ነገረ- “CADUTI” እና አስገራሚው የንጉሡ ውሳኔ

ስለ ዓድዋ ያልተባለ እንደሌለ ሁሉ ያልተነገረለትም አለ። ስለ ዓድዋ እና ድሉ ያልተፃፈ፣ ያልተዜመ፣ ያልተሣለ፣ ያልተገጠመና ያልተደረሰ፤ ያልተጠና ሁሉ የሌለ ይመስላል እንጂ በተቃራኒውም ስለ መኖሩ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለምና ዛሬ ስለዚሁ “ምስጢር” እንነጋገራለን።

ስለ እናት-አባቶቻችን ታሪካዊ ገድል፣ ዘላለማዊ ክብር፤ ጀግንነታዊ መዋዕል እንናገራለን እንጂ፤ ጀግንነታቸውን፣ ክብር እና መዋዕለ ዜናቸውንና ዘመን ተሻጋሪ አርበኝነታቸውን ከእኛ በላይ ስለሚናገረው፤ ስለሚመሰክረው ታሪክ የምናውቀው ነገር የለምና ዛሬ ስለዚሁ፣ የፋሺስት ሞሶሎኒን የራስ በራስ ተገላልጦ እምንለው ይኖር ዘንድ ፈቅደናል።

የአውሮፓውያንን መብት ረጋጭነት፤ ነፃነት ገፋፊነት፤ ባሪያ ፈንጋይነት፤ ባጭሩ የነጭን የአፍሪካ ተቀራማችነት ፍላጎት በአርበኞቻችን ተጋድሎ እንደ ጉም መብነኑ በሁሉም ሁሌም ይነገር እንጂ፤ እንደ CADUTI እውነቱን ፍንትው (Firsthand Information እንደሚባለው አይነት) አድርጎ የሚናገር ያለ አይመስልምና ስለ ተናጋሪው ሐውልት (ካዱቲ) እዚህ ማውራቱ የግድ ይሆናል።

ብዙ ጊዜ አሸንፈናል፤ ድል አድርገናል፤ ሲጋልብ የመጣን አህያ ቀርቀብ አድርገን በመጫን ሥራችንን ሠርተናል፤ ከላይ የነበረውን የበላይነት ወደ ስር እንዲገባ አድርገነዋል ወዘተ እንላለን እንጂ ይሄንን ሁሉ አሳምሮ ከሚመሰክረው፤ “አዎ፣ ተሸንፌያለሁ፤ ድል ተደርጌያለሁ፤ ያለ አጥቢያዬ ስጋልብ በመምጣቴ ምክንያት ቀርቀብ ተድርጌ ተጭኜ ጀርባዬ እስኪላጥ ተገርፌያለሁ፤ ከላይ ነበርኩና ለዘልዓለሙ ከላይ እሆናለሁ ስል እስር ውያለሁ፤ ተዋርጃለሁ” የሚለውን ተናጋሪ ሐውልት ብዙዎቻችን የመናገር ዕድል አልሰጠነውምና ከዛሬ ጀምሮ እንሰጠው ዘንድ ወደ እዚህ ገጽ ይዘነው መጥተናል።

እውነት ወዳድ፣ ሃይማኖተኛና የኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ወዳጆች፣ ከፈረንሣይ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ለጦር መሣሪያ ጥገና የመጣውንና ወደ ሀገሬ አልመለስም በማለት ከአርበኞቻችን ጋር ወደ ዓድዋ ያቀናውን ካፒቴን ኦርዲናንስን የመሳሰሉ (ከሀገራትም የአውሮጳ መንግሥታት ሩሲያና ፈረንሳይ የዓድዋን ድል ከልብ መደገፋቸውን ልብ ይሏል) ሳይቀሩ የተሳተፉበት (ጄኔራል አልቤርቶኒ በምርኮኛነት ኢትዮጵያ ውስጥ ቆይቶ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ በፃፈው መጽሐፍ ላይ “ከሚፎክሩት ጥቁር የነፃነት ተዋጊዎች መሐከል አንዱ እንደ እኛው ነጭ አውሮጳዊ ነው” በማለት መመስከሩንም ልብ ማለት ይገባል) ዓድዋ የሚገኘውና ከእኛው የአራት ኪሎው የሰማዕታት ሐውልት ጋር በ”እኩያነት” ይቆም ዘንድ ታስቦ ለአደባባይ የበቃው ካዱቲ ሐውልት ስለ ሁሉም ነገር የሚለው አለውና እዚህ እንመለከተው ዘንድ ከተደበቀበት ጥሻ ውስጥ፤ ሣሩን ገለጥለጥ አድርገን ብቅ አድርገነዋል።

በየትኛውም መድረክም ሆነ አደባባይ ስለዚህ፣ ስለ አርበኞቻችን ወደር የለሽ ጀግንነት ተናጋሪ ሐውልት ሲነገርም ሆነ ሲዘከር አለመስማትና መታየቱም እዚህ ይዘነው ብቅ እንል ዘንድ እንደ አንዱ ምክንያት ሆኖ አገልግሏል።

ይህ በቡዙዎቻችን ብዙም የማይታወቀው ሐውልት በአንዳንድ ጸሐፍት ሥራዎች ላይ “ያልታወቀው የጣሊያን ወታደር ሐውልት” የሚል ካፕሽን ከስሩ ተፅፎበት ይገኛል። ለምሳሌ ይህንን አበበ ሐ/ወይን (ዶ/ር) አድርገውታል፤ በ2008 ዓ.ም መቶ ሃያኛው ዓመት የዓድዋ ድል ዝክረ-በዓልን ምክንያት በማድረግ ባቀረቡት ሰፋና ታሪካዊ የሆነ ጽሑፍ ላይም ሌሎች ደግመውታል።

ይህ ስህተት ነው። CADUTI ማለት በጣሊያንኛ በጦርነቱ ምክንያት እዚህ የተሰዋችሁ ወገኖቻችን ሁሌም እናስታውሳችኋለን፤ እናስባችኋለን” ማለት ሲሆን፤ ሐውልቱ ልክ እንደ እኛው የአራት ኪሎው የሰማዕታት ሐውልት መሆኑ ነው። ይህ ትርጓሜ ይህ ጸሐፊ እቦታው (ዓድዋ ከተማ) ላይ ተገኝቶ ከሚመለከታቸው አካላት የተሰጠው ማብራሪያ ነው።

በመሆኑም፣ ሐውልቱ እነ ሞሶሎኒ “ሠማዕታት” ያሏቸውን የፋሺስት ሠራዊት ሁሉ በአንድ የሚወክል እንጂ የአንድ “ያልታወቀው የጣሊያን ወታደር ሐውልት” አይደለም። ይህ ስህተት በሌሎችም እንዳይደገምና የታሪክ ዝበት እንዳይፈጠር በማሰብ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ራሱን ችሎ እዚህ እንዲሰፍር ተደርጓል። (ይህ ሐውልት አሁንም በዚሁ ስፍራ ስላለ ሄዶ መመልከት፤ የቆመበትን ዓላማም መጠየቅ (ጀስቲፋይ ማድረግ) ይቻላል።

እዚህ ላይ ቦታው ላይ ተገኝተን ከተሰጡን አስገራሚ አስተያየቶች መካከል አንዱ በቀጥታ ከሞሶሎኒና ዳግማዊ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ ጋር የተያያዘ ነው። ጉዳዩ እንዲህ ነው። “የነጭን አንገት ያስደፋ በሀፍረት ያሸማቀቀ በፍርሀት ያርበደበደ፤ ኢትዮጵያዊነት ኩራት፣ አፍሪካዊነት ኩራት፣ ጥቁርነት ክብር መሆኑን ያስመሰከረ የአፍሪካውያን ኩራት የዓድዋ ድል” የተባለለት የዓድዋው ጦርነት በኢትዮጵያውያን አርበኞች አማካኝነት፣ በኢትዮጵያ የበላይነት በድል ተጠናቀቀ። ጥቂት ተራፊ የፋሺስቱ አባላትም በተደረገላቸው ምሕረት አማካኝነት ወደ መጡበት ተመለሱ።

በአጠቃላይ መለየት አቃተን ዳንሱን ከዳንሰኛ የሚለው ውድቅ ሆኖ አሸናፊውና ተሸናፊው፤ ድል አድራጊውና ድል ተደራጊው፤ እውነተኛና ሐሰተኛው፤ በዳይና ተበዳዩ — ተለይተው፤ ካባውን ከደረበው ማቁን ከተከናነበው ተለይቶ አቢሲኒያ ምድር ላይ የድል ሸማ፤ ሮማ ላይ የሀፍረት ማቅ ተለብሶ የተሸናፊነት ሥነልቦና ነግሷል። ይህ ባለበት ሁኔታ ሞሶሎኒና ቡድኑ አንድ ነገር ትዝ አላቸው፤ ዓድዋ ላይ በለኮሱት ጦርነት ምክንያት ዶጋ-መድ ለሆኑት ወገኖቻቸው አንድ መታሰቢያ ሐውልት መትከል እንዳለባቸው ተገነዘቡ። ግን እንዴት፣ እንዴት ሆኖ?

ይህንን ሀሳብ እያብላሉ እያሉ ከወደ ፋሺዝም መንደር አንድ “ግሩም” ሀሳብ መጣለት፤ ለሰማዕታት ወገኖቻቸው እዛው፣ እቦታው – ዓድዋ ላይ አንድ የመታሰቢያ ሐውልት ይሠራ ዘንድ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን መጠየቅ። ግን እንዴት ሆኖ፤ ምንስ ተብሎ ይጠየቅ? ማንስ ደፍሮ ንጉሡ ፊት ቆሞ “ክቡርነትዎ • • •” ብሉ ይጠይቅ? የተሸናፊነት ልቦናስ እንዴት ብሎ ከንፈር እና ከንፈር ይላቀቁ ዘንድ ይፍቀድ፤ የትኛውስ ወንድ ነው “ለሰማዕቶቻችን • • •” (እኔን ሰማዕት ያድርግኝና) ብሎ፣ ደፍሮ፣ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘንድ (ፊት) ቆሞ ጥያቄውን እሚያቀርብ?

ሄዶ ሄዶ ጥያቄው መቅረቡ አልቀረምና፣ የፋሺስቱ ሥርዓት ዓይኑን በጨው አጥቦ (በልቡ በዓድዋ ጦርነት ተማርኮ “የምኒልክን ፊት ከማይ ግደሉኝ” ያለውን በማስታወስ) የሰማዕታት ሐውልት መገንቢያ ስፍራ ይሰጡት ዘንደ ንጉሡን ጠየቀ። በጣም አስገራሚ ተግባር በንጉሡ የተፈፀመው እዚህ ጋ ነው። ንጉሡ “ቆይ ልምከርበት” አሉ። የጊዜ ቀጠሮም ሰጡ። በቀጠሮው መሠረትም ለእነ ዱቼ መፈቀዱ ተነገራቸው። ያልተጠበቀ ነበርና ከነድንጋጤያቸው እጅ ነስተው ውሳኔውን ተቀበሉ። ርዕሰ ጉዳዩም በዓለም ዙሪያ መነጋገሪያ ሆነ። “እማይታመን ነው” ያሉ የመኖራቸውን ያህል የንጉሡን ብልህነት፣ አርቆ አስተዋይነትና በሳል መሪነት የሚያውቁ ሁሉ “ያደርጉታል፤ ሆኗል” ሲሉ ደመደሙ። እምነታቸውን በነበር፤ ዓላማም አላቸውና ንጉሡ አድርገውታል-ፈቅደዋል።

በተፈቀደው መሠረት ይህ ከላይ የተመለከተው ሐውልት በፍጥነት ተገነባ። መልዕክቱም CADUTI (በጦርነቱ ምክንያት ሰማዕት ለሆኑ ወገኖቻችን መታሰቢያ ይሁንልን) ይሆን ዘንድ ከወደ ሮማ ተወስኖ ነበርና ሆነ። ይህ በ“እስኪቃል ምረጡ” (ካየን አዳም፣ 2006 ዓ•ም)

ዓድዋን ለመግለጽ ስነሳ ቃላቶች ያጥሩኛል፣

አፉን እንዳልፈታ ሕጻን ያደርገኛል።

እስኪ ሆሄ አዋጡ እስኪ ቃል ምረጡ፣

የዓድዋን ታላቅነት የሚገልጽ በቅጡ።

በተባለላት፣ ታላቁ የጥቁር ሕዝቦች ድል ስፍራ የሆነችው፤ የፓን-አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ይገነባባት ዘንድ የመሠረት ድንጋይ የተጣለባት (ከብዙዎቹ አንዱንና ይህንን ጸሐፊ እጅጉን የመሰጠውን፣ የገበየሁ አየለ ተካን “ኢትዮ-አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ” መጽሐፍን መመልከት ጠቃሚ ነው) ውዷ ዓድዋ ላይ በኢጣሊያዊው መንግሥት የተገነባው፣ በሕያው ምስክርነት ቆሞ የሚታየው CADU­TI “የሰማዕታት” ሐውልት የሚናገራቸው በርካታ አንኳር አንኳር የድል ታሪኮች ያሉ ቢሆንም ጎልቶ የሚሰማው ግን ሽንፈትን፣ ውርደትን በራስ አንደበት፣ በራስ ሥራ፣ በራስ ዐሻራ፣ በራስ ውክልና ወዘተ አማካኝነት የተሰጠ የተሸናፊነት ሥነልቦና (ማረጋገጫ) እና ታሪክ መኖሩን ነው።

ይህ ጸሐፊ በቦታው ተገኝቶ በነበረበት ወቅት (እአአ 2005) አብሯቸው ሲወያይ ከነበሩት ሰዎች (የሥራ ባልደረቦችና የከተማዋ ነዋሪዎች) ጋር ሰፊውን ጊዜ ወስዶ ሲያወያይና ሲያስገርም የነበረው የሞሶሎኒ ጅልነት ብቻ ሳይሆን የንጉሡ አርቆ አስተዋይነት ጭምር ነበር።

ወቅቱ በግፍ ተወስዶ፣ በ1930ዎቹ ጣሊያን በምፅዋ ወደብ በኩል በመርከብ ከኢትዮጵያ የወሰደችው፤ ለ68 ዓመታት በባዕድ አገር (ሮም) ባይተዋር ሆኖ የቆየው የአክሱም ሐውልት ከሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጭ (በጣሊያን መንግሥት) የተደረገበት የመልሶ ተከላ ተግባር የተከናወነበት (ወደ ነበረበት አክሱም ከተማ እንዲመለስና ዳግም እንዲቆም የተደረገበት) ልዩ ሥነሥርዓት ወቅት ስለ ነበር ጊዜው ራሱ ከድልና ድል ዜናና ዲስኩር ውጪ ይነገር ዘንድ አይፈቅድም ነበርና የዓድዋው ድልም ሆነ የካዱቲ (CADUTI) ጉዳይ ቢያነጋግሩ ምንም የሚገርም ነገር አልነበረም። በመሆኑም፣ ከዲስኩሮቹ ሁሉ ሰፋ ያለውን ጊዜ ወስዶ የነበረው፣ ከላይ እንዳልነው የሞሶሎኒና አንጃው ጅልነት ብቻ ሳይሆን የምኒልክ አስተዋይነት ነበር።

ይህ የንጉሡ አስተዋይነት ሊያነጋግር የቻለበት ዋናው ምክንያት ደግሞ በዛ የተበዳይነት ስሜት ውስጥ ሆነው፤ በዛ የድል ባለቤት ስሜት ውስጥ ሆነው፤ በዛ የአሸናፊነት ሥነልቦና ውስጥ ሆነው፤ በዛ የዓለም ሁሉ የፖለቲካ ሙቀትና ግለት ሰማይ በደረሰበት፤ የኢትዮጵያ የድል ብሥራት ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ በናኘበት፤ የዓለምን ታሪክ ከመሠረቱ የናደና የላዩን ታች አድርጎ የገለበጠ ድል በተመዘገበበት ወቅት ውስጥ ሆነው ወዘተ ወዘተ እንዴት ለፋሺስቱ ሞሶሎኒ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ፤ እንዴት “ሂድ ከፊቴ ጥፋ”፣ “ዓይንህን አልይ” • • • በማለት ፋንታ ከባለሥልጣኖቻቸው ጋር መክረውና ዘክረው ፋሺስቱ ሞሶሎኒ ሐውልቱን ይገነባ ዘንድ ፈቀዱ?” የሚለው ነበር። ይህ እስካሁንም ድረስ ጉዳዩን ለሚያውቁ ሁሉ እንደ ተዓምር የሚታይ የንጉሡ ውሳኔ ነው።

እውነትም ነው፤ አይደለም ያኔ የዛሬ ዘመን መሪዎች እንኳን ያደርጉታል ተብሎ በማይታሰብ ደረጃ ንጉሡ ያንን የሞሶሎኒ ጥያቄ ተቀብለው ማስተናገዳቸውና ፍቃድ መስጠታቸው (እንደ ንቀትና ዳግም ተደፈርኩ ባይነት እምቢ አለማለታቸው) ለብዙዎቻችን ግርምትን ቢፈጥርም፤ የንጉሡን ትክክለኛነት የምንገነዘበው ግን ፋሺስቱ ያንን ሐውልት በማቆሙ ብዙም ሳይቆይ መፀፀቱንና በኋላም ያነሳው (ያፈርሰው) ዘንድ ጠይቆ እማይቻል መሆኑ የተነገረውን ታሪክ ስንሰማ ብቻ ሳይሆን እማይቻለው፣ እማይሞከረው ሀበሻ ሀገር መጥቶ ውርደቱንና ቅሌቱን ተከናንቦ መሄዱን፣ ወገኖቹን ገብሮ የሚሊዮን ቢሊዮን ዓመታት የሽንፈት ታሪኩን በራሱ እጅ፣ ብሩሽና ቀለም ጽፎ መሄዱን ስንገነዘብ ነው። አዎ፣ ስለ ዓድዋ ድል ከእኛ በላይ ካዱቲ ይናገራልና “ዘላለማዊ ድል ለሰማዕቶቻችን!!!” ስንል በኩራት ነው።

በዚህ ጸሐፊ እምነት CADUTI በዓድዋ ሙዚየም ሳይቀር በፎቶግራፍ መልክ ተቀምጦ የራሱን ታሪክ ራሱ መናገር አለበት። ሐውልቱ ፋሺስቱ የሠራውን ግፍ በራሱ በፋሽስቱ እጅ ያረጋገጠበት በደም የተጨማለቀ ዐሻራው ነውና በተገቢው ስፈራ ተቀምጦ ተገቢውን ታሪክ መናገር አለበት። የዓድዋን ድል መናገር ያለብን እኛ ብቻ ሳንሆን እራሱ ፋሺስቱም ጭምር ነውና ሐውልቱ ያስፈልገናል። ሐውልቱ የፋሺስቱ ዘላለማዊ ሽንፈትና ክስረት ሕያው ምልክት ነውና በአግባቡ ሊያዝ ይገባል። ምስሉም በተለያዩ መልኮች ሊሰራጭ ግድ ነው።

CADUTI “አዎ፣ ተሸንፌያለሁ፤ ዜጎቼን ገብሬያለሁ፤ እማያገባኝ ውስጥ ገብቼ እኔንም፣ ሀገሬንም አዋርጃለሁ፤ ሕዝቤን ላልተፈለገ የቅስም ስብራት፣ ለከፋ ውርደትና አናሳነት ዳርጌያለሁ • • •” የሚል የፋሺስት ድምፅ አለና ሌላው የዓድዋ ምስክር በመሆኑ እንፈልገዋለን። እስከ ዛሬ በብዙዎች ያልተነገረለት CADUTI ለፈጠራ ሥራዎቻችን ሁሉ ያልተነካ ግብዓት ነውና ተፈላጊነቱ ጥግ ድረስ ነው። CADUTI:-

ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ

መድፍ አገላባጭ ብቻለብቻ፤

***

የዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፤

ለሚለውም ሆነ፤ ኢትዮጵያ “በጦርነት እና በወታደራዊ መረጃ (Military Security Intelligence)፤ በዲፕሎማሲና በፖለቲካ ጥበብ” የበላይነቷን ማሳየቷ የተረጋገጠበት ስፍራ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ ሌሎች ሁሉ CADUTIም ራሱን የቻለ ምስክር ነውና ሠሪውንም፤ ፈቃጁንም ስናመሰግን በምክንያት ነው።

“ለነፃነታቸው፣ ለሕልውናቸው፣ ለእናት ሀገራቸው፣ ለሰንደቅ ዓላማቸው፤ እንደዚሁም ለሰብዓዊ ክብራቸው ሕይወታቸውን ገብረው ለዛሬ ላበቁን ወገኖች ዘላለማዊ ክብር ይሁን።” የሚሉት ወገኖች ላይ “ዘላለማዊ ክብር ለአርበኞቻችን!!!” የሚለውን ጨምረን ጽሑፋችንን በዚሁ እናጠናቅቃለን።

ሠላም!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You