የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቀደምት ዘገባዎች በእጅጉ ተነባቢ ዛሬም ላገኛቸው በእጅጉ ተነባቢ ናቸው፡፡ እኛም ከእነዚህ ዘገባዎች ጋዜጣው በ1950ቹ ያስነበባቸውን ወጣ ያሉ ዘገባዎች ለዛሬ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ኃ/ማርያም ወንድሙ
በሰሐራ መሬት ውስጥ ሐይቅ ተገኘ
ከማድሪድ፡- የእስፓኒሽ ሰሐራን ወደ አንድ ሰፊ የሆነ የአትክልት ሥፍራና የከብት ማርቢያ መስክ ለመለወጥ የሚችል የመሬት ውስጥ ሐይቅ በዚሁ ሥፍራ የተገኘ መሆኑን አንድ የእስፓኒሽ የሳይንስ ሊቅ ባፈው ሐሙስ አስታውቀዋል፡፡
በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙት የእስፓኝ ቅኝ ግዛቶች የማዕድንና የአፈር ምርመራ ጥናት ኃላፊ የሆኑት እኚሁ የእስፓኒሽ የሳይንስ ሊቅ ሐይቁ በአትላንቲክ ውቅያኖስ የባህር ዳርቻ ከምትገኘው ቪላ ሴሴኔሮስ ከተባለችው ወደብ ጀምሮ እስከ 60 ማይሎች ድረስ ወደ ሰሐራ ምድረ በዳ የዘለቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የእስፓኙ የሳይንስ ሊቅ ሲኞር ጃዋን ኩምባ ኤዝኩራ ጠቅላላ ስፋቱ 23, 000 እስኩዌር ማይሎች ከሆነው ከዚሁ ሐይቅ የሚገኘው ውሃ ለእርሻና ለከብት ማርቢያ በማገልገል የእስፓኒሽ ሰሐራንም ምድረ በዳ ወደ አንድ ሠፊ የሆነ የአትክልት ቦታና የከብት ማርቢያ መስክ ሊለውጠው የሚችል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ይህ ሐይቅ አለ ተብሎ በተገመተበት ሥፍራ ላይ ጥልቀቱ 1,400 ጫማዎች የሆነ ጉድጓድ ተቆፍሮ ውሃ የተገኘ መሆኑን ሲኞር ኤዝኳራ ገልጸዋል፡፡ ጉድጓዱ ልክ እንደተቆፈረ የሐይቁ ውሃ ከመሬት በላይ 250 ጫማዎች ያህል ወደ ሰማይ የተፍለቀለቀ መሆኑ ታውቋል፡፡
ታሣሥ 10/ 1957
ጀርሞችና ትንኞች የሚጠፉበት የግድግዳ ቀለም ተሠራ
በምዕራብ ጀርመን የሚገኘው የባየር ላቦራቶር ከግድግዳ ቀለም ጋር ተጨምሮ የሚቀባ አንድ ፀረ ማይክሮብ መድኃኒት መሥራቱን አስታውቋል፡፡ ይህ መድኃኒት የተጨመረበት ቀለም ከተቀባው ግድግዳ ላይ የሚያርፉ ትንኞችና ሌሎችም ነፍሳቶች ወዲያውኑ እንደሚሞቱ ታውቋል፡፡
መድኃኒቱ ለሰው ምንም ዓይነት አደጋ አያደርስም። ይህ ዓይነቱ ቀለም ለግል መኖሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆን ህክምና በሚሰጥባቸው ክፍሎች ብዙ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አዳራሾች በመታጠቢያ ቤቶችና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ከፍ ያለ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገምቷል፡፡
ከዚህ በስተቀር ከዚህ መድኃኒት ተመሳሳይ የሆነ ከወለል መወልወያዎች ጋር በመደባለቅ ጀርሞችን የሚያጠፋ አንድ ሌላ መድኃኒት በመሥራት ላይ ነው፡፡ እንዲሁም ሐኪሞች ኦፕሬሽንና ሕክምና በሚያደርጉበት ወቅት በእጆቻቸው ላይ የሚያጠልቁት ላስቲክ የሚታጠብበት ኃይለኛ መድኃኒት በመፈልሰፍ ላይ መሆኑን አንድ የጀርመን ቡሉቲን ገልጹዋል፡፡
ታኅሣሥ 10/ 1957
ወደ ጠፈር የተላከ
ዝንጀሮ
በአሜሪካ መንግሥት የጦር ሠራዊት መሥሪያ ቤት ፤ ሰው ከጠፈር ወዲያ በሮኬት በተላከ ጊዜ የሚያጋጥመውን ሁኔታ ለማጥናት መጀመሪያ ሕያው ዝንጀሮ በመተኮስ ለመመርመር ያቀደውን ፕላን ፈጽሞታል፡፡
ጎርዶ የሚባለውን አንድ ፓውንድ የሚመዝን ትንሽ ዝንጀሮ ለ300 ማይል ወደ ላይ ተኩሰው መልሰው ሳያገኙት በመቅረታቸው የእንስሳት ወዳጆችና የማኅበራዊ ኑሮ ድርጅት ኃላፊዎች የአሜሪካ ጦር ሠራዊት መሥሪያ ቤትን ተቃውመውታል። ይህም መሥሪያ ቤት ፍተሻ የተደረገው ወደፊት ሰው ወደ ጠፈር በሮኬት አማካይነት ተልኮ ሲጓዝ በሕይወቱና በአዕምሮው ላይ የሚደርስበትን ለማወቅ ከሰው ጋር የተፈጥሮ እጅግ ተመሳሳይነት ያላቸው እንስሳት አስቀድሞ መላክ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስታውቋል።
(ጥቅምት 1951)
(ሮይተርስ)
አሳሳች ኒውስ
ዊክ
የኒውስ ዊክ መጽሔት ደንበኞች ምናልባት በዚህ ሳምንት ውስጥ ልዩ ዓይነት እትም ሳያጋጥማቸው አይቀርም፡፡ የኢንተርናሲዮናል እትሙ ሐሰተኛ አምሳያ በአፍሪቃና ምናልባትም በምዕራብ አውሮፓ በመሠራጨት ላይ መሆኑን የኒውስ ዊክ መጽሔት ከኒውዮርክ አስታውቋል፡፡ አንዳንድ ቅጂዎችም የዩናይትድ ስቴትስ መግባታቸው ተገልጧል፡፡
የኒውስ ዊክ መጽሔት ስለዚሁ ሐሰተኛ እትም ባወጣው መግለጫ ሀሰተኛው እትም እ.ኤ.አ ኅዳር 18 ቀን 1963 የሚል ሲሆን፣ በውስጡም በአሜሪካ ላይ በተለይ የቀለምን ልዩነት በሚመለከት ጉዳይ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሞልቶበታል፡፡
የቀለም ልዩነት ግጭቶችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችና አሳሳች መግለጫዎች አሜሪካንን የሚቃወሙ ንድፎች አሉበት፡፡ እነዚህ ሁሉ በእውነተኛው ኒውስ ዊክ አልተገለጡም ነበር። ኒውስ ዊክ ጉዳዩን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር የተነጋገረበት ከመሆኑም በላይ ምንጩን ለማግኘት የራሱን ምርመራ በማድረግ ላይ ነው ብሏል፡፡
ታኅሣሥ 9 ቀን 1956 ዓ.ም የወጣ አዲስ ዘመን በፊት ገጽ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2013