ብስለት
እውነት እናንት እነማን ናችሁ? ከየት ነው የመጣችሁት? ማንስ ነው የወለዳችሁ? ግራ ገባኝ። እኔ የማወቀው እናንተ መጣንበት የምትሉት ህዝብና እናንተ እየሆናችሁት የላችሁትን ነገር ማስታረቅ ከበደኝ። የምሰማውን አደረጋችሁት የተባለው ነገር ከአእምሮዬ በላይ ሆኖብኝ፡፡ እናንተን የምጠራበት ስም ቢጠፋኝ ስም ባጣላችሁ እኮ ነው ይህን ሁሉ ጥያቄ መጠየቄ። በዓለም ላይ ያሉ የክፋት ጥጎችን በሙሉ በእምዬ ላይ እንዲሆን ስለፈቀዳችሁ እኮ ነው ግራ መጋባቴ።
እኔን ያሳደገኝ እጅ፤ የወለደኝ ማህፀን እናንተን ወልዶ አሳድጎ ከሆነ በዚህ ልክ አረመኔያዊነትን ከየት አመጣችሁት? እነዛ በእንግድነት እንኳን ቤታችን ሲመጡ በልጅነት አይኔ የማያቸው እንስፍስፍ ፊቶች ጨዋ ህዝቦች እናንተ ከምትሰሩት ስራ ጋር በምንም መስፈርት አልገጣጠም ያለኝ እኔ እናንተ ማናችሁ? ከየት ነው የመጣችሁት እያልኩ እጠይቃለሁ።
በፍፁም ድህነት እስካሁን ድረስ በባዶ እግሩ ብዙም ምርት የማያቀመሰውን አፈር እየገፋ የሚኖረው ገበሬ በልቶ እንኳን ሳይጠግብ ኑሮውን ከድጡ ወደ ማጡ ለማድረግ ደፋ ቀና ስትሉ ስመለከት እውነት እናንተ ከትግራይ ናችሁ እንድል ያደርገኛል።
የእምነት የሀይማኖት መነሻ፤ ፈሪያ እግዚአብሄር ያደረበት ህዝብ፤ በፍፁም ጨዋነትና መከባበር ያለውን ተካፍሎ በአመስጋኝነት የሚኖረው ማህበረሰብ፤ ሌብነትን የሚፀየፍ፤ በእጁ ድንጋይ ጠርቦ አቢያተ ክርስትያናትን ያነፀ ቤተ እምነቶችን የገነባ፤ የእምነት እኩልነትን የሚያከብር፤ ከጥንት ጀምሮ ባእዳንን እንኳን በክብር ተቀብሎ ተንከባክቦ ያኖረ ታላቀ ህዝብ፤ በጥልፉ በወርቁ በተለያየ ጥበብ ባለ እጅ የሆነ ከስራ ከሀይማኖት በቀር ምንም አይነት አስተሳሰብ የማይመራው ህዝብ እንዴት በምን መስፈርት እናንተን ሊፈጥር እንደቻለ ሊገባኝ ባይችል እኮ ነው ከሰማይ ይሆን የወረዳችሁት ወይስ ካልታወቀ ዓለም ውስጣችን የተጣላችሁ የሰይጣን ቁራጮች ናችሁ እያልኩ ማሰቤ።
እራሰ ወዳድነት ከሰብአዊነት በላይ፤ የስልጣን ጥም እናት አባትን ወገንን እስከ መጥላት ያደርስ ይሆን እንዴ? የምትመሩት የፖለቲካ አስተሳሰብ ፈጣሪን እስከ መርሳት ሰብአዊነትን ከውስጣችሁ አሟጦ እስከ ማጥፋት ይደርስ ይሆን እያልኩ አስባለሁ። ድሮ እንደዚህ አይነት ድርጊት በሩቁ በሚሰማበት ጊዜ ሀገራችን የአማኞች ሀገር ፈጣሪ የሚፈራ ህዝብ የሚኖርባት ምድር እያልኩ አስብ ነበር።
በዚህ ልክ ፈጣሪን ረስተው የገዛ ወገናቸው ደም እንደ ውሃ ሲፈስ ግድ የሌላቸው፤ ለህዝቡ እንውቅላችኋለን የምትሉት እናንተ እውነት እናት ቤተሰብ አላችሁ? ሀገር ፍቅር ምናምን የሚባሉ ሰብአዊ ስሜቶች በውስጣችሁ ይመላለሳሉ?
የእናንተ ክፋት ቋንቋችንን ሳይደበላለቅብን በፊት ቀደምት አባቶቻችን የከፋ ነገር ሲገጥማቸው ምህላውንም፣ ዱአውንም ሆነ ፀሎቱን ይዘው ‹‹የመጣውን እሳት አብርድልን›› ብለው ሲለማመኑት የመጣን መዓት መለስ ይላል።
የአሁኑ መዓት ግን ይለያል፡፡ እየተሰማ ያለው ግፍ ሲወራ ደግሞ ለማሰብ ይከብዳል፡፡ በፊት እንኳን የአገር መሪ የትኛውም ሽማግሌ ሲናገር ይሰማል፤ ታላቅ ከተቆጣ ይከበራል፤ ሰው ሸሽቶ ሰው ስር ሳይሆን በዛፍ ከተከለለ እንኳ፤ ግዑዙ ዛፍ ክብር ተሰጥቶት ገላጋይ ሆኖ ጠብ ያበርድ ነበር።
አሁን ምን መጥቶ ይሆን የአገር መሪ አዋጅ ሰምተን ወደ ሰላም ወደ ይቅርታ መምጣት ያቃተን? ምን ሆነን ነው? ሲናገሩ አይደለም ሰው ፊት ሲቆሙ ግርማቸው የሚከብደውን ሽማግሌዎች የገፋችሁትስ ለምንድን ነው? ለዚህ ኩሩ ህዝብ ስትሉ እንኳን በደላችሁን አምናችሁ ቅጣታችሁን ለመቀበል ያልደፈራችሁትስ ስለምንድነው? እውነት እናንተ በይቅርታ እጁን ወደ ፈጣሪ ከሚዘረጋው ህዝብ ነው የተወለዳችሁት ወይስ ድንገት የበቀላችሁ አረሞች ሆናቸሁ ይሆን?
ከክብርስ በላይ የሰው ነፍስ ያላስጨነቃችሁስ ምክንያቱ ምንድን ነው? እጁ የሌለበት ምስኪን ሰው በግፍ ሲገደል ሀገሪቱ በደም ጎርፍ ስትታጠብ መሸሸጊያ ቤተ እምነቶች ሌላ የቤት ሰራ የያዙት ስለምድን ነው? ምን አይነት የክፋት ዘር ብትዘሩ ነው ማልቀሻችንን ያሳጣችሁን? በታላቁ መፅሃፍ ቅንጣት ታህል እምነት ተራራ ታነሳለች የሚል ፅሁፍ እየተነበበ ሀገራችን ከገባችበት ውጥንቅጥ ሊያወጣን የሚችል እምነት አንዳችን ጋር እንኳን ያልተገኘው እንዴትስ ነው? እንዴትስ ብታቆስሉት ነው ፀሎተኛው ህዝብ በእናንተ ያቄመባችሁ? ቂም ፀሎቱ ዱአው ከሰማየ ሰማያት እንዳይደርስ የጋረዳበት እንዴት አይነት የጥላቻ ዘር መካከላችን ብታፈሱ ነው?
የእናቶቻችን ሀዘን ከፍቶ ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው እያለቀሱ እንኳን ልባችሁ ደንገጥ ሊል ያልቻለበት ምክንያትስ ምንድነው? እንኳን እናንተ ተጨምራችሁበት መከፋት፣ ሰቆቃ፣ በሽታ እና ሞት በዓለም ላይ በርቀት ሲሰማ እየዘገነን፣ በቅርባችን እየተመለከትን ነው፡፡
ይህን እያዩ መላው የኢትዮጵያ ልጆች በአንድ መንፈስ እጃቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው ምህረትን የሚለማመኑበት ቀንስ እንዲጠፋ አንድነት ግራ ገብቶት የጎጥ የቀበሌ ወሬ ብቻ ሀገራችን ውስጥ እንዲወራ ያደረጋችሁበት ዘር ምንድነው? ማርከሻ ምሳችሁስ ምንድነው? ማናችሁ? ከየትናችሁ? በምንም በምኑም የተጣባችሁን ችግሮች ከላያችን ትራገፉልን ዘንድ ከየት እንደመጣችሁ ንገሩንና መጠፊያ መላችሁን እንድንፈልግ አድርጉን።
የክፋት ዘራችሁን ከዘራችሁባት ቅድስት ምድራችን እንደ አረም እንነቃቀላችሁ ዘንድ ምን እናድርግ፤ ሀገራችን ልጆቿ የሚያድጉበት ሁኔታ ያሳስባታል። ሀገር እናት ሆና ነፍስ ኖሯት ቆማ የልጆቿን ስራ ስትመለከት ምንኛ ልቧ ይሰበር ይሆን? እኔ ለህፃናቱ ማደጊያ ልቤ ሲንሰፈሰፍ እማማ ኢትዮጵያ በህልውናዋ ላይ የመጣው የልጆቿ መከፋፈልና መበታተን ምን ያህል እያሳዘናት ይሆን? ምን ያህል ቁስሏስ ጠልቆ እያመረቀዘ እየቆጠቆጣት ይሆን እያለኩ አስባለሁ።
እናንት መጠሪያ የጣሁላቸሁ የክፋት መልእክተኞች ከመስኪኑ ህዝብ ጫንቃ ወረዳችሁ ልቀቁት። ምርጫችሁ ያደረጋችሁትን የወደዳችሁትን ጥፋት የመትተገብሩበት ሌላ ሀገር ፈለጉ። ከእንግዲህ በእምዬ ምድር ለቀሶና ዋይታ እንዳታሰሙን፤ ይብቃችሁ ብዬ አበቃሁ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2013