አመራሮቹ ሊከፈላቸው ከሚገባው ጥቅማ ጥቅም በላይ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመንግሥት ከፍተኛ ተሿሚዎች የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ሕግ መሠረት በአንድ ዓመት ውስጥ ሊከፈል ከሚገባው ብር በላይ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ መከፈሉን በፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታውቋል፡፡

ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ተቋማቸው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የሂሳብ የፋይናንስ የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 1224/2012 (እንደተሻሻለ) አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የዋና ኮሚሽነር፣ የምክትል ዋና ኮሚሽነር እና ሌሎች ኮሚሽነሮች ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅሞች በመንግሥት ከፍተኛ ተሿሚዎች መሠረት ተፈጻሚ እንደሚደረግ የተገለጸ ነው፡፡

ነገር ግን ኮሚሽኑ ከግንቦት 2015 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም ድረስ ባለው መከፈል የነበረበት ብር 1 ሚሊዮን 18ሺህ 190 ቢሆንም ብር 5 ሚሊዮን 267ሺህ 8 ብር በመክፈል አለአግባብ ብር 4 ሚሊዮን 248ሺህ 818 የተከፈለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ለቤት አበል በመመሪያው ከተቀመጠው በላይ 211ሺህ 500 ብር ብልጫ የተከፈለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ክትትል እና ፕሮጀክቶች አፈፃፀም በተመለከተ፤ የፕሮጀክት ፕሮፖዛሎች ሲቀርጽ በፕሮፖዛል የሚተገበሩ ተግባራቶች እንደ አማራጭ የተቀመጡ መሆኑ አመልክተው፤ ኮሚሽኑ በገንዘብ ሚኒስቴር ከወጣው የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የጊዜያዊ ሠራተኞች ቅጥር አፈጻጸም መመሪያ 413/2013 አንቀጽ 11.3 መሠረት ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልግ ባለሙያ ሳይቀጠር ወይም ሳይመደብ ለቋሚ ሠራተኞች ደመወዝ፣ ጥቅማ ጥቅም እና የጡረታ መዋጮ ከፕሮጀክት በጀት የሚጠቀም መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዚህም በአጠቃላይ ከ2014 እስከ 2016 ዓ.ም ለቋሚ ሠራተኛ ብር 9 ሚሊዮን 403ሺህ 103 ከፕሮጀክቶች በጀት ያለአግባብ ወጪ የተደረገ መሆኑም ገልጸዋል ፡፡

አያይዘውም በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጣን ምላሽ የመረጃ ቋት ለማበልፀግ ከኅዳር 22 ቀን 2015 እስከ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም 20ሺህ ዩሮ የተመደበ ቢሆንም የመረጃ ቋቱ እንዲበለፅግ አለመደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You