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም በሰላምና ደህንነትና በሕገወጥ ከተማ ሰፈራ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሠርቷል። በዚህም ከንድፈ ሃሳብ ቀረጻ ጀምሮ እስከ ሂደቱ ድረስ ተጠቃሚ አሳትፈን ነው ስንሠራ የነበረው።

በአጠቃላይ የምንሠራቸው የምርምር ሥራዎች በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ ተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ላይ እንደሀገር ትኩረት ሰጥተው ሥንሠራ ቆይተናል። የዚህ ዓመት ሆነ የቀጣይ የተወሰኑ ዓመታት በዚህ ላይ ትኩረት የሚሠሩ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በተያዘው በጀት ዓመት የተመረቁት 22 የምርምር ፕሮጀክቶች ፋይዳቸው ምንድነው?

አስራት (ዶ/ር)፡– እነዚህ የምርምር ፕሮጀክቶች በጣም ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። መማር ማስተማሩንና ምርምሩን፣ ከማገዝ፣ በተለይ የምንሰጠውን የሆስፒታል አገልግሎት ከማሳለጥ አኳያ ድርሻቸው የሰፋ ነው። ጥራት ከመጨመር አኳያ ትልቅ ፋይዳ አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ተደራሽነትን፣ የመቀበል አቅም፣ አገልግሎትን የመስጠት አቅምን ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ አላቸው።

እነዚህ 22 ፕሮጀክቶች ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የተጠናቀቁ ቢሆኑም የዩኒቨርሲቲውን የሰባና የማስተማሪ ሆስፒታሉን የ 100 ዓመታት ምሥረታ በዓል አካባበር አካል ሆነው ሰብሰብ አድርገን አስመረቅናቸው እንጂ ፕሮጀክቶቹ ቀደም ሲል በነበሩ አመራሮች ተጀምረው አሁን የተጠናቀቁም አሉ።

ከእነዚህ መካከል አምስት የሚሆኑት ቀደም ባሉት አመራሮች የተጀመሩ ሲሆኑ እነርሱን የማስቀጠልና የማጠናቀቅ ሥራ ተሠርቷል። ቀሪዎቹ 17 የሚሆኑትን ፕሮጀክቶች ደግሞ በእኛ ዘመን ተጀምረው የተጠናቀቁ ናቸው። እነዚህ ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ ሆስፒታል ላይ የሚገኙ እንደመሆናቸው የሆስፒታሉን አገልግሎት፣ የሆስፒታሉን የጤና ትምህርትና የሆስፒታል የመቀበል አቅም ከመጨመር አኳያ የሚኖራቸው ፋይዳ ብዙ ነው።

ለምሳሌ የካንሰር የጨረር ህክምናን በሀገር አቀፍ ደረጃ አራት ማዕከላት ብቻ ያሉት ሲሆን ይሄንኛው አምስተኛ ነው። የዚህ ማዕከል መከፈት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ለአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ክልሎችም (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ትግራይና ሱዳን) ሳይቀር አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ጎንደር የምትታወቅበት ታሪኳ የበለጠ እንዲጎላና የህክምና ማዕከል እንድትሆን በማድረግ የህክምና ቱሪዝምን የሚያስፋፋ ነው።

የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከሉም እንዲሁ ቀደም ሲል ኦክስጂን አዲስ አበባ ወይም ከባህርዳር ነበር የምናመጣው። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኦክስጂን በወቅቱ ማምጣት ከባድ ፈተናዎች ገጠመውናል። አሁን ኦክስጂን ለእኛ ብቻ አይደለም ለአካባቢያችን ላይ ላሉ ሆስፒታሎች ጭምር ማከፋፈል እንችላለን። እኛ ጋር ደግሞ በተለይ 90 በመቶ ያህሉ ታካሚ ኦክስጂን የሚፈልግ ነው። ስለሆነም በሲሊንደር ከቦታ ቦታ ማድረሱ እንዳለ ሆኖ ኦክስጂን ከማምረቻው በመስመር ወደ ታካሚ እንዲደርስ ተደርጓል።

የሰው ሠራሽ አካል ማምረቻ ማዕከልም ከተመረቀው ፕሮጀክት አንዱ ነው። በጦርነት፣ በመኪና አደጋ፣ በተለያዩ ጉዳቶች ምክንያት የአካል ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። ይሄንን በሰው ሠራሽ አካል የመተካት ሥራ እየተሠራ ነው።

ሌሎች ብዙ የተሠሩ ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን የከተማ የኮሪዶር ልማት ጋር ተያይዞ ዩኒቨርሲቲያችንን ውብ በማድረግ የጊቢ ውበት ሥራዎች ተሠርቷል። ዩኒቨርሲቲያችንን እጅግ ውብ ለተማሪዎች፣ ለሠራተኞቻችንና ለደንበኞች ማራኪ፣ ውብና ምቹ  ሆኖ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲያከናውን የሚያስችል አውድ ፈጥረናል።

ሌላው ከፕሮጀክቶቹ መረሳት የሌለበት የማህበረሰቡ ሬዲዮ ነው። በርግጥ ለመጀመር ዘግይተናል። ይሁን እንጂ በማህበረሰብ ሬዲዮ ለጎንደርና አካባቢዋ ማህበረሰብ ተደራሽ ሆነናል። በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በንቃተ ሕግ ማህበረሰቡን የምናነቃበትና እኛም ደግሞ ከማህበረሰብ ግብዓት የምንሰበስብበትና አገልግሎታችንን የምናሻሻልበት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ከጋዜጠኝነትና ብሮድካስት ጋር ተያያዥ የሆኑትን ትምህርት ክፍሎች የተግባር ትምህርት የምንሰጥበት ነው። ይህም ጥራት ያለው ባለሙያ እንዲወጣ ሆስፒታሉ ለጤና ምሩቃን እንደሚሰጠው አይነት አገልግሎት እንዲሰጥ ያግዛል።

በአጠቃላይ በ22ቱም አሁን የምንፈልገውን ጥራት የሚያመጡ፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ምቹ የሥራ ቦታን የሚፈጥሩ ናቸው። እነዚህ ፕሮጀክቶቹም አሠራራችንን በማዘመን ወጪ ቆጣቢና ተጠያቂነትን የሚያሰፍንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ናቸው። በሁሉም ፕሮጀክቶቻችን ያለው ድምር ውጤት ተልዕኳችንን ማሳካት ያግዛል። መማር ማስተማሩ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠትና ጥራት ያለው ብቁ ዜጋ እንዲወጣ ያስችላል። በተመሳሳይ የምንሠራቸው የምርምር ሥራዎች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ ያስችላል። የምንሰጣቸው የማህበረሰብ አገልግሎቶችንም እንዲሁ በተመሳሳይ የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ እንዲሆኑ ያግዛል።

አዲስ ዘመን፡- የመማር ማስተማር ሂደቱን በማዘመን ዲጂታል ከማድረግ አኳያ እየተሠሩ ያሉት ሥራዎች ምንድናቸው?

አስራት (ዶ/ር)፡- ዩኒቨርሲቲው ዲጂታላይዜሽን ላይ ትኩረት ሰጥቶ ብዙ ሥራዎች ሠርቷል። አሠራሮቻችን ወረቀት አልባ፣ ፈጣንና ደንበኛ ተኮር እንዲሆኑ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ለምሳሌ ‹ስቱደንት ፎርሜሲስ ሲስተም› ከምዝገባ ጀምሮ እስከ ምረቃ ድረስ ያለው የተማሪዎች ውጤትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚይዝ የመረጃ ሥርዓትን ተዘርግቷል።

ተማሪዎቹ ከዩኒቨርሲቲው ከወጡ በኋላ ምሩቃን ወይም አልሙናይ የምንከታተልበት የመረጃ ሥርዓት አለን። እንዲሁም ተማሪዎቻችን የትምህርት ክፍል ሲመርጡ የምንለይበት ግልጽ የሆነ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር አድርገናል። እንዲሁም ደንበኞች አገልግሎት ሲፈልጉ ኦንላይን አሠራር በመጠቀም የሚፈልጉት አገልግሎት የሚጠይቁበትን ሥርዓትም ተዘርግቷል።

አሁን ላይ ትምህርት ሚኒስቴር የጀመራቸው የቁልፍ ውጤት አመላካች /ኪፐርፎርማንስ ኢንዲኬተር/ የምንከታተልበት ዳሽ ቦርድ የሚባል ሶፍት ዌርም ሳይቀር ወደ ሥራ ገብቷል። ይህም በሆስፒታላችንም በዚህ ዓመት የምናስመርቀው ፕሮጀክት መካከል አንዱ ነው።

የኤሌክትሮኒክስ ሜዲካል ሪከርድ ወይም ወረቀት አልባ በሆነ አሠራር የታካሚዎቻችን መረጃ ሚስጥራዊነታቸው በተጠበቀ መንገድ በዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ማያያዝ አንዱና ትልቅ ሥራ ነው። ይህም በዚህ ዓመት የተከናወነ ትልቅ ስኬት ነው።

የዩኒቨርሲቲው መምህራን ለምርምር ሲወዳደሩ ቀደም ሲል የሚያስገቡት ሥርዓት ብዙ ወረቀት ይፈጅ ነበር። አሁን ግን አዲስ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ተግባራዊ አድርገናል። ተሽከርካሪዎቻችን የምንቆጣጠርበት ኢ-ፊሊት ማኔጅመንት ሲስተም ተግባራዊ አድርገናል። የደህንነት ካሜራዎች አሉ።

ቤተመጻሕፍታችን ዘመናዊ አሠራር የተዘረጋ ሲሆን ቤተመጻሕፍት አያያዝ ሥርዓቱ ከመግቢያ በር ጀምሮ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለውን ሂደት የደህንነት ክትትል ያደርጋል። ለምሳሌ ተማሪው በር ላይ ሲገባ ውስጥ ላይ ምን ያህል ወንበር እንደቀረና የሚፈልገውንም መጽሐፍ የሚያገኝበት ሁኔታ ያመላክታል። ለቤተመጻሕፍት ለሠራተኞችም እንዲሁም ያለ ቦታው የተቀመጠ መጽሐፍ ካለ የሚለይና ወደ ነበረበት ቦታ እንዲመልሱ የሚያግዛቸው እጅግ ዘመናዊ የሆነ ሥርዓት ነው።

የሰዓት መቆጣጠሪያ (አቴንዳንስ ሲስተም) ሠራተኞች ጣት ዐሻራ ቁጥጥር የሚያደርግበትን ሥርዓት ዘርግተናል። ሌሎች በሂደት ላይ ያሉ የሶፍት ዌር ሲስተሞችም አሉ። ለምሳሌ ኮምፒዩተር ቤዝድ ቴስቲንግ (በኮምፒዩተር ብቻ ፈተናዎችን መስጠት) ከዚህ ቀደም በወረቀት ይሰጥ የነበረው የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት በኮምፒዩተር ብቻ አድርገነዋል። መምህራን እድገት ሲጠይቁ በወረቀት ሲሠራ የነበረው በሲስተም እንዲሆን ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። ዘመናዊ የሆነ የዳታ ማዕከል ግንባታው እየተጠናቀቀ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው ሌሎች ዘርፈ ብዙ የሆኑ ዘመናዊ ዲጂታል ሥርዓት እየዘረጋ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ጊዜያት ራስ ገዝ እንዲሆን ከተመረጡት መካከል አንዱ ነው። ራስ ገዝ እንዲሆን የማድረጉ ዝግጅት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አስራት (ዶ/ር)፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚ ሆኖ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ምሳሌ እየሆነ ይገኛል። ከእሱ ቀጥሎ ራስ ገዝ የመሆን አቅም አላቸው ተብለው ዘጠኝ የሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ተለይተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነው። ራስ ገዝነት ዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ የአስተዳደር ነጻነት የሚያጎናጽፉ ተልዕኮዎቻችን ላይ ትኩረት አድርገን ጥራት ያለው መማር ማስተማር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ ምርምር ሊሰጥ የሚያስችል ነው።

ከዚህ ረገድ ባለፉት አራት ዓመታት ዩኒቨርሲቲው ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ቀደም ብለን ነው የጀመርነው። እንደሀገር 2013 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው የአስር ዓመት እድገት እቅድም አካል ነው። ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ከ40 በላይ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች፣ ተዘጋጅተዋል። ሀብት ለመፍጠር የሚያስችሉ የገቢ ተቋማት ተፈጥረዋል። በተለይ ከ2013 ጀምሮ ከመማር ማስተማሩና ከምርምሩ ጋር እያስተሳሰርን በአንድ በኩል ገቢ እየፈጠሩ ነው። በሌላ በኩል መማማሪያና ምርምር መሥሪያም እየሆኑ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ እድል እየፈጠሩ ያሉ ገቢ የምናገኝባቸው ተቋማትን ፈጥረናል። ሞዴል ፋርማሲ አለን። በእነዚህ የጤና ባለሙያዎች ይሳተፉባቸዋል። ለአካባቢው ጥራት ያለው መድኃኒት ያቀርባሉ። የሥራ እድልን ፈጥረዋል። ጥራት ያለው መድኃኒት በማቅረብ ገበያም ያረጋጋሉ። በተጨማሪም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (አይሲቲ)ና የምህንድስና ማማከር አገልግሎት ይሰጣል። እነዚህም መምህራንና በቀጥታ ተያያዥ የሆኑ ትምህርት ክፍሎች ይሳተፋሉ። ትምህርታቸውን አብረው እየተገበሩ ሙያቸውን እያዳበሩ ለመማር ማስተማሩም የመመራመር አቅም እየጨመሩ ነው።

ሌሎች የእንጨትና ብረታብረት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የማተሚያ ቤት፣ የሲኦሲ ማዕከል እና ሌሎች 10 በላይ የሆኑ ዘርፎች አሉት። ስለሆነም አቅምን ከመፍጠር አኳያ ሰፊ ሥራዎችን ሠርተናል።

ሌላው ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስለራስ ገዝ ምንነት እንዲያውቅ ማድረግ፣ አውቆት ጥቅሙን ተረድቶ በአፈጻጸም አጋዥ እንዲሆን ወደ ራስ ገዝነት ማሰለፍ እንዲቻል የሚያስችሉ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር በተደጋጋሚ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተሠርተዋል።

ከዚህ ባሻገርም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአሜሪካ ኤምባሲዎች፣ እና ሌሎች ራስ ገዝ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ተሞክሮዎችን መውሰድ ተችሏል። በቅርቡም የፈረንሳይ ዩኒቨርሲተዎችን ተሞክሮ ለመውሰድ ዝግጁቱን አጠናቅቋል። ተሞክሮዎችን በመውሰድ እያዳበርን ተቋማችን በትክክል የምርምርና ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀዋል።

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር ራዕይና ተልዕኮውን ከማሳካት ባሻገር የተረጋጋ ሰላማዊ አካባቢ ከመፍጠር አንጻር እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

አስራት(ዶ/ር)፡- መማር ማስተማር፣ ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ሰላምን ይፈልጋል። ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የሰላም መድረኮችን ሲያዘጋጅ ቆይቷል። በተለያየ ጊዜያት የተፈጠሩ ሀገራዊ አካባቢያዊ ግጭቶችም ወቅት ከሰላም ጋር ተያያዥ የሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች ወጣት አደረጃጀቶችን የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ያሳተፉ መድረኮች ተካሂደው ነበር። ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር ሂደት ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ‹‹የጎንደር ቃልኪዳን ቤተሰብ››በሚል ሰፊ ሥራዎች ሠርቷል።

ይህ የጎንደር ቃልኪዳን ቤተሰብ በ2012ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ለ6ኛ ዙር ተካሂዷል። ከክልል የሚመጡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጡ ባይተዋርነት እንዳይሰማቸውና ስጋት እንዳያድርባቸው ጎንደር ላይ ቃል ገብቶ እንደ ልጁ የሚንከባከብና የሚያግዝ ቤተሰብ የመፍጠር ሥራ ነው። ይህ ፕሮጀክትም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲፈጠር በማድረግ ሰፊ ውጤት አምጥቷል።

ተማሪዎቻችን ተረጋግተው ተማሩ ማለት የሚጠበቅባቸውን እውቀት ክህሎትና አመለካከት ይዘው እንዲወጡ ያስችላል። ወላጆቻቸውን እንዲረጋጉ አስችሏቸዋል። በተለይም ደግሞ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ትልቅ ስጋት ውስጥ ያለ ወላጅ ወደጎንደር ዩኒቨርሲቲ ልጁን አልክም የሚል ስጋት እንዳይገባው ትልቅ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። ይህንንም አጠናክሮ መያዝ እንደፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን በቋሚነት የሲቪል ሰርቪስ መደብ ተፈቅዶለት እየተሠራ ይገኛል። የሰላም ሚኒስቴርም ይህ ተሞክሮ እንዲሰፋ ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች ከተሞችና ከንቲባዎች የያዘ ጎንደር ከተማ ላይ ያካሂዳል። ለዚህ የሚሆኑ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ተቋማችን መማር ማስተማሩን ሥራና ተልዕኮዎቹን እንዲያሳካ ማድረግ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው የሰው ኃይል በማብቃት በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚሠራቸው ሥራዎች ካሉ?

አስራት (ዶ/ር)፡- የሰው ኃይል ለማብቃት የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን በመስጠት ብዙ ሥራዎች ይሠራሉ። ከረጅም ጊዜ አኳያ ሁሉም መምህራን የሦስተኛ ዲግሪ እንዲኖራቸው ይፈለጋል። ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ በትንሹ ተባባሪ ፕሮፌሰርና ከዚያ በላይ መሆን መቻል አለበት። ይህንን ለማሳካት አንዱ የሰው ኃይል ልማት በትኩረት እየሠራን ነው። አሁኑ ሰዓት ከ700 በላይ መምህራን በሀገር ውስጥና በውጪ በተለያዩ ሀገራት ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እየሠሩ ይገኛሉ። በተቋማችንም የሚማሩ መምህራን በርካታ ናቸው። ከመምህራን ውጪው የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት የትምህርት እድል የሚያገኙበት ሥርዓት ዘርግተን በየአመቱ ኮታ እየሰጠን እናስተምራለን።

ከዚህ ባሻገር አጫጭር የሥራ ላይ ስልጠናዎችን በትኩረት እንሰጣለን። በተለይ ተተኪ አመራር ለማፍራት ‹የፖስት ግራጅዌት ኤንድ ሊደርሺፕ ዲፕሎማ› በሚል ሠራተኞችን በመመልመል የአንድ ዓመት ስልጠና ይሰጣል። ሌሎች አጫጭር ልዩ ስልጠናዎችንም ለሴት መምህራን ይሰጣል። ለወጣት ተመራማሪዎች ልዩ ስልጠናዎች እንሰጣለን። ተሞክሮ ያላቸው ታዋቂ ስኬታማ ሰዎችንም በማምጣት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስልጠና እንሰጣለን። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤቱ የመምህራን ልማት የሠራተኛ አቅም ማሳደግ ነውና ሰው ላይ ካልሠራን ይህ ሁሉ የምንሠራው መሠረተ ልማት ብቻው ዋጋ የለውም። ለዚህም አመለካከትን የሚቀየሩ፣ እውቀትና ክህሎትን የሚጨምሩ የሥራ ላይና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሠሩ ነው የሚገኙት።

አዲስ ዘመን፡- የማህበረሰብ አገልግሎት ከማስፋት አንጻር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

አስራት (ዶ/ር)፡– ማህበረሰብ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ እጅግ ዘርፈ ብዙ ሰዎች ይሠራሉ። በትምህርት ለክልሉና ለአካባቢው ማህበረሰብ የትምህርት እድል በመስጠትና የአካባቢውን ትምህርት ቤቶችን የማጠናከር ሥራ ይሠራል። ዩኒቨርሲቲው ሞዴል ትምህርት ቤት ያለው ሲሆን ከኬጂ ጀምሮ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርት ይሰጣል። ይህም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ልጆች የሚማሩበት ነው። ይሁን እንጂ ለአካባቢው ትምህርት ቤቶች እንደሞዴል ሆኖ ስታንዳርዱን ጠብቀው በማስተማር የጥራት ተምሳሌት እንዲሆን በማድረግ አርአያ ሆኗል። ሌሎች የአካባቢው ትምህርትቤቶች ይህንን አርአያ ተከትለው እንዲሠሩ የማድረግ ሥራ ሠርተናል።

በጤናው በተመሳሳይ ሰፋፊ ሥራዎች ናቸው የሚሠሩት። በሆስፒታል ውስጥ ከሚሰጡ አገልግሎቶች በተጨማሪ የጤና ባለሙያዎቻችን ከቦታ ወደ ቦታ እየተንቀሳቀሱ የሚሰጡት አገልግሎት በጣም ሰፊ ነው። ለምሳሌ የዓይን ሞራ ግርዶሽ በሁሉም ክልሎች አካባቢዎች ከቦታ ወደ ቦታ እየተንቀሳቀሱ አገልግሎቱን በመስጠት ለበርካቶች ተደራሽ መሆን ችለዋል።

በግብርና ዘርፍም የግብርና መካናይዜሽን እንዲተዋወቅ በማድረግ ትራክተሮችና፣ ኮምባይነሮች ተገዝተዋል። በተለይ በምስራቅ ደንቢ አካባቢ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ የተሠራው ሥራ አርሶ አደሩን ከተለምዶ አሠራር እንዲወጣ የሚያስተምሩና ግብርና መካናይዜሽን ላይ ባለሀብት እንዲገባበት የሚያደርጉ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል።

በተጨማሪም በአትክልትና ፍራፍሬም በአካባቢው የማይታወቁ የማምጣትና የማላመድና አርሶ አደሩን ማሰልጠን በሥራው እንዲሰማራና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። የግብርና ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ሥራም ተሠርቷል። በተለይ ሩዝ ምርት ዘሩን ተደራሽ በማድረግ በደንብ እንዲተዋወቅ ተደርጓል።

ስማርት ሲቲን ከመፍጠር ረገድ ጎንደር ከተማ ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን አዲስ አበባ ጨምሮ የሌሎች ከተሞችን ተሞክሮ በመውሰድ እየተተገበረ ነው። በኮሪዶር ልማቱ የጎንደር ከተማ ዲዛይን በዩኒቨርሲቲው ነው የተሠራው። 15 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ከዲዛይን እስከ ክትትል እየተሠሩ ናቸው።

በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ጋር ያለው ትስስር ከፍተኛ ነው። በእያንዳንዶች ዘርፎች የማህበረሰብ አገልግሎት ይሰጣሉ። በሕግ ዘርፍ በጎንደርና በአካባቢው 18 የሚሆን በነጻ የሕግ ማዕከላት አሉ። ጠበቃ ገዝተው መከራከር ለማይችሉ ወገኖች የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት መምህራንና ተማሪዎች ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ይሰጣሉ። ይህም በአንድ በኩል እንደ ሕጋዊ ክሊኒክ ስለሆነ ተማሪዎች በሙያቸው የተግባር ትምህርት የሚያገኙበት ነው። በሌላ በኩል በተለይ ሴቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያንን የመሳሰሉ ጠበቃ ማቆም ለማይችሉ ዜጎች ተጠቃሚ ያደርጋል።

ባለፉት ዓመታት ተከስቶ በነበረው ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች መልሶ በማቋቋም ረገድ የተሠሩ ሥራዎች ብዙ ናቸው። መልሶ ከማቋቋም ባሻገር የጉዳቱን መጠን በማጥናት ለክልሉ መንግሥት አቅርበናል።

ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ ተሳትፎ ከማህበረሰቡ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው። በዚህ ምክንያት የአካባቢ ማህበረሰብ ተቋሙን እንደብቸኛ ነው የሚያየው። ጉዳቶች እንዳይደርሱም ሕዝቡ ይጠብቀዋል። ይህም አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጓል።

አዲስ ዘመን፡-የዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ዓመታት የትኩረት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው? ምን ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለው ያስባሉ?

አስራት (ዶ/ር)፡- ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከተመረጡ ስምንቱ ዩኒቨርሲተዎች አንዱ ነው። የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብሎ መመደቡ ብቻውን በቂ አይደለም። እንደምርምር ዩኒቨርሲቲ የሚጠበቁበት ሥራዎች አሉ። ሙሉ የምርምር ዩኒቨርሲቲ የመሆን ሥራዎች ትኩረት ሰጥተውን የምንሥራባቸው ይሆናል። ራስ ገዝ ከመሆን አኳያም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ስለሚገኙ እውን በማድረግ ወደ ራስ ገዝነት መሸጋገር ሥራዎች ትኩረት ተደርገው ይሠራሉ።

ዩኒቨርሲቲው መማር ማስተማርም፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የሚያሳልጡ በሂደት ላይ ያሉ ብዙ ፕሮጀክትቶች አሉ። እነዚህ የማጠናቀቅ ሥራዎች እንሠራለን። ከ70ኛና 100ኛ ዓመት ጋር ተያይዞም ገና ይፋ የሚደረጉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች አሉ። ምቹ የሥራ አካባቢን ከመፍጠር አኳያም የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም የሚቀሩ ሥራዎች ስላሉ እነዚህ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ከሠራናቸው ያልሠራናቸው ሥራዎች ይበልጣሉ ብለን ስለምናስብ ብዙ ሥራዎች ይቀሩናል ብለን እናምናለን።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ ምስጋና እናቀርባለን

አስራት(ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You