‹‹ትውልዱ የዓድዋን የነጻነት ድል በኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለመድገም በጽናት ሊሠራ ይገባል›› – ልጅ ዳንኤል ጆቴ

ልጅ ዳንኤል ጆቴ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት

የዓድዋ ድል ስለእኩልነት፣ ስለፍትሕ፣ ስለሰብዓዊ መብት ፣ስለሀገር ሉዓላዊነት፣ ስለ ወገን ፍቅር፣ ስለሀገር ክብርና ነጻነት ሲሉ ጥንታዊዎቹ አባቶቻችን እና እናቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘ አንጸባራቂና አኩሪ ድል ነው። ድሉ ሀገራችን ኢትዮጵያን በቅኝ ገዢዎች መንጋጋ እንዳትታኘክ ያደረገና ህልማቸውን በከንቱ ያስቀረ፤ የሕዝቦቿን አይበገሬነት ለዓለም ሕዝብ ያሳየና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራትና ድምቀት የሆነ ነው።

ይህ የካቲት 23 1888 በዓድዋ ተራሮች የተበሰረው ድል ዘንድሮም ለ129ኛ ጊዜ “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ ቃል ይከበራል። የዝግጅት ክፍላችን በዓሉን አስመልክቶ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍንን አናግሮ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

የጣሊያን ወረራና የንጉሱ የክተት ጥሪ አኩርፈው የነበሩ መሳፍንቶችንም ወደ አንድ ያመጣ ነበር።

ልጅ ዳንኤል ስለዓድዋ ዝክረ-በዓል ሲናገሩ፤ ‹‹የዓድዋ ድልን በየዓመቱ የምናከብረው ግፍና ጭቆናን ታግሎ ለመጣል እኩልነትንና ፍትህን ለማንገስ የቀደሙት አባቶቻችን እና እናቶቻችን የከፈሉትን ዋጋ ለማስታወስ ነው። ዝክረ በዓሉን የምናከብረው አባቶቻችን እና እናቶቻችን የከፈሉትን ዋጋ ለማስታወስ ብቻም ሳይሆን ለሕግ መገዛት፣ ለሕዝብ እና ለሀገር መቆም የሚኖረውን ጥቅምም መለስ ብለን ለማየት እንዲረዳን እንጂ ከዛሬ 129 ዓመት በፊት ከጣሊያን መንግሥት ጋር በተደረገው ጦርነት ቂምና ቁርሾ ይዘን ያንን ለማስታወስና ጣሊያንን በጠላትነት መንፈስ ለመመልከት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል ይላሉ።

በጦርነቱ ሂደት ብዙ ነገሮች ተከስተዋል የሚሉት ልጅ ዳንኤል፤ በመጀመሪያ ንጉስ ምኒልክ የጦርነትን አስከፊነት ስለሚያውቁ ጦርነቱ እንዳይካሄድ ከጣሊያን መንግሥት ጋር በተቻላቸው መንገድ ሁሉ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ብዙ አይነት ንግግርም፣ ውይይትም፣ ስምምነትም ለማድረግ ሙከራዎችን እንዳደረጉ የታሪክ መጻሕፍት እንደሚያስረዱ ይጠቅሳሉ።

የዓድዋ ጦርነት በ1888 ከመደረጉ በፊት ራስ አሉላ አባ ነጋ ዶጋሊ ላይ ከጣሊያኖች ጋር ጦርነት ገጥመው ድል አድርገዋቸዋል። የጣሊያን መንግሥት በመሸነፉ በጣም ተናዶ ሌላ ጦር እስከማስመጣት ደርሷል። ከዚያም በኋላ ቢሆን ራስ መኮንን እና ራስ መንገሻ በተለያዩ ቦታዎች ጣሊያኖችን ገጥመው ነበር።

አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያውያን ከጣሊያን ወታደሮች ጋር ጦርነት ቢገጥሙ ማሸነፍ እንደሚችሉ ቀደም ሲል በተደረጉት ትንንሽ ውጊያዎች በሚገባ ተረድተዋል። ይሁንና ከጣሊያን መንግሥት ጋር ድርድር ሲያደርጉ የነበረው አሸንፋለሁ ብለው ሳይሆን ሰው እንዳይጎዳና ነገሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በማሰብ ነበር ይላሉ።

ውይይቱና ንግግሩ እንደማይሳካ ሲያውቁ ግን ሸዋ ላይ ሆነው ክተት ሠራዊት ብለው ነጋሪት በማስጎሰም በአንዲት ትዕዛዝ ብቻ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ነቅሎ ወደ ዓድዋ እንዲዘምት አድርገዋል። በወቅቱ ከአጼ ምኒልክ ጋር የተቃቃሩ መሳፍንቶች ሳይቀሩ ኩርፊያቸውን ወደ ጎን ትተው ሀገር አስቀድመው የንጉሱን የክተት ጥሪ የሀገር ጥሪ ነው ብለው በአንድ ወገን ተሰልፈዋል።

ንጉሱ በመልዕክታቸው ‹‹ሕዝቤ ሆይ ሀገርን፣ ንብረትህን፣ ሚስትህን የሚወርስ የውጭ ወራሪ መጥቶብሃል እና ወረኢሉ ላይ ከትተን ላግኝህ›› ብለው ሕዝብን አነቃንቀው ወደ ዓድዋ ዘምተዋል። ወደ ግንባር የዘመቱት ሕዝቦች ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተነስተው የሄዱ በመሆናቸው በቋንቋ ለመግባባት የሚቸገሩ ነበሩ።

የቋንቋ እና የሃይማኖት ልዩነት ቢኖሯቸውም የመጣባቸው የውጭ ወራሪ ጠላትን ተባብረው ለመምታት ልብ ለልብ የሚግባቡና የሚናበቡ ነበሩ። በወቅቱ የተከሰተው ረሃብና የእንስሳት በሽታም ፈተና ሆነውባቸው ነበር። እንግዲህ ያን ሁሉ ተቋቁመው ነበር የዓድዋን ጦርነት በድል የቋጩት።

እንደ ልጅ ዳንኤል ገለጻ፤ ከዚህ ድል ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ አፍሪካውያንም ብዙ አትርፈውበታል፤ ኢትዮጵያ ከሮማ ‹ኢምፓየር› ጋር በተያያዘ በአውሮፓውያን ዘንድ ገናና ተብሎ የሚጠራውን የጣሊያን መንግሥት አንድ ቀን ባልሞላ ጦርነት ማሸነፏ ውርደቱ ለጣሊያን መንግሥት ብቻ ሳይሆን ለመላው አውሮፓ ነው። ያም ብቻ ሳይሆን ሽንፈቱ በኢምፔሪያሊስት አገዛዝ የሚያምኑ ነጮችን በሙሉ ወሽመጣቸውን የበጠሰ ነበር።

በወቅቱ አንዳንድ ጣሊያናውያን የምኒልክን ማሸነፍ ሲሰሙ መንግሥታቸውን ለመተቸት በጎዳናዎቻቸው እየወጡ ቪቫ ምኒልክ፤ ቪቫ ጣይቱ በማለት ንዴታቸውን ይገልጹ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ድሉ ለመላው ጥቁር ሕዝብ መነቃቃት የፈጠረና ለፓን አፍሪካኒዝም መመስረትም መሰረት የጣለ ነው። ከዓድዋ ድል በኋላ በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የአፍሪካ ሀገሮችም ነጻነታቸውን ለማረጋገጥ አመጾችን ማድረግ ጀምረዋል። ይህ ድል አውሮፓውያንን ያስቆጣና አፍሪካን በቅኝ ግዛት የያዙ ሀገራትን በሙሉ ያስደነገጠ ነው።

አዲሱ ትውልድ እንደቀደሙት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ዛሬም ጋሻ እና ጦር ይዞ ወደ ጦርነት መግጠም አይጠበቅበትም። የቀደሙት ትውልዶች አጥንታቸውን ከስክሰው እና ደማቸውን አፍስሰው ያስረከቡትን ሀገር አዲሱ የአሁኑ ትውልድ በሚከተለው አዲስ አስተሳሰብና ሥልጣኔ መንገድ ተጉዞ፤ ሀገሩን በትምህርት ማሻገር ይኖርበታል። ሀገሩን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ማሳደግ፤ በኢኮኖሚም መገንባት ይጠበቅበታል። ይህን ማድረግ ሲችል የትናንትናው ትውልድ የከፈለው ዋጋ ፍሬ አፈራ ማለት ነው።

ወጣቱ የአባቶቹን አደራ አስጠብቆ ለመጓዝ ከሁሉ በፊት ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይገባዋል። ትናንት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ያቀያየመው ምን ነበር? ለምንድን ነው ሁልጊዜ እርስ በእርሳችን የምንጨቃጨቀው? ለምንድን ነው ግጭት ውስጥ የምንገባው? የሚሉትን መረዳት ይኖርበታል።

ትውልዱ ከስሜታዊነት ወጥቶ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምክንያታዊና አዎንታዊ መልስ መስጠት አለበት። ያለፈው ስህተት እንዳይደገም ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፤ የተሳሳቱ ታሪኮችን እና በተሳሳተ መንገድ የተተረጎሙ ድርጊቶችን ለትምህርትነት ሊጠቀምባቸው ይገባል እንጂ እነርሱን እያጎላ ለመጥፎ ዓላማ ሊጠቀምባቸው አይገባም። ይልቁንም ከተለያየ አካላት የሚሰነዘሩ መጥፎ አስተሳሰቦችን መመከት ይኖርበታል እንጂ የተባለውን መጥፎ ነገር ሁሉ እየሰማ እውነት ነው እያለ የሚቀበል መሆን የለበትም።

ወጣቱ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ከሚነዙ እና ከሚያጋጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል። እኛ ሰዎች በተፈጥሯችን ደካሞች ነን፤ ጥሩ ነገር እንደሚያስደስተን ሁሉ መጥፎ ነገርም ስንሰማ ቶሎ እንቀየማለን፤ እንጠራጠራለንም፤ ስለሆነም አዲሱ ትውልድ ራሱን በእውቀት አበልጽጎ በቴክኖሎጂ የመጠቀም እድሉን አስፍቶ ዘመኑ በሚፈቅደው መንገድ ሀገሩን መጥቀም ይኖርበታል እንጂ በሶሻል ሚዲያ የሚሰማቸውንና የሚያያቸውን ነገሮች እውነት ናቸው ብሎ በመቀበል ሰላምና ጸጥታ በሚያደፈርሱ፤ በሕዝቦች መካከል መቃቃርና ልዩነቶችን በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ የለበትም።

ባለንበት ዘመን መንግሥትን ለማዳከም እና ሕዝብን ለመከፋፈል የሚፈልጉ አካላት ስላሉ ወጣቱ እነዚህን መጥፎ ይዘት ያላቸው መልዕክቶችና ቅስቀሳዎች ወይም የጥላቻ ንግግሮች እየመረመረ በማስተዋል ሊጓዝ ይገባዋል።

ትውልዱ ልማትና ዕድገትን የሚደግፍ መሆን አለበት፤ ከዘመኑ አስተሳሰብና ስልጣኔ ጋር የሚሄዱ አሠራሮችን የሚከተል፤ ምክንያታዊ አስተሳሰቦችን የሚያራምድ እና ለታናናሾቹ አርዓያ የሚያደርጉትን ተግባራት ማከናወን ይጠበቅበታል።

መተቸት ብቻ ሳይሆን በተሠሩ ሥራዎች እና በታዩ ለውጦችም ማመስገንን መለማመድ አለበት፤ እንደሀገር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በየአካባቢው የተሠሩ የቱሪስት መዳረሻዎች የስልጣኔ መገለጫዎች እንጂ ወደ ኋላ የሚመልሱ ኋላ ቀር ድርጊቶች ስላልሆኑ መደገፍና መተባበር ከአዲሱ ትውልድ ይጠበቃል። ሀገርን ወደፊት የሚያሻግሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን፣ የከተማ ልማቶችን በመደገፍ አባቶቹ ያስረከቡትን የዓድዋ ድል ማድመቅ ይኖርበታል እንጂ ያለምንም ሥራ እና ለውጥ በየዓመቱ የዓድዋ ድል እያሉ ማክበር ብቻ የተከፈለውን መስዋዕትነት እንዳያደበዝዝብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

የጥናታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የፖለቲካ ማህበር አይደለም ያሉት ልጅ ዳንኤል ጆቴ፤ አባቶቻችን እና እናቶቻችን የተሰዉት ለሀገር ክብርና ለሕዝብ ጥቅም እስከሆነ ድረስ ማህበሩም የእነርሱን አርማ አንግቦ የተነሳ ነውና ለሀገር የሚበጁ ሥራዎችን በሙሉ የመደገፍ ግዴታ አለበት፤ ሀገርን የሚጎዱ ድርጊቶችንም ይነቅፋል፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ጉዳይ ጉዳዩ ነው። ይህ ደግሞ ከአባቶቻችን እና ከአያቶቻችን የወረስነው ነው። ማህበሩ በሀገር ጉዳይ አይደራደርም፤ ስለዚህ ትውልዱ ትናንትን የሚዘክረው ዛሬን የተሻለ ለማድረግ ስለሆነ፤ ትናንት አባቶቹ የወደቁለትን እና የከፈሉለትን መስዋእትነት የሚያጸናው ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ሥራዎችን ሠርቶ ሀገሩን እና ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ሲችል ነው ይላሉ።

ወጣቱን በመምከርና ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲመጣ በማድረግ ፋንታ በተሳሳተ መንገድ እንዲሄድ የሚያደርጉ ትልልቅ ሰዎችም ስለ ቀደሙት አባቶቻቸው ተጋድሎና ስለ ሕዝቦች ደህንነት ሲሉ ራሳቸውን ከስህተት መንገድ መግታት ይኖርባቸዋል። አባቶቻችን የዓድዋን ጦርነት በድል የተወጡት ከቀደመ ልምድና ተሞክሮ በመነሳት ነው፤ እንግሊዞች አጼ ቴዎድሮስን ፣ ሱዳኖች አጼ ዮሐንስን ማጥቃት የቻሉት በወቅቱ የነበሩት መሪዎች የመተባበርና የመደጋገፍን ጥቅም በውል ባለመረዳታቸው ነው።

ይህ ስህተት ከዚያ በኋላ ለተከሰተው የዓድዋ ጦርነት ትምህርት ሆኗል። ጠላትን ማንበርከክ የሚቻለው በተበታተነ ኃይል ሳይሆን በመተባበር እንደሆነ አሳምኗል። ለዚህም ነው በዓድዋው ጦርነት የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ጠላቱን በመፋለም ለመላው ጥቁር ሕዝብ የተረፈ ድል ያስመዘገበው።

በ38ኛው የአፍረካ ኅብረት ጉባኤ የባርባዶሷ ጠቅላይ ሚኒስትር የተናገሩት ታሪካዊ ንግግር፤ የዓድዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ያረጋገጠ ነው። ይህ ድል የተገኘው በአንድ ሰው ሳይሆን በመላው ሕዝብ መደጋገፍና መተባበር ነው። ዓድዋ ሲታሰብ የአፍረካ ሕዝብ ነጻነት ይታሰባል፤ ዓድዋ ሲታሰብ ፓን አፍሪካኒዝም ይታሰባል።

ግጭት በማህበረሰብ ውስጥ ምንጊዜም ሊከሰት የሚችል ጉዳይ ነው፤ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳን በባልና በሚስት ፣ በመንታ ወንድማማቾችና እህትማማቾችም ጭምር ሊከሰት ይችላል። ባልሰለጠኑ ሀገራት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ድረስ እንደ ሩሲያ እና ዩኩሬንን በመሳሰሉ የሰለጠኑ ሀገራትም ሲከሰት አይተናል። በእኛም ሀገር ቢሆን ግጭት አለ፤ ዋናው ጉዳይ ግጭቱ እንዴት ተወለደ? ማን ወለደው? ለምን እንዲኖር ተፈለገ? የግጭቱ ተጠቃሚ ማነው? ተጎጂውስ ማነው? የሚለውን መረዳት ላይ ነው።

የአሁኑ ትውልድም ከዓድዋው ድል አንድነትን፣ ኅብረትን መማር አለበት፤ እንደአባቶቹ ሁሉ ለሀገሩ ሰላምና ደህንነት፣ ለሕዝቡ ፍቅርና አንድነት ቅድሚያ መስጠት አለበት። እንደድሮው ዘመን ችግሮችን በመሣሪያ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ቁጭ ብሎ መነጋገርን የመጀመሪያው መፍትሔ ማድረግ ይኖርበታል። ከእውቀት፣ ከፍቅርና ከሰብዓዊነት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል።

በተለይም አሁን እንደ ሀገር የተጀመረውን ሀገራዊ የምክክር መድረክ መጠቀም ይኖርበታል። ከሁሉ በፊት ሰላሙን ማረጋገጥ አለበት፤ ሰላምን ለማስፈን ደግሞ ዱላና ጠመንጃ ማንሳት አይጠበቅበትም። በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በችግሮች ላይ መነጋገርና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገውን መስመር መከተል ይገባዋል።

ከዚህ ጋር የሕዳሴ ግድቡን ጉዳይ ማንሳት ያስፈልጋል፤ ግድቡ ሲጀመር ተቃውሞ ያሰሙ ሀገራት ነበሩ፤ ምዕራባውያንም ጫና ማሳደር ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሥራው እየተሠራ ጎን ለጎን ውይይት ይደረግ ነበር፤ ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ የደረሰው እየተነጋገሩ በአንዳንዶቹ ጉዳዮችም ቢሆን መግባባት ላይ በመደረሱ ነው። ስለዚህ ንግግርና ውይይት ሁልጊዜም አሸናፊ ነው።

ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የበለጠ ወጣቱ ትውልድ ሀገሩን የማስቀጠል ኃላፊነት አለበት፤ ስለሆነም በአዕምሮው ውስጥ የተዘሩ መጥፎ ነገሮችን አውጥቶ በመጣል አንድነቱን እና ሰላሙን ማስጠበቅ እንደሚገባው መክረዋል። የእድሜ ባለጸጋ የሆኑ ሰዎችም ወጣቶችን በመምከር፣ አንድነታቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መልእክት አስተላልፈዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You