ለምለም መንግሥቱ
ከደረቅ ቆሻሻ ማዳበሪያ (ኮፖስት) በማዘጋጀት፣ ከኢንደስትሪና ከተለያየ ቦታ የሚወገደውን ፍሳሽ ቆሻሻ ደግሞ በማከም ንጹሁን ለይቶ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በተለይም ደረቅ ቆሻሻ ለኃይል ምንጭነት በመዋል የጎላ ሚና አለው። ዜጎችም የሚሰበሰበውን ደረቅ ቆሻሻ ወደ ገንዘብ በመለወጥ ኑሮአቸውን ሲመሩ እያየንና እየሰማን ነው።በየመኖሪያችንና አካባቢያችን እንደምናስተውለው ቆሻሻ ጥቅሙ ዘርፈብዙ ሆኖ አወጋገዱ ዛሬም ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል።
ቆሻሻን ማስወገድ ውበትን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ለሚፈለገው ጥቅም እንዲውል ባለመደረጉ ለሙቀት አማቂ ጋዞች መጨመር መንስኤ ሆኗል።ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ በሚብላላበት ወቅት የሚመነጨው ጋዝ ወደ ከባቢ አየር በቀላሉ ይሰራጫል።ብክለትን በማስከተል በመተንፈሻ አካል ላይ የጤና ጉዳት ያስከትላል።በደቂቃዎች የሚያጋጥመው የአየር መለዋወጥ የዚህ መንስኤ ሳይሆን ይቀራል?
ወደ ከባቢ አየር ከሚለቀቁ የሙቀት አማቂ ጋዞች የደን መጨፍጨፍ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝና በደን መጨፍጨፍ በየዓመቱ 20 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የሙቀት አማቂ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር እንደሚለቀቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ።ለከፍተኛ ሙቀት መጨመርና ለተደጋጋሚ ድርቅ መከሰት ምክንያት መሆኑም ተጠቁሟል።ከደረቅ እና ከፍሳሽ ቆሻሻ፣ ከተሽከርካሪ፣ ከኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች፣ እንዲሁም ከእንስሳት በሚወጣው ትንፋሽና እበት የሚወጣው አማቂ ጋዝ እንዲፈጠር በማድረግ ተጽዕኖውን ከፍ እንደሚያደርገው ይነገራል።በአጠቃላይ ሙቀትን ያምቃሉ የሚባሉት ጋዞች ካርበንዳዮክሳይድ፣ሚቴይንና ናይትሮይድ ኦክሳይድ እንደሚባሉ በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የአየር ንብረት ለውጥ ቡድን መሪ ወይዘሮ ፋንቱ ክፍሌ ያስረዳሉ።
እንደ ወይዘሮ ፋንቱ ማብራሪያ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ችግር እየጎላ የመጣው ከኢንደስትሪ የስልጣኔ አብዮት ከ‹‹ኢንደስትራላይዜሽን ሪቮሉሽን››ወዲህ ነው።ከተሞችና ኢንደስትሪዎች ተስፋፍተዋል።የህዝብ ቁጥር ጨምሯል።ዕድገቱ የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንዲጨምር በማድረጉ የሙቀት አማቂ ጋዝ ከፍ እንዲል ምክንያት ሆኗል።መጠኑ ከፍ አለ ማለት ደግሞ በምድር ላይ ተንጸባርቆ የሚመለሰው የሙቀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲታመቅና ከባቢ አየር ሙቀት እንዲጨምር በአጠቃላይ ምድር እንድትሞቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።ወደ ህዋ አልፎ የሚሄደው ይቀርና የምድርን ከባቢ የአየር ሙቀት ይጨምራል።ይህ ሲሆን የምድር መሞቅ (ግሎባል ዋርኒግ) የሚባለውን ያስከትላል።
የሙቀቱ መጨመር የተለያዩ መገለጫዎች አሉት።ከመገለጫዎቹ ምድርን የሸፈነው በረዶ መቅለጥ መጀመርና ጎርፍ ማስከተል፣የበረሃማነት መስፋፋት፣የተለያዩ በሽታዎች መከሰት፣ደጋማ አካባቢዎች ወደ ቆላማነት መቀየር ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ከስተቶች ሆነው ይጠቀሳሉ።በሙቀት አማቂ ጋዝ ለሚከሰቱ ለነዚህ ችግሮች ደግሞ ባላቸው የህዝብ ቁጥርና በተለያዩ ምክንያቶች ከተሞች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።የከተሞች ቅድመ ፕላንም የራሱ አስተዋጽኦ አለው።አረንጓዴ ስፍራዎችን በህንፃ መተካት፣ከተለያየ ሥፍራ የሚመነጩ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በአግባቡ አለማስወገድ ጥቂቶቹ ሲሆኑ፣በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ከተማ ማሳያ ናት።
እንደ ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ፣ግብርና ሚኒስቴር፣የአዲስ አበባ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ ኤጀንሲ፣የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ እና ሌሎችም ባለድርሻ የሆኑ መንግሥታዊ ተቋማት ሙቀት አማቂ ጋዝን ለመከላከል ቀድመው ካልሰሩ ለሙቀት አማቂ ጋዝ በማጋለጥ ሚናቸው ከፍ ያለ መሆኑን ወይዘሮ ፋንቱ ይናገራሉ።በሁሉም ባለድርሻ ተቋማት የአየር ንብረት ለውጥ ሥራ እንዲሰራ እኤአ በ2015 ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚል ሰነድ የተዘጋጀ ሲሆን፣ሰነዱ ሥራዎች በምን መልኩ መከናወን እንዳለባቸው ማስተግበሪያ ነው።ተቋማቱ ሰነዱን መሠረት አድርገው ዝርዝር ዕቅድ በማውጣት እንዲተገብሩም ያስችላቸዋል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ ዕቅድ ነድፈው ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ በመቀነስ ሚናቸውን መወጣታቸውን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ክትትል ያደርጋል።በዚሁ መሠረትም እኤአ በ2012 እና በ2016 እያንዳንዱ ፈጻሚ ተቋም ያከናወነው ተግባር ተዳስሷል።ወይንም የቆጠራ ሥራ ተሰርቷል።
የዳሰሳ ሥራው በተሰራበት በሁለቱ ዓመታት በትራንስፖርት ዘርፉ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት እየጨመረ መምጣቱንና በወቅቱም በተገኘው መረጃ ዘርፉ እያስከተለ ያለው ጉዳት ወደ 78 በመቶ የደረሰ እንደነበር ተረጋግጧል።ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁሉም ተቋማት ሚና ነበራቸው።የከተማ ግብርና ግን ከሌሎቹ አንጻር ሚናው አነስተኛ ነበር።ምክንያቱ ደግሞ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሲስፋፋ በከተሞች የከብት እርባታ እየቀነሰ መምጣት እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
እንደባለሙያዋ እንስሳቱ ሲያመነዥጉ ከሚያወጡት ትንፋሽና እበታቸው ሲብላላ ከሚፈጠረው ሚቴይን የተባለው ሙቀት አማቂ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲለቀቅ ያደርጋል።ሚቴይን የተባለው ከካርበንዳይኦክሳይድ ሙቀት አማቂ ጋዝ 20 በመቶ ሙቀትን በማመቅ ብልጫ ያለው በመሆኑ ጉዳቱ ከፍ ይላል።ከዶሮ የሚለቀቀው ሚቴይን ጋዝ ከቀንድ ከብት ያነሰ በመሆኑ በከተማ ግብርና የዶሮ እርባታን ማበረታታት፣ለግብርና ሥራው የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም፣አረንጓዴ ቦታዎችን ማስፋፋት፣ደን መትከል ጉዳቱን ይቀንሰዋል።
ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ ለመከላከል በመንግሥት በበጎ የሚታይ እርምጃ እየተወሰደ ነው።ከእርምጃዎቹ አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ ላለፉት ዓመታት ለቆሻሻ ማስወገጃ ሲውል የነበረውና በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የተገነባው ቆሻሻን ወደ ኃይል የሚቀይረው ፋብሪካ ይጠቀሳል።
ፋብሪካው በአግባቡ ተግባሩን ከተወጣ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ መቀነስ ይቻላል።ለሽያጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ታክስ በመጣል፣በፋብሪካዎች ተገጣጥመው ለገበያ በሚቀርቡ አዲስ መኪናዎች ላይ ታክሱን በመቀነስ የተወሰዱ እርምጃዎች ከመኪኖች የሚወጡ በካይ ጭሶችን ለመቀነስ የሚረዱ ናቸው።የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም በጋራ በየወሩ ከተሽከርካሪ ነፃ የሆነ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲደረግ እያከናወኑ ያለው ተግባርም አጋዥ እንደሆነ መጥቀስ ይቻላል።በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ መኪኖች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረገው እንቅስቃሴም ሊበረታቱ ይገባል።
እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ቢኖሩም ከዚህ በላይ መሰራት እንደሚጠበቅ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል።ወይዘሮ ፋንቱ እንዳሉት ለጉዳዩ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ተሰጥቷል።የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ስምንት አባላት ያለው ቡድን በማቋቋም የአየር ንብረት ለውጥ ሥራ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል።ቡድኑ ፈጻሚ ተቋማት የከተማዋን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጅን በዕቅዳቸው ውስጥ አካተው እንዲተገብሩ በማድረግና ግንዛቤ በመፍጠር ኃላፊነትና ተግባራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችል የማነቃቃት ሥራ በመሥራት ለውጥ እንዲመጣ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።ቡድኑ በአንድ ዓመት ቆይታው የትራንስፖርት ቢሮ የሙቀት አማቂ ጋዝ የልዕቀት መጠንን ለመቀነስ የሚያስችል ስትራተጅ ነድፎ እንዲንቀሳቀስ የማገዝ ሥራ አከናውኗል።እንደ ተቋም የአምስትና የአሥር ዓመት ዕቅድ የተነደፈ ሲሆን፣የፈጻሚ መስሪያቤቶችን አጠቃላይ ድምር በመውሰድ በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ የሙቀት አማቂ ጋዝን ወደ 13 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ግብ ተቀምጧል።
አሁን ባለው ሙቀት አማቂ ጋዝ በማስከተል የትራንስፖርት ዘርፍ 75 ከመቶ፣የከተማ ግብርና ከ25 በመቶ በታች ሲሆን ፣በዚህ ክልል ውስጥ ያሉ የሌሎችም አማካይ ነው የተወሰደው።ፈጻሚ ተቋማቱ ዘጠኝ መሆናቸውንና ሁሉም በዕቅድ የተቀመጠውን መተግበርና ውጤት ማምጣት ሲችሉ የታለመለት ግብ ላይ መድረስ እንደሚቻል ወይዘሮ ፋንቱ ያስረዳሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ሁሉም በየሚሰሩበት ዘርፍ የቅነሳ እቅድ በማስቀመጥ ነው የሚተገብረው። ባስቀመጠው ዕቅድም በየጊዜው በምን ያህል ሙቀት አማቂ ጋዝ እየቀነሰ እንደሄደ በክትትል ይለያል። አዲስ አበባ ከተማ በሙቀት አማቂ ጋዝ ቅነሳ ላይ ከዓለም ተውጣጥተው ‹‹ኢ 40 ሲቲስ ክላይሜንት ቼንጅ ሊደር ሺፕ ግሩፕ›› በሚል ስያሜ ካቋቋሙት መካከል አንዷ ሆና በመሥራት ላይ ትገኛለች።አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ 11 የአፍሪካ ከተሞች የተካተቱበት ይህ ተቋም በእንግሊዝ ሀገር ይገኛል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ ማዕከል ትምህርት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ተሾመ ሶሮምሳ‹‹ለሙቀት አማቂ ጋዝ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ለይቶ እነሱን ማከም መፍትሄ ነው››ይላሉ።ያደጉ ሀገሮች ጭስ አልባ(ካርበን ፍሪ) መኪኖችን ማምረት በመጀመራቸው ወደዚህኛው አማራጭ ለመሄድ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት ለሙቀት አማቂ ጋዝ መፈጠር አንዱ ችግር የኦዞን መቀደድ በመሆኑ ችግኝ በስፋት በመትከል የደን ሽፋንን መጨመር ይገባል።ደን በባህሪው የተቃጠለ አየር(ካርበንዳዮክሳይድን) ወደ ውስጥ አምቆ ስለሚያስቀር ኦዞን ላይ የሚደርሰውን የመሸንቆር አደጋ መከላከል ይቻላል።
ከኢንደስትሪ የሚወጣውን ፍሳሽ ባለንብረቶቹ እንዲቆጣጠሩ፣አክመው ለተለያየ ጥቅም እንዲያውሉ በህግ የተቀመጠ አሰራር ቢኖርም እየተተገበረ ባለመሆኑ ችግሩ ሥር እንዲሰድ ምክንያት ሆኗል።ህጉን በመተግበር መታደግ ይቻላል።አንዱ ህግ ለማስከበር ጥረት ሲያደርግ ሌላው በዝምድናና በምልጃ እርምጃው እንዲቀር ካደረገ ውጤታማ መሆን አይቻልም።
አንዳንድ የእርምጃ ተሞክሮች ጤናማ አለመሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል። ለተሻለ ሥራ የጋራ ጥረት ይጠይቃል።በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ኢንደስትሪዎች በሥፋት በመኖራቸው ሊታሰብበት ይገባል።በአረንጓዴ ልማት ዕድገት ማስመዝገብ የሚቻለው ኢኮኖሚውና አካባቢው ሲጣጣም ወይንም ሁለቱንም በማያያዝ ወደፊት መራመድ ሲቻል እንደሆነ ፕሮፌሰር ተሾመ ይናገራሉ።ፕሮፌሰሩ በተለየ ሁኔታ ሙቀት አማቂ ጋዞች ላይ የጥናት ሥራ ባያከናውኑም በተዘዋዋሪ ከደንና ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ በሰሩት የጥናት ሥራ ችግሩን ለመጠቆም ጥረት ይገልጻሉ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 8/2013