በአማራ ክልል ከሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ሁሉን አቀፍ መንገድ ሊገነባ ነው

-15 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን ታቅዷል

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት ከሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር፣የአስፓልትና ድልድዮችን ያካተተ ሁሉን አቀፍ መንገድ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ መንገድ ቢሮ አስታወቀ፡፡ በበጀት ዓመቱም 15 ሺህ ኪሎ ሜትር ጉዳት የደረሰበትን መንገድ ለመጠገን መታቀዱ ተጠቁሟል፡፡

የአማራ ክልል የመንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤በአማራ ክልል የገጠሩንና የከተሜውን ማህበረሰብ በማገናኘት የገበያ ትስስር ለመፍጠር፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቁርኝትን ለማሳደግ የሚያስችል የመንገድ መሠረተ ልማት ለመገንባት እየተሠራ ነው፡፡ በዚህም በ2017 በጀት ዓመት ሁለት ሺህ 200 ኪሎ ሜትር የጠጠር፣አስፓልትና ድልድዮችን ያካተተ ሁሉን አቀፍ መንገድ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት የገጠሩን ማህበረሰብ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፤ ከተሜውን ከገጠሩ ማህበረሰብ ለማስተሳሰር የሚያስችል አንድ ሺህ 97 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ለመሥራት ታቅዶ በተደረገ ክንውን 705 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገናና 265 ኪሎ ሜትር መንገድ የመገንባት ሥራ ተሠርቷል ያሉት ኃላፊው፤ የጥገናና የግንባታ ሥራው የተሠራው ከማህበረሰቡ በተዋጣ 931 ሚሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የክልሉን የመንገድ መሠረተ ልማት በማሳደግ ማህበረሰቡን በኢኮኖሚ፣በማህበራዊ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ባለው ሥራ 139 ኪሎ ሜትር መንገድ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመገንባት ሥራ ተከናውኗል ያሉት ጋሻው (ዶ/ር)፤ የዜጎችን የመሸጋገሪያ ድልድይ ችግር ለመፍታት 92 ድልድይ ለመሥራት ታቅዶ በተሠራ ሥራ 74 ድልድዮችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ሁለት ሺህ 200 ኪሎ ሜትር ሁሉን አቀፍ መንገድ በመገንባትና 15 ሺህ ኪሎ ሜትር በመጠገን የገጠሩን ማህበረሰብ ከከተሜው የማገናኘት ሥራ ይሠራል፤ ይህም የክልሉን የንግድ የትስስር አድማስ ያሰፋል፤ ማህበራዊ ቁርኝትም ያሳድግል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የታቀደውን ሁለት ሺህ 200 ኪሎ ሜትር ሁሉን አቀፍ መንገድ ግንባታና 15 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና እውን ለማድረግ አንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ከማህበረሰቡ ለመሰብሰብ እንደታቀደ ገልጸው፤ የክልሉ መንግሥትም እቅዱን ውጤታማ ለማድረግ አንድ ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መበጀቱን አብራርተዋል፡፡

የክልሉ ማህበረሰብ የመንገድ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸው፤ የክልሉ መንግሥትም የማህበረሰቡን የመንገድ የልማት ጥያቄ ለመመለስ ጠንካራ ሥራ እየሠራ ነው፤ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You