የኢሬቻበዓልን ከማክበር ባለፈ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት እንዲሆን እየተሠራ ነው

– በአዲስ አበባ “ኢሬቻ ኤክስፖ 2017” የተሰኘ አውደ ርዕይ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፡- የኢሬቻ በዓልን ከማክበር ባለፈ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት እንዲሆን እየተሠራ ነው ሲል የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው በትናንትናው እለት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ፤ በአይነቱ ለየት ያለ “ኢሬቻ ኤክስፖ 2017” የተሰኘ ታላቅ ዓመታዊ ዓውደ ርዕይ ከመስከረም 18 ቀን እስከ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ደራራ ቱለማ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፤ ኢሬቻ የክረምት ወቅት አልፎ አዲስ ዓመት ሲጀመር የሚከበር ታላቅ የምስጋና በዓል ነው።

ቢሮው የኦሮሞን ባህልና ታሪክ አጉልቶ ለማሳየት ከተለያዩ አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የኦሮሞ ሕዝብ መገለጫ የሆነውን የኢሬቻ በዓል ከማክበር ባለፈ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ቢሮው ከመስከረም 18 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ “ኢሬቻ ኤክስፖ 2017” የተሰኘ አውደ ርዕይ ከሀገሬ ኢቨንትስ ኤንድ ፕሮሞሽን ጋር በመሆን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

አቶ ደራራ፤ “ኢሬቻ ኤክስፖ 2017” የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ታዳሚ የሚሆኑበት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ እና በሚቀጥሉት ዓመታት ግን በቋሚነት የሚዘጋጅ ዓመታዊ ሁነት መሆኑን አንስተው፤ ኤክስፖው ወሳኝ ኢኮኖሚያዊ እድሎችን የሚፈጥር ደማቅና ሰፊ ዝግጅት መሆኑን ጠቁመዋል።

በዘንድሮ ኢሬቻ በዓል ከ10 ሚሊዮን ሰዎች በላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሀገሬ ኢቨንትስ ኤንድ ፕሮሞሽን ኃላፊ ሃወኒ እሸቱ በበኩላቸው፤ ኤክስፖው ኢሬቻ ከበዓል በተጨማሪ በኢኮኖሚ ላይ ያለውን አስተዋጽኦ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በኤክስፖው ከባህላዊ ኤግዚቢሽኖች እና ትርኢቶች እስከ የእደ ጥበብ ወርክሾፖች፣ የአገልግሎትና ምርቶች ባዛር እና የማህበረሰብ ተሳትፎ ክፍለ ጊዜዎችን ጨምሮ በርካታ ተግባራት የሚቀርቡበት ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ የንግድ፣ የባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ፣ የእጅ ሥራዎች፣ የባህላዊ ምግቦች፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ የፓናል ውይይትና ሌሎችም ዝግጅቶች እንደተካተቱበት ጠቅሰዋል።

በኤክስፖው ከ200 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉበትና ከ250 በላይ የንግድ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ያቀርቡበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You