ሰላማዊት ውቤ
የአንድ ከተማ ፕላን የሚሰራው ሦስት ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ ነው። እነዚህም የህዝብን ደህንነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶቹን ማዕከል ማድረግ እንዲሁም ዕድገቱን መምራት ማስቻል ናቸው።
የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም የአፍሪካ መዲና የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን በተለያየ ጊዜ ለመቅረጽ ተሞክሯል። ይሁንና የአዲስ አበባ ፕላን አሁንም መመዘኛዎቹን ማሟላት አልቻለም።
ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋነኞቹ የመሬት ጥበትና የሕዝብ ብዛት ናቸው። እነዚህን ቁልፍ ችግሮች ለመቅረፍ ብዙ አማራጮች መኖራቸውን የከተማ ፕላን ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። አማራጮቹ የከተሞችን ውበት መጠበቅ የሚያስችሉ እንደሆኑም ይጠቅሳሉ። የሕዝብ መጨናነቅና የሥራ አጥ ቁጥሩን መቀነስም እንደሚያስችል ይናገራሉ።
የከተማ ፕላን ደረጃውን የጠበቀ መሆን የሚችለው ገና ከጅምሩ ታቅዶና ወደፊት ያሉ ጉዳዮችንና ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ታሳቢ አድርጎ ሲነደፍና በዚሁ መሰረት ሲመራ ብቻ ነው። ይሄን ታሳቢ አድርጎ ያልተነደፈንና በትክክለኛው ንድፉ መሰረት ያልተመራን ፕላን ለማስተካከል መሞከር እምብዛም አይመከርም።
ሆኖም አማራጮቹ ይሄንን በመጠኑም ቢሆን ለማስተካከል መፍትሄ ይሆናሉ። ሊሰሩ የሚችሉትም ደግሞ ከሌሎች እህት ከተሞች ጋር እርስ በእርስ በመመካከርና በመቀናጀት ሊሆን ይችላል።
በመፍትሄዎቹና በአጠቃላይ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ ከፕላን ጋር ተያይዞ ከሙያ አንፃር በተጨባጭ የሚስተዋለው ሁኔታ ምን ይመስላል ስንል ላነሳነው ጥያቄ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህንፃ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ጥበቡ አሰፋ የሚከተለውን ሙያዊ ምላሽ ሰጥተዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ የአንድ ከተማ ፕላን የህዝብን ደህንነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶቹን ማዕከል አድርጎ ከመሰራት አንፃር አዲስ አበባ የተዋጣላት ናት ማለት አይቻልም። አሁን ላይ ለማስተካከል እየተሠሩ ያሉ አንዳንድ ጅምሮች ቢኖሩም ፕላንዋ ዕድገቷን መምራት አስችሏልም ለማለት አያስደፍርም። የሕዝብ ጫና ከአቅሟ በላይ ሆኖ ዕድገቷን ቀድሟል።
ሕዝቡ በከተማ ውስጥ ሞልቶ ተትረፍርፎ እየፈሰሰ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በከተማዋ ውበት፣ የንግድ፣ የጽዳት አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች አሉ። ፕላኗ ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ አይደለም። ይሄ ሁኔታ ታድያ ከተማዋ ፕላን አላት ለማለት አያስችልም።
ምክንያቱም ፕላን ሲኖር ቀድሞ ይህን ያህል ሕዝብ ይመጣል፣ ይህን ያህል ሀይል አለን ብሎ ለማሰብ ይረዳል ከተማ ለመገንባት ይህን ያህል ግብዓት ያስፈልገናል ለማለትም ዓይነተኛ መፍትሄ ነው። አዲስ አበባ ላይ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ ይለያል። ጥቅም ላይ እየዋለ ካለው ቦታ አብዛኛው በፕላኗ መሰረት የተደለደለ አይደለም።
ከቦታ አንፃር ያለው የሀብት ክፍፍልም ሚዛናዊ ነው ማለት ያስቸግራል። ታናሽ ታላቅ ሽንጥ ዓይነት የሚባለውን ዋናውን ብልት ቦታ ሀብታሞች ናቸው የተቀራመቱት። የሚሰሯቸው ሪል ስቴቶች እንኳን ዝቅተኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም።
የሚያከራይዋቸው የእንግዳ መቀበያዎች ለሀብታሙ የተሰሩ ናቸው። አንድ ህንፃ ሲገነባ አንድ ሺህ ዜጎች ከገጠር ወደ ከተማ ይፈልሳሉ። የሚፈልሱት ደግሞ የሥራ ዕድል ፍለጋ ነው። ይህ በየጊዜው እየመጣ የሚከማች ሕብረተሰብ ከፍተኛ ቁጥር አለው። እየኖረ ያለው ግን ለሰው መኖሪያ ሊሆን በሚችል ቦታ አይደለም።
እጅግ ጥግግት ያለው ቦታ በመኖሩም ጤንነቱን ጨምሮ ሁለንተናዊ ችግር ፈጥሯል። የመሬት ጥበቱ በወለደው ችግር ሕዝቡ ለከፋ እንግልት እየተጋለጠ ነው። አንድ ህንፃ በተሰራ ቁጥር ከገጠር እየመጣ አዲስ አበባ የሚቀረው የመኖሪያ ጥያቄ ከማቅረብ በተጨማሪ ሥራ ይፈልጋል።
ለዚህ ፍላጎቱ ማስተንፈሻ የሚሆነው ዕውቀትና ልምድ የማይጠይቀው ንግድ ነው። የንግዱ ዓይነት ደግሞ ባህላዊ ሲሆን አንድ ዕቃ ከመርካቶ ሸምቶ ሰው ወደ በዛበት ቦታ በመዘዋወር ቆሞና አንድ ቦታ ይዞ ሲሸጥ የሚታይ ነው።
ረዳት ፕሮፌሰሩ ሁኔታውን ‹‹አዲስ አበባ ላይ የተሰራው ፕላን አልሰራም ማለት ነው›› ሲሉ ይገልፁታል። ይህን ለማስተንፈስም መንግሥት ራሱና ሕብረተሰቡም የላስቲክ ቤቶችን ጭምር የሚሠሩበት ሁኔታ እንዳለ ያነሳሉ። የአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአርባንስ አርክቴክቸር ተማሪዎችም የድርሻቸውን የተወጡበት ሁኔታ መኖሩንም ያስታውሳሉ። አምና ተማሪዎቹ የፈጠሯቸው በቀላሉ ሊተጣጠፉ የሚችሉ፣ ከተማን የማያቆሽሹ ቦታ የማይፈጁም ነበሩ።
ለከተማዋ ውበት የሚያጎናጽፏት፣ ለተሸካሚውና ሥራውን ለሚያከናውነውም ቀላል እንደነበሩም ያስረዳሉ። ሆኖም ያበረታታቸውና ሀሳቡን ገዝተን የከተማችንን ችግር እንፍታ ያላቸው አካል ባለመኖሩ ተግባር ላይ መዋል አልቻሉም። አሁንም ፈጠራውን ወስዶ ለሚያለማ በራቸው ክፍት ነው። ገና ከጅምሩ እነዚህ ቢተገበሩ በአዲስ አበባ ጎልቶ እየተስተዋለ ያለው የቦታ እጥረትና የህዝብ ብዛት ሊከሰት እንደማይችልም ይናገራሉ።
በከተሞች ውስጥ የቦታ እጥረትና የህዝብ ብዛት ከተከሰተ በኋላ አቻችሎ መኖር የሚያስችሉም አሠራሮች አሉ። ለምሳሌ፦ አዲስ አበባ ላይ በቀለበት መንገዱ እንደ መገናኛ አካባቢ ያሉትን በአርማታ የሚሰሩ ልሙጥ ግድግዳዎችን መጥቀስ ይቻላል። በእነዚህ ከፍና ዝቅ ተደርገው በተሠሩ የመንገድ ግድግዳዎች ላይ ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ አንዳንድ ሜትር መደርደሪያዎችን በቀላሉ መለጠፍ ይቻላል። ጥራታቸውን የጠበቁና ማታ የሚቆለፉ መሆን አለባቸው።
በቀለማት ቢያሸበርቁም ለዓይን ይማርኩና ገበያ ይስባሉ። መገናኛ አካባቢ ከመናሀሪያው በላይ ያለው ግድግዳ አንድና ሁለት ሜትር ገባ ብሎ መዘጋትና መለጠፍ የሚችሉ መደርደሪያዎችን መሥራት እንደሚቻልም ለአብነት አንስተዋል። ይህም ላስቲክ ከመኮልኮልና የከተማዋን ውበትና ፕላን ከማበላሸት ያድን ነበር። የቦታ ብክነት፣ ብክለትና መጨናነቅንም ማስቀረት ይችላል።
‹‹አሁንም መከላከልና መፍታት የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ›› ሲሉም ያለመርፈዱን ምክር ደጋግመው ይገልፃሉ። እንደ ሙያዊ ምክራቸው ለሕዝቡ የሥራ ዕድል የሚከፍቱ አሠራሮችን ዘመናዊ መንገድን መከተል ያስፈልጋል። ወጣቱ በቀላሉ ሊመለከታቸውና ሊሰራቸው የሚችሉ ልማቶችን ማካሄድ አንዱ ነው። እንደ አዲስ አበባ ከክልል እህት ከተሞች ጋር በመቀናጀት ትልልቅ የማዕድን ቦታዎችና እርሻዎችን ማልማት ይገባል።
ለዚህ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎች ይገኛሉ። በየገጠሩ የሚገኙ የእርሻ ቦታዎች፣ ተራራዎች፣ በረሀ ውስጥ ያሉ ጠፍ መሬቶች ይጠቀሳሉ። ወንዝ የሸረሸራቸው የተቦረቦሩ መሬቶችንም መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ ማዋል ይቻላል።
እነዚህን በመንገድ ላይ ቆመውና ቁጭ ብለው ለሚነግዱ ዜጎች በመስጠት ከተማዋ የሕዝብ ብዛት ጫናውን እንድትቋቋመው ማድረግ ይቻላል። በአጥሮቹ ላይ የተመጠነ ዕቃ የሚይዝ አንዳንድ ሜትር መስጠቱ በተለይ ችግሩን መቅረፍ ከማስቻሉም ባሻገር ብዙ ጥቅሞች አሉት። የአጥሩንና የአካባቢውን ውበትና ደህንነት ይጠብቃል።
ወንጀልንም ይከላከላል። የሰው እንቅስቃሴን ያሳልጣል። መንገዶች ሰርጎድ ሰርጎድ ተደርገው ቢሰሩም ለንግዱ ምቹ ይሆናሉ፤ ከተማዋንም ያስውቧታል። አያሌ ዜጎችም ገበያ እንዲያገኙ ያደርጋል። ሰፋፊ ቦታ የያዙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ልማቱን በማከናወን እገዛ ማድረግ እንደሚችሉ የሚመክሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ትምህርት ሚኒስቴርንና ግብርና ሚኒስቴርን ለአብነት ይጠቅሳሉ።
ግብርና ሚኒስቴር በግቢው ውስጥ፣ ጣሪያውና ግድግዳው ላይ እርሻ መሥራት የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሉ። እነዚህ ትልልቅ መሥሪያ ቤቶች የያዟቸው ትልልቅ ቦታዎችን አጥርም ለንግድ አገልግሎት ማዋል በአንድ ጎኑ የቦታ ብክነትን መቀነስ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ውበታቸውንና ደህንነታቸውን ይጠብቃል።
በእርግጥ ብዙዎቹ አትንኩንና አትድረሱብን ዓይነት አሰራር ያላቸው በመሆናቸው አያመቹም። ይህ በከተማ ፕላን ሥራ ሂደት ፍፁም ስህተት ነው። ምክንያቱም ከተማ የፊት ለፊቱ እንቅስቃሴ ሞቅ ደመቅ ያለና ቀልብ ሳቢ መሆን አለበት። በከተማ ፕላን ዕቅድ ንግድ ግንባር መፈለጉ መታወቅ አለበት። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ዓይነት ትላልቅ መሥሪያ ቤቶች መሐል ከተማ ውስጥ መቀመጥ የለባቸውም ሲሉ ይናገራሉ።
አሁን ባሉበት ሁኔታ እንኳን ቢያንስ ወደ ውስጥ ገባ እያሉ ፊት ፊቱን ለነጋዴ መልቀቅ ይኖርባቸዋል። ከፍተኛ የቦታ ጥበትና የሕዝብ ብዛት ጎልቶ በሚስተዋልባት አዲስ አበባ ያለው ሌላው የፕላን ችግር ግለሰቦች ትልልቅ ህንፃዎችን ለብቻቸው የሚይዙበት ሁኔታ በመኖሩ ነው። ይህ በከተማዋ ውስጥ የቦታ ጥበት ብቻ ሳይሆን ብክነትም እንዳለ ያመለክታል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚመክሩት የቦታ ጥበትን ከሕዝብ ብዛት ጋር ለማስታረቅ ብዙ መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ። ከዚህ ፕላን አኳያ ሕዝብ በሚበዛባቸው እንደ አራት ኪሎ ባሉ አካባቢዎች መሸጋገሪያ ድልድይ ከመሥራት ይልቅ መሸጋገሪያ ህንፃ ቢሰራ ይመረጣል።
ምክንያቱም በህንፃ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች እየገበዩ የሚሄዱበትን ዕድል ይፈጥራል። በተጨማሪም በምዕራብ ያሉት ጠዋት ጥላ ያገኛሉ። በምስራቅ ያሉት ደግሞ ፀሐይ እንዲያገኙ ለማድረግ ይረዳል። እግረ መንገዱንም ሰዎች የሚሰሩበት የሚዝናኑበትና የሚገበያዩበት ቦታ ይሆናል።
ሁለት ወይም ሦስት መንገዶች የሚገናኙባቸውና ሕዝብ ከሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ጎን ትልልቅ አደባባዮች መኖር አለባቸው። እነዚህ አደባባዮች ሰዎች እየተዝናኑ የሰውን እንቅስቃሴ የሚያዩባቸው ማስተንፈሻ ቦታዎች ናቸው። ማህበራዊ ግንኙነትም ይመሰርቱባቸዋል። መንገድ ላይ የሚኖረውን መጨናነቅም ይቀንሳሉ።
በአጠቃላይ አዲስ አበባ ከሙያቸው አንፃር እንዳስተዋሏት ከከተማ ፕላን ጋር አብሮ የማይሄድና የማይመጣጠን ግንባታ፣ መንገዶች፣ መንገድ መካች ልሙጥ ግድግዳዎች ለነዋሪዎቿ መስጠት የሚገባቸውን ጥቅም አለመስጠት፣ የትላልቅ መሥሪያ ቤትና ህንፃ አጥሮች የማህበረሰቡን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፍላጎትና የከተማዋን ዘላቂ ዕድገት ታሳቢ አድርጎ አለመታነፅ ችግሮች ጎልተው የታያሉ።
አዲስ አበባ ፕሮ-አክቲቭ ወይም በአማርኛው አጠራር አማታሪ የሚባለውን ፕላን መሆን አልቻለችም። ወይም ቀድሞ ፕላን ተብሎ ታቅዶ የነበረው በሕዝብ ብዛትና በመሬት ጥበት ምክንያት ፕላን መሆን አልቻለም። አሁን ያለው ፕላን ችግሮች ከተፈጠረና ከተቀጣጠለ በኋላ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረግ እሩጫ ዓይነት ነው። እንዲህ ዓይነቱ የከተማ ፕላን ደግሞ ሪ-አክቲቭ ፕላን ይባላል።
በመሆኑም አሁን አዲስ አበባ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ሦስት አማራጮችን ማየት የግድ ይላል። አንዱ ከመሬት ስር ውስጥ ለውስጥ ያለን ቦታ መጠቀም፤ ሁለተኛው ከመሬት ላይ ያለውን ቦታ ማየት ሲሆን ሦስተኛው ከመሬት በላይ አየር ላይ ያለን ቦታ መጠቀም ናቸው። የሕዝብ ቁጥር በየጊዜው እየበዛ ይሄዳል በማለት የወደፊቱን ታሳቢ አድርጎ መስራት እና ቀድሞ ማልማት ያስፈልጋል ብሎ ፕላን ማድረግ ደግሞ ፕሮ- አክቲቭ ወይም በአማርኛው አማታሪ ይሰኛል።
ሦስተኛው አብሮ ተቀናጅቶ የሚሰራ ወይም ኢንተግሬትድ ተብሎ የሚጠራው ፕላን ነው። ይህ አብሮ ከተቀናጀ ፕላን ጎን ለጎን ሁሉንም እኩል ለማስተናገድ ሰፊ ዕድል ይሰጣል። ረዳት ፕሮፌሰር ጥበቡ በዓለማችን ያሉ እንደነ ጀርመን ያሉ ከተሞች የከተሞቻቸውን ፕላንና ፅዳት ያስጠበቁት እንዲህ ዓይነቶቹን ውጤታማ የከተማ ልማት ስትራቴጂዎች በመንደፍ መሆኑን ጠቅሰው ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013