ማህሌት አብዱል
በአምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትግራይ ክልል ተወካይ ናቸው፡፡ የተወለዱት ሽሬ እንደስላሴ ከተማ ሲሆን ያደጉትም ሆነ የተማሩት በዚያው ከተማ በሚገኙት “ጸሃዬ ቤት ትምህርቲ” በተባለ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ሽሬ እንደስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡
የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በጥሩ ውጤት በማለፍ በ1978 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ በኬሚስትሪና በሂሳብ ትምርት ክፍል ገብተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመያዝ ችለዋ፡፡ በወቅቱ በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አዲስ የኦዲት ስርዓት ለመዘርጋት ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር ለሚተገብረው ፕሮጀት ከተመለመሉ ከፍተኛ ውጤት ካላቸው ተመሪዎች አንድዋ ለመሆን በቁ፡፡
በተቋሙ ውስጥም የፐርፎማንስ ኦዲቲንግ ስልጠና ለስድስት ወራት ወሰዱና ተቀጠሩ፡፡ ለአምስት አመታት በዋና መስሪያ ቤቱ ካገለገሉ በኋላ ትግራይ ክልል በተቋቋመው አዲስ ቢሮ ሃላፊ ሆነው እንዲሰሩ ተመደቡ። በዚያም በተመሳሳይ ለአምስት አመት ካገለገሉ በኋላ በሴቶች ጉዳይ ቢሮ ከሌሎች ክልሎች በተለየ መልኩ በጀቱ እያለ በፀሃፊ ብቻ ይመራ ሥለነበር ይህም አሰራሩ ተገቢ አለመሆኑ በመንግስት ታምኖበት ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ተዛውረው መምሪያ ሃላፊ ሆነው ተወዳድረው ተመደቡ፡፡
ዋና ኦዲተር ሆነው በሚሰሩበት ጊዜ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ቢጀምሩም ወደ ትግራይ በመዛወራቸው ምክንያት ያቋርጣሉ፡፡ ሆኖም መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በዝውውር ትህምርታቸውን ቀጠሉና ዲፕሎማቸውን አግኝተዋ፡፡
በትግራይ ሴቶች ጉዳይ ቢሮም ለአንድ አመት ካገለገሉ በኋላ ትዳር ይዘው ሁለት ልጆች ያፈሩባትን መቀለ ከተማን ለቀው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሴቶች ጉዳይ ቡድን መሪ ሆነው በማገልገል ላይ ሳሉም ጎን ለጎን ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በዴቨሎፕመንት ስተዲስ ሰሩ፡፡
በእውቀትና በአቅም ለመጎልበት ቀን ከሌሊት መትጋት የማይሰለቻቸው እኚሁ ሴት በፌደራል ስራና ከተማ ልማት ሚኒስትር የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ተወዳድረው በመግባት ለሁለት አመት አገለገሉ፡፡
በኋላም በሴቶችና ህጻናት ሚኒስትር በተመሳሳይ ደረጃ ተዛወሩና የሴቶች ፖሊሲና ስትራቴጂ ዳይሬክተር እንዲሁም የህጻናት መብትና ደህንነት ዳይሬክተር ሆነው ለሁለት ዓመት ሰሩ። ከስድስት ዓመት በፊት በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ተወዳድረው ምክር ቤት ከገቡ በኋላም ቢሆን ከመማር አልቦዘኑም፡፡
ሁለተኛውን የማስተርስ ዲግሪአቸውን በስነ ምግብ ጥናት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ማግኘት ቻሉ፡፡ አሁን ለደረሱበት ደረጃ ወላጆቻቸው፤ አብሮ አደጋቸውና የትዳር አጋራቸው ዶክተር ሙሉ ነጋ እገዛ ከፍተኛ እንደነበር የሚገልጹት እንግዳችን በተለይም ሶስት ልጆችን በስነምግባርና በእውቀት ተገንብተው እንዲያድጉ በማድረግ ሂደት ውስት የባለቤታቸው ድጋፍ እንዳልተለያቸው ይናገራሉ፡፡
ላመኑበት ነገር ወደኋላ ማለትን የማያውቁት ወይዘሮ ያየሽ ተስፋሁነኝ የዛሬ የዘመን እንግዳችን ናቸው። እንግዳችን በተለይም መስከረም 25 2013 ዓ.ም ጁንታው የህወሓት ቡድን ያቀረበላቸውን የአመፅ ጥሪ ባለመቀበል ለአገራቸውና ለወከላቸው ህዝብ ያላቸውን ተዓማኒነት በተግባር አስመስክረዋ፡፡ በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበና፡፡
አዲስ ዘመን፡– ልጆች እያሳደጉ፣ ቤተሰብ እየመሩ ያለማቋረጥ በተለያዩ የትምርት መስኮች የመማርንና የማደግን ፅናት ሚስጥር ምን እንደሆነ ያጫውቱንና ውይይታችንን ብንጀምር ?
ወይዘሮ ያየሽ፡– እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ሽሬ እንደስላሴ ነው የተማርኩት፡፡ በወቅቱ ብዙ ሴቶች እንዲማሩ የሚያበረታታ ማሕበረሰብ አልነበረም፡፡
እኔ ግን እልኸኛ ስለነበርኩኝ በተቻለ መጠን አንደኛ ለመውጣት በጣም ጥረት አደርግ ነበር፡፡ እስከ 12 ኛ ክፍል ድረስ የደረጃ ተማሪ ነበርኩኝ፡፡ እንዳውም 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቅሁት በከፍተኛ ውጤት በመሆኑ ከአጠቃላይ ተማሪዎች ለመሸለም ችያለሁኝ፡፡
በመሆኑም ያለገደብ መማር፤ ራስን ማብቃት፤ ጠንካራ ሆኖ መገኘት እንደሚገባኝ የማምን ሰው ነኝ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ እጅ መስጠት እንደሌለብኝ ተነግሮኝ ነው ያደግሁት፡፡ ሰው ከተማረ ከተጣጣረመድረስ በሚገባው ቦታ ላይ ይደርሳል የሚል እምነት እንዲኖረኝ ተደርጌ ስለተቀረጽኩም ነው በተቻለኝ አቅም ጊዜዬን ያላአግባብ ሳላባክን እዚህ መድረስ የቻልኩት፡፡
ቤተሰቦቼ በትምህርት የሚያምኑ ናቸው፡፡ በተለይም እናቴ በጣም ነበር የምትደግፈኝ፡፡ ሳጠና እና ስማር እናቴ የተለየ ማበረታቻ ነበር የምታደርግልኝ፡፡ የቤት ውስጥ ሥራ እንኳን ስታዘዝ ትሳሳለች፡፡ ‹‹እኔ ስላልተማርኩ ነው ቤት የቀረሁት፤ እናንተ ግን መማር አለባችሁ›› ትለን ነበር፡፡ እናታችን ራስዋን ጎድታ እኛ እንድንማር ትደግፈን ነበር፡፡ አባታችንም እንደዚሁ ብዙ ወግ አጥባቂ የሚባል አልነበረም፡፡
ሴት ልጅ ወጣ ወጣ ማለት የለባትም ብሎ የሚያምን አይነት አባት አልነበረም፡፡ እናም ከልጅነታችን ጀምሮ የቤተሰብ ድጋፍ አልተለየንም ነበር፡፡ በተለይም እናቴ ሌሊት ቁጭ ብለን ስናጠና አብራን ቁጭ ትል ነበር። በአጠቃላይ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ እንድደርስ እናቴ ትልቅ ጽናት ሆናኛለች፡፡
በጣም ታታሪና ሥራ ወዳድ ናት፡፡ ቁጭ ብላ የምታባክነው ጊዜ የላትም፡፡ ቀኑን ሙሉ ስለቤተሰባችን ብቻ የምትጨነቅ፤ ስትባክንና ስትባዝን ነው የምትውለው፡፡ እናም ከእሷ የወረስኳቸው ብዙ ነገሮች አሉ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ካገባሁም በኋላም ባለቤቴ ልጆቻችንን በማሳደጉ ሂደትም ሆነ በትምህርት ገፍቼ እንድሄድ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርግልኝ ነበር። በነገራችን ላይ ባለቤቴ ዶክተር ሙሉ የትዳር አጋሬ ብቻ ሳይሆን አብሮ አደጌና ጉዋደኛዬም ጭምር ነው፡፡ የመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አብረን ነው የተማርነው። ስለዚህ እየተግባባን እሱ ራሱን ሲያበቃ እኔም ራሴን እያበቃሁኝ ነው የኖርነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትግራይ ክልል ብቸኛ ተወካይ ኖት፡፡ ሌሎች አባላት ሕዝብ የጣለባቸውን ሃላፊነት ጥለው ሲወጡ እርሶ ግን ሃላፊነታዎን ጥለው አልወጡም፡፡ እንዲህ አይነቱን ውሳኔ የወሰኑበት የተለየ ምክንያት ይኖርዎት ይሆን?
ወይዘሮ ያየሽ፡– እንደምታስታውሽው ትግራይን ሲመራ የነበረው መንግስት ወይም ድርጅት ከሌላው የኢትዮጵያ ክልሎች በተለየ ሁኔታ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካስቀመጠው አቅጣጫና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ባፈነገጠ መልኩ የፌዴራል መንግስቱና የምክር ቤቱ ዘመን እንዳበቃ በመግለፅ ኢ-ህገመንግስታዊ ተግባር ይፈፅም ነበር፡፡
እነዚህ ሰዎች በተለይም በምርጫ ቦርድ አቋማቸው ልክ እንዳልሆነ እየተነገራቸው ነው ምርጫ ያካሄዱት፡፡ የሚገርመው ምርጫ ማካሄዳቸው አልበቃ ብሏቸው የፌደራል መንግስቱ ህገወጥ ስለመሆኑ መስከረም 25 ስልጣኑ ያበቃለታል የሚል ጥሪ በየማህበራዊ ሚዲያው በትነዋ፡፡
እንዲሁም በነበረው ቴሌቪዥናቸው ቀርበው ሁሉም ተወካዮች ወደ ምክር ቤት እንዳይገቡ መመሪያ ሰጥተናል የሚል አቋም ይዘው አስተላለፉ፡፡ እኔም እንደማንኛውም ሰው በመገናኛ ብዙሃን ስለጥሪው ሰምቻለሁ፡፡ ሆኖም ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረው የዚያ ድርጅት አሰራር ሁኔታ ልክ ያልሆኑ ነገሮች እንደነበሩበት አውቃለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ምክር ቤቱ በተከፈተበት ወቅት ብቻ ሳይሆን ቀደም ብዬም ቢሆን የሚሰሩትን ስራና የሚያስተላልፉትን ውሳኔ በትዝብትና በአንክሮ ነበር የማየው፡፡ እነሱ የተለያየ የፌደራል መንግስቱ የሚያቀርባቸውን ውሳኔዎች ወደ ምክር ቤት ሲመጡ ከምክር ቤቱ በተለየ ሁኔታ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ እንዲሁ በጭፍን እጅ በማውጣት ይቃወሙ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜም ቢሆን እኔ ከእነሱ ጋር ወግኜ እየተቃወምኩኝ አልነበረም፡፡
እኔ ሁልጊዜም ቢሆን ለህሊናዬ ብቻ ማደር አለብኝ ብዬ የማምን ሰው ነኝ፡፡ እርግጥ ነው የሚያሳምነኝ ጉዳይ ከተገኘ ከእነሱ ጋር የምስማማበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላ፡፡ ነገር ግን እነሱ በአንድ ድምፅ ዝም ብለው ሲቃወሙ አብሬ አልወግንም፤ ይልቁንም ከእነሱ በተቃራኒ በመቆም ከሌሎቹ የምክር ቤት አባላት ጋር በጋራ ውሳኔዎቹን ስደግፍ ነበር የኖርኩት፡፡ የእነሱ ሃሳብና አካሄድ ለህዝብ የማይጠቅም፤ ምክንያታዊ ያልሆነ፤ ሊገለፅ የማይችልና ሊያሳምን የማይችል፤ መነሻቸውም ህዝባዊ ያልሆነና ለአንድ ቡድን ጥቅም ያደረ ነው፡፡
አብዛኞቹ አባላት ያ ቡድን በሚያዛቸው መሰረት እጃቸውን የሚያወጡ ናቸው፡፡ ይሁንና ለእኔ እንደዚህ አይነት አካሄድ ፈፅሞ ልቀበለው የምችለውም አይደለም፤ ባህሪዬም አይደለም፡፡ እንዳልኩሽ ላመንኩበት የምቆም ሰው ነኝ፡፡ በተጨማሪም ደግሞ በሴቶች መብት ዙሪያ ብዙ አመት የሰራሁኝ ሰው እንደመሆኔ እንደሴትነቴ ምክንያታዊ ሆኜ የመሰለኝ ልደግፍ፤ ያልመሰለኝን ልቃወም ካልቻልኩኝ እኔ ማንንም ላስተምር አልችልም፡፡ ለወጣቱም ላስተምርም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም ውሳኔ ላይ ልወግን አልችልም፡፡ ይህ ማለት መስዋእትነት እንደሚያስከፍል አውቃለሁኝ፡፡ ከዚያ በፊትም በጣም ብዙ ጫና ያደርሱብኝ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስቲ ይደርሰቦት ከነበሩት
ተሰጥቶሽ ነው›› የሚሉ ስም የማጥፋትና ማስፈራሪያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የሚገርምሽ እንዲህ አይነቱ ዛቻ ይደርስብኝ የነበረው ከለውጡ በፊትም ጀምሮ ነው። ምክንያቱም ይህ ድርጅት ከመጀመሪያውም የሃሳብ ልዩነትን የማይቀበል አምባገነን ስለነበረ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ታዲያ ልዩነቶችን በምን መንገድ ነበር ይገልፁ የነበሩት?
ወይዘሮ ያየሽ፡– አብዛኛውን ጊዜ በምክር ቤት ውስጥ ነበር ልዩነቶቼን እገልፅ የነበረው፡፡ ከእነሱ የፖለቲካ ድርጅት ከመጀመሪያውም በሙሉ ልቤ ያልገባሁበት በመሆኑ ከምሰበሰብበት ይልቅ የማልሰበሰብበት ጊዜ ይበልጣ፡፡ ምክንያቱም ሁኔታቸው ልክ ስላልነበረና በሚያደርጉትም ነገር ስለማላምንበት ነው፡፡ እኔ ምክር ቤቱ ቀኑ ሲያበቃለት የት ያገኙኛል፤ በሚል ቀን እየጠበቅሁኝ ነበር፡፡
ከዚያ ባሻገር ግን ያደርጉት በነበረው አብዛኛው እንቅስቃሴ አልሰማም ነበር፤ ይህንንም በግልፅ ነበር የማሳየው፡፡ ብዙ ሰዎች ፊት ለፊት አትጋፈጪ ራስሽን ጠብቂ ይሉኝ ነበር። በተለይ ህወሓቶች የሚፈሩበት ዘመን ብዙ ሰዎች ስለእኔ ይሰጉ ነበር፡፡ እናም እኔ እነሱን የተቃወምኩት መስከረም 25 አይደለም፡፡
ለምሳሌ ወሰን የማስከበር ኮምሽን ሲቋቋም እኔ ደግፊያለሁ፡፡ የደገፍኩበት አብይ ምክንያትም በአገሪቱ ስለወሰን ጥያቄ በበርካታ አካባቢዎች ይነሳ ስለነበርና ይህ ጥያቄ መመለስ አለበት ብዬ ስለማምን ነው፡፡
እነሱ በእርግጥ በህገመንግስቱ ተመልሷል ነው የሚሉት፡፡ ነገር ግን በህገመንግስቱ ቢመለስ ኖሮ ላለፉት 27 ዓመታት በየቀኑ ይህ ጥያቄ ሊነሳ አይችልም ነበር፡፡ ባለመመለሱ ነው በበርካታ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ደጋግመው የሚያነሱት፡፡
ስለዚህ አመላለሱ ችግር አለበት ማለት ነው የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ ህዝብ የራሱን ውሳኔ እንዲወስን ተጨማሪ ምቹ ሁኔታ መዘርጋት እንዳለበት፤ ባለሙያዎች ተመድበው ሂደው ህዝቡን አነጋግረው ታሪካዊ ዳራው ምን እንደሆነ ፈትሸው፤ በሙያ የታገዘ ግብአት ይዘው፤ በህግ አግባብ መፍታት እንዲቻል ተጨማሪ ስራ መስራቱ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም የሚል ፅኑ አቋም ነበረኝ፡፡
በተመሳሳይ ሌሎችም በምክርቤቱ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ የመሰለኝን በግልፅነት አቋም ወስጄ ከእነሱ እየተለየሁ ነው የመጣሁት፡፡ እናም ወደ ጥያቄሽ ስመጣ መስከረም 25 ምክር ቤት እንዳልገባ በተለያየ መንገድ መልዕክት ቢተላለፍም እኔ አልተቀበልኩትም፡፡ ምክንያቱም እኔ ምርጫው የተራዘመው በኮቪድ ምክንያት መሆኑ አሳምኖኛ፡፡ ኮቪድ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ችግር አይደለም፡፡ አለምን ያናጋ፤ ብዙዎቻችንን ያስደነገጠና ያስፈራራ ክስተት ነው፡፡
ይህንን በሽታ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያመጣው አይደለም፤ አልያም ምክር ቤቱ ያመጣው አይደለም፤ የአለም ወረርሽኝ እንጂ። አለምአቀፍአዊ ወረርሽኝ ስለመሆኑ ደግሞ የአለም የጤና ድርጅት አበክሮ የነገረን እውነት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ታስታውሺ እንደሆነ መጋቢት 4 ቀን እኛ አገር ከተከሰተ ወዲህ የነበሩት ሁኔታዎችን በጣም የሚያስፈራ ነበር። ብዙ ሰው ከቤቱ አይወጣም ነበር፡፡
ምክንያቱም የቫይረሱን ገዳይነት በነጣሊያን፤ እነ እስፔን አይተነዋልና ነው፡፡ በተለይ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሉን ነገር መሞከራቸውን፣ ከአሁን በኋላ የፈጣሪ ምሕረት በተስፋ እንደሚጠብቁ በተናገሩበት ጊዜ ብዙዎቻችን ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ ገብተን ነበር፡፡
ይህ የሚያሳየው አደጉ ሰለጠኑ የምንላቸው አገራት እንኳን ችግሩ አሳሳቢና ተስፋ አስቆራጭ እንደነበር ነው። አፍሪካ ውስጥ 23 ሚሊዮን ሰው ሊሞት እንደሚችል የአለም የጤና ድርጅትም ትንቢት ያመለከተበትና በፅሁፍም ተሰንዶ ያለ ነው፡፡
በተለይ አፍሪካ ትልቅ ስጋት ሆኖ እየተነገረ ባለበት በዚያ ወቅት ብዙዎቻችን የደነገጥንበት ወቅት ነበር፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ከጫፍ ጫፍ ተንቀሳቅሰን፤ ያስመራጭ ቦርዱን አሰልጥነን፤ ሌሎች ስራውን አከናውነን ምርጫ ማካሄድ አንችልም ብሎ በባለሙያ በተደገፈና አሳማኝ በሆነ መልኩ ለምክር ቤቱ አቅርቧ፡፡ ምክር ቤቱም በህግ በተቀመጠው አግባብ ውሳኔውን አስተላልፏ፡፡ ምርጫ ሲራዘም ደግሞ ዝም ብሎ ያለምንም ጥናት እንዳልነበር ይታወቃ፡፡
ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ የህግ ባለሙያዎች በሚያስደንቅ ሁኔታ የምርጫ ቦርድ መራዘሙ ለምን እንዳስፈለገ አብራርተዋ፡፡ የጤና ጥበቃና የኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች አማካኝነት ተብራርቶ አይናችን እያየ አሳማኝ ጭብጥ በዝርዝር ቀርቦበት ሁላችንም መክረንበት የተወሰነ ነው፡፡
ስለዚህ እኔ የምርጫው ልክ አይደለም ለማለት ብቁም አይደለሁም ብዬ ነው የማምነው፡፡ ምክንያቱም በሙያው ላይ ባሉ ሰዎች ጥልቅ ምርመራና ሰፊ ክርክር ተካሂዶበት ነው የተራዘመው፡፡ የሚገርመው ምርጫው ሲራዘም ግን ህወሃትም ሆነ ሌሎች በየክልሉ ያሉ መንግስታት እንዲቀጥሉ ነው የተወሰነው፡፡ ያ ከሆነ ምን ፍለጋ ነው ታዲያ ምርጫ ካልተካሄደ ሞተን እንገኛለን ሊባል የሚችለው፡፡
ለእኔም ሆነ ለማንም ሊያሳምን የማይችል ነው፡፡ ግልፅ የሆነ ጉዳይ ሆኖም አላገኘሁትም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ አትግቡ ማለት ልክ አይደለም፤ ፈፅሞ ልቀበለው አልችልም፡፡ ቀድሞ ነገር እነሱ ማን ስለሆኑ ነው እንደዚያ የሚሉት? ለእኔ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብን መናቅም ጭምር ነው፡፡ እነሱ እንጨነቅለታለን የሚሉት ዲሞክራሲ ሌላው ስለማይገባው ነው እንዴ? እነሱ ብቻ በተለየ መንገድ ስለሚገባቸው ነው? ስታስቢው ይህ አይነቱ ጉዳይ ፈፅሞ አሳማኝ አይደለም፡፡
ስለማያሳምን እኔ ደግሜ ደጋግሜ አሰብኩበትና ነው ያንን አይነት ውሳኔ የወሰንኩት። አይደለም ለራሴ አንዳንዶቹም የምቀርባቸው የፖለቲካ አባላት ልክ እንዳልሆኑና ወደ ምክር ቤት እንዲገቡ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ስልጣኑ እንደሆነ ለህወሃት የትም እንደማይሄድበትና ይህ አይነቱ ውሳኔያቸው ጠቀሜታ እንደሌለው ገልጬላቸዋለሁ፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ህወሃትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ይላሉ፡፡ በመሰረቱ ህወሃትና የትግራይ ህዝብ አንድ ከሆነ ምርጫ ለምን ያስፈልጋል? ለምን ሃብትና ጊዜስ ይባክናል?፡፡ ስለዚህ በየትኛው አግባብ ነው ምርጫ የሚካሄደው የሚል ጥያቄ አንስቼላቸው ነበር። ስለዚህ አሳማኝነት ሳይሆን ጭራሽ ከመስመር የወጣ ተግባር ነበር። ለማንም የማያስተምር ነው፡፡ ደግሞም እንደዚያ ይሉ የነበረው ምስኪኑን የትግራይ ህዝብ ለመጥቀም ቢሆን ኖሮ አይቆጭም ነበር፡፡
ያ ቢሆን ኖሮ እኛም ልንቀበለው እንችል ነበር፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ አንቺ ያሰብሽው ብቻ ልክ ላይሆን ይችላ፡፡ ሌላው ልክ ለሆነበት ጉዳይ ባያሳምንሽም ተገዝተሽ ልትሄጂ ትቺያለሽ፡፡ ግን የእነሱ ምዘና ከተቸገረውና ጭቁኑ የትግራይ ህዝብ መሰረት ያለው አይደለም፡፡
ይልቁኑም የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ያደረጉት ነው፡፡ እነሱ ብቻ አዋቂ ነን ባይነታቸው፤ ለዘላለም የማስተዳደር ሂደቱ እንዲቀጥልላቸው ስለሚሹ ያደረጉት ነው፡፡ ይህንን አይነቱን አላማ ደግሞ እንዳውም መታገል ነው እንጂ ያለብኝ ህወሓቶች ያሉትን፤ ለግለሰቦችና ለጥቂት ሰዎች ጥቅም አላጎበድድም፤ አልቆምም፡፡
አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ በእኔ አስተዳደግና እምነት ይህ አይነቱ ሁኔታ ነውርና ግፍ ነው፡፡ ነገ ጠዋት ልጆቼ ላይ ነው ይህ በደል የሚደርሰው፡፡ ምክንያቱም እኔ ከትግራይ ነው የመጣሁት፤ ዘመዶቼ እዛ ነው ያሉት፤ የትግራይ ህዝብ እንዴት እየኖረ እንደሆነ አውቃለሁ።
የትግራይ ህዝብ ወደ ቁልቁል እንጂ ወደ ከፍታ እያደገ አይደለም፡፡ የተወሰኑ ከእነሱ ጋር ጥገኛ የሆኑ ሰዎች ያለፈላቸው ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ብዙሃኑ ህዝብ አሁንም በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ነው እየኖረ ያለው። ውሃ የለም፤ ተማሪዎች አሁንም በዳስ ነው እየተማሩ ያሉት፡፡ አሁን ደግሞ የተማሪው ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል፤ ይህንን አዲስ ትውልድ በአግባቡ ሊቀርፅ የሚችል ተቋም አልተገነባም፡፡
ለክልል ምርጫ ይህን ያህል ገንዘብ ማውጣት ምን ማለት ነው? ለምርጫ የሚያባክኑት ገንዘብ እኮ ለእነዚህ ትምህርት ቤቶች ቢውል ኖሮ፤ ውሃ ለጠማው ለእዛ ህዝብ የውሃ መሰረተ ልማት ቢገነቡለት፤ መንገድ ለሌለው መንገድ ቢሰሩለት ምን ያህል ጠቃሚ እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ እነሱ ግን ይህንን አላደረጉም፡፡ የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ነው ያስቀደሙት፡፡
ያካሄዱት ምርጫ ለህዝብ የሚጠቅም ቢሆን ኖሮ እኔ ልክ ነኝ ያልኩትን ነገር ለህዝብ ስል እተወው ነበር፡፡ ነገር ግን ጥቅሙ ለህዝብ ከመሆን ይልቅ ህዝብን የሚጎዳ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ይህ ነገር ስር እየሰደደ እነሱ በገዢነት መደብ ቁጭ ብለው አድራጊና ፈጣሪ ሆነው የሚቀጥሉበትን እድል መስጠት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር መቆም አለበት የሚል አቋም ስላለኝ ነው የእነሱን ሃሳብ ሳልቀበል ምክር ቤት ልገባ የቻልኩት፡፡
አዲስ ዘመን፡– ይህንን የተለየ ሃሳቦትን በብቸኝነት ሲያራምዱ መገለል አላጋጠሞትም ?
ወይዘሮ ያየሽ፡– እንዳልሽው በተለይ የትግራይ ሊሂቁ፤ ልምድ ያለው ከሰፊው ማህበረሰብ ሻል ያለውና ለማህበረሰቡ ትንሽ ፈር ሊቀድ የሚችል ሰው አብዛኛው እነሱን ሲደግፍ ስታይ እኔ በጣም አዝናለሁ፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ እኔና አንቺ ወደዚህ አለም ስንመጣ የተለያየን ሰዎች ሆነን ነው፡፡ የተለያየ አላማም አለን፡፡
አንድ አይነት ልናስብ አንችልም፡፡ አንዳንዶቹ እነሱን ከመፍራት ዝም ብሎ ልክ አይደለም እንዲህና እንዲህ ያደርጓችኋል ከሚል ነው አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ዝምታን የመረጠው፡፡ እነሱን ብንቃወም ማን ይደርስልናል? የሚል ስጋት ስለነበራቸው ችለን እንኑር የሚለው በጣም ይበዛ፡፡ አንዳንዱ ከጊዜያዊ ጥቅም በመነሳት ሊሆን ይችላ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ እዚህም ሆኖ የሚፈራቸው አለ፡፡
የሚገርምሽ ውጭ አገር ሆኖ ራሱ የሚፈራቸው አለ፡፡ አሜሪካ ሆኖ አንቺ ጋር ቢደውል እነሱ እንዳይሰሙት የሚፈራም አጋጥሞኛ፡፡ እናም በእዚህ ረገድ ህወሓት እድሉን ተጠቅመዋል ባይ ነኝ፡፡
እኔ ጋር እየደወሉ ዝም ብትይ አይሻልም ወይ፤ እኛ እኮ ጠፍቶን አይደለም የሚሉኝ አሉ፡፡ በጭፍን እነሱን የሚደግፈው ደግሞ ይሳደባል፤ለማስፈራራትም ጥረት ያደርጋል፡፡ በእኔ በኩል ገና ለውጡ ሲመጣ ነው የተቀበልኩት፡፡ እናም አንዳንድ ነገር ስፅፍ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰሩትን ስራ በማህበራዊ ሚዲያው ድጋፌን ስገልፅ ብዙ ውርጅብኝ ነበር የሚወርድብኝ፡፡ ሆን ብለው ሰዎች ተመድበውልኝ እየተከታተሉ የሚሰድቡኝና የሚያስፈራሩኝ ሰዎች ነበሩ፡፡
ይህንንም ለታሪክ ሰንጄ አስቀምጬዋለው፡፡ ለውጡ ከማንም በላይ ለትግራይ ህዝብ ነው የሚጠቅመው ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ለአመታት ተጨቁኗ፡፡ የትግራይ ህዝብ በስሙ ብቻ ለአንተ ብለን ታግለናል በማለት ብዙ ጭቆና የደረሰበት ስለሆነ እኔ ለውጥ ሲመጣ በእውነት በጣም ነው የደገፍኩት።
ይህንንም የሚያውቁ አካላት ጥቃት ሊያደርሱብኝ ሞክረዋል፤ ግን እኔ የሚያስፈራኝ ነገር የለም፡፡ አንደኛ ለህዝብ እስከጠቀመ ድረስ ምንም የሚያሸማቅቀኝ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም እኔ የምበላውም ሆነ የምሰራው አላጣሁም ነበር፡፡ በምክር ቤት ዘመኔም ሲያልቅና ስወጣ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ተወዳድሬ ራሴንና ልጆቼን የማበላበት ስራ አላጣም። ግን ህሊናዬ የማያምንበትን በማድረግ ለጥቅም የምኖር ሰው አይደለሁም፡፡ ደግሞም ከወጣቶቹ ይልቅ እኔ ልምድ አለኝ፡፡
የተሻለውንና ትክክል የሆነውን የማወቅ እድሉን አግኝቻለሁ፡፡ በመሆኑም ለትውልድ አርአያ ሆኖ መኖር እንዳለብኝ ነው የማምነው። ያ በመሆኑ አሁን ላይ በወሰንኩት ውሳኔ ደስተኛ ነኝ። ስለዚህ እኔ ፈጣሪ ይጠብቀኛል ብዬ ስለማስብ በይፋ እቃወማቸው ነበር። ደግሞም ያጠፋሁት ጥፋትም የለም። ወይም የተለየ ጥቅም አገኛለሁ ብዬ አሰላስዬ አይደለም። ንፁህ ህሊናዬን ይዤ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመሰለኝን በማድረጌ ምንም አይደርስብኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡– ህወሓት እንደ ድርጅት ከሚከተለው ርዕዮተ አለም አንፃር ውስጣዊ ዲሞክራሲ ነበረው ማለት ይቻላል?
ወይዘሮ ያየሽ፡– በነገራችን ላይ እኔ ድርጅቱን የተቀላቀልኩት በ1997 ዓ.ም ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ አባል አልነበርኩም፡፡ ባለቤቴም ከዚያ በኋላ ነው የገባው። ምክንያቱም እኛ የሙያ ሰዎች በመሆናችን ብዙ ፖለቲካ ላይ ገብተን መፈትፈት አለብን የሚል አቋምም የለንም። እኛ ፊደል ቆጥረን መጥተናል፤ በሙያችን ስራ ተቀጥረናል፤ በተማርነው ትምህርት አስተዋፅኦ ማድረግም ጥሩ ነው የሚል አቋም ያለን ቤተሰብ ነን። እናም በ1997 ዓ.ም ምርጫ የነበሩት ቅስቀሳዎች ያስፈሩ ነበሩ። ሃይለኛ የዘር ቅስቀሳ፤ ፅንፍ የሄደ የዘውግ እንቅስቃሴ ስለነበር እፈራ ነበር፡፡
‹‹የትግራይ ሰው ወደ መቀሌ እቃ ወደ ቀበሌ›› የሚባልበት ወቅት ስለነበር። በዚህ ምክንያትም ስጋት ስለነበረኝ በፖለቲካ ድጋፍ ማግኘትና መብቴን የሚያስከብርልኝ የፖለቲካ ድርጅት ከመሻት ነው ድርጅቱን የተቀላቀልኩት፡፡ ግን ውስጡ ገብተሽ ስታይው በጣም የተለየዩ ነገሮች ነው የምታይው፡፡
አንደኛ እልም ያለ ያዛዥና ታዛዥ ሥርዓት የሰፈነበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡ የሃሳብ ልዩነትን የማያስተናግድ፤ በፍፁም ንቅንቅ የማታይበት አፋኝ ድርጅት ነው፡፡ እርግጥ ነው በኢኮኖሚ በኩል ያሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂ ጥሩ የሚባሉ ነበሩ፡፡ የፖለቲካ አመራሩ ግን ብዙ ልክ ያልሆኑ ነገሮች የሚስተዋሉበት ነው፡፡
አብዮታዊ ዲሞክራሲ ልማታዊ መንግስት እንደመሆኑ እንደኛ ሌላ ድሃ አገር ለህዝቡ የሚጠቅሙ መሰረተልማቶችን ለመዘርጋት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ውጤት አምጥቷ፡፡ ግን ደግሞ ልማታዊ ዲሞክራሲ ሲታሰብ አንድ ሰው ሳይበላ፥ ራሱ ሳያልፍለት ሌላው እንዲያልፍለት ማድረጉ በራሱ ከፍተኛ ችግር አስከትሏ። ይህንን የምለው ሰዎች እኩልና አብረው ሲያድጉ ነው መኖር የሚችሉት የሚል አቋም ስላለኝ ነው፡፡
ይህንን የሚያስፈፅም ፍፁም የሆነ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ለማለት ይከብደኛ፡፡ ይህንን ርዕዮተ አለም ያልደገፈ ደግሞ ተቋዋሚና ጠላት አድርጎ የሚታይበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ነገሮችን እንደየሁኔታው ማስተናገድ የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም። ፅንፍና ፅንፍ ከመርገጥ ይልቅ ወደመሃል መጥቶ ለህዝብ የሚጠቅም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ብዙ ተነሳሽነቱ አይታይም፡፡ ስለዚህ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ካለው ነበራዊ ሁኔታ አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈፀም አይችልም፡፡
በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሊተገብር የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን እሱና እሱ ብቻ ነው መንገዳችን ብለሽ የምትሄጂ ከሆነ ሊያዋጣ አይችልም፡፡ በብልፅግና መርሆ ሁኔታዎችን እያየን ለህዝብ የሚጠቅመውን እያስተካከልን እንሄዳለን የሚል ነው። ወደ መሃል በመምጣት እየተግባባን ለህዝብ መስራት የምንችልበትን ምህዳር የሚፈጥር ነው፡፡
በነገራችን ላይ የዘር ፖለቲካ የትም ሊያደርሰን አይችልም የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ እኔ ከየትም ልምጣ ለእኔ የሚመጥነኝ ቦታ በእውቀቴ ተወዳድሬ በሙያዬ መስራት መቻል አለብኝ ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይህ ሲሆን ነው ወጣቱ በውድድር መንፈስ ማደግ እንዳለበት የሚያምነው፡፡
ሲሰራ ብቻ ማደግ እንደሚችል፤ ለመስራት ደግሞ መማር፣ መወዳደርና ማደግ እንደሚገባው ነው ልናስተላልፍለት የሚገባው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻልን ወጣቱን እያኮላሸነው ነው የምንሄደው፡፡ እኛ አገር ግን የተለመደው የሆነ ቦታ ላይ ዘመድ ስላለሽ የምትቀጠሪበት ሁኔታ ተንሰራፍቶ ነው የኖረው፡፡ በራሱ የሚተማመን ሞራል ያለው ሃሞተ ቆራጥ ወጣት ማግኘት በራሱ ፈተና ነው የሆነው፡፡
እኔ አንዳንዴ የትኛው ነው ትክክል እያልኩ ራሴን በመጠየቅ የምወዛገብበት ሁኔታ ተፈጥሮብኝ በጣም የምጨነቅበትና የምከራከርበት ጊዜ ነበር፡፡ ስራ ሰርቶ የሚጠበቅበትን ያበረከተው ነው ትክክል? ወይስ ወገን ስላለው ብቻ ወደፊት የመጣው ነው ትክክል? ብዬ በተደጋጋሚ ራሴን እጠይቅ ነበር፡፡
እኩል ሄደሽ ሰርተሽ ዘመድ ያለው እየተመረጠ የሚጠቀምበት፤ አንቺ ግን ቁልቁል የምትሄጂበት ሁኔታ ነበር የነበረው። የስራ ሞራልሽም ይሞታ፡፡ በዚህ ሁኔታ ስንት አዋቂና ለአገር የሚጠቅም ዜጋ ስነልቦናው ተሰልቦበታ፡፡ ለዚህ እኔ ራሴ ምስክር ነኝ፡፡
በዘርሽ ብቻ የምትለይበትና የምትመረጭበት ሁኔታ ተንሰራፍቶ ነው የቆየው፡፡ በዘር ብቻ ተመርጦ የሚሾመው ሰው ደግሞ ወይ አውቆ አያስተምርሽም፤ ወይም ደግሞ ነፃነትሽን ሰጥቶሽ ሰርተሽ እንድትለወጪ አያደርግሽም፡፡ ነገር ግን እንዳትበልጭው አንቺን ይጨፈጭፋል፤ እንዳያስተምርሽም ካንቺ አይበልጥም። ወጣቱ ራሱን እንደማብቃትና በራስ የመተማመን ችሎታውን እንደማሳደግ ጠባቂ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯ፡፡
ብዙዎቻችን በጠባቂነት ተሸብበን ነው የኖርነው፡፡ ካለፈው ስርዓት የምጠላው ጉዳይ አንዱ ይህ ነገር ነው፡፡ ታዛሹና እሺ ባዩ ምንም ሳይሰራ አንቺ ላይ የሚረማመድበት ሁኔታ ነበር፡፡ አንቺ ግን ችለሽም፤ አውቀሽም፤ ሰርተሽም፤ መሬቷን መርገጥ የምትፈሪበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። እንዲህ አይነት ነገሮች ነበሩ ትልቁ የስርዓቱ ውድቀትና ለአገራችን ልማት ነቀርሳ የነበሩት፡፡ እኔም ፓርቲ ውስጥም ሆኜ አጥብቄ ነበር የምቃወመው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ህወሓት ያቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው የሄዱ የምክር ቤቱ አባላት በእርግጥ የህዝብ ተወካዮች ነበሩ ለማለት ይቻላል?
ወይዘሮ ያየሽ፡– እነዚህ ሰዎች የህዝብ ተወካዮች አልነበሩም፤ ይልቁንም የፓርቲ ተላላኪዎችና በሪሞት የሚቆጣጠሯቸው ሰዎች ሆነው ነው የተገኙት፡፡ የምክር ቤት አባል መሆን ትልቅ ክብር የሚያሰጥና የ100ሺ ህዝብ ውክልና ይዘሽ ነው የምትገቢው፡፡
ምንአልባት አመጣጥሽ በፓርቲ በኩል ወይም በግልሽ ተወዳድረሽ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከገባሽ በኋላ ያ የወከለሽን ህዝብ ጥቅም ነው ማስቀደም የሚገባሽ፡፡ ለህሊናሽና ለዚያ ህዝብ ነው ተጠሪነትሽ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ከህዝብ ውክልናቸው የወጡ እና ለፓርቲ የመላላክ ስራ ሲሰሩ ነው የኖሩት፡፡ እኔ ለእነሱ ነው ያፈርኩት፡፡ በጣምም አዝኜባቸዋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ ብቻዎትን የተጋፈጡለት እውነትም ሆነ ህዝብ ነፃ ወጥቶ ሲያዩ ምንአይነት ስሜት ፈጠረቦት?
ወይዘሮ ያየሽ፡- እኔ በእውነት ነው የምልሽ በቃላት ልገልፀው የማልችለው ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ እውነት ለመናገር እንደዚህ ነገሮች በአጭር ጊዜ ይሆናሉ ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡
ብዙ መስዋዕትነት ሊያስከፍለኝ እንደሚችል አውቄና አምኜ ነው የገባሁበት፡፡ ግን እግዚአብሄር የተመሰገነ ይሁን እንደሰጋሁት አልሆነም። በኢትዮጵያ እናቶች ፀሎትና እምባ የከፋ ነገር ሳይደርስ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ የዚህ ሃይል መጨረሻ ለማየት ችለና፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይም የተከበረው የመከላከያ ሰራዊታችን በጣም ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት ጥንካሬ እልህ በተሞላበት ደረጃ ምላሽ ባይሰጥና ባይንቀሳቀስ ኖሮ በእውነት እዚህ ልንደርስ አንችልም ነበር፡፡
ስለዚህ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በዚህ ሂደት ላይ መግለፅ የምፈልገው ነገር ኢትዮጵያዊነት ትልቅ ሚስጥር ያለው ነው የሚመስለኝ፡፡ ያለፈው 30 ዓመት ነው እንጂ ጉድ ያመጣብን ከመሰረቱም ሁላችንም በኢትዮጵዊነታችን ከማንም በላይ የምንኮራና ለአገራችን በጋራ የምንቆም ዜጎች ነበርን፡፡ እንደነገርኩሽ እኔ በ1978 አዲስ አበባ የገባሁት፤ ነገር ግን አንድም ቀን በኢትዮጵያዊነቴ ላይ ጥያቄ ኖሮኝ አያውቅም፡፡ ማንም ቢሆን ይህንን ጥያቄ አንስቶ አያውቅም ነበር፡፡
የመከላከያ ሰራዊታችን በጥሩና ጠንካራ በሆነ ኢትዮጵያዊነት መሠረት ላይ ነው የተገነባው፡፡ እንዳውም ለሌሎች አፍሪካ አገራት ትልቅ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሰራዊት ነው፡፡ አሁን የተፈጠረው ባጋጠመን ችግርና ህግ በማስከበር ሂደቱ ያየሁት ነገር ደግሞ ኢትዮጵያውያን የበለጠ ጠንካራ ግንኙነት እንዳለን ለማረጋገጥ አስችሎኛ። ምን ያክል ህዝብ ለህዝብ የጠነከረ ግንኙነትና በቀላሉ የማይነቃነቅ ግንኙነት፤ ወርቅ የሆነ አስተሳሰብ እንዳለ ተገንዝቤለሁ፡፡ የበለጠ ኢትዮጵያዊነት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን ተምሬአለሁ፡፡
ትልቅ የሆነ የአብሮነት ጥንካሬ በቀላሉ የማይፋቅ፤ በምንም አግባብ የማይነቃነቅ መሆኑን ያየሁበትና የተማርኩበት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በገንዘቡም ሆነ በተለየያ አግባብ ላሳየው ድጋፍና ተጋድሎ እጅግ ክብርና ምስጋና እንዳለኝ ለመግለፅ እወዳለሁኝ፡፡ በተለይ የመከላከያ ሰራዊታችን ያሳለፉት ችግር፤ ለእኛ ሲሉ የከፈሉት ዋጋ ትልቅ ምስጋና እና ክብር የሚያሰጣቸው ነው፡፡
የአማራ ሚሊሻና ልዩ ሃይልም እገዛና ድጋፍ ወደዚህ ምዕራፍ መድረሳችን በቀላሉ ልናየው የሚገባ አይደለም፡፡ በእርግጥ ጁንታው እቅድ ይህ አልነበረም፡፡ እኛ እርስ በርስ እንድንጨፋጨፍ ነበር መሻቱ፤ ነገር ግን ፈጣሪ ይመስገን ይህ አልሆነም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት በፅኑ አለት ላይ የተመሰረተና የተገነባ በመሆኑ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– እንደ ህዝብ ተወካይነቷዎ የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ምን ነበር፤ ምርጫውን ማድረግስ ዋነኛው ጥያቄው ነበር ይላሉ?
ወይዘሮ ያየሽ፡– የትግራይ ህዝብ ጦርነት አልነበረም። ምርጫውንም ቢሆን በግዳጅ እንዲመርጥ እንጂ ፈልጎ ያደረገው አይደለም፡፡ ወደ ጦርነቱም ተገዶ ነው የገባው። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ከማንኛውም ህዝብ በላይ የጦርነትን ጉዳት ያውቀዋ፡፡ ጦርነት ምን እንደሚያስከትል ይገነዘባ፡፡ ደግሞም ገና ከድህነት ያልወጣ ህዝብ ነው። የሞላለትም ህዝብ ቢሆን ጦርነት አይመኝም፡፡ እኔ በልጅነቴ እንደነገርኩሽ ትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነቶች ሲካሄድ ስላየሁኝ ምን አይነት ችግር ስናሳልፍ እንደነበር በወሬ ሳይሆን በተግባር አይቼው ነው ያሳለፍኩት፡፡ በየአልጋ ስሩ በየምሽጉ ተደብቀን የምናሳልፋቸው ሌሊቶች በርካታ ነበሩ፡፡
እላያችን ላይ የቤታችን ጣሪያ እየተናደና ቅጠሎች ሳይቀሩ በጦርነቱ እየወዱሙ የቆዩበትን በጣም ሰቅጣጭ የሆነ ልጅነት ነው ያሳለፍኩት፡፡ ስለዚህ ጦርነት ምን እንደሆነ እኔ የበለጠ አውቃለሁኝ፡፡ የትግራይ ህዝብ ደግሞ ከሊቅ እስከደቂቅ ያውቀዋ፡፡ እንደዛም ሆኖ በጦርነት አልፎ ደግሞ ምን አገኘ የሚለው ነገር የትግራይ ህዝብ ያውቀዋ፡፡ የፈየደለትም ነገር የለም፡፡
ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ጦርነት እንደማይፈልግ እኔ መመስከር እችላለሁ፡፡ የፌደራል መንግስት አገር እንደሚያስተዳድር የፌዴሬሽን ምክር ቤት መንግስት መከበር አለበት፡፡ መንግስት ዝም ብሎ ሳይሆን ህገመንግስቱን መሰረት አድርጎ ያስተላለፈው ውሳኔ መከበር አለበት፡፡ ውሳኔን የሚያከበር ታላቅ ህዝብ ነው። እንደእምነት በምርጫው የተሳተፈው እነሱ አስገድደውት እንጂ ፈልጎት አይደለም፡፡
የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው፡፡ ወጥቶ ገብቶ ሰርቶ መኖር የሚፈልገው። አሁንም ወደ ነበረበት ሁኔታ ተመልሶ ሰላሙን አግኝቶ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መኖር ነው የሚፈልገው። በፖለቲካውም ቢሆን ልክ እንደሌላው ህዝብ ምህዳሩ እንዲሰፋለት ይሻ፡፡ የትግራይ ህዝብ እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲመጣ የሁልጊዜ ምኞቱ ነበር፡፡
እኔ አሁን ባለኝ መረጃ ለምሳሌ ሽሬ እንደስላሴን ብትወስጂ የወረዳ ምክር ቤት ምርጫ አልተካሄደም፤ ልክ እንደህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀጥል ነው የተደረገው፡፡ አሁን እዛ ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር የወረዳው ምክር ቤት አባላት እንደነበሩ እንዲቀጥሉ ጥሪ ቢያቀርብም ህዝቡ ግን ፈፅሞ አልፈለገውም ነበር፡፡ ህዝቡ ‹‹እነሱ ሌቦች ናቸው አንፈልጋቸውም ›› ነው ያለው። ስላላመኗቸው አልፈለጓቸውም፡፡ ስለዚህ ታማኝ የሆነ አመራር እንዲመጣለትና የፖለቲካው ምህዳሩ ሰፍቶለት በተዓማኒነትና በነፃነት መምረጥ ነው የሚፈልገው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ህወሓት ህዝቡ ላይ ያደርስ ከነበረው ስነልቦናዊ ጫና አንፃር አሁንም ቢሆን ተመልሶ ይመጣል የሚል ስጋት ያለው ማህበረሰብ እንዳለ ይታወቃል፤ ከዚያ አንፃር የዚያን ህዝብ አመለካከት ከመቀየርና ስጋቱን ከማስወገድ አንፃር ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ወይዘሮ ያየሽ፡– ልክ ነሽ የህዝቡ ስጋት የእኔም ስጋት ነው፡፡ እስከመጨረሻው ይህንን ችግር ያመጡብን የጁንታው መሪዎችን ለፍርድ የማቅረብ ሂደቱ ምን ላይ እንደደረሰ ለህዝቡ መገለፅ አለበት፡፡ የጁንታውን አባላት የተገባበት ተገብቶ ለህግ መቅረብ ከቻሉ ብቻ ነው የትግይ ህዝብ ከጫንቃው እንደለቀቁለት አምኖ በነፃነት መንግስትን የሚደግፈው ብዬ የማስበው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጁንታውን አባላት አሳልፎ ከመስጠት አኳያ ከህዝቡ ምን ይጠበቃል?
ወይዘሮ ያየሽ፡- ህዝቡ እነዚህ ወንጀለኞች እንዲያዙለት መፈለጉ አንድ ነገር ሆኖ ህብረሰቡ ተባባሪ መሆን አለበት፡፡ እንደሚባለው አሁንም በህዝቡ ጉያ ተደብቀው ከሆነ ህዝቡ አሳልፎ መስጠት ይገባዋ። ምክንያቱም የመንግስት አይንና ጆሮ ህዝብ ነው፡፡ ያለ ህዝብ ድጋፍና ተባባሪነት ምሉዕ የሆነ ውጤት ሊመጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ተባበሪ ሆኖ ከመከላከያ ጎን ተሰልፎ መቆም አለበት ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ህወሓት በሰራው ወንጀል ምክንያት የትግራይ ህዝብ ከእያንዳንዱ ህዝብ ጋር ሲያጋጨውና ጠላት ሲያበጅለት ነው የኖረው። አሁንም በህወሓት ሰዎች ስራ ምክንያት ልንጠቃ እንችላለን የሚለውን የህዝብ ስጋት ከመቅረፍ አኳያ ምን ሊሰራ ይጋባል?
ወይዘሮ ያየሽ፡– እንዳልሽው አሁን ያለውን ለውጥ በጥርጣሬ እንዲያየው የፈጠረበት አንዱ ስጋት አንቺ ያነሳሽው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ለዘመናት ‹‹በጠላት ተከበሃል›› በሚለው የህወሓት ማስፈራሪያ ሲሰጋ
ነው የኖረው። በዚህ በኩል አማራ መጣህብ፤ በሌላ በኩል ሻቢያ ሊወርህ ነው፤ አልፎ ተርፎም የፌደራል መንግስት ይመጣብሃል የሚል ማስፈራሪያ ሲደረግበት ነው የኖረው። እኔ ለዚህ ህያው ምስክር ነኝ። እህቶቼ ጋር ደውዬ ደህንነታቸውን ስጠይቃቸው እንኳ «እስካዛሬ ደህና ነን፣ የነገን አናውቅም›› የሚል በፍርሃት የተሸበበ መልስ ነበር የሚሰጡኝ። አንደኛ አብዛኛው ሰው የሚሰማው ሚዲያ የእነሱን ነው። ከሁሉም የከፋ ደግሞ በአንድ ለአምስት ጠርንፈውታ።
ስለዚህ እነሱ የሚፈልጓትን ብቻ በአንድ ለአምስት ጭንቅላቱ ላይ ሲጫንበት ነው የኖረው። ያ ስጋት በአጭር ጊዜ ይወገዳል ተብሎ አይታሰብም። በመሆኑም መከላከያ በሚያሳየው ድጋፍ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚሰራው ፍትሃዊና የተሳለጠ አገልግሎት አቅም በፈቀደ መጠን ግልፀኝነት በተሞላበት አካሄድ መሄድ ይጠበቅበታ። ያልቻለውን ለህዝቡ እውነታውን ማስረዳት ይገባዋ። በተቻለ መጠን ህዝቡ ከዚያ ፍርሃትና ስጋት እንዲወጣ ለማድረግ ከፍተኛ የግንዛቤ ስራ መሰራት አለበት።
አሁን በዚህ ህግ ማስከበር ጊዜ ሽሬ አካባቢ ሰው ከቤት መውጣት አይፈልግም፤ ነገር ግን ህዝቡ ውስጥ ሆነው ለመጥፋት ነው ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት። በዚህ ሂደት የተጎዱ ሰዎች አሉ። ወደ ቤታችሁ እንዲመለሱ ለማድረግ መከላከያ ብዙ ጊዜ ነው የወሰደበት። ይህ የሆነው በተሰራው ክፉ አስተሳሰብ ምክንያት ነው። ገዳቶች ይመጡብኛል ብሎ ይፈራ። ፍጹም እውነት ሊሆን የማይችል ውሸት እየዋሹ ህዝቡን እንዲፈራ ሲያደርጉ ስለነበር ሚዲያዎቻችን በዚህ ላይ መስራት አለባቸው። ጊዜያዊ አስተዳደሩም ወደ ህዝቡ ወርዶ ትክክለኛ ተዓማኒነቱን በተግባር ማሳየት አለበት።
አዲስ ዘመን፡– ክልሉን እንደአዲስ የማደራጀቱን ስራ ህዝቡ በምን መልኩ ነው የተቀበለው ብለው ያምናሉ?
ወይዘሮ ያየሽ፡– እኔ የተሟላ መረጃ ባይኖረኝም አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ ሽሬ ያለው ህዝብ በሚያስገርም ሁኔታ ነው የደገፈው። እንዳውም የነበሩትን የወረዳ አስተዳደሩንም ሆነ መላውን አመራር አንፈልግም ነው ያሉት። ሌቦች ስለሆኑ አያስፈልጉንም ብለው አዲስ አመራር እንዲመጣ ነው የጠየቁትና የመረጡት። የሰላምና የመረጋገት ስራ እንዲሰራ ከራሳቸው ከህዝቡ መሃል ተመርጦ ዘብ ያቆመበት ሁኔታም አለ። ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር አብረን እንሰራለን ብሎ በተግባር አስመስክሯ። ይሄ ጥሩ ምሳሌ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡– ጁንታው በማይካድራ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በእርግጥ ህዝቡ ያውቀዋል ወይ? በዚህስ ላይ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
ወይዘሮ ያየሽ፡– የትግራይ ህዝብ ያውቀዋል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም መብራት እና ቴሌ ስላልነበረ ሌሎች መገናኛ ብዙሃንን የሚያገኝበት አማራጭ ስላልነበረው በዚህች አገር በትክክል ምን እየተከናወነ እንደነበር ጠንቅቆ የሚያውቅበት ሁኔታ አልነበረም። እነሱ የሚያውቁት ቀድሞ በተደራጀው የአንድ ለአምስት ቡድን የሚፈሰውን መረጃ ብቻ ነው። አንቺ የጠቀስሽው ስለ ማይካድራው ጭፍጨፋ ያላቸው ግንዛቤ የተለየ ነው። የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ካወጣው መረጃ በተቃራኒ የፌደራል መንግስቱ እንዳደረገው ነው የተነገራቸው። ይህንን ሃቅ የትግራይ ህዝብ አያውቅም።
አንዳንዴ የሞቱት የትግራይ ህዝብ ናቸው ሲሉ ትሰሚያለሽ፤ አንዳንዴ ገዳዮቹ ሌሎች ናቸው ሲሉ ትሰሚያለሽ። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ህወሓት በማይካድራም ሆነ በመከላከያ ላይ የሰራውን ኢሰብአዊ ድርጊቶች በአግባቡ ሊረዳው የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር የሚቻለው የሚል እምነት አለኝ። በአቅርቡ እንኳ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ህወሓትን ሲቃወም የነበረውን ደጀን ገብረ መስቀል የተባለ ወጣት አገር ሰላም ብሎ በተኛበት ነው የገደሉት። ያስገደሉት ደግሞ ከፌደራል የሄዱ የጁንታው አባላት ናቸው። እንደዚህ አይነት ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በአግባቡ ተቀምረው ለህዝቡ ማሳወቅ ይገባል።
በነገራችን ላይ ህወሓትን ከማንም በላይ የሚያውቀው የክልሉ ህዝብ ነው። ምክንያቱም ህወሓት በትግሉ ጊዜ ጀምሮ ህፃናት ወጣቶችን ሳይቀር ካልደገፉት የሚጨፈጭፍበት ሁኔታ እንደነበር ህዝቡ ያውቃ። እናም መሃል አገር ካለው ህዝብ በበለጠ የትግራይ ህዝብ የህወሓትን ማንነትና መሰሪነት ያውቃ። ስለዚህ በደንብ አድርጎ ሲቀርብላቸው ከማንም በላይ ይቀበለዋል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በዚህ ችግር ምክንያት የተሰደዱ ዜጎችን በማስመለስ ሂደት ምንአይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለው ያምናሉ?
ወይዘሮ ያየሽ፡- እኔም በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ ስጋት ነው ያለኝ። መደበላለቅ የለበትም። የእውነት ንፁሃን የሆኑትን መለየትና ወደ አገራቸው እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋ። ምክንያቱም ጦርነት ሁልጊዜም ቢሆን አስፈሪ ነውና። በመሆኑም ጦርነቱን ሸሽተው የሄዱ ዜጎቻችንን በተሻለ መጠን አሳምነን መመለስ አለብን።
እዚህ ላይ መስራት መቻል አለብን። ምክንያቱም ጠላት ያልሆነውን ጠላት ሆኖ እንዳይቀየር ስጋት ስላለኝ ነው። አሁን እዚህ መጣብህ ተከበብክ እያሉ ሲያሳምኑት እንደኖሩት ሁሉ እዛም ሊሰሩ ስለሚችሉ መልሶ የሰላማችን ጠንቅ እንዳይሆኑ ለይቶ ግንዛቤ መስጠትና መመለስ ይገባ።
በሁለተኛ ደረጃ ማይካድራ ላይ ጭፍጨፋ ፈፅመው ያመለጡ የሳምሪ ቡድኖችንም ሆነ አባላትን ባለን ጥሩ ዲፕሎማሲ በመተባበር ልክና መልክ መያዝ አለበት ብዬ አስባለሁ። እነዚህ ቡድኖች ሸሽተው ሄደው ተጠናክረው የሰላም ጠንቅ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ስራ መሰራት አለበት። ይሄ ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም። ምክንያቱም ተጃምሎ መሄድ እንዳይኖር ስጋት ስላለኝ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ያየሽ፡– እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013