ምክክሩ ስለ ኢትዮጵያ ከፍታ የጋራ እይታን የፈጠረ ነው

እንደ መግቢያ

መመካከር፣ መነጋገር፣ መወያየት፣ ሃሳብ መለዋወጥ፣… ለችግሮች መፍትሄን ብቻ ሳይሆን፤ የአንዱን ህልምና ሃሳብ ሌላኛው እንዲረዳው በማድረግ የወል መረዳት የሚፈጥር ነው። ይሄ የወል መረዳት ደግሞ የወል እሳቤን፣ የወል ሕልምን፣ የወል ትልምና ግብን ያስጨብጣል። ከሰሞኑም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሲያደርጉ የቆዩት ውይይትም በዚሁ ማሕቀፍ የሚታይ ነው።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፣ “ኢትዮጵያ ከሕዝቦቿ ጋር እየመከረች ተግዳሮቶችን በመሻገር ስኬቶቿን ታስቀጥላለች!” ሲል የገለጸውም ለዚሁ ነው። ምክንያቱም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በነበራቸው ውይይቶች ከንግዱ ማሕበረሰብ ተወካዮች፣ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ከመምሕራን፣ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ከጤና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ከሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ተወካዮች ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

እነዚህ ውይይቶች በአንድ በኩል ሙያ ተኮር እና በየዘርፉ ያሉ ችግሮችን ብሎም መልካም እድሎችን በመለየት፤ ለችግሮቹ መፍትሄን፣ ለመልካም እድሎቹም ተባብሮ መቆምን የጋራ ርዕይ ያስጨበጡ ነበሩ። ለምሳሌ፣ በዚህም ችግሮቹ በነቂስ ተለይተው በዋናነት በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ሥራ፤ አለፍ ሲልም በረዥም ጊዜ ጥረት እልባት እንደሚያገኙ መግባባት ላይ ተደርሷል።

በዘርፉ የተሠሩ እና እየተሠሩ ያሉ ጅምርና ውጤታማ ተግባራትም በልካቸው ተገልጠው ሁሉም እንዲገነዘባቸው ብቻ ሳይሆን፤ በአካል ቀርቦም እንዲመለከታቸው ተደርጓል። በተለይ እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው በርካታ ፕሮጀክቶች በተወያዮች እንዲጎበኙ መደረጉ የዚህ አንድ ማሳያ ነው። ከዚህ ባሻገር በየዘርፉም ሆነ እንደ ሀገር ያሉ መልካም እድሎችን የማመላከት እና ተግባራቶችንም የመለየት ምክክር ተደርጎ፤ እድሎቹን በጋራ ለማላቅ፤ ተግዳሮቶቹንም በወል አቅም ለመሻገር መግባባት ላይ ተደርሷል።

እነዚህ ሙያ እና ዘርፍ ተኮርም ሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ታዲያ፤ እንደየ ሙያ ዘርፉ አጀንዳዎች የየራሳቸው ምልከታ ያላቸው ነበሩ። ይሁን እንጂ ሀገራዊ ጉዳይና አጀንዳን በተመለከተ ግን ሁሉም በየሙያውና እውቀቱ፤ በየችሎታና አቅሙ ልክ የራሱን አበርክቶ መወጣት የሚቻልባቸውን አማራጮችና መንገዶች ያመላከተ ሆኗል። እኔም ለዛሬው እነዚህን መድረኮች በወፍ በረር ልዳስስ እሞክራለሁ።

ከንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያው የምክክር መድረክ፣ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ነበር። ይሄ ደግሞ ንግድና ኢንቨስትመንት እንደ ሀገር ያለውን ፋይዳ ከትኩረት ያስገባ ይመስላል። በተለይ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ ደረጃ ብሎም የቴክኖሎጂ ግስጋሴን የሚመጥን የንግድና ግብይት ብሎም ኢንቨስትመንት ሥርዓት ሊኖር የተገባ ነው።

በዚህ ረገድ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የሞራልና ሥነምግባር ሁኔታ የተስተካከለ መሆን የሚገባው እንደሆነ እሙን ነው። ከዚህ ባሻገር ግን ዘርፉ እውቀት ይፈልጋል። እውቀት አንድም የንግድና ግብይቱን የሚገነዘብ አቅም መያዝን ሲሆን፤ ሁለተኛው ዘርፉን ሊያሳልጡ የሚችሉ ዘመን ወለድ ቴክኖሎጂዎችን በልካቸው ተገንዝቦ መተግበርና መጠቀም የሚያስችል ክህሎትን መጨበጥ የግድ ይላል።

ምክንያቱም፣ ንግድ ከገንዘብ ጋር ይገናኛል። ገንዘብ ደግሞ ለአንድ ሀገር መንግሥት መንግሥታዊ ሥራዎች ማሳለጫ የጀርባ አጥንት ነው። በመሆኑም የገንዘብ ሥርዓቱ በአግባቡ ካልተመራና በተገቢው የግብይት ሰንሰለት ካልተጓዘ የመንግሥታዊ ተግባራት የጀርባ አጥንት ላይ እንከን መፍጠራቸው አይቀሬ ነው።

ከዚህ ባለፈም፣ የንግድና ግብይት ሂደቱ በሥነምግባር ያልተቃኘ፤ የእኔነት ብቻ መንፈስ ከተላበሰ ሀገር እና ሕዝብ ከዘርፉ ማግኘት ያለባቸውን እንዳያገኙ ያደርጋል። በአጭሩ በደሃ ሀገር ውስጥ እና ድሆች በበዙባት ሀገር ውስጥ ጥቂት የናጠጡ ሀብታሞች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ይሄ ሲሆንም መንግሥት በባለገንዘቦች ጡንቻ መፈተኑ፤ ሕዝብም በኑሮ ውድነት መጠበሱ ስለማይቀር፤ ሀገርና ሕዝብ ወደ ችግር እንዲገቡ መደላድል ይፈጥራል።

ይሄን መሰል አካሄድና ችግሮች ቀድሞ ከማስረዳትና ከወዲሁ ከመከላከል አኳያ ታዲያ ይሄ መድረክ ትልቅ እድል የፈጠረ ነው። ምክንያቱም በመድረኩ የንግዱ ማህበረሰብ አሉኝ የሚላቸውን ጥያቄዎች ጠይቋል፤ ፈተና ሆኑብኝ የሚላቸውን ችግሮችም አቅርቧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የንግዱን ማህበረሰብ ችግሮችና ጥያቄዎች አድምጠው በልካቸው እንዲፈቱ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ከዚህ ባሻገር ግን፣ የንግዱ ማህበረሰብ ከራስ ወዳድነት እና ካልተገባ የደላሎች ሰንሰለት ዘርፉን በማላቀቅ በሀገርም፤ በሕዝብም ላይ አንዳች ለውጥ የሚያመጣ ተግባራት እንደ ግልም፣ እንደ ዘርፍም መከወን እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይ የግብይት ሂደቱ ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ፤ በገንዘብ ዝውውር ሂደት የሚስተዋሉ ያልተገቡ አካሄዱችን በማረም፤ ከገቢና ግብር ስወራ ጋር ያሉ አሻጥሮችን በመቅረፍ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ያሳሰቡበትም ነበር።

በጥቅሉም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደ መንግሥት እስካሁን ከሠራቸው ባሻገር ያሉ የሚጠበቁበትን የቤት ሥራዎች ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት ገልጸዋል። የንግዱ ማኅበረሰብም የማኅበረ-ኢኮኖሚ ግንባታን በሚያፋጥኑ፣ ተወዳዳሪነትን እና ምርታማነትን በሚጨምሩ እንዲሁም የሥራ ባህልን በሚያሳድጉ ተግባራትን እንዲያጎለብቱ ጠይቀዋል። የሥራ እድል ፈጠራን እንዲያስፋፉ እና የሀገራዊ ልማት ውጥኖችን በማሳካት ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች

ከኢኮኖሚያዊ አውዱ ጉዳይ ቀጥሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረክ የሆነው የፖለቲካው አውድ ነው። ምክንያቱም፣ በአንድ ሀገር ልማትና እድገት ውስጥ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ሊኖር፤ የፖለቲካ ሥርዓቱም ዴሞክራሲያዊ አውድ ሊፈጠርለት የተገባ መሆኑ እሙን ነው። በመሆኑም ሁለተኛው መድረክ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር የመከሩበት ነበር።

በዚህ መድረክ ከዛሬው ባሻገር ያሉ የሰላምና ደህንነት፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ጠንካራ ሀገራዊ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲሁም ሁሉን አቀፍ አስተዳደር የመገንባት ጉዳይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መነጋገር የተቻለበት ነው። ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተበታተነ አካሄድ ሰብሰብ ያለና ጠንካራ ሆኖ የመውጣት አስፈላጊነት የተመከረበትም ነው።

በጥቅሉ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በነበረው ውይይት፤ በገዢ ፓለርቲካ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል እያደገ የመጣው የመወያየትና የመመካከር ባሕል ለሀገር ግንባታና ለፖለቲካው ምህዳር ዴሞክራሲያዊ አውድ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል። በቀጣይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ገንቢ ተሳትፎና የሰከነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እጅጉን አስፈላጊ ስለመሆኑ፤ ይሄን መሰሉ ውይይት ቀጣይነት ኖሮት ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ተቀራርበው መሥራት እንደሚገባቸው መግባባት ላይ ተደርሷል።

ከመምህራን እና ከጤና ባለሙያዎች

ሌላኛው መድረክ በአንድ በኩል ተተኪ ትውልድን በእውቀትም፣ በሥነምግባርም፣ በሞራልም አብቅተው ከሚቀርጹ መምህራን ጋር የተደረገው ውይይት ሲሆን፤ በሌላው መልኩ ደግሞ ትውልዱ አጠቃላይም የሰው ልጆች ጤናቸው እንዲጠበቅ፣ ቢታመሙም ታክመው እንዲድኑ ተግተው ከሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች ጋር የተመከረበት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለቱም ባለሙያዎች ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ጥያቄዎቻቸውን ያደመጡ ሲሆን፤ እንደየጥያቄዎቹ ባህሪም ለምላሹ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል። ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎቻቸው ባልተገባ መንገድ እንዲቀርቡ በሚያደርጉ አካላት ተጠልፈው ላልተገባ ፍላጎት እንዳይውሉ አስፈላጊውን ሥራ መሥራት እንዳለባቸውም ለባለሙያዎቹ አሳስበዋል።

በጥቅሉም ከሁለቱ የሙያ ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር የተደረገው ውይይት፤ የሰው ልጆችን በእውቀትና ክህሎት በመገንባትም ሆነ የሰው ልጆችን ጤና ከመጠበቅና ሕይወት ከመታደግ አኳያ ያላቸውን ጉልህ ድርሻ ተገንዝበው እንዲሠሩ፤ በማንሳትም ለእነዚህ ባለሙያዎች በሚመጥናቸውና የሀገር አቅም በሚፈቅድ ልክ ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ፤ ችግሮቻቸውንም ለመፍታት እንደሚሠራ፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ግን ሁሉም ሚናውን በልኩ ተገንዝቦ የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት ከመግባባት ላይ ተደርሷል።

ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች

ኪነጥበብ በሀገር ግንባታ ላይ ያለው አበርክቶ ይታወቃል። በመሆኑም የኪነጥበብ ዘርፉም ሆነ ባለሙያው ይሄን ሚናውን ከመወጣት አኳያ ያሉበት ችግሮች የተለዩበት፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት፤ ባለሙያዎች ለሙያቸው ክብርም፣ ለሀገር ከፍታም ሲሉ ምን መሥራት እንዳለባቸው እና በመንግሥት በኩል ምን መደገፍ እንደሚገባው የተመከረበት ሌላው መድረክ ደግሞ፣ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር የተካሄደው ምክክር ነው።

በዚህ ምክክር ጥበብም የሚያድገው፤ ጥበበኛም የሚበዛው ሀገር ስትኖር፤ ሀገር ስታድግና ስትበለጽግ እንደመሆኑ፤ ዘርፉ በሀገር ግንባታ ውስጥ ያለውን ሚና እንዲወጣ በማስቻል በኩል የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከግላዊ ዝና ባሻገር ያላቸውን ሀገር እያሰቡ መሥራት እንደሚገባቸው የወል ግንዛቤ የተያዘበት ነው።

ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች

በመጨረሻ የተካሄደው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግል እና ከሕዝብ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነት ተወካዮች ጋር የመከሩበት ነበር። ከግል እና የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን እና የሕዝብ ግንኙነት ተወካዮች ጋር በነበራቸው ምክክርም ነፃ እና ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ ዴሞክራሲን ለማስፈን ያለውን ወሳኝ ሚና አፅንዖት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ረገድ መንግሥት የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣ ቃል የገቡበትም ነው።

በተለይ የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎች ኢትዮጵያዊ እሴትን የተላበሱ፣ ብሔራዊ ጥቅምን እንደ መልህቅ የያዙና በሙያዊ ሥነ-ምግባር የታነጹ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት። ይሄ ሲሆን ሚዲያ እንደ አራተኛ መንግሥት ሆኖ በሀገረ መንግሥት ግንባታ እና በወል ትርክት ስርጸት ላይ ሚናውን መወጣት ይችላል። ይሄ እንዲሆንም ሁሉም ሙያዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል።

እንደ መውጫ

በጥቅሉም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፉት ሳምንታት ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ከመምህራን ተወካዮች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ጋር ሁሉን አቀፍ እና ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን መገንዘብ ይቻላል። ውይይቶቹም በየዘርፉ ያሉ ፍላጎቶችና ተግዳሮቶች በነቂስ ተነስተው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሁሉንም በልኩ ያስገነዘቡበት ነበር።

በመሆኑም ይሄን መሰል መድረክ መፈጠሩ፣ በአንድ በኩል በየሙያ ዘርፉ ያሉ ችግሮች በየደረጃው ሲቀርቡ ከነበረበትና በተቆራረጠ መልኩ ሲቀርቡ ከነበረበት አካሄድ ተላቅቀው በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋ እንዲቀርቡ እድል የሰጠ ነው። ይሄ ሲሆን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎቹን በልካቸው ተገንዝበው ለመፍትሄዎቻቸው ተገቢውን አቅጣጫ ለመስጠት እድል የሰጠ ነው።

ከዚህ ባሻገር የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህልም፣ ትልምና ተግባር ባለሙያዎቹ ከራሳቸው አንደበት ፊት ለፊት አድምጠው ለህልሞቻቸው መሳካት በየዘርፉ የራሳቸውን አበርክቶ እንዲወጡ የሚያስችላቸውን ግንዛቤ የፈጠሩበት ነው። በመሆኑም የውይይት መድረኩ ከችግሮችና ፈተናዎች ባሻገር ተመልክቶ የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ውስጥ የጋራ አረዳድ ፈጥሮ በጋራ መሥራት የሚያስችል የተደመረ አቅምን ከመፍጠር አንጻር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው።

ማሙሻ ከአቡርሻ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You