ትውልድ በኩራት የሚዘክረው ባለ ታላቅ ገድል ልማት ነው

ኢትዮጵያ ታሪካዊት አገር፤ ሕዝቧም የዚህ ታላቅ ጀብዱ ባለቤት ነው። ይህ ጀግና ሕዝብ የብሔር፤ የሃይማኖት፡ የጾታ እና ሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ሳይበግሩት ወደ ዓድዋ በአንድነት በመትመም ቅኝ ገዢዎችን አሳፍሮ መልሷል። ለሉአላዊነቱና ለነጻነቱ ቀናኢ ሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገሩ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ልትወድቅ መሆኑን በሰማበት ቅጽበት ቀፎ እንደተነካበት ንብ ከአራቱም ማዕዘናት በአንድነት ተሰባስቦ ሀገሩን ታድጓል፤ ታሪክ ጽፏል፤ ለመላው ጥቁር ሕዝቦችም መከታ ሆኗል።

ዛሬም ይህ ኩሩ ሕዝብ ሌላ ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች፣ በነጻነትዋ የኮራች፣ የብዙ ባሕልና ቋንቋ ባለቤት የሆነ ሕዝብ የሚኖርባት ታላቅ ሀገር ነች። ከአፍሪካ የቀደምት (ጥንታዊ) ስልጣኔ ባለቤት የታላላቅ ወንዞች መፍለቂያ እና የበርካታ ሀይቆችም መገኛ ናት።

ኢትዮጵያ ከድህነት ተላቃ በምጣኔ ሃብት እድገት ለማስመዝገብ የተፈጥሮ ሃብቷን በተለይም የውሃና ኢነርጂ እምቅ አቅሟን ለማልማት ቆርጣ በመነሳት በትልቁ ዓባይ ወንዝ ላይ በራስ አቅም ግድብ ለመገንባት መጋቢት 24 /2003 ዓ/ም ይፋ አደረገች። ይህ ታሪክ ከተጻፈ አስራ አራት ዓመታት አስቆጠረ።

የግድቡ ይፋ መደረግ የዘመናት ቁጭትና ወኔ ሊቋጭ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ዓድዋ ጦርነት በመላው ሀገሪቱ ከተሞች አደባባይ በመውጣት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለልማት በድጋፍ ሰልፍ ከተሞች ተጥለቀለቁ። ሕዝቡ በያለበት አንድም ሰው የቀረ እስከማይመስል ድረስ ግልብጥ ብሎ በመውጣት “በተፈጥሮ ሃብታች መጠቀም ሉዓላዊ መብታችን ነው!” “ያለማንም ድጋፍ እና ብድር ተባብረን ዓባይን እንገድባለን!”፣ “ዓባይን በፍትሃዊነት በጋራ እንጠቀማለን!”፣ “ድሮም ተካፍሎ መብላት ባሕላችን ነው!” ሲሉም በአደባባይ በመፈክር፣ በጃሎታ እና በዜማ ገለፁ።

ዓባይ ሁሉንም በጋራ አንድ አድርጎ በማሰለፉ ከልጅ እስካዋቂ፣ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል፣ ሃብታም ድሀ ሳይል፣ ምንም አይነት የፖለቲካ፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ወዘተ ልዩነት ሳያግደው ለግድቡ ድጋፍ ለማበርከት ከጫፍ ጫፍ በአንድነት ተሰለፈ። ሰራተኛው ከወር ደሞዙ፣ አርሶ አደሩ ከምርቱ፣ አርብቶ አደሩ ከሚያረባቸው እንስሳቱ፣ ነጋዴው ከንግዱ፣ ባለሃብቱ ከጥሪቱ፣ ምሁሩ በእውቀቱ፣ የኪነ ጥበብ እና ስነ ጥበብ ባለሙያው በሙያው፣ ተማሪው ከወር ቀለቡ፣ የቀን ሰራተኛ ከእለታዊ ገቢው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት መስክ ከሚያገኘው ቆጥቦ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በመደገፍ ግንባታውን ጀምሮ ለመጨረስ ተነሳ።

በመላው ሀገሪቱ ያለምንም የውጭ ሀገራት ብድርና ዕርዳታ በራሳችን አቅም ግድባችንን መገንባት እንችላለን ሲል ለግድቡ በሞራል፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት፣ በሙያና በፐብሊክ ዴፕሎማሲ ድጋፉን አጠናክሮ ቀጠለ። በዓባይ ወንዝ ላይ በራስ አቅም ግድብ መስራት የልማት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነትና የማንነት ጉዳይ መሆኑን ሕዝቡ በተጨባጭ ድጋፍ አረጋገጠ።

የሀገር ውስጡን የሕዝብ የድጋፍ ማዕበል ተከትሎ በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እና በትውልድ ኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገሩ ልማት በጋራ በመነሳት ታላቁ የሕዳሴ ግድብን መገንባት ሀገራዊ ግዴታ ነው ሲል፣ በገንዘቡ፣ በዕውቀቱ እና በፐብሊክ ዴፕሎማሲው መስክ ለሀገሩ አምባሳደር በመሆን ድጋፉን አጠናክሮ ቀጠለ። ዲያስፖራው ለሀገሩ ግድብ በውጭ ምንዛሬ ቦንድ በመግዛትም ሆነ በስጦታ ሲያበረክት ርቀትም ሆነ ድንበር አልገደበውም።

መላው ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚገኙት ለግድቡ ያሳዩት የድጋፍ መነሳሳት ሰፊና ሁሉን አቀፍ በመሆኑ ይህን ድጋፍ ለማስተባበር የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የሆነ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ተቋቋመ። በምክር ቤቱ በተቻለ መጠን በሀገር ውስጥ የሚገኙ የሲቪል ማሕበራት እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች፣ ሙያ ማሕበራት እና ታዋቂ የሀገራችን ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወዘተ… የተካተቱ ሲሆን የምክር ቤቱንም ተግባር ለማከናወን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በደንብ ቁጥር 244/2003 ዓ/ም ተቋቁሞ ወደ ተግባር ተገባ።

የሕብረተሰቡ ድጋፍ በዓይነትም ሆነ በብዛት ሰፊ ከመሆኑ አንጻር ተሳትፎውን በዘላቂነት ለማስቀጠል እና በትክክል ለታለመለት ግብ እንዲውል ለማስቻል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ በተግባር ላይ በማዋል ለግድቡ በየወሩ ከደሞዝ ላይ እስከ አስር በመቶ እየቆረጡ በመደገፍ እግረ መንገድም የዜጎችን የቁጠባ ባሕል ማሳደግ ተቻለ።

ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በብሔራዊ ደረጃ እና በክልሎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች በሚከናወኑ የንቅናቄ እና ሃብት ማሰባሰቢያ ሁነቶች ከሕዝብ በስጦታ የሚመጡ ልዩ ልዩ ድጋፎችን (የቀንድ ከብት ግመሎች፣ ሌሎች እንስሳት፣ አዝርዕቶች፣ የቅባት እህሎች፣ ማዕድናት፣ ቁሳቁሶች፣ ወዘተ…) በገንዘብ ተለውጠው በልገሳ እንዲገቡ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል። እስካለፈው ጥር ወር ድረስ በቦንድ ግዢ እና በስጦታ ባለፉት ዓመታት ባጠቃላይ ከሀገር ውስጥ 17 ቢሊዮን 994 ሚሊዮን 511ሺ ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ዲያስፖራውም ከተለያዩ ዓለማት 1ቢሊዮን 502 ሚሊዮን 390 ሺ ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

ሕብረተሰቡ በቦንድ ግዢ እና ልገሳ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያ እና ንቅናቄ መፍጠሪያ ሁነቶች በስፋት የተካሄዱ ሲሆን በተለይም በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ወገኖችን በቀላሉ ማሳተፍ እንዲቻል የ8100 -A የሞባይል አጭር መልዕክት ዕጣ ተዘጋጅቶ ለሶስተኛ ዙር በአየር ላይ በማዋል በአንድ መልዕክት ሶስት ብር በመላክ በአንደኛው እና በሁለተኛው ዙር ወደ 140 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል። ለ8100 A እና ለተለያዩ ሕዝብ ተሳትፎ እንዲውሉ ከተለያዩ ድርጅቶችና ባለሃብቶች በልገሳ የተሰበሰቡ ከመኖሪያ ቤት እና ከዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ጀምሮ በርካታ ዕጣዎችን ለደረሳቸው ዕድለኞች በመሸለም በርካቶች በሕዳሴ ግድብ ገጸ-በረከት ተንበሽብሸዋል። ዕጣ ያልደረሳቸውም ቢሆኑ በግድቡ ላይ የጣት አሻራቸውን በማሳረፍ የታሪክ ባለቤት ሆነዋል።

በዓለማችን የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ በሀገራችንም ስጋት በደቀነ ጊዜ ሕብረተሰቡን በማሰባሰብ የሚከናወኑ ሁነቶችን እና መድረኮችን ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ከኮቪድ ስጋት ነጻ ሆኖ በጣቱ ሞባይሉን በመጫን በ8100-A ለግድቡ ቤተሰብ በመሆን 1 ብር ድጋፍ የሚያደርግበት አሰራር በሥራ ላይ በማዋል ሶስተኛው ዙር ከተጀመረበት የካቲት 2012 ዓ/ም እስከ ታህሳስ 2017 ድረስ) በዘላቂነት በመቀጠል ከፍተኛ ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሏል። በዚህም ባለፉት ዓመታት የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ እያንዳንዱ ሞባይል ተጠቃሚ በየዕለቱ የሚያስታውሰው አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል። ጽህፈት ቤቱ ባከናወናቸው 8100-A እና በልዩ ልዩ ሁነቶች ባጠቃላይ 1 ቢሊዮን 218 ሚሊዮን 997 ሺ ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ከቦንድ ሽያጭ እና ከስጦታ ጋር በድምሩ 20 ቢሊዮን 715 ሚሊዮን 899 ሺ ብር በላይ ከሀገር ውስጥና ከዲያስፖራ ድጋፍ ተሰባስቧል።

ባለፉት ዓመታት የሀገራችን አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጠቀሜታ በመረዳት ግድቡ ከተያዘለት የአገልግሎት ዘመን በላይ ተሻጋሪ እንዲሆን ግድቡን በደለል እንዳይሞላ በማለት በመላው ሀገሪቱ የተፋሰስ ልማት (የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ) ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ሕዝብና መንግሥት ለተፋሰስ ልማት ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ ተችለዋል። ከግብርና ሚኒስቴር በመጣ መረጃ መሰረት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በማለት በያመቱ በአማካኝ 30 ቀናት በተፋሰስ ሥራ ላይ ያዋለው ጉልበት በገንዘብ ሲተመን ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ግድቡ በሀገሪቱ ዕድገት ላይ ምን ያህል የለውጥ ተነሳሽነት እንደፈጠረ ማሳያ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሚቃወሙት አካላት የሚነሱ ክሶች ስም ማጥፋቶችና አሉታዊ መረጃዎችን በመመከትና በመድፈቅ ኢትዮጵያውያን፣ በትውልደ ኢትዮጵያውን እና ወዳጆቻችን የሆኑትን በዓለም ዙሪያ በማስተባበር በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጫና በማሳደር የተሰራው ሥራም ለመደበኛ ዲፕሎማሲው ቀላል የማይባል እገዛ አድርጓል። “አንድ ድምጽ ለግድባችን!” “One Voice for Our Dam!” በሚል በተለያዩ ሀገራት በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያውን ለግድባቸው ድጋፋቸውን እንዲገልጹ በማድረግና ፒቲሽን ፊርማ በማሰባሰብ እንዲሁም ለግድቡ የድጋፍ ሰልፍ በማድረግ የምዕራባውያን ሀገራትን ከተሞች በማጨናነቅ ዲያስፖራው የሰራው በውጭ ሀገር ሆኖ ለሀገሩ የመቆም ተግባር በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖር፣ ትውልድን የሚያኮራ ታላቅ ገድል ነው። ለዚህም ነው እስከ የተ.መ.ድ ፀጥታው ምክር ቤት ድረስ ተከሰን በድል የወጣነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያዊ “ዓባይ የኔ ነው!” በሚል በባለቤትነት እየገነባው ያለ የግንባታውን ሂደት ለማየት የሚመኘው ግድብ ነው። በዚህ የተነሳ ቦታው ከመሀል ሀገር እጅግ ርቀት ቢኖረውም ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ እና ምስራቅ ጫፍ ተነስተው በርካታ ዜጎች በቡድን እና በግል ጭምር ግድቡን ጎብኝተውታል። ዲያስፖራዎችም ባገኙት አጋጣሚ በቡድን ሆነው ግድቡን ጎብኝተዋል።

ከኢትዮጵያውያንም በዘለለ የግድቡ ዜና በመላው ዓለም የተገናኘ በመሆኑ ከዓለም ዙሪያ በርካታ ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶች እና ከፍተኛ የልዑካን ቡድኖች እና መሪዎች ግድቡ ድረስ በመሄድ አይተዋል፣ ተደንቀዋል፣ ከመደነቅም በላይ ግድቡ የማይቀለበስ እና ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የተሰለፉበት፣ ለሀገሪቱ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ተረድተዋል። በዚህም ያለ ምንም ዓለም ዓቀፍ ድጋፍ ኢትዮጵያ በሕዝቦችዋ እና በመንግሥት የተቀናጀ ጥረት ማደግ እንደምትችል ግድቡ ራሱ መስክሯል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የውሃ ሃብቷ ተጠቅማ ድህነነትን ታሪክ ለማድረግ ከምትገነባቸው ፕሮጀክቶች ግንባር ቀደም የሆነው ከላይ በተዘረዘሩትና ተነግረው በማያልቁ በርካታ ድጋፎች፣ እንዲሁም በሀገሪቱ ያስነሳው የይቻላል ስሜት እና የድጋፍ ማዕበል ጭምር ነው።

ግድቡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የዘመናት ቁጭትና ምኞታቸውን በትውልድ ቅብብሎሽ ያሳኩበት፤ ሲሆን ግድቡን ከጥንት ነገሥታት ጀምሮ ለመገደብ ሲያልሙት የነበረ፤ ግድቡ በአፄ ኃይለ-ስላሴ ቢጠናም፣ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ሙከራ ቢያደርጉም በአቶ መለስ ዜናዊ ግንባታው ተጀምሮ፣ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የመርህ ስምምነት ተፈርሞ፣ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የግድቡ ችግሮች ተፈተው ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ነው።

በዚህም የሀገራችን መሪዎች ግድቡን በቅብብሎሽ በመገንባት አሁን ለደረሰበት የፍጻሜ ደረጃ አድርሰውታል። ይህ ትውልድም ከመሪዎቹ ጎን በመሰለፍ ያለምንም ልዩነት ባለው አቅም ተረባርቦ ግንባታው በተግባር እውን እንዲሆን በማድረጉ በታሪክ ማሕደር በትልቅ ሥፍራ ተመዝግቦ ትውልድ በኩራት የሚዘክረው ባለ ታላቅ ገድል የሆነበት ልማት ነው::

(ይህንን ጽሁፍ ለማሰናዳት ብሔራዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የተገኙ አሃዛዊ መረጃዎችን በምንጭነት ተጠቅመናል)

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You