የዓድዋ ድል- የትውልድ ስንቅ

የዓድዋ ድል በታሪክ መጽሐፍት ምዕራፎች ብቻ ተከትቦ የቀረ ሳይሆን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ የሚነድ ነበልባል ነው። መሬቱን በሞፈር ጠምደው የሚያነጋግሩ ገበሬዎች፣ አርበኛ የጦር ተዋጊዎች፣ ሴቶች እና መሪዎች ዳር ድንበራቸውን ‹‹ኃያላን ነን›› ካሉ የአውሮፓ ጦር ለመከላከል በታላቅ መነቃቃት ተንቀሳቅሰው ዓለምን ያስደመመ ታላቅ ድል የተቀዳጁበት ነው ።

ጦርነቱ በእኩል አቅም ባሉ ተፋላሚዎች መካከል የተደረገ ሳይሆን ለግምት በሚከብድ ልዩነት ውስጥ ባሉ ኃይሎች መካከል የተደረገ ነው። ኢትዮጵያውያን በታላቅ ወኔ፣ ኢትዮጵያዊ ጀግንነትና፤ ነፃነት እና የሀገር ፍቅር ስሜት፤ ጣሊያኖች ዘመኑን በሚዋጅ ትጥቅና ዝግጁነት የተጠናከሩ ነበሩ ።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩትን ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘናት ወደ ዓድዋ በመትመም በዓድዋ ተራሮች ላይ ‹‹ኢትዮጵያ በፍጹም ቅኝ አትገዛም›› የሚል በብዙ መስዋዕትነት የታጀበ የድል ብሥራት መልዕክት ለመላው ዓለም አስተላልፈዋል። ይህ ታላቅ ድልና ታሪክ ለመላው ኢትዮጵውያን ከኩራት በላይ፤ የማንነታችን መሠረት ነው።

በዚህም እንደ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያ ታሪክ በባዕድ ገዥዎች አልተሰረዘም። ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶቹ እና ባሕሎቿ በቅኝ ግዛት ጭቆናና ጫና ጠባሳ አላረፈባቸውም። ኢትዮጵያውያን የቀድሞ አባቶቻቸው ሀገራቸውን እንዴት ከጠላት እንደጠበቁ፤ ኢትዮጵያዊ አኗኗር ዘይቤ፣ ባሕልና ወግ እንዴት ከጥፋት እንደተከላከሉ እየሰሙ አድገዋል።

ወጣቱ ትውልድ የምዕራቡ ባሕል ወይም የዘመኑ ወራሪ ማንነትን የሚያጠፋ እሳትን እንዳላደባለቀ፤ እንዳልበረዘ ወይም እንዳልተጫነ በሚገባ ተምሯል። ይህንን ኢትዮጵያዊ እሴት እና ኅብረ ብሔራዊነት ለመጠበቅ የቀደሙት አባቶች ደምና መስዋዕትነት የግዴታ አስፈልጓል።

ይህንን ድል ለማምጣት የአባቶችን ብልሀት እውቀት ጥልቅ የሆነ የሀገር ፍቅርና የሀገር ባለቤትነት ስሜት ጠይቋል። ይህ ትውልድም የአባቶቹን የማይበገር መንፈስ እንዲወርስና ‹‹ያልተሰበረ ማንነት›› እንዳለው እንዲያውቅ የዓድዋ ድል ታላቅ ምሳሌ መሆን ችሏል።

በቅኝ ያልተገዛች ኢትዮጵያ እና ጠንካራ የጀግንነት መንፈስ ለዚህ ትውልድ ስጦታ ነው። በሌሎች የአፍሪካ ክፍሎች ቅኝ ግዛት ብዙ ጠባሳ ጥሏል። የውጭ ገዥዎች የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን በራሳቸው ተክተዋል። ታሪክን እንደገና ፅፈዋል፤ በባሕልና በእምነት ተቀባይነት የሌላቸው ድርጊቶችን በሕዝቡ ላይ ጭነዋል፤ የተፈጥሮ ሀብቶችን በዝብዘዋል። ይህ ለኢትዮጵያውያን እና አሁን ላለው ትውልድ ብዙ ትርጉም አለው።

አፍሪካውያን ከነፃነት በኋላም ማንነታቸውን መልሰው ለመገንባት በብዙ ታግለዋል። ወጣቶቻቸው ዛሬ የቀደመ ማንነታቸውን መልሰው ለማግኘት እና ዳግም ባሕላቸው እንዳይጠፋ ይተጋሉ። ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች ግን ይህ አሳሳቢ አይደለም፤ ምክንያቱም አባቶቻችን ቀድመው ሥራውን በዓድዋ ድል በግማሽ ቀን አጠናቀውታል።

የኢትዮጵያ ማንነት አሊያም ከቀደመው ዘመን ጋር የተገናኘው ግንድ በቅኝ ግዛት ሰበብ ሥሩ ተቆርጦ አያውቅም። ቋንቋዎች፣ የግዕዝ ፊደል፣ የቡና አፈላል ሥነ-ሥርዓት፣ የደመቁ በዓላት-ሁሉም ሕያው ሆነው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ ዛሬም ድረስ አሉ። ይህ የዓድዋ ድል ያስገኘው በረከት፤ የጥንት አባቶቻችን የጀግንነት ሕያው ምሳሌ ነው።

ድሉ የአባቶቻችን ስጦታ ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች የቀደመውን እና ዛሬም ድረስ ሕያው የሆነውን ማንነታቸውን በሙዚየምም ሆነ በአሮጌ ሰነዶች ውስጥ መፈለግ አይጠበቅባቸውም። በወላጆቻቸው ቤት፤ በአብያተ ክርስቲያናት፣ በመስጊዶቻቸው፣ በገበያ ስፍራ በአደባባይ በዓላትና ዓድዋን በመሰሉ የድል አብሳሪ ተራሮች ውስጥ በቀላሉ ያገኙታል።

ለምሳሌ የደቡብ የሽምግልና ሥርዓቶች፣ ጥብቅ ኢትዮጵያዊና ማኅበራዊ ትስስር፣ አልባሳት፣ የሰሜኑ ክፍል መገለጫዎች (የሀበሻ ቀሚስ ወይም ጋቢ) ያሉ የባሕል ልብሶችን ጨምሮ የቀደመው ትውልድ ከባሕል ወረራ ያተረፋቸው እሴቶች ናቸው። አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ ወይም የትኛውንም የኢትዮጵያ 74 ቋንቋዎች ሲናገሩ፣ ቅኝ ገዢዎች ዝም ሊያሰኘው ያልቻለውን ድምፅ በአባቶቻችን ድል የተገኘ መሆኑን ይህ ትውልድ ጠንቅቆ ማወቅ ይኖርበታል።

የዓድዋ የሥነ-ልቦና ትጥቅ

ይህ ትውልድ የራሱ ትግል አለበት። ለብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሕይወት ቀላል አይደለም። ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና ዓለም አቀፍ ጫናዎች የለት ተለት ትግልን ይፈጥራሉ። ነገር ግን የዓድዋ ድል መንፈስ ማንም ሊወስደው የማይችለውን ኃይል፤ የሥነ ልቦና ጥንካሬ ለትውልዱ ይሰጣል። ይሄ ትውልድ በየትኛውም መልኩ ሽንፈትን ማስተናገድ የለበትም:: የሽንፈት ስሜት ቢሰማው እንኳን ከራሱ ጋር ትግል መግጠም ፤ የዓድዋን ድል ባለቤቶች የአባቶቹን ጀግንነት ቆም ብሎ ማስታወስ አለበት::

ትግሉን ቆም አድርጎ ዓድዋ ላይ የተፋለሙትን ገበሬዎች ማስታወስ ያስፈልጋል:: የእቴጌ ጣይቱን በመቀሌ ማይንሽተይ፣ እንዳየሱስ ተራሮች ስር የጣሊያን ሠራዊት እጅ እንዲሰጥ የተጠቀመችውን ብልሀት ማስታወስ፤ ቅድመ አያቶቻችን ዘመናዊውን የጦር መሣሪያ በጦርና በጋሻ ተራራውን ፣ ሸለቆውን፣ ጉድባውንና ጢሻውን ተጋፍጠው እንዴት ወራሪን ድል እንደነሱ በዓይነ ሕሊና ማሰብ ይገባል:: ያን ጊዜ ዛሬ የገጠምነው ትግል ከዚያ በብዙ እጅ ያነሰ እንደሆነ ይገባዋል። ይህ የዓድዋ ድል መንፈስ ታላቅ የኩራትና የማሸነፍ በር ይሆንለታል።

የዓድዋ ድል ትውልዱን ከተስፋ ቢስነት አርቆ ጋሻ ሆኖ ይጠብቀዋል። ‹‹አንተም ትችላለህ›› የሚል ድምፅ ከዓድዋ ተራሮች ውስጥ ይደመጣል። የዛሬው መምህራን እና ትምህርት ቤቶች ስለ ዓድዋ ድል ለልጆቻቸው የሚያስተምሩት ታሪኩን የመዋጋትና የመገዳደል ምሳሌ አድርገው ሳይሆን (ጦርነት ብቻ ሳይሆን) ኢትዮጵያውያን አንድ ሲሆኑ የጋራ ድል በየትኛውም የሕይወት መስክ ላይ ሊያገኙ እንደሚችሉ በማስረጃነት በማጣቀስ ነው።

ኢትዮጵያውያን የዓድዋን ድል የሚያከብሩት በኃዘን ሳይሆን በዘፈን፣ በፉከራና በሽለላ ታሪኮች ነው። ድሉ የተጋፈጥነውን ፈተና የመቋቋም አቅም ይፈጥርልናል። ወጣቶች ዛሬ የሚያደርጉት ትግል ቅድመ አያቶቻችን የጀመሩት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የተፈጥሮ ሀብትን ከዘመናዊ ቅኝ ግዛት አትርፈው የኢትዮጵያን ሕልውና ለመታደግ የአባቶቻችንን መንፈስ መውረስ ይኖርብናል።

ዳግም ዓድዋ

ዛሬ ዓለም ላይ ያለው የባሕል ወረራ እና ስግብግብነት እንደያኔው (በ1888 ) አይነት አይደለም። ቅኝ ገዥዎች ጦር ይዘው ባይመጡም የባሕል ወረራ በተለያየ መልኩ እያደረጉ ነው። የውጪ ፊልሞች፣ ዓለም አቀፍ ፋሽን ዝግጅቶች፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ጨምሮ በርካታ ስልታዊ መንገዶች ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ባሕላቸውን እየጠበቁ ሳይሆን ‹‹የድሮ ዘመን›› ላይ ተቸንክረው እንደቀሩ እንዲሰማቸው ሊያደርጉ ይችላሉ።

ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ለም መሬት፣ ማዕድናት እና ወንዞች ተገቢውን ዋጋ ሳይከፍሉና ለሀገር ውስጥ እድገት ቅንጣት ሳይሠሩ፤ በአንድ ወቅት ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ ላይ እንዳደረጉት የሀብት ኮንትሮባንድ ለማስፋፋት ተደጋጋሚ ሙከራ ያደርጋሉ። የአሁኑ ትውልድ ከዚህ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለመውጣት ድርሻው ምንድነው?

የዓድዋ ድል መንፈስ ሊጋባበት እና መሰል ሥልጣኔ መሳይ ወረራን መከላከል ሲችል ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያውያን በጉዳዩ ላይ መልካም አረዳድ አላቸው። በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ወጣቶች ቅርሶችን የመጠበቅ ጥረት ያደርጋሉ። ሙዚቀኞች ባሕላዊ መሣሪያዎችን ተጠቅመው ማንነታቸውን ለመግለፅ ሲሞክሩ ይስተዋላል፤ ሰዓሊያን በጥበባዊ ሥራዎቻቸው የኢትዮጵያን ጀግኖች በሥዕል ለትውልዱ ያሻግራሉ።

ጸሐፊዎች ስለ ዓድዋ ታሪክ በመጽሐፍ እና በመገናኛ ብዙኃን ይተርካሉ። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አክቲቪስቶች የሀብት ስርቆትን እና የአካባቢ ውድመትን በመቃወም ይሞግታሉ። ዛሬ ዳግማዊ ዓድዋ ድል ማሳካት የሚገባው ‹‹አባቶቻችን በዓድዋ ድል ይህችን ታላቅ ሀገር አዳኑልን። ለቀጣዩ ትውልድ እኛም ከዘመናዊ ወረራ ጠብቀን ማዳን አለብን›› የሚል ወኔ በሁላችንም ዜጎች በተለይም በወጣቶች ዘንድ ሊኖር ይገባል።

ለአንድ አፍታ እስኪ ይህንን እናስብ:: በትግራይ ደጋማ አካባቢ ያለውን ወጣት ገበሬ ለመመልከት እንሞክር። ቅድመ አያቶቹ ከወረራ የተከላከሉትን ተመሳሳይ አፈር ያርሳል። ድርቅ ሲመጣ ተስፋ አይቆርጥም ምክንያቱም ዓድዋ ላይ የተፋለሙትን የአያቶቹን ፅናት ያስታውሳል።

ወይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለች አንዲትን ተማሪ በዓይነ ሕሊናችን እንመልከት። ታሪክን የምታጠናው ፈተና ለማለፍ ብቻ ሳይሆን አያቶቿ በዓድዋ ተራሮች ላይ ተዋድቀው ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንዴት እንደጠበቁ ለመረዳት ጭምር ነው።

አንዲት ደራሲ ስለ እቴጌ ጣይቱ የምትፅፈው እኩዮቿን ለማነሳሳት ዳግማዊ እቴጌ ጣይቱዎችን ለመፍጠር ነው። ይህንን ታላቅ ዕድል ሌሎች በቅኝ የተገዙ አፍሪካውያን አያገኙትም። በመሆኑም ዛሬ ዳግም ከድህነት፣ ከድንቁርና ጋር ተፋልመን የአባቶቻችን ልጅ መሆናችንን ማስመስከር አለብን።

አሁን ያለው ትውልዱ ይህንን ቢረዳ እና በየራሱ ትናንሽ አሊያም ተራ የሚመስሉ ኃላፊነቶችን ቢወጣ የሁሉም ድምር ውጤት ታላቋን ኢትዮጵያን እና የቀደመውን የሥልጣኔ ልዕልና መመለስ ይችላል። በአንድነት ኢትዮጵያን ከዘመናዊ ቅኝ ግዛት ሙከራ እና ከምዕራባውያን ጫና ጋሻ ሠርቶ መከላከል ይቻላል::

አንድ ታዳጊ ባሕሉን የሚገልፅ ውዝዋዜ፣ እውቀት እና ጥበብን በተማረ ቁጥር፤ አንድ ቤተሰብ አሊያም መንግሥት አባቶቹ ጠብቀው ያቆዩትን መሬት ለውጭ ኩባንያዎች ለመሸጥ ፈቃደኛ ባልሆነ ቁጥር፣ ነጋዴው ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች ይልቅ የኢትዮጵያን ምርቶች ምርጫው ባደረገ ቁጥር ዳግማዊ ዓድዋ ድል እና ክብርን መጎናፀፍ ይቻላል።

ይህ እውነታ ለክብርና ማንነትን ለመጠበቅ የሚደረግ ትግል መቼም ቢሆን እንደማያልቅ የሚያረጋግጥ ነው። ለዚህ ነው የአባቶቻችንን ወኔና መንፈስ መላበስ አለብን የምንለው።

ከድሉ ምን ተምረናል?

የአሁኗ ኢትዮጵያ የብሔር፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት መለያየት ተጋርጦባታል። ነገር ግን የዓድዋ ድል ዜጎች ማንኛውም ዓይነት ልዩነታቸው ከጋራ ማንነታቸው ያነሰ እንደነበር አሳይተውናል፤ ይህን እናስታውሳለን:: ዳግማዊ ምኒልክ ርስ በርስ በግዛትና በሥልጣን የሚፋለሙ ሀገረ ገዢዎችን አንድ አድርገው የጋራ ጠላትን ለመጋፈጥ ችለዋል።

ይህ ትውልድ የዘመኑን ስጋት ለመጋፈጥ አንድ መሆን አለበት። ዓድዋ ይህንን ያስታውሰናል። ሙስና፣ የአካባቢ ብክለትና የተፈጥሮ ብዝበዛ የዚህ ትውልድ ፈተናዎች ናቸው። ድል አድርጎ ለመውጣት የዓድዋ ምልክት የሆነውን የጋራ ጥንካሬ ይጠይቃሉ። ለዚህ ነው ምንም ሳናቅማማ የአባቶቻችንን ወኔ መላበስ ይኖርብናል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች የዓድዋን ድልና አኩሪ ታሪክ ዛሬም ደግመው ደጋግመው ይማራሉ። የቀደመውን ድል ያቀዳጁን ንጉሡና ንግሥቲቷ ብቻ ሳይሆኑ ድፍረትን የመረጡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ማወቅ ይገባል። ሀገርን መውደድ ሌላውን መጥላት አይደለም፤ ይልቁኑ የትውልድ ሀገርን እና ልዩ የሚያደርገን ማንነት ዋጋ መስጠት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ባሕል ውድ ሀብት መሆኑን ከዓድዋ ድል መማር ይቻላል።

የዓድዋ ድል ኮምፓስ ነው። ወጣቶች በትዕቢትና በሁከት ሳይሆን በጥበብና በጀግንነት ቅርሶቻቸውን፣ ማንነት እና ሉዓላዊነትን እንዲጠብቁ አቅጣጫ ያሳያል። ወጣቱ ትውልድ ሀገሩን ተረክቦ ረጅም ርቀት መራመድ እንዲችል ያመላክታል። ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ይህ ትሩፋት ብርሃን ብቻ አይደለም። በሁሉም ልብ ውስጥ መቀጣጠል ያለበት፤ መጥፋት የሌለበት እሳት ነው።

የዓድዋ ድል ለዓለም የኢትዮጵያ ጥንካሬ ዘላለማዊ መሆኑን ያመለከተ የማይጠፋ እሳት ነው። ‹እኛስ የት ቦታ ቆመናል? በአያቶቻችን ስፍራ? ወይስ በቅኝ ገዢዎች መንደር? ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። ዘላለማዊ ድል በዓድዋ ተራሮች ስር ለተሰው ኢትዮጵያውያን ሁሉ።

ሰላም!!

አዶኒስ (ከሲኤምሲ)

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You