
በብሔር እና በጎጥ ቡድንተኝነት የሚያስብ ሰው ባጋጠመኝ ቁጥር አንድ የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ገጠመኝ ትዝ ይለኛል፤ ለሀገር ያለው አደጋም እንደ አቅሜ ያሳስበኛል። ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ‹‹ጠርዝ ላይ›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ የጻፉት ነው። ዶክተር በድሉ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በአንድ ኃላፊነት ላይ ሆነው ያጋጠማቸው ነው። ታሪኩ እንዲህ ነው።
አንድ ተማሪ የተማሪዎች ካፍቴሪያ ውስጥ የምትሠራ አንዲት ሴት ያፈቅራል። ልጅቷ የአካባቢው ተወላጅ ናት። ዶክተር በድሉ የአፍቃሪውን ብሄር በስም ጠቅሰው ባይናገሩም ‹‹ታዳጊ ክልሎች›› ከሚባሉት አካባቢ የመጣ መሆኑን ጠቁመዋል። ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ… ብለን ልንገምት እንችላለን።
ይሄው ልጅ ፍቅሩን ለተፈቃሪዋ ይናገራል። ልጅቷም ፈቃደኛ አልሆነችም። ልብ በሉ እንግዲህ! ይሄ በብዙ ሴቶች ላይ የሚታይ ነው። ለጠየቃት ሁሉ ‹‹እሺ›› ልትል አትችልም። ጓደኛም ይኖራት ይሆናል። ይህኔ የራሷ ብሄር ለሆነ ወንድ ራሱ ‹‹እምቢ›› ብላ ይሆናል።
አፍቃሪው ልጅ ልጅቷን መበቀል አሰበ። እሷን ብቻ ሳይሆን አካባቢውን ሁሉ መበቀል አሰበ። ለዚህም ይህን ዘዴ ፈጠረ። የራሱ ብሄር የሆኑ ጓደኞቹ ጋር ሄዶ ‹‹በብሄሬ ምክንያት እምቢ አለችኝ፣ በብሄሬም ሰደበችኝ›› አለ።
የልጁ ብሄር ተወላጆች እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ተሰባስበው መጡ። የምትሠራበት ሄደን ካልገደልናት አሉ። ጊቢው በግጭት ተናወጠ። በፌዴራል ፖሊስ ተጥለቀለቀ። እንደምንም በፀጥታ ኃይሎች ጥረት ነገሩ ተረጋጋ። ግጭት አድራሾችም ተያዙ።
አሁን በዩኒቨርሲቲው ሕግ መሠረት ሥራ ተጀመረ። ዩኒቨርሲቲው ለዲሲፕሊን ቅጣት ያወጣው ሕግ አለ። ሕጉን መሠረት አድርገው እነ ዶክተር በድሉ ሥራ ጀመሩ። በወጣቶቹ ላይ የተገኘው ጥፋት ከዩኒቨርሲቲ የሚያስባርር ሆኖ ተገኘ። ልብ በሉ! ጥፋታቸው ሰው ለመግደል የተደረገ ከባድ ወንጀል ነው።
በዚህ መሠረት ተማሪዎቹ ሊባረሩ ውሳኔ ተወሰነ። ሕጉ ግን ሊከበር አልቻለም። ከክልሉ መንግሥት ቀጭን ትዕዛዝ መጣ። ‹‹የሚባረሩት ተማሪዎች የአንድ ብሄር ተወላጆች ስለሆኑ ሆን ተብሎ ነው ያሰኘናል›› አለ የክልሉ መንግሥት። እነ ዶክተር በድሉ ‹‹እሱ አይመለከተንም! እኛ ሕጉን ጠብቀን ነው የምንሠራው!›› ቢሉም ከአቅም በላይ ሆነ። ሕጉ ይሻራል እንጂ አታደርጉትም ተባሉ። የክልሉ መንግሥት ፍራቻም የሚባረሩት ተማሪዎች የዚህ ብሄር ተወላጆች ስላልሆኑ በብሄራቸው ምክንያት ነው እባላለሁ ብሎ ነው። በእርግጥም ሊባል ይችል ነበር፤ ግን ሕግ ተጣሰ!
እዚህ ላይ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን እንመልከት። አንደኛው፤ ቅጡን ባጣው የብሄር እሳቤ ምክንያት ሕግ ተሻረ። የብሄር ጣጣን በመፍራት እንዲህ አይነት ብዙ ተመሳሳይ የሕግ ጥሰቶች ተሠርተዋል ማለት ነው። ሁለተኛው ነገር፤ በብሄር ስም ብዙ ማጭበርበር እንደሚሠራ ነው። አፍቃሪው ልጅ እንደማንኛውም ወንድ ነው እምቢ የተባለው። ብዙ ወንዶች ተመሳሳይ ገጠመኝ ነው ያላቸው። ልክ ሴት ልጅ ላይ አሲድ እንደሚደፉት ወንዶች ቂሙን መወጣት ሲፈልግ ይሄን ዘዴ ፈጠረ። ነገሩን የብሄር መልክ ካስያዘው ትልቅ ግጭት እንደሚፈጠርለት ያውቃል። ይቺን ዘዴ ተጠቅሞ የግል ቂሙን መወጣት ፈለገ። ጥቅም የሚያስገኝ ነገር ሲሆንም እንዲህ በብሄር ስም ይነገዳል ማለት ነው።
እንዲህ አይነት ነገሮች በየጊዜው እና በየቦታው የምናያቸው እና የምንሰማቸው ሆነዋል። ለምሳሌ፤ የሙዚቃ ውድድር ውጤትን ተከትሎ የነበሩ ክርክሮችን እናስታውሳለን። ውጤት ሲገለጽ ወዲያውኑ ነው የማህበራዊ ገጾች ንትርክ የሚጀመረው። ቀጥሎ ደግሞ የጋዜጦችና መጽሔቶች አጀንዳ ይሆናል። የተወዳዳሪዎችን ብሄር በምን ፍጥነት እንደሚያሰሉት ይገርማል። ነገሩን የማህበራዊ ገጾች አጀንዳ ነው ብሎ ንቆ ማለፍ ይቻል ነበር፤ ግን የማይቻልበት ምክንያት ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚነሳው ወቀሳም ተመሳሳይ ስለሆነ ነው። ይቺን ቀላሏን ነገር መነሻ አድርገን ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮችም ከሚዛናዊ ፍትህ ይልቅ የብሄር አስተሳሰብ ተፅዕኖ እንደሚያደርግባቸው ለማየት ያስችላል። የብሄር ጭቅጭቅን ፍራቻ ከሳይንሳዊ ደረጃዎች በታች ይሠራል። አንድ ምናባዊ ምሳሌ እንውሰድ።
ለምሳሌ ለአንድ የሆነ ነገር ውድድር ተደረገ እንበል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሁሉም ተወዳዳሪዎች ከአንድ ብሄር ቢሆኑ ውጤቱ በቀጥታ ይነገራል ብላችሁ ታስባላችሁ? በምዘናው መሠረት እኮ መስፈርቱን የሚያሟሉት እንደ አጋጣሚ ከአንድ ብሄር ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስልብናል በሚል የብሄር ተዋፅዖ ይደረግበታል። መስፈርቱን የሚያሟሉት የ‹‹ሀ›› ብሄር ተወላጆች ቢሆኑ፤ ለብሄር ተዋፅኦ ሲባል ብቃት የሌለው የ‹‹ለ›› ብሄር እንዲገባ ይደረጋል። ያ የተወዳደሩበት መስክ ከፍተኛ ብቃት የሚፈልግ (ለምሳሌ ህክምና ቢሆን) የሰው ሕይወት ላይ እየተቀለደ ነው ማለት ነው። ሙያዊ ወታደራዊ ሳይንስ የሚጠይቅ ቢሆን ሀገራዊ ክስረት ተፈጠረ ማለት ነው። በአንድ ሐኪም ወይም ወታደር ምክንያት የምትፈጠር ስህተት ትልቅ ጥፋት ታመጣለች።
ለምሳሌ፤ አንዳንድ ውድድሮች ላይ የሕዝብ ድምጽ የሚባል ነገር አለ። እንዲህ አይነት አሠራሮች ላይ ሲያጨቃጭቅ የምናየው ነገር፤ የተመልካቾች የአጭር የጽሑፍ መልዕክት ድምጽ ነው። የተመልካች ድምጽ ከዳኞች ውጤት ጋር ይደመራል። ይህ አሠራር እንደሚኖር (የሕዝብ ድምጽ) ሲነገር፤ የተወዳዳሪዎች ብሔር ተወላጆች በየፊናቸው ቅስቀሳ ይጀምራሉ። ምረጡት የሚሉት ብቃቱን በመግለጽ ሳይሆን ‹‹የእኛ ልጅ ነው›› በሚል ነው። እንዲህ አይነት ነገር በጣም ሲጦዝ አወዳዳሪዎች ሊሰርዙት ይችላሉ።
መሰረዙ ደግሞ እንደገና ሌላ ክርክር ይፈጥራል። መሰረዙን አግባብ ነው አግባብ አይደለም የሚል ማለት ነው። አግባብ ነው የሚሉት ወገኖች፤ ሙያዊ ምዘና የሚጠይቅ እንዲህ አይነት ውድድር ሙያውን በሚያውቅ ዳኛ እንጂ በመንጋ ድጋፍ መሆን የለበትም በሚል ነው። ግልጽ ሆኖ የታየው ነገርም ተወዳዳሪዎች የሰፈራቸውን ልጆች እየጠሩ ይናገሩ ስለነበር ነው። ከሰፈር አልፎ የብሄር ውድድርም ስለሆነ ማለት ነው። የተወዳዳሪውን ብሄር አይተው ይመርጣሉ።
መቅረቱ አግባብ አይደለም የሚሉት ደግሞ፤ የተመልካቾችም ድምጽ መከበር አለበት በሚል ነው። ፍርድ ለዳኞች ብቻ ሳይሆን ለሕዝብም መሆን አለበት በሚል ነው።
በበኩሌ ሙያዊ ምዘና የሚጠይቁ ውድድሮች በባለሙያ ነው መለካት ያለባቸው። ለዚያውም በዚህ ጎሰኝነት አቅሉን በሳተበት ነባራዊ ሁኔታ በሕዝብ ድምጽ ቢባል ሙያዊ ልኬታውን ማግኘት ይከብዳል። ሲሸነፉም ውጤቱን በፀጋ ከመቀበል ይልቅ ‹‹በብሄሬ ምክንያት…›› ይላሉ። ይሄ በብሄሬ ምክንያት የሚባል ነገር ከቀልድ አልፎ ትልቅ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው።
በአጠቃላይ፤ የብሄር አስተሳሰብ ከእግር ጥፍራችን እስከ ራስ ፀጉራችን ወሮናል። ይሄ ደግሞ ፍትህን እያዛባ ነው። በፈተና ውድድርም ሆነ በመንግሥታዊ ሹመት ላይ የብሄር ተዋፅኦ በግልጽ የሚደረግ ነው። አሁን ግን እስከ ጥቃቅን ነገሮች ድረስ እየወረደ ነው። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ሙያዊ ምዘና ማድረግ ይቻላል? ፍትሐዊ አሠራር ማስፈን ይቻላል?
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም