ሲምፖዚየሙ የጉራጌን ሕዝብ ባህልና ቋንቋ ወጥ የሆነ ይዘት እንዲኖረው እንደሚያደርግ ተጠቆመ

ወልቂጤ፡- ሲምፖዚየሙ የጉራጌን ሕዝብ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ወጥ የሆነ ይዘትና ቅርጽ እንዲኖረው ያደርጋል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የጉራጌ ባህል ቋንቋ እና ታሪክ ሲምፖዚዬም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በጉራጌ ባህል ማዕከል አዳራሽ ትናንት ሲከበር እንደገለጹት፤ የጉራጌ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ሲምፖዚየም የሕዝቡን ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ወጥ የሆነ ይዘትና ቅርጽ እንዲኖረው ያደርጋል። ጉራጌ ዘመናትን ያስቆጠረ የባህል፣ የቋንቋና የታሪክ ዕሴት ያለው ማኅበረሰብ ነው ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ሕዝቦች በጋራ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ታሪካቸውን ለመሰነድ፣ ቋንቋቸውን የጋራ ለማድረግና ባህላቸውን ለማስተሳሰር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይቷል ብለዋል።

የጉራጌ ሕዝብ አንድነቱን በማጠናከር ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ያለውን ትስስር በላቀ መልኩ እንዲያጠናከር የተጀማመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።

የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሐሰን የጉራጌ ባህልና ቋንቋ ሲፖዚየም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመግለጽ፤ ሲፖዚዬሙ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጎልበት ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር ለዘመናት በአብሮነት የቆየውን ትስስር ይበልጥ ለማጽናት የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

አቶ ሙስጠፋ፤ የጉራጌ ሕዝብ ሥራ ወዳድ፣ ታታሪ፣ ቁጠባን ባህሉ አድርጎ የራሱ ሕይወት ከማሻሻል እስከ ሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲሁም በንግድ ሥራ ጠንካራ ማኅበረሰብ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ የጉራጌ ማኅበረሰብ የበርካታ ቱባ ባህላዊ ዕሴቶች፣ ሀገር በቀል እውቀቶች፣ ቋንቋ እና ታሪክ ባለቤት መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህን ለማጥናትና ለትውልድ ለማስተላለፍ ጠንክሮ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ቋንቋ የማንነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ የጉራጊኛ ቋንቋ እንዲለማ፣ እንዲዳብርና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም አሳስበዋል።

በሲምፖዚየሙ የጉራጌ ማኅበረሰብ ባህል፣ ወግና ዕሴት የሚዳስስ “ኤማንዳ” የተሰኘ ፊልም ለእይታ ቀርቧል። ዘጋቢ ፊልሙ የጉራጌ መስቀልና አረፋ፣ ጢያ ዓለም አቀፍ ትክል ድንጋይ ገፅታ፣ የጉራጌ እናቶች አንትሮሽት አከባበር፣ ስለተለያዩ የዞኖቹ መስኅቦች፣ የጉራጌ ድምቀት የሆነው አዳብና በዓል አከባበር ይዳስሳል።

የጉራጌ ሕዝብ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ሲምፖዚዬም የሁለቱ የጉራጌ ዞን አስተዳደሮች፣ የጉራጌ ልማትና ባህል ማኅበር እና የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በጋራ እንዳዘጋጁት ታውቋል።

ያሬድ ጌታቸው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You