መላኩ ኤሮሴ
የመልካሳ-ሶደሬ-ኑራሔራ-መተሐራ የመንገድ ፕሮጀ ክት ግንባታ የተጀመረው በ2010 ዓ.ም ነው።94 ኪ.ሜ የሚሸፍነው ይሄ ፕሮጀክት በ2012 ዓ.ም ሐምሌ ወር ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ታስቦ ነው ወደ ግንባታ የተገባው። እስከ ፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ወቅት መገንባት የተቻለው ግን 18 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ባለፉት ስድስት ወራትም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የመንገድ ግንባታ ስራው በሐምሌ ወር ከነበረበት ፈቀቅ አላለም።
መንገዱን በአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊየን ብር ወጪ እየገነባ የሚገኘው የንኮማድ ኮንስትራክሽን የስራ ተቋራጭ ድርጅት ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ኢ ሲ ዲ ኤስ ደብሊዩ ሲ ኤክስ የተባለ ድርጅት እያከናወነ ይገኛል። የግንባታ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው።
በምስራቅ ሸዋ እና በአርሲ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ አምስት ወረዳዎችን የሚያገናኘው ይህ መንገድ በተለይም በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ከተማን፤ ቦሰትና ፈንታሌ ወረዳዎችን የሚያስተሳስር ሲሆን በአርሲ ዞን ደግሞ በጀጁና መርቲ ወረዳዎችን ያቆራኛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ የወረዳዎቹን ነዋሪዎች የመንገድ ችግር ከመቅረፍ ባሻገር በአካባቢው የሚመረቱ የተለያዩ ምርቶች ወደ ማዕከላዊ ገበያ ያለ መስተጓጎል እንዲገባ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
የግንባታው መጓተት የአካባቢው ነዋሪዎች የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ የሰነበተ ሲሆን፤ የቅሬታ ምንጭም ሆኗል። የመንገድ ግንባታው ሲጀመር የመንገድ ችግር ይቀርፋል የሚል ተስፋ ሰንቀው እንደነበር እና የሚያመርቱትን ምርት ያለ እንቅፋት ወደ ገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር እምነት ጥለው እንደነበር የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች የግንባታው መጓተት ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የቡድን መሪ አቶ ተወዳጅ መልካሙ እንደሚሉት፤ የመንገድ ግንባታውን በ2012 ሐምሌ ለማጠናቀቅ የታቀደ ቢሆንም ይጠናቀቃል ተብሎ በታቀደበት ጊዜ አንድ አራተኛ እንኳን ማጠናቀቅ አልተቻለም። ለግንባታው መጓተት የወሰን ማስከበር ችግር ዋነኛው መንስኤ ነው።
የወሰን ማስከበር ችግርን በመቅረፍ የመንገድ ግንባታውን ለማፋጠንና ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አመራሮች እና የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የመንገድ ግንባታው በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ የዞን እና የወረዳ አመራሮች ጋር የመንገድ ፕሮጀክቱ ያጋጠመውን የወሰን ማስከበር ችግር ለመፍታት ያለመ የምክክር መድረክ በቅርቡ በአዳማ ከተማ ማካሄዳቸውን አቶ ተወዳጅ ያብራራሉ።
የመድረኩ ዋነኛ ትኩረት ፕሮጀክቱ ባለበት ከፍተኛ የሆነ የወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት የተጓተተ በመሆኑ እነዚህ የወሰን ማስከበር ችግሮች በአስቸኳይ ተቃለው ፕሮጀክቱን ለማፋጠን ያለመ ነው።
በመድረኩም ላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ የሚጠበቅበትን አገልግሎት መስጠት ይችል ዘንድ በመንገድ ግንባታ ክልል ውስጥ ያሉ ቤቶችና ንብረቶች የአካባቢው መስተዳድር አካላት በፍጥነት ማስነሳት እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል።
እንደ አቶ ተወዳጅ ማብራሪያ፤ ከወሰን ማስከበር ጎን ለጎን የስራ ተቋራጭ ድርጅት ሆነ አማካሪው አፈፃፀማቸውን ይበልጥ ሊያሻሽሉ እንደሚገባ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ከመንገዶች ባለስልጣን በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አመራሮች አሳስበዋል።
የየአካባቢዎቹ የመስተዳድር አካላት በበኩላቸው የተነሱት ችግሮች ተጨባጭ መሆናቸውን በመገንዘብ ለፕሮጀክቱ መፋጠን ይበልጥ ለመስራት የጋራ ግብ መቀመጡን ያብራሩት አቶ ተወዳጅ፤ የተቀመጠው የጋራ የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲተገበር መላ የአካባቢውን ህዝብ በማስተባበር ችግሩ እንዲፈታ እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንም ደግሞ ከወሰን ማስከበር በተጨማሪ በኮንትራክተሩ እና በአማካሪ ድርጀቱ በኩል የሚታዩ ውስንነቶች ካሉ እንዲታረሙ ይበልጥ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል።
የመልካሳ-ሶደሬ-ኑራሔራ-መተሐራ የመንገድ ፕሮጀ ክት ሶደሬን መዝናኛ እና የመተሃራ የስኳር ፋብሪካ የመሳሰሉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ተቋማት አካባቢ የሚገነባ የመንገድ ፕሮጀክት እንደመሆኑ መጠን የግንባታው መፋጠን ለአካባቢው እና ለሀገሪቱ ያለው ፋይዳ ላቅ ያለ ነው። በመሆኑም የመንገድ ግንባታው ፕሮጀክት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
የፌዴራል የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አመራሮች በቦታው በመገኘት የመንገድ ግንባታው እንዲፋጠን የአካባቢው ማህበረሰብ እና አመራሮች የወሰን ማስከበር ችግር እንዲፈታ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ አቅጣጫ ያስቀመጡ ቢሆንም፤ ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ያለበትን የጊዜ ገደብ አለማስቀመጣቸው ትልቅ ክፍተት ነው።
የግንባታው መጓተት ግን በመንግስት ላይ ተጨማሪ ወጪ እንደማያስከትል ይናገራሉ። የፕሮጀክቱ ግንባታ መጀመሪያ ውል በተገባበት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊየን ብር እንደሚጠናቀቅም ከኮንትራክተሩ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ነው ያብራሩት።
የፕሮጀክቱ አማካሪ አቶ ሲሳይ ጃገማ ፕሮጀክቱ እጅግ መጓተቱንና እስካለፈው ህዳር 2013 ድረስ ግንባታው 26 በመቶ ደርሷል ብለዋል። ፕሮጀክቱን የተለያዩ ችግሮች ያጋጠሙት ቢሆንም ዋናው እና ትልቁ የወሰን ማስከበር ችግር መሆኑን ነው የተናገሩት። በአሁኑ ወቅትም በከተሞች አካባቢ የወሰን ማስከበር ችግር አለመፈታቱን ይናገራሉ።
አካባቢው ከፍተኛ የእርሻ ስራ የሚሰራበት እንደመሆኑ ሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት በመኖራቸው የወሰን ማስከበር ስራውን አዳጋች አድርጎት ቆይቷል። በቅርቡ የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና የመንገዶች ባለስልጣን የስራ ሀላፊዎች ከአካባቢው አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት የወሰን ማስከበር እና ንብረት የማስነሳት ስራ በአንድ ወር ውስጥ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ መቀመጡን ያብራሩት አቶ ሲሳይ እስከ 2014 መስከረም ድረስ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ መታቀዱንም አንስተዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013