መንግሥት ሀገሪቱንና ዜጎቿን ከድህነት አላቆ ወደ ብልጽግና ያደርሳል በሚል ለትምሀርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡ ሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችን እያስፋፋች የምትገኘው በቀጣይ የሚያስፈልጋትን የተማረ የሰው ሀይል ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም የተማረ ሰው መላ ያፈላልጋል ከችግር መውጫ መንገዱን አያጣም ብላም ነው፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከዚህ አንጻር ብንመለከት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የተወሰኑ ኮሌጆች ብቻ የነበሯት ሀገራችን አሁን በመንግሥት እጅ ብቻ 50 የሚደርሱ ዩኒቨርሲቲዎች ባለቤት ሆናለች፡፡ ከፍተኛ በጀት እየተመደበም አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲከፈቱ ነባሮቹ እንዲስፋፉ እየተደረገ ነው፡፡
በየዓመቱ ወደ ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚገቡት ተማሪዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሲሆን፤ የሚያስመርቋቸው ተማሪዎች ብዛትም እንዲሁ ከአንድ መቶ ሺ በላይ ደርሷል፡፡ በዚህ ላይ የቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ፣የግል ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች ሲታከሉ ሀገሪቱ ለትምህርቱ ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
የተቋማቱ ተማሪዎች ራሳቸውን ለታላቅ ተግባር ከማብቃት በተጨማሪ ይህን የመንግሥት ተግባር ማሳካት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ትምህርታቸውን በሚገባ መከታተል ሲችሉ ነው፡፡
አሁን አሁን በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ ከማቅረብ ይልቅ ለሁከት በር የሚከፍት አዝማሚያ በሚፈጥር መንገድ ማንጸባረቁ አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ተማሪዎች ጥያቄያቸውን በስርዓቱ ካላቀረቡ ችግራቸውም አይፈታም ፤የትምሀርት ስዓአቱ ይናጋል፡፡ የእኩይ ተግባር አራማጆች መሳሪያም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በቅርቡም አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ከተማሪዎች ጋር በተፈጠሩ አለመግባባቶች ሳቢያ ትምህርታቸው ተስተጓጉሏል፤ ድርጊቱ ደግሞ ጸረ ሰላም ሀይሎች አጀንዳቸውን በተዘዋዋሪ መንገድ ለማስፈጸም የሚያቀነባብሩት ሴራ ስለመሆኑ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶች በተቀሰቀሱ ወቅት መገንዘብ ተችሏል፡፡
በዚህም የተነሳ ተማሪዎች እንደተጎዱ፤ ትምህርትም እንደተቋረጠ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ አግባብነት የሌለው ድርጊት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ይህን ድርጊት ለመከላከል መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡ ተማሪዎች፣መምህራን እና መላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የግቢያቸውን ሰላምና መረጋጋት መጠበቅ አለባቸው፡፡ በዚህም ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን አስቀድሞ መቆጣጠር ይቻላል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከግቢው ውጪ በሚገኝ የእምነት ተቋም ጸሎት ላይ በነበሩ ተማሪዎቹ ላይ ደረሰ የተባለውን ችግር ተከትሎ ባደረገው ፍተሻ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁከት የመፍጠር ዓላማ ያላቸው አካላት በድብቅ እንደሚንቀሳቀሱ ጠቋሚ ነው፡፡ የተገኘው መረጃም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ፍተሻ ማካሄድ እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ሰሞኑን ያካሄደውን ፍተሻ አስመልክቶ ይፋ ባደረገው ማስታወቂያ ላይ እንደተመለከተው፤ በፍተሻው 395 ያልታደሰ ፣ ሀሰተኛና ፎቶ የሌለው መታወቂያ እንዲሁም ዱላ፣ጩቤ ፣ድንጋይ በተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ተገኝተዋል፤በርካታ ሲም ካርድ የያዙ ሁለት ተማሪዎችም ተይዘዋል፡፡ በስምንት ተማሪዎች አካውንት ላይ ከ30 እስከ 86 ሺ ብር ተገኝቷል፡፡ 37 ተማሪዎች መታወቂያ ሳይዙ ተገኝተዋል፡፡ በተጠርጣሪዎች ላይ የማጣራት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፤
ዩኒቨርሲቲው ያገኘው መረጃ ገና በመጣራት ላይ ቢሆንም፤ የተገኙት ማስረጃዎች ግን የዩኒቨርስቲውን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ጥርጣሬው ሲኖራቸው ምን ያህል ርቀት ተጉዘው መስራት እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡
የዩኒቨርሲቲው እርምጃ በግቢ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከግቢ ውጪም ያለውን የተማሪዎች እንቅስቃሴ መከታተል ጭምር እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባል፡፡ ከውጪ የጀመረ ግጭት ወደ ውስጥ ሊዘልቅ እንደሚችል መከታተል ያስፈልጋል፡፡
ከተማሪዎች ጋር ተመሳስለው የሚኖሩ፣ ለእኩይ ድርጊት ያደሩ ተማሪዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገመት የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቦች እያንዳንዱን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተው መከታተል ጥርጣሬው ሲኖራቸውና ሲበረታባቸውም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ፍተሻ ማድረግ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ከወዲሁ ለማረም ይጠቅማል፡፡
የጸጥታ ሀይሎች በዩኒቨርሲቲ ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ መግባት ባይኖርባቸውም ስራው የጋራ በሆነ ጊዜ ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ከሁሉም በፊት ደግሞ ይህን መሰሉን ድርጊት አስቀድሞ መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለዩኒቨርሲቲ ጥበቃዎች አልፎም ተርፎ ማህበረሰብ ስልጠና መስጠትም ይኖርባቸዋል፡፡
በሀገራችን የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማናጋት እየተፈፀሙ የሚገኙት ወንጀሎች የተለየ መልክ ይዘው ሊመጡ እንደሚችሉም ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶች ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎች የጸረ ሰላም ሃይሎች መንቀሳቀሻ እና የግጭት አውድማ እንዳይሆኑ አተኩሮ መስራት፣ ጥንቃቄውንም ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡