በሊባኖስ በመገናኛ መሳሪያዎች የተፈጸመው ጥቃትና መነሾው

በሊባኖስ “ፔጀር” የተሰኙ የመረጃ መለዋወጫ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ፍንዳታ የዘጠኝ ሰዎችን ህይወት ቀጥፎ ከ2 ሺህ 800 በላይ ሰዎችን አቁስሏል።

“ፔጀር” በመባል የሚታወቁት በእጅ የሚያዙ የሬዲዮ የመገናኛ መሳሪያዎች በብዛት በሄዝቦላ ታጣቂዎች ዘንድ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው። መገናኛዎቹ ሰሞኑን በተለያዩ ስፍራዎች በተመሳሳይ ሰአት በመፈንዳት በሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡

ከሟቾቹ ውስጥ ስምንቱ ተዋጊዎቹ እንደነበሩ የገለጸው ሄዝቦላህ ለፍንዳታው እስራኤልን ተጠያቂ አድርጓል።

የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰተውን ፍንዳታ “የእስራኤል የሳይበር ጥቃት” ነው ብሎታል።

እስራኤል ዝምታን ብትመርጥም የሊባኖስ የደህንነት ምንጮችን የሚጠቅሱ ዘገባዎች ግን ቴል አቪቭ ጥቃቱን ከጅምሩ እስከፍጻሜው መርታለች ብለው እንደሚያምኑ አመላክተዋል።

ሬውተርስ ያነጋገራቸው የሊባኖስ የደህንነት ባለስልጣን የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) የመረጃ መለዋወጫ መሳሪያዎቹ ለሊባኖሱ ሄዝቦላህ እንዲደርሰው ማድረጉን ይገልጻሉ።

5 ሺህ የሚደርሱት “AR-924” የተሰኙት መልዕክት መለዋወጫ መሳሪያዎች ወደ ሊባኖስ ከመግባታቸው ከወራት በፊትም የሚፈነዱ መሳሪያዎች ተቀብሮባቸዋል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ ጊዜ እንዲፈነዱ ትዕዛዝ የሚሰጡ ምስጢራዊ መልዕክቶችም በመሳሪያዎቹ ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ያነሳሉ።

የደህንነት እና የሳይበር ጉዳዮች ተንታኞች እስራኤል የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቹን ባትሪዎች በተመሳሳይ ሰአት እንዲግሉ አድርጎ ፍንዳታን ያስከተለ የሳይበር ጥቃት መፈጸሟን እየገለጹ ነው።

“AR-924” ምንድን ነው? አምራቹ ኩባንያስ?

የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ተዋጊዎቹ በእስራኤል የሳይበር ጥቃት ኢላማ እንዳይሆኑ የስማርት ስልኮችን እንዳይጠቀሙ አድርጓል።

በምትኩም በድምጽ እና በጽሁፍ መልዕክት ለማስተላለፍ የሚውሉና ደህንነታቸው የተጠበቁ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን እንዲጠቀሙ ሲያደርግ ቆይቷል።

ከነዚህ መሳሪያዎች መካከልም “AR-924” የተባሉ “ፔጀር” ተጠቃሽ ናቸው።

አነስተኛ መጠን ያላቸው የግንኙነት መሳሪያዎቹ በድጋሚ ኃይል በሚሞሉ ሊቲየም ባትሪዎች የሚሰሩ መሆናቸውንና ባትሪያቸው እስከ 85 ቀናት የመቆየት አቅም እንዳለው አምራቹ ያወጣው መረጃ ያሳያል።

ይህም እንደ ሊባኖስ ባሉ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በስፋት በሚታይባቸው ሀገራት ተመራጭ መረጃ መለዋወጫ መሳሪያ አድርጎታል።

“ፔጀርስ” ከስልኮች በተሻለ በተለያዩ ገመድ አልባ ኔትወርኮች መስራታቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሆስፒታሎች አሁንም ድረስ ዋነኛ መልዕክት ለመለዋወጥ ተመራጭ እንዲያደርጓቸው ምክንያት ሆኗል።

የታይዋን የኢኮኖሚ ጉዳዮች ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ከነሃሴ 2022 እስከ ነሃሴ 2024 ድረስ 260 ሺህ ”AR-924” ፔጀርስ ወደተለያዩ የአውሮፓና አሜሪካ ሀገራት መላካቸውን ገልጿል። ይሁን እንጂ አምራቹ “ጎልድ አፖሎ” ወደ ሊባኖስ በቀጥታ ምርቶቹን እንደላከ ነው ባወጣው መግለጫ የጠቆመው።

በትናንትናው እለት በሊባኖስ የፈነዱት መሳሪያዎች በሃንጋሪ መዲና ቡዳፔስት የተመረቱ መሆናቸውንም ጎልድ አፖሎ ይፋ አድርጓል።

የቡዳቤስቱ “ባክ ኮንሰልቲንግ” የተባለው ኩባንያ የጎልድ አፖሎ የምርት ስያሜ ለመጠቀም ፈቃድ ቢያገኝም የሚያመርታቸው “ፔጀርስ” ዲዛይንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የተለዩ በመሆናቸው ኃላፊነቱን አልወስድም ብሏል የታይዋኑ ኩባንያ።

ሄዝቦላህ ለ”ፔጀር” ፍንዳታው ምን ምላሽ ሰጠ?

የሊባኖሱ ቡድን በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ያነጣጠረው የሳይበር ጥቃትና ፍንዳታን ከእስራኤል ውጭ ማንም ሊፈጽመው አይችልም ብሏል።

በሊባኖሳውያን ንጹሃን እና በተዋጊዎቹ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት አጸፋዊ እርምጃ እንደሚወስድም በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ዝቷል።

የሊባኖስ ሆስፒታሎችን አጨናንቆ ኢራን፣ ቱርክ፣ ግብጽ፣ ኢራቅና ሶሪያ ተጎጂዎችን ተቀብሎ ለማከም ዝግጁ መሆናቸውን ያሳወቁበት ከባድ ጥቃት ቡድኑ በጋዛ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን የሚያሳየውን ተቆርቋሪነት እንደማይቀንሰውም ገልጿል።

ተንታኞች እስራኤል የሊባኖሱን ጥቃት ለባላንጣዎቿ ከወታደራዊ ባሻገር የሳይበር አቅሟ መፈርጠሙን ለማሳየት እንደተጠቀመችበት ያምናሉ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 9/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You