ኢራን “በወራት ውስጥ” ቦምብ ለመሥራት የሚያስችል ዩራኒየም ማበልፀግ እንደምትችል ተጠቆመ

ኢራን ቦምብ ለመሥራት የሚያስችል ዩራኒየምን እንደገና “በወራት ጊዜ ውስጥ” ማበልፀግ ለመጀመር የሚያስችል አቅም እንዳላት፣ የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ኃላፊ ተናገሩ። የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮስሲ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ አሜሪካ በሦስት የኢራን የሚሳዔል ተቋማት ላይ ያደረሰችው ድብደባ ከባድ ቢሆንም “አጠቃላይ” ጉዳት አለመድረሱን ተናግረዋል።

ይህ የኃላፊው ሃሳብ ዶናልድ ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት “ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል” ሲሉ ከተናገሩት ጋር ይቃረናል። “እውነቱን ለመናገር አንድ ሰው ሁሉም ነገር እንደወደመ እና ምንም የቀረ የለም ብሎ መናገር አይችልም” ሲሉ ግሮሲ ተናግረዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 13 ቀን 2025 እስራኤል ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመሥራት ተቃርባ ነበር በማለት በኢራን የኒውክሌር እና ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት አድርሳለች። በኋላ ላይም አሜሪካ ጥቃቱን በመቀላቀል በሦስቱ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት፡ ፎርዶ፣ ናታንዝ እና እስፋሃን ላይ የከባድ ቦምብ ድብደባ አካሂዳለች፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በኒውክሌር ተቋማቱ ላይ የደረሰው ትክክለኛ የጉዳቱ መጠን ግልጽ አይደለም ተብሏል።

ግሮሲ እንደተናገሩት ቴህራን “በወራት ጊዜ ውስጥ… ጥቂት ሴንትሪፉጆችን (ማብላያዎችን) በማሽከርከር የበለፀገ ዩራኒየም ያመርታሉ” ብለዋል። አክለውም ኢራን አሁንም “የኢንዱስትሪ እና የቴክኖሎጂ አቅሞችን ይዘዋል… ስለዚህ ከፈለጉ ይህንን እንደገና መጀመር ይችላሉ” ብለዋል ።

የተባበሩት መንግሥታት የኢራን የኒውክሌር አቅም አሁንም ሊቀጥል እንደሚችል ሲጠቁም የመጀመሪያው ተቋም አይደለም። በተጠናቀቀው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፔንታጎን የደኅንነት ተቋም ግምገማ የአሜሪካ ጥቃቶች የኢራንን የኒውክሌር መርሐ ግብር በወራት ብቻ ወደ ኋላ እንዲመለሱ አድርጓል ሲል ተናግሯል።

ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ሲሉ በቁጣ ምላሽ የሰጡ ሲሆን የመገናኛ ብዙኃንን “በታሪክ ውስጥ ስኬታማ ከሆኑ ወታደራዊ ጥቃቶች አንዱን ለማሳነስ ሙከራ አድርገዋል” ሲሉ ከስሰዋል። ለጊዜው ኢራን እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተዋል። ትራምፕ ኢራን ዩራኒየሟን እንደገና እንደምታበለፅግ የሚያሳይ መረጃ ካገኙ ዳግም “ያለማቅማማት” ድብደባ ለመፈፀም እንደማያወላውሉ ተናግረዋል።

ኢራን በበኩሏ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበት እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መልዕክቶችን አስተላልፋለች። የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ ባለፈው ሐሙስ ዕለት ባደረጉት ንግግር ጥቃቱ ምንም ፋይዳ የለውም ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አባስ አራግቺ ግን “ከመጠን በላይ እና ከባድ” ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ኢራን ከመንግሥታቱ ድርጅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙነት ረቡዕ ዕለት ፓርላማው ከአቶሚክ ተቆጣጣሪው ጋር ያለውን ትብብር ለማቆም ሲወስን፣ ኤጀንሲው ከእሥራኤል እና ከአሜሪካ ጋር ወግኗል ሲል ወንጅሎታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ወር ቴህራን ከ 20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባችውን ግዴታ ጥሳለች ማለቱን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ኢራንን አጥቅተዋል። ኢራን የኒውክሌር መርሐ ግብሯ ለሰላማዊ ጥቅም ብቻ እንደሚውል በተደጋጋሚ ትናገራለች።

ኢራናውያን ከመንግሥታቱ ድርጅት ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ ግሮሲ አሁንም ከቴህራን ጋር መደራደር እንደሚቻል ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል። “ከኢራን ጋር ቁጭ ብዬ ይህን ጉዳይ ማየት አለብኝ። ምክንያቱም በስተመጨረሻ ላይ ይህ ሁሉ ነገር ከወታደራዊ ጥቃት በኋላ ዘላቂ መፍትሔ ሊኖረው ይገባል። ያ ደግሞ ያለ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ሊሆን አይችልም” ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ከዓለም ኃያላን ሀገራት ጋር በተደረገው የኒውክሌር ስምምነት ኢራን ከ 3.67 በመቶ በላይ ዩራኒየም እንድታበለፅግ አልተፈቀደላትም። በዚህን ያህል መጠን የበለፀገ ዩራኒየም ለኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ነዳጅ ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ደረጃ ያሟላ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለ15 ዓመታት በፎርዶ የኒውክሌር ተቋም ምንም ዓይነት ዩራኒየም ማበልፀግ አልተፈቀደላትም። ሆኖም ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ስምምነቱን ኢራንን ቦምብ ለመሥራት ከሚወስዳት መንገድ ለማስቆም በጣም ጥቂት ነገር ብቻ ነው ያከናወነው በማለት ማዕቀብ ጥለዋል።

ኢራን በምላሹ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ዩራኒየም ከማበልፀግ ጋር የገባችውን ስምምነት ጥሳለች። እአአ በ 2021 በፎርዶ ዩራኒየም ማበልፀግ የጀመረች ሲሆን፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ተቆጣጣሪ ዘጠኝ የኒውክሌር ቦምቦችን መሥራት የሚያስችል 60 በመቶ የበለፀገ ዩራኒየም አከማችታለች ሲል ሪፖርት አድርጓል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You