የእግር ኳስ ዳኞችን የስፖርት ትጥቅ አቅርቦት ችግር ይፈታል የተባለው ስምምነት

የእግር ኳስ ስፖርትን ተወዳጅ እና ተናፋቂ ከሚያደርጉ መሪ ተዋናዮች መካከል ዳኞች ትልቁን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ስፖርቱን ከስህተት ለማጥራት የማይቻል ቢሆንም ዳኞች ለተወዳጅነቱ የሚኖራቸው ሚና ትልቅ መሆኑ አያከራክርም፡፡ የእግር ኳስ ዳኞች በጨዋታ ወቅት ከሚያስፈልጓቸው መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል ደግሞ ከተጋጣሚ ቡድኖች የሚለያቸው ማሊያቸው ነው፡፡

እንደ እግር ኳስ ተጫዋቾች ሁሉ ዳኞች ሙሉ የስፖርት ትጥቆችን ማድረጋቸው ውድድራቸውን በተሳለጠ መልኩ ለመምራት ወሳኝ ነገር ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የሚሰሩ ዳኞችም ብዙ ከባባድ ችግሮችን ተጋፍጠው ጨዋታዎችን የሚመሩ ሲሆን፤ ቀላል የሚመስለውና ትኩረት የማይሰጠው የትጥቅ ችግር ዋነኛው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ወንዶችና ሴቶች ፕሪምየር ሊግን ጨምሮ በሌሎች የሊግ እርከኖች የሚያጫወቱት ዳኞች ለበርካታ ዓመታት ያልተቀረፈ የስፖርት ትጥቅ ችግር አለባቸው፡፡

የብሔራዊ ቡድኖችን የስፖርት ትጥቅ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ከተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል የስፖርት ትጥቅ አምራቾች ጋር የሚሰራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የእግር ኳስ ዳኞችንም የስፖርት ትጥቅ ችግር የሚፈታ ስምምነት ማድረግ ችሏል፡፡ የእግር ኳስ ዳኞች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግና በሌሎች የሊግ እርከኖች የሚለብሱትን ማሊያ አቅርቦት ከሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቆች አምራች ጎፈሬ ኩባንያ ጋር ከትናንት በስቲያ መስከረም 7/2017 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እና የጎፈሬ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን አከናውነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወንዶችና ሴቶች ፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ላይ የሚያጫውቱ ሁሉም ዳኞች በተደረገው ስምምነት መሰረት በድጋፍ እና ከፍተኛ በሆነ ቅናሽ የማጫወቻ ማሊያን እንደሚያገኙ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም ጎፈሬ ለወንዶች ፕሪምየር ሊግ ሙሉ የማሊያ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ ለሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 75 ከመቶ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የዳኞች ስፖርት ትጥቅ አቅርቦት ስምምነቱ ለሶስት ዓመታት የሚዘልቅና ከፍተኛ ወጪ እንደሚደረግበትም ተገልጿል፡፡

ለዳኞቹ በተለያዩ መልኮች አራት አይነት የማጫወቻ 400 ማሊያዎችን እና 200 ቁምጣዎችን ጨምሮ 100 የማሟሟቅያ፣ 100 የጉዞ፣ የቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ላይ የሚለበሱ ቲሸርቶች እና 100 ቱታዎች በድጋፍ መልክ ይቀርባል፡፡ በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ በስሩ በሚያካሂዳቸው ሌሎች ውድድሮች እንደየደረጃው ለዳኞች ቅናሽ ተደርጎ የስፖርት ትጥቆችን እንደሚያገኝም ተጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የዳኞች የስፖርት ትጥቅ አቅርቦት እንደሆነ በተገለጸው ስምምነት ትጥቆቹ “አጋፋሪ” እና “ገላጋይ” የሚል ስያሜን መያዛቸውም ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሸዋንግዛው ተባባል የስምምነቱ መደረግ ለእግር ኳስ ዳኞች ትልቅ ድል መሆኑን ገልጸው፤ የዳኞች የትጥቅ ችግር ምን ያህል እንደሆነ የገፈቱ ቀማሽ ዳኞች በደንብ ስለሚያውቁት ትልቅ ቀን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዳኞች ችግር ሲፈጠር ብቻ አጀንዳ ከመሆን አልፈው ችግራቸውን የሚያውቅ ባለመኖሩ በማሊያ ችግር ይፈተናሉ፡፡ የሚያጫውቱበትን ማሊያ እየገዙ መሆኑን የሚናገሩት የኮሚቴው ሰብሳቢ፤ እሱም የሚገዛ ማለያ ከተገኘ ነው ብለዋል፡፡ ለብዙ ጊዜ ሲንከባለል የመጣ ችግር በመሆኑ በፌዴሬሽኑ ሀብት ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ የመጣው እድል የዳኞችን የትጥቅ ችግር እንደፈታ ሁሉ በሌሎችም የገቢ ምንጮች ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ከጎፈሬ ጋር ለረጅም ጊዜ አብሮ ለመስራትና ከገቢውም ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበትን መንገድ ለመፍጠር ይሰራልም ብለዋል፡፡

የስፖርት ትጥቆች አምራች መስራችና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን፣ ለዳኞች የስፖርት ትጥቆችን ለማቅረብ የተደረገው ስምምነት ልዩ የሚያደርገው አንድ ፌዴሬሽን ለዳኞች ትጥቅ አቅርቦት ስምምነት በማድረግ መስራቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዳኞች ማሊያ ችግር ከፍተኛ መሆኑን እና ዳኞች ጨዋታ ሲመሩ እየተቀያየሩም ጭምር ለብሰው ወደ ሜዳ የሚገቡበትን ሁኔታ በማስቀረቱና ተመሳሳይ የዳኞች ማሊያን ማቅረብ ማስቻሉም ልዩ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ ዳኞች ውድድሮችን ለመምራት የስፖርት ትጥቆችን ለማግኘት አስቸጋሪ ጊዜያት እንዳለፉ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት ዳኞች ትጥቅ ለማግኘት ከባድ በመሆኑ ጨርቅ አሰፍተው ይለብሱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ወደ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሄደው የሚያገኟቸውን ትጥቆች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እየተዋዋሱ ይጠቀማሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከስያሜውም ጋር ተያይዞ ሁሌም የሚያሳስበው ጉዳይ በመሆኑ ከሶስት ዓመት በፊት የአምብሮ ትጥቅን ለዳኞች መስጠት ተችሏል፡፡ ዳኞቹ እስከ አሁን እሱን ተቀያይረው የሚያጫወቱ በመሆኑ ችግራቸውን የሚቀርፍ ስምምነት መሆኑን ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ ስምምነቱ ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግና የዳኞችን ማሊያ ማቅረብና ምርታቸውን ማስተዋወቅ ከሚፈልጉ አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁነት መኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

 አዲስ ዘመን መስከረም 9/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You