አዲሱ ገረመው
ሰሞኑን አልባሌ ቦታ ከማመሽ ብዬ አንዲት ጎሮሰሪ ውስጥ (እዚህ ጋር ትዕምርተ ስላቅ ይሰንቀርልኝ) ሚሪንዳዬን አዝዤ ቁጭ ብል የመብራት ወሬ ከፖለቲካና ጦርነት ትንታኔ እኩል ሲስተናገድ ሰማሁላችሁ፡፡ በእርግጥም መብራት የሚለው ነገር የታወሰኝ በዚሁ አጋጣሚ ነው፡፡
እኔምለው ለካንስ መብራት ከቤት ብቻ ሳይሆን ከጎዳናም ጠፍቷል፡፡ እነ ወይዘሮ አልታዬ በግሮሰሪዋ ውስጥ ሆነው የሚያወሩት ነገር ጉድ አይደል እንዴ እናንተዬ። በየመንገዱ የቆሙ የመንገድ ዳር የመብራት ምሰሶዎች በመብራት እጦት ተሰቃይተው “የብርሀን ያለህ” እያሉ ነው በማለት ያወራሉ፡፡
የመብራት መጥፋት ለእኛ አይነቱ ሰፈር እንግዳ ባይሆንም የመብራት ምሰሶዎቹ ሌላ አገልግሎት እንኳን መስጠት የሚችሉበትን እድሜያቸውን በከንቱ ሲያሳልፉ ያሳዝናሉ፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ከሚያለያየን ነገር አንድ የሚደርገን ነገር ይበልጣል፡፡ ሁላችንም መብራት አስመርሮናል፡፡ እኛና መብራት ስንገናኝ የምንደሰተውን ያህል ብዙ ዓመት የጠፋ ልጇን ያገኘች እናት እንኳን አትደሰትም፡፡መብራት ጠፍቶ ልክ ሲለቀቅ በየሰፈራችን የሚሰማው የደስታ ድምጽ ለእዚህ ምስክር ነውና መልሳችሁ አድምጡት፡፡ ይህ በየሰፈራችን ያለ ህያው ተግባር ነው፤ታሪክ አይደለም፡፡ ይህ የአንድነታችን መገለጫ ነው፡፡ ይኸው እኔማ አሁን አሁን ነገሮችን በጣም ከመርሳቴ የተነሳ ነው መሰለኝ መብራት ምን እንደሆነ ራሱ እየጠፋብኝ መጥቷል፡፡ ምክንያቱም በሰፈሬ መብራት የማላይበት ጊዜ ይበዛል፡፡
በአገራችን አሁንም አንዳንድ ሥራዎቻችን በብዛት ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ ኪራይ መሰብሰቢያ ሆነዋል። በጎላው በመናገር ባህላችን መሠረት ደግሞ የመብራት አገልግሎት ሥራዎች ለኪራይ ሰብሳቢዎች ክፉኛ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሁሉም ባለሙያ ብሎ መናገር ድፍረት ቢሆንም ቅሉ የዚህ መስሪያ ቤት ሥራ አፋዊ ሥራ ሆኗል፡፡
ይህን ያልኩበት በምክንያት ነው፡፡ አንድ ትራንስፎርመር ሲበላሽ እንኳን ተጠርተው ሲመጡ ቅዳሜና እሁድ የሥራ ቀን ስላልሆነ በሚል ሰበብ ከመንደርተኛው ብር ተሰብስቦ ይሰጣቸዋል ፡፡ ይህ ኪራይ ሰብሳቢነት እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል፡፡
ለዚህ ተጠያቂው ህብረተሰቡ ነው ትሉ ይሆናል፡፡ጨለማ ያማረረው ህብረተሰብ ምን ሊያደርግ እንደሚችል መገመት ቢቻልም፣ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ ኪራይ መሰብሰቡን በመጠቆም በኩል ግን አንዳንድ የአገልግሎቱ ሰራተኞች ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል መጠርጠር ይቻላል፡፡
ያደለው በለጋ እድሜው የሃገሪቱ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰው ይሆናል ፤ የኛው ምግባረ ብልሹ የመብራት ኃይል ሠራተኛ ደግሞ ህዝቡን የሰዓት እላፊ ሥራ ነው ብሎ ጭማሪ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ እንዲህ አይነቶቹን የሚሰሩትን ያውቃሉና ይቅር አትበላቸው ከማለት ውጭ ምን ይባላል?
በየመንደራችን ያሉ አንዳንድ እድሜ ጠገብ የመብራት ምሰሶዎች ገንፎ ቀርቦ ማንኪያ የለምን ይመስላሉ። እነርሱ ቆመዋል መብራት ግን የላቸውም፡፡ ህዝቡም የመብራት ጉዳይ ስለሰለቸው ቸል ብሏቸዋል፡፡ ጉዳዩ ግድ የማይሰጣቸው ነገር ግን የሚመለከታቸው ሰዎች ለምን ተብለው ቢጠየቁ ኬክ በእንጀራ ካልበላሁ አይነት ፈሊጥ ከመንቀባረር ሌላ ምላሽ አይሰጧችሁም፡፡ ኧረ ግድ የለም
ወይ በየመንገዱ የቆሙትን ምሰሶዎች የመብራት ባለቤት አድርጉ፤ አሊያም ጨለማን እንዴት መጋፈጥ እንዳለብን ኮርስ ስጡን ፤ ካልሆነ ደግሞ መንገዱን ለኛ ልቀቁልን!
ጎበዝ ምሰሶ አሳይቶ መብራት መንሳት ምን የሚሉት ነገር ነው? የእነዚህ ሰዎች ኃላፊነት የሚመስላቸው የራስን ሰዓት ጠብቆ ቢሮ መግባት እንጂ የመንገድ ላይ መብራት በራ አልበራ የሚለው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ እንዲያ ባይሆንማ ብዙ መንገዶች መብራት አጥተው ጦማቸውን አያድሩ ነው፡፡
አንዳንዴ ሆን ብዬ ስታዘብ መብራት ኃይል ባለበት አካባቢ ጥሩ መንገድ ከጥሩ መብራት ጋር አለ፡፡ በሌላ ቦታ መንገዱም ግራ የገባው መብራቱም እንደዛው ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ስታዩ መብራት ኃይሎች ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ከሚል ሀሳብ ወጥተው የህብረተሰቡን ጥያቄ የሚመልሱበት ቀን አይናፍቃችሁም?
ልብ ብሎ ላስተዋለው አዲስ አበባ ውስጥ ፍትሐዊ የሆነ የመብራት ዝርጋታ ራሱ የለም፡፡ ለምሳሌ በኛና በቦሌ ሰፈር ያለው የመንገድ ላይ መብራት ምሰሶ አገልግሎት ክፍተቱ ሰፊ ነው፡፡ የኛ ሰፈር ስል “የሚረዳኝ የለምና ከእኔ አትራቅ” የሚል ጥቅስ ግድግዳቸው ላይ የሚለጥፉ ቤቶች የበዙበትን ሰፈር ነው፡፡
እናም የቦሌው የመብራት ምሰሶ በገፍ የሚያገኘውን መብራት ለኛ ሰፈሩ ማስተላለፍ ሲገባው ጭራሽ ረስቶናል፡፡ እናም የኛ ሰፈር ምሰሶዎች መብራት አልባ ሆነው ቆሞ ቀር እየተባሉ ይጠራሉ፡፡
ታዲያ ይሄ ቆሞ ቀር ምሰሶ ወይ አላሻገረ፤ ወይ አልተሻገረ፤ ራሱን የረሳ ሆኖ ግራ እንደገባው አለ፡፡ ወይ ሰውን ከንብረት ዘረፋና ወንጀል አልታደገ፤ እኛን ለጨለማ ዳርጎ የሌባ ሲሳይ አድርጎናል፡፡ ምንም ሀሳብ ሳይኖረው ዕድሜውን እያቃጠለ ይገኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ መብራት ኃይል እውነታውን ዋጥ አድርጎ ለመለወጥ መነሳት ይኖርበታል፡፡
የተከበረው ምክር ቤት ማለቴ የተከበረው አንባቢ እንዲያውቅልኝ የምፈልገው፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጉዳዩን በጥልቅ ተመልክቶ ማስተካከያ ካደረገም የመብራት ምሰሶዎች መንገድ ላይ ተክሎ ብርሀን እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ ለእያንዳንዳችን በነፍስ ወከፍ ተጠባባቂ ብርሀን ሰጪ ምሰሶዎችን ካላደልን ዋስትና አይኖረንም፡፡
የዲም ላይት ያህል መብራት እንኳን ሳይኖራቸው የመብራት ምሰሶዎች ብሎ መጥራት በራሱ ያሳፍራል። አንዳንዶች መብራት እንዲለግሱ ከቁሙለት ዓላማ ውጭ የሞዴሊስት ስራን ሲወጡ የምናይበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ለመብራቱ የሰጡትን ትኩረት ከነፈጉት እኮ ዓመታት አለፉ፡፡
ወገን እናንተስ ብትሆኑ ከተማችን በመብራት አልባ ምሰሶዎች ስትጨናነቅ ግን ምንም አታሳዝናችሁም? በከተማችን አዲስ አበባ በመንገድ ዳር መብራት እጦት ብቻ ሺዎች የወንጀል ሰለባ ሲሆኑ በላይ ለምን ታልፋላችሁ?
አንድ ቀን አንዱ ባልደረባዬ ማታ ማታ የሚበራው ትል የት ገባ ብለው መብራት ኃይል አስገድሎታል አለኝ። የእውነት ግን መብራት ኃይሎች መብራት ሲበራ ትናደዳለችሁ እንዴ? ነገሩ እውነት ቢሆንማ ነው አንዳንድ ሰው የተላጠ ኤሌክትሪክ ገመድ በመንካት ለመብራት ኃይል ያለንን ንቀት እናሳይ እያለ የሚሳለቀው።
የምር በመንገድ ላይ መብራት እጦት የተማረረ ሰው በረኪና መጠጣት ሲያንሰው ነው፡፡ ዳሩ የኛ ሀገሩ በረኪና ለሆድ ቁርጠት መድኃኒት ተብሎ የተሸጠ ነው እንጂ፡፡
መብራት አጥተው ዓመታትን በቁም የቀሩ የመብራት ምሰሶዎችን ነፍሳቸውን በአጸደ መብራት ኃይል ያኑርልን። የእለቱ መራር ምርቃት ነው! ቸር ሰንብቱ!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013