አካዳሚው ለስምንተኛ ጊዜ ሠልጣኞቹን አስመረቀ

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ለስምንተኛ ዙር በስምንት የስፖርት ዓይነቶች ያሠለጠናቸውን ስፖርተኞች ከትናንት በስቲያ አስመርቋል። የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ባለፉት ተከታታይ አራት ዓመታት በስምንት ስፖርት ዓይነቶች ያሠለጠናቸውን 43 ሴት እና 57 ወንድ በድምሩ 100 ተተኪ ስፖርተኞችን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንድ፣ የተመራቂ ወላጆች፣ አሠልጣኞች፣ ታዋቂ አትሌቶች፣ ክለቦች፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች፣ የአካዳሚው አጠቃላይ ሠራተኞች እና የስፖርት ቤተሰቦች በተገኙበት በአካዳሚው የሲኒማ አዳራሽ አስመርቋል።

የምርቃት ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው እንደገለፁት፤ አካዳሚው በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ሠልጣኞችን በማሠልጠን እንደሀገር የተተኪ ስፖርተኞች እጥረትን እየፈታ ይገኛል።

አካዳሚው ለአራት ዓመታት በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቦክስን ጨምሮ በስምንት የስፖርት ዓይነቶች ያሠለጠናቸውን 100 ሠልጣኞች ያስመረቀ ሲሆን፣ ባለፋት ሰባት ዙሮች አካዳሚው አሠልጥኖ ካስመረቃቸው ሠልጣኞችም 90 በመቶ የሚሆኑት ክለቦችን በመቀላቀል ውጤት እያስመዝገቡ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በአካዳሚው የሚሰጠው ሥልጠናም ከስፖርታዊ ሥልጠናዎች ባለፈ በሥነምግባር የሚያበቃ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አንስተው፤ ይህም በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገርን ስምና ባንዲራ ከፍ የሚያደርጉ አትሌቶችን ለማፍራት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

በመሆኑም የዘንድሮ ተመራቂዎች በስፖርታዊ ብቃትና ጨዋነት የሀገራቸውን ስም እንዲያስጠሩ አደራ በማለት፤ ክለቦችም ሠልጣኞችን ተቀብለው በመያዝ ውጤታማ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ አካዳሚው ተመራቂ ስፖርተኞች በአራት ዓመታት ቆይታቸው በሀገር አቀፍ፣ አኅጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የላቀ ውጤት ያስመዝገቡ ተመራቂ ሠልጣኞችን፣ አሠልጣኞችን፣ በመደበኛ ትምህርት ውጤታማ የነበሩ ሠልጣኞችን እና በዶርምና በንፅሕና አጠባበቅ ለሌሎች አርዓያ የነበሩ ተመራቂዎችን እውቅናና ሽልማት አበርክቷል።

በመጨረሻም የዕለቱ የክብር እንግዶች ከአካዳሚው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የዕለቱ ተመራቂዎች የአካዳሚውን የአራት ዓመታት ሥልጠና ማጠናቀቃቸውን የሚገልፅ ሰርተፍኬት በማበርከት እና ተመራቂ ስፖርተኞች ቃለ-መሐላ በመፈፀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በድምቀት ተጠናቋል።

ከተመራቂዎች 100 ስፖርተኞች መካከል 31 አትሌቶች ከወዲሁ ክለብ መቀላቀል መቻላቸውንና በርካታ ክለቦች ተመራቂ ስፖርተኞቹን ለማዛወር ለአካዳሚው ጥያቄ ማቅረባቸውን በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተቋቋመበት 2005 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በ2017 ዓ.ም ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ 196 ታዳጊዎችን ተቀብሎ በልዩ ልዩ የስፖርት ዓይነቶች እያሠለጠነ ይገኛል።

በተጨማሪም በስፖርቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የጥናትና ምርምር እንዲሁም የባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች 172 ሠልጣኞችን በመያዝ ሥልጠናውን የጀመረው አካዳሚው ከጊዜ ወደ ጊዜ የምልመላ ሂደቱን እና የሠልጣኞቹን ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ውጤታማና ወጣት ተተኪ ስፖርተኞችን እያፈራ ይገኛል።

በእግር ኳስ፣ ቮሊቦል፣ ቅርጫት ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ቦክስ፣ ውሃ ዋና፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ብስክሌትና አትሌቲክስ ስፖርቶች ውጤታማና የኢትዮጵያን ባንዲራ በዓለም አደባባይ ማውለብለብ የቻሉ አትሌቶችን አበርክቷል። ለሀገር፣ አኅጉርና ለዓለም አቀፍ ውድድሮች በአካልና በአዕምሮ የላቁ እንዲሁም በሥነምግባር የታነፁ ወጣት ስፖርተኞችን በማፍራት ተስፋ ሰጪ ቁመና ላይ ይገኛል፡፡

አካዳሚው ከ2008 ዓ.ም እስከ 2012 ዓም ብቻ በሀገር ውስጥ ውድድሮች ባደረገው ተሳትፎ በአትሌቲክስ 268 ሜዳሊያዎችን እና በርካታ ዋንጫዎችን እንደወሰደ መረጃዎች ያመለክታሉ። በውሃ ዋና 97 ሜዳሊያና 2 ዋንጫ፣ በቦክስ 19 ሜዳሊያና 1 ዋንጫ፣ በወርልድ ቴኳንዶ 5 ሜዳሊያ፣ በጠረጴዛ ቴኒስና ብስክሌት 7 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብም ችሏል። በተጠቀሰው ዓመት ውስጥ አካዳሚው በእነዚህ የስፖርት ዓይነቶች በድምሩ 129 ስፖርተኞችን ለብሔራዊ ቡድን ማስመረጥ ችሏል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You